የታሪክ መስኮት
ታላቁ ቂሮስ
በጊዜያችን የዘመን አቆጣጠር መሠረት ጥቅምት 5/6 ቀን 539 ዓ.ዓ. የባቢሎናውያን ግዛት ዋና ከተማ በነበረችው በባቢሎን ላይ ፈጽሞ ያልታሰበ ነገር ደረሰ። በዚያ ታሪካዊ ምሽት ታላቁ ቂሮስ ተብሎ በሚጠራው በፋርሳዊው ንጉሥ ቂሮስ አዝማችነት የመጣው የሜዶናውያንና የፋርሳውያን ሠራዊት ከተማዪቱን ወረረ። የውጊያ ስልቱ በጣም አስደናቂ ነበር።
ቂሮስ ባቢሎንን ድል ያደረገው እንዴት ነው?
የጥንቶቹ የዓለም መሪዎች—ታላቁ ቂሮስ (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ “ቂሮስ በባቢሎን ላይ ዓይኑን በጣለበት ጊዜ ባቢሎን ከመላው የመካከለኛው ምሥራቅ ከተሞች፣ ምናልባትም በዚያን ጊዜ ከነበሩት የዓለም ከተሞች በሙሉ ከፍ ተደርጋ የምትታይ ከተማ ነበረች” ይላል። ባቢሎን በኤፍራጥስ ወንዝ ላይ የተገነባች ሲሆን ወንዙ የከተማዪቱን ግዙፍ ግንብ ይከብ የነበረውን ሰፊና ጥልቅ የሆነ ቦይ ይሞላ ነበር፤ ከተማዪቱ ድርብ በሆነ ግንብ የታጠረች በመሆኑ ማንም ሊደፍራት የማይችል ትመስል ነበር።
የቂሮስ ሰዎች ከባቢሎን ከፍ ብለው የኤፍራጥስን ወንዝ የፍሰት አቅጣጫ በመቀየራቸው በከተማዋ ውስጥ የሚያልፈው ውኃ ጎደለ። ከዚያም ወታደሮቹ ወንዙን ተሻግረው ክፍቱን በተተወው የከተማዋ በር ገቡና ይህ ነው የሚባል ውጊያ ሳይገጥማቸው ባቢሎንን ተቆጣጠሯት። ሄሮዶተስና ዜኖፎን የተባሉት ግሪካውያን የታሪክ ምሁራን እንዳሉት ከሆነ ባቢሎናውያኑ በከተማቸው ቅጥር አይበገሬነት እጅግ በመታመናቸው ጥቃቱ በተሰነዘረበት ምሽት ንጉሡን ጨምሮ ብዙዎቹ በታላቅ ፈንጠዝያ ላይ ነበሩ! ( “የእጅ ጽሑፍ በግድግዳው ላይ ታየ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ከዚህም በላይ በቂሮስ ወረራ አማካኝነት አንዳንድ አስደናቂ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል።
ቂሮስ ባቢሎንን ድል እንደሚያደርግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተተንብዮ ነበር
አስደናቂ የሆኑ ትንቢቶች
በተለይ ኢሳይያስ የተናገራቸው ትንቢቶች በጣም የሚያስደንቁ ናቸው፤ ምክንያቱም ትንቢቶቹ የተጻፉት ከ200 ዓመት በፊት፣ ምናልባትም ቂሮስ ከመወለዱ ከ150 ዓመት በፊት ነበር! የሚከተሉትን ትንቢቶች ተመልከት፦
ቂሮስ የሚባል ሰው ባቢሎንን ድል አድርጎ አይሁዳውያንን ነፃ ያወጣል።—ኢሳይያስ 44:28፤ 45:1
የኤፍራጥስ ወንዝ ደርቆ የቂሮስ ሠራዊት የሚሻገርበት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል።—ኢሳይያስ 44:27
የከተማዋ በሮች ክፍት ይተዋሉ።—ኢሳይያስ 45:1
የባቢሎን ሠራዊት ‘አይዋጋም።’—ኤርምያስ 51:30፤ ኢሳይያስ 13:1, 7
ተአምራዊ በሆነ መንገድ ነፃ መውጣት
ቀደም ሲል በ607 ዓ.ዓ. የባቢሎን ሠራዊት ኢየሩሳሌምን አውድሞ ከእልቂቱ የተረፉትን አብዛኞቹን ሰዎች ወደ ባቢሎን አግዞ ነበር። አይሁዳውያኑ በግዞት የሚቆዩት ለምን ያህል ጊዜ ይሆን? አምላክ “ሰባው ዓመት ከተፈጸመ በኋላ፣ የባቢሎንን ንጉሥና ሕዝቡን፣ የባቢሎናውያንንም ምድር ስለ በደላቸው እቀጣቸዋለሁ . . . ለዘላለምም ባድማ አደርጋታለሁ” ብሎ ነበር።—ኤርምያስ 25:12
ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ቂሮስ በ539 ዓ.ዓ. ባቢሎንን ድል አድርጎ ያዘ። ከዚያ ብዙ ሳይቆይ አይሁዳውያንን ነፃ አወጣቸው፤ በመሆኑም አይሁዳውያን ከተጋዙ ከ70 ዓመት በኋላ በ537 ዓ.ዓ. ወደ አገራቸው መመለስ ጀመሩ። (ዕዝራ 1:1-4) ባቢሎን ግን “ባድማ” ሆነች፤ ይህም የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ ሌላ ማስረጃ ነው።
ስለ ቂሮስ ማወቅ ለምን አስፈለገ?
ይህን ልብ በል፦ መጽሐፍ ቅዱስ (1) አይሁድ በግዞት የሚቆዩበትን 70 ዓመት፣ (2) ቂሮስ ባቢሎንን ድል እንደሚያደርግ እና የውጊያ ስልቱን ዋና ዋና ገጽታዎች እንዲሁም (3) የባቢሎንን ዘላለማዊ ጥፋት ተንብዮአል። ተራ የሆኑ ሰዎች እንዲህ ያለ ትንቢት ሊናገሩ አይችሉም! ይልቁንም “መቼም ቢሆን ትንቢት በሰው ፈቃድ አልመጣም፤ ከዚህ ይልቅ ሰዎች ከአምላክ የተቀበሉትን ትንቢት . . . ተናገሩ” ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው። (2 ጴጥሮስ 1:21) በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ልንመረምረው የሚገባ መጽሐፍ ነው።
^ አን.36 ቃሎቹ የሚያመለክቱት የገንዘብ መለኪያዎችን ነበር። ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 7 ተመልከት።