ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና
ልጅህ ስለ ሞት ሲጠይቅህ
ተፈታታኙ ነገር
የስድስት ዓመት ልጅህ “አባባ፣ አንተም ትሞታለህ?” ብሎ ጠየቀህ። በጥያቄው ደንገጥ ብለህ ‘ልጄ የዚህን ጥያቄ መልስ ሊረዳ የሚችልበት ዕድሜ ላይ ነው? ስለ ሞት የምነግረው እንዴት ብዬ ነው?’ እያልክ ማሰብ ትጀምራለህ። *
ማወቅ የሚኖርብህ ነገር
ልጆች ስለ ሞት ያስባሉ። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ አብረው ሲጫወቱ አንደኛው የሞተ ለመምሰል ይሞክራል። ስለዚህ ስለ ሞት ጨርሶ ማውራት እንደሌለብህ ሊሰማህ አይገባም፤ እንዲሁም ልጅህ ስለ ሞት የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች መሸሽ አይኖርብህም። አልፎ አልፎ ከልጅህ ጋር ስለ ሞት በግልጽ ማውራትህ በቤተሰባችሁ ውስጥ ሐዘን ቢያጋጥም ልጅህ ሁኔታውን ለመቋቋም ይረዳዋል።
ስለ ሞት ማውራት ልጁ በፍርሃት እንዲሸበር አያደርግም። እንዲያውም ፍርሃቱ እንዲቀንስ ይረዳዋል። ይሁን እንጂ ልጅህ ስለ ሞት ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖረው መርዳት ሊኖርብህ ይችላል። ለምሳሌ አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ከሆነ ከስድስት ዓመት በታች የሆኑ ብዙ ልጆች አንድ ሰው ሲሞት ከሕልውና ውጭ እንደሚሆን አይገነዘቡም። በሚጫወቱበት ጊዜ እንደሞተ ያስመሰለው ልጅ ትንሽ ቆይቶ ይነሳል።
ትንሽ አደግ ሲሉ ግን የሞትን ክብደት መገንዘብ ይጀምራሉ፤ ይህም በተለይ አንድ የቤተሰባቸው አባል በሚሞትበት ጊዜ በአእምሯቸው ውስጥ ጥያቄዎች እንዲፈጠሩ እንዲሁም ስጋትና ጭንቀት እንዲያድርባቸው ያደርጋል። ስለዚህ ይህን ጉዳይ አንስታችሁ መነጋገራችሁ አስፈላጊ ነው። ማሪዮን አዛ የተባሉ የአእምሮ ጤና ባለሙያ እንዲህ ብለዋል፦ “አንድ ልጅ፣ ቤት ውስጥ ስለ ሞት ማውራት እንደማይፈቀድለት ከተሰማው ከሞት ጋር በተያያዘ ስጋትና ጭንቀት ይፈጠርበታል።”
ምን ብዬ ልንገረው ብለህ ከልክ በላይ አትጨነቅ። አንድ ጥናት እንዳመለከተው ልጆች የሚፈልጉት “እውነቱን በደግነት የሚነግራቸው ሰው” ነው። ልጆች መልሱን ለመስማት ካልፈለጉ ቀድሞውንም ቢሆን ጥያቄውን እንደማያነሱ አስታውስ።
ምን ማድረግ ትችላለህ?
ስለ ሞት ለመናገር የሚያስችሉህን አጋጣሚዎች ፈልግ። ልጅህ የሞተ ወፍ መንገድ ዳር ወድቆ ሲመለከት ወይም የምትወዱት የቤት እንስሳ ሲሞት አጋጣሚውን ተጠቅመህ ቀላል ጥያቄዎችን በመጠየቅ ስለ ሞት እንዲያወራ አበረታታው። ለምሳሌ እንዲህ ብለህ ልትጠይቀው ትችላለህ፦ “የሞተ እንስሳ ይሠቃያል? ሊበርደው ወይም ሊርበው ይችላል? አንድ እንስሳ ወይም ሰው መሞቱ የሚታወቀው እንዴት ነው?”—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ መክብብ 3:1, 7
እውነቱን ተናገር። አንድ የምታውቁት ሰው ወይም ዘመድ ሲሞት ልጁን ላለማስደንገጥ ብለህ “ሌላ ቦታ ሄዷል” እንደሚለው ያሉ አባባሎችን አትጠቀም። ልጅህ፣ የሞተው ሰው ከሄደበት እንደሚመለስ ሊጠብቅ ይችላል። ከዚህ ይልቅ ቀላልና ቀጥተኛ የሆኑ አገላለጾችን ተጠቀም። ለምሳሌ እንዲህ ልትለው ትችላለህ፦ “አያትህ ስለሞተች ሰውነቷ መሥራቱን አቁሟል። አሁን ልናነጋግራት አንችልም፤ ይሁን እንጂ ፈጽሞ አንረሳትም።”—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ኤፌሶን 4:25
ትናንሽ ልጆች ሞት ሊተላለፍ ይችላል ብለው ሊሰጉ ስለሚችሉ እሱ ምንም እንደማይሆን በመንገር ልጅህን አረጋጋው
ልጅህን አረጋጋው። ልጅህ ግለሰቡ የሞተው እሱ ባደረገው ወይም ባሰበው ነገር ምክንያት እንደሆነ ሊሰማው ይችላል። ለሰውየው ሞት ምክንያት የሆነው እሱ እንዳልሆነ በመናገር ብቻ ከመወሰን ይልቅ “የአንተ ጥፋት እንደሆነ እንድታስብ ያደረገህ ምንድን ነው?” ብለህ ጠይቀው። ስሜቱን እንደ ቀላል ነገር አድርገህ ሳትመለከት በደንብ አዳምጠው። በተጨማሪም ትናንሽ ልጆች ሞት ሊተላለፍ ይችላል ብለው ሊሰጉ ስለሚችሉ እሱ ምንም እንደማይሆን በመንገር ልጅህን አረጋጋው።
ልጅህ የውስጡን እንዲናገር እርዳው። ልጅህ የማያውቃቸውን ዘመዶችህን ጨምሮ ስለሞቱ ዘመዶቻችሁ በነፃነት አውራ። ስለ አክስትህ፣ ስለ አጎትህ ወይም ስለ አያትህ አንድ ደስ የሚልህን ትዝታ አንስተህ ንገረው። እንደነዚህ ስላሉት ሰዎች በነፃነት ስታወራ ልጅህ ስለሞቱ ዘመዶቹ መናገርም ሆነ ማሰብ እንደሚችል እንዲገነዘብ ትረዳዋለህ። በሌላ በኩል ደግሞ ልጅህ እንዲያወራ ማስገደድ አይኖርብህም። ትክክለኛ እንደሆነ በሚሰማህ ጊዜ ጉዳዩን አንስተህ ልታወያየው ትችላለህ። —የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 20:5
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሞት ምን እንደሚል ልጅህን ለማስተማር የሚረዳ ሐሳብ ለማግኘት ከታላቁ አስተማሪ ተማር በተባለው መጽሐፍ ላይ ምዕራፍ 34 እና 35ን ተመልከት። ላይ በነፃ ማውረድ ይቻላል። የሕትመት ውጤቶች > መጻሕፍትና ብሮሹሮች በሚለው ሥር ተመልከት።
^ አን.4 በዚህ ርዕስ ውስጥ ስለ ልጆች ስንናገር በወንድ ፆታ የተጠቀምን ቢሆንም የቀረቡት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።