የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መኖር ምን ዋጋ አለው?
ሁኔታዎች ይለወጣሉ
“በየአቅጣጫው ብንደቆስም መፈናፈኛ አናጣም፤ ግራ ብንጋባም መውጫ ቀዳዳ አናጣም።”—2 ቆሮንቶስ 4:8
ራስን ማጥፋት “ጊዜያዊ ለሆነ ችግር ዘላቂ የሆነ መፍትሔ መስጠት” እንደሆነ ተደርጎ ይገለጻል። ለማመን ቢከብድህም እንኳ ማንኛውም ዓይነት አስጨናቂ ሁኔታ ሌላው ቀርቶ ከአንተ ቁጥጥር ውጭ እንደሆነ የሚሰማህም ጭምር ጊዜያዊ ሊሆን ይችላል። እንዲያውም ባልጠበቅከው መንገድ ሊስተካከል ይችላል።— “ሁኔታቸው ተለውጧል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
ይህ ባይሆን እንኳ ስለ ነገ ሳትጨነቅ ዛሬ በሚያጋጥሙህ ችግሮች ላይ ብቻ በማተኮር መፍትሔ መፈለግህ የተሻለ ነው። ኢየሱስ “ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ፤ ምክንያቱም ነገ የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉት። እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለው” ብሏል።—ማቴዎስ 6:34
ይሁንና ሁኔታህ ሊለወጥ የማይችል ቢሆንስ? ለምሳሌ ሥር የሰደደ ሕመም ይኖርብህ ይሆናል። አሊያም ያስጨነቀህ ነገር የትዳር መፍረስ ወይም የቤተሰብህን አባል በሞት እንደማጣት ያለ ልትቀይረው የማትችል ነገር ቢሆንስ?
በዚህ ጊዜም ቢሆን ልትለውጠው የምትችለው ነገር ይኖራል፤ ስለ ሁኔታው ያለህን አመለካከት መለወጥ ትችላለህ። ልትለውጠው የማትችለውን ነገር ተቀብለህ ለመኖር ስትጥር ነገሮችን ይበልጥ አዎንታዊ በሆነ መንገድ ማየት ትጀምራለህ። (ምሳሌ 15:15) በተጨማሪም ሞትን እንደ መፍትሔ ከመቁጠር ይልቅ ሁኔታውን ለመቋቋም የምትችልባቸውን መንገዶች መፈለግ ትጀምራለህ። ውጤቱ? ልትቆጣጠረው የማትችለው እንደሆነ ይሰማህ የነበረውን ሁኔታ በተወሰነ መጠንም ቢሆን መቆጣጠር ትጀምራለህ።—ኢዮብ 2:10
ይህን አስታውስ፦ አንድን ተራራ በአንድ እርምጃ ለመውጣት መሞከር የማይመስል ነገር ነው፤ ይሁን እንጂ ቀስ በቀስ እየተራመድክ አስቸጋሪውን ጉዞ መወጣት ትችላለህ። አብዛኞቹ የሚያጋጥሙህ ችግሮች ምንም ያህል እንደ ተራራ ገዝፈው ቢታዩህ በተመሳሳይ መንገድ ልትወጣቸው ትችላለህ።
ዛሬ ምን ማድረግ ትችላለህ? ሁኔታውን በተመለከተ ከአንድ ሰው ምናልባትም ከጓደኛህ ወይም ከቤተሰብህ አባል ጋር ተነጋገር። ይህ ሰው ያለህበትን ሁኔታ ይበልጥ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እንድታይ ሊረዳህ ይችል ይሆናል።—ምሳሌ 11:14