መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መሲሑ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ መሲሑ ወደ ዓለም እንደሚመጣ እንዲሁም ሰዎችን ከበሽታ፣ ከመከራና ከሞት እንደሚያድን ተንብዮአል። ታዲያ ይህ መሲሕ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው?
ሰዎች መሲሑ ማን እንደሆነ ማወቅ የሚችሉት እንዴት ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንደሚናገረው መሲሑ ወይም ክርስቶስ የሚመጣው ሁለት የተለያዩ ዓላማዎችን ለማከናወን ነው፤ እነዚህን ሁለት ዓላማዎች ለማከናወን የሚመጣው በተለያየ ጊዜ ነው። * የመጀመሪያውን ዓላማ የሚያከናውነው ሰው ሆኖ በምድር ላይ በመኖር ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች መሲሑን በግልጽ ለይተው የሚያሳውቁ ከሕይወቱና ከአገልግሎቱ ጋር የተያያዙ በርካታ ትንቢቶችን በጽሑፍ አስፍረዋል። እንዲያውም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የተጻፉበት ዋነኛ ዓላማ “ስለ ኢየሱስ ለመመሥከር ነው።”—ራእይ 19:10
ኢየሱስ ሰው በነበረበት ወቅት ያደረጋቸው ነገሮች ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር ሲሆን በመላው ምድር ላይ የሚያከናውነውን ነገር በትንሹ የሚያሳዩ ናቸው
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መሲሑ . . .
-
ከንጉሥ ዳዊት የዘር ሐረግ ይመጣል።—ኢሳይያስ 9:7፤ ሉቃስ 3:23-31 *
-
‘ምሥራቹን’ በትሕትና ይሰብካል።—ኢሳይያስ 61:1፤ ሉቃስ 4:43
-
የተናቀና የተጠላ ይሆናል።—ኢሳይያስ 53:3፤ ማቴዎስ 26:67, 68
-
በ30 የብር ሳንቲሞች አልፎ ይሰጣል።—ዘካርያስ 11:12, 13፤ ማቴዎስ 26:14, 15
-
ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ የሞት ፍርድ ሲበየንበት በከሳሾቹ ፊት ዝም ይላል።—ኢሳይያስ 53:6, 7፤ ማቴዎስ 27:12-14
-
ኃጢአትን ለማስተሰረይና የሰው ልጆች በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋም እንዲኖራቸው ለማድረግ የመሥዋዕት “በግ” ሆኖ ይቀርባል።—ኢሳይያስ 53:7፤ ዮሐንስ 1:29, 34, 36
-
በሚገደልበት ወቅት ከአጥንቶቹ አንዱም አይሰበርም።—መዝሙር 34:20፤ ዮሐንስ 19:33, 36
-
ከሀብታሞች ጋር ይቀበራል።—ኢሳይያስ 53:9፤ ማቴዎስ 27:57-60
-
በሦስተኛው ቀን ከሞት ይነሳል።—ማቴዎስ 16:21፤ 28:5-7
እነዚህና ሌሎች በርካታ ትንቢቶች በኢየሱስ ላይ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። በተጨማሪም ኢየሱስ ሕመምተኞችን ፈውሷል፤ እንዲሁም የሞቱትን አስነስቷል። ይህን ማድረጉ መሲሕ መሆኑን የሚያረጋግጥ ከመሆኑም ሌላ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈሩት ተስፋዎች ወደፊት በመላው ምድር ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ እንደሚያደርግ ያሳያል። (ሉቃስ 7:21-23፤ ራእይ 21:3, 4) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ በአምላክ ‘ቀኝ’ የተቀመጠ ሲሆን መሲሕ በመሆን የሚያከናውነውን ሥራ የሚያጠናቅቅበትን ጊዜ እየተጠባበቀ ነው።—መዝሙር 110:1-6
“ክርስቶስስ በሚመጣበት ጊዜ ከዚህ ሰው የበለጠ ብዙ ምልክቶች ያደርጋል እንዴ?”—ዮሐንስ 7:31
መሲሑ ሥራውን የሚያጠናቅቀው እንዴት ነው?
በኢየሱስ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን መሲሑ ከሮም የቅኝ አገዛዝ ነፃ እንደሚያወጣቸውና ዳግም በሚቋቋመው የእስራኤል መንግሥት ላይ እንደሚነግሥ ይጠብቁ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 1:6) አይሁዳውያን የሆኑት የክርስቶስ ተከታዮች፣ ኢየሱስ መሲሕ በመሆን የሚያከናውነውን ዓላማ ከግብ የሚያደርሰው ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ በሰማይ ትልቅ ሥልጣን ሲሰጠው እንደሆነ የተረዱት ከጊዜ በኋላ ነበር።—ማቴዎስ 28:18
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መሲሑ ሁለተኛውን ዓላማውን ከግብ ሲያደርስ . . .
-
የአምላክ መንግሥት ንጉሥ በመሆን መላውን ዓለም ያስተዳድራል።—ዳንኤል 7:13, 14፤ ራእይ 11:15
-
በእሱ ለሚያምኑ የሰው ልጆች በሙሉ በረከት ያመጣል።—ዘፍጥረት 22:17, 18፤ መዝሙር 72:7, 8
-
እሱን የሚቃወሙትን መንግሥታትና መሪዎቻቸውን ያጠፋል።—ኢሳይያስ 52:15፤ ራእይ 19:19, 20
-
ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” የሚሆኑ ጻድቅ ሰዎች ሰላም በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ ያደርጋል።—ራእይ 7:9, 10, 13-17
-
የሞቱ ሰዎች በይሖዋ አምላክ እርዳታ ትንሣኤ አግኝተው ገነት በምትሆነው ምድር ላይ እንዲኖሩ ያደርጋል።—ሉቃስ 23:43፤ ዮሐንስ 5:21, 28, 29
-
ተገዢዎቹ ሰላማዊ እንዲሆኑ ያስተምራል።—ኢሳይያስ 11:1, 2, 9, 10
-
የበሽታ እና የሞት ዋነኛ መንስኤ የሆነውን ኃጢአትን ያስወግዳል።—ዮሐንስ 1:29፤ ሮም 5:12
-
በመጨረሻም የሰይጣንን ሥራዎች በሙሉ የሚያፈርስ ከመሆኑም ባሻገር የሰው ልጆች በሙሉ ይሖዋ አምላክ የሚያስተዳድረው አንድ ቤተሰብ ክፍል እንዲሆኑ ያደርጋል።—1 ቆሮንቶስ 15:25-28፤ 1 ዮሐንስ 3:8
ኢየሱስ መሲሕ በመሆን የሚያከናውነውን የመጀመሪያ ዓላማ ከግብ አድርሷል። ሁለተኛውን ዓላማውንም ከፍጻሜው ያደርሳል። ኢየሱስ “እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ” ብሏል፤ በመሆኑም ጥበበኛ ሰዎች ስለ እሱ በሚገባ መማራቸው አስፈላጊ ነው።—ዮሐንስ 14:6
“በዘመኑ ጽድቅ ይሰፍናል፤ ጨረቃ ከስፍራዋ እስከምትታጣ ድረስም ሰላም ይበዛል። . . . እስከ ምድር ዳርቻ ይገዛል።” —መዝሙር 72:7, 8