የወጣቶች ጥያቄ
ከትዳር ምን መጠበቅ እችላለሁ?—ክፍል 2
ባለፈው እትማችን ላይ ትዳር ስለሚያስገኝልህ አንዳንድ ጥቅሞችና ሊያጋጥሙህ ስለሚችሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ተመልክተን ነበር።
በዚህ እትም ላይ ደግሞ ያልጠበቅኸው ነገር ሊያጋጥምህ እንደሚችል መጠበቅ የሚኖርብህ ለምን እንደሆነ እንወያያለን።
ከሚከተሉት ምርጫዎች መካከል የአንተን አመለካከት በሚያንጸባርቁት ነጥቦች ላይ ✔ አድርግ። ከእነዚህ ነጥቦች ውስጥ ትልቅ ቦታ ከምትሰጠው በመጀመር ነጥቦቹን በቅደም ተከተል አስቀምጣቸው።
የወደፊት የትዳር ጓደኛዬ . . .
-
ቆንጆ እንድትሆን እፈልጋለሁ
-
ለራሴ ጥሩ ግምት እንዲኖረኝ የምታደርገኝ እንድትሆን እፈልጋለሁ
-
ግቦቿ ከእኔ ጋር ተመሳሳይ እንዲሆኑ እፈልጋለሁ
-
እኔ የምወዳቸውን መዝናኛዎች የምትወድ እንድትሆን እፈልጋለሁ
* ከሆነ የምታገባት ሴት ቀደም ባለው ገጽ ላይ የተዘረዘሩትን ነጥቦች እንድታሟላ መጠበቅህ ስህተት አይደለም። እንዲያውም እነዚህን መሥፈርቶች ሁሉ የምታሟላ ሚስት ልታገኝ ትችል ይሆናል። ይሁንና እውነታው እንደሚያሳየው በጊዜ ሂደት ሰዎች ይለወጣሉ፤ አንዳንድ ሁኔታዎችም እንደ ቀድሞው አይሆኑም።
ለማግባት የምታስብዋናው ነጥብ፦ ትዳርህ የተሳካ እንዲሆን ያልጠበቅኸው ነገር ሊያጋጥምህ እንደሚችል መጠበቅ ይኖርብሃል።
ደስ የሚለው ነገር፦ በትዳር ውስጥ ሊያጋጥሙ ከሚችሉ ያልተጠበቁ ነገሮች መካከል አንዳንዶቹን እየወደድካቸው ልትሄድ ትችላለህ።
“እንጠናና ከነበረበት ጊዜ ይልቅ ከተጋባን ወዲህ የማሪያን * ተጫዋችነት ማድነቅ ጀምሬያለሁ። ስለ ራሳችን ሚዛናዊ አመለካከት ስላለን ያጋጠሙንን ችግሮች እንኳ ያን ያህል አክብደን አንመለከታቸውም።”—ማርክ
የሚያሳዝነው ነገር፦ በትዳር ውስጥ ሊያጋጥሙ ከሚችሉ ያልተጠበቁ ነገሮች አንዳንዶቹ የሚያሳዝኑ ሊሆኑ ይችላሉ። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት፦
ከመጋባታችሁ በፊት፣ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውራችሁ የማገልገል ግብ ነበራችሁ እንበል። ይሁን እንጂ ከተጋባችሁ በኋላ የትዳር ጓደኛህ ከባድ የጤና ችግር ቢያጋጥማትና ግባችሁ ላይ መድረስ ባትችሉስ? ይህ በሕይወት ውስጥ ሊያጋጥም የሚችል ነገር ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን “መጥፎ ነገሮች በሁሉም ሰው ላይ ይደርሳሉ” በማለት ይናገራል። (መክብብ 9:11 ሆሊ ባይብል—ኢዚ ቱ ሪድ ቨርሽን) የትዳር ጓደኛህ የገጠማት ሁኔታ እንዲሁም ግባችሁ ላይ መድረስ አለመቻላችሁ ሊያሳዝንህ እንደሚችል ጥርጥር የለውም። ይሁንና እንዲህ ዓይነት ያልተጠበቀ ሁኔታ ቢያጋጥምህ እውነታውን ተቀብለህ አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ ይኖርብሃል። ደግሞም ያገባኸው ግለሰቧን እንጂ ግቧን አይደለም።
ዋናው ነጥብ፦ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የሚያገቡ ሰዎች አንዳንድ “መከራ” ያጋጥማቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 7:28) አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ያለው መከራ የሚመጣው ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ሲከሰቱ ነው።
ታዲያ ያልጠበቅኸው ነገር ሊያጋጥምህ እንደሚችል በማሰብ ራስህን ማዘጋጀት የምትችለው እንዴት ነው? ትዳር ከመሠረትህ ሁለት ነገሮች ያስፈልጉሃል።
1. እውነታውን ያገናዘበ አመለካከት
አንተና የምታገባት ሴት የቱንም ያህል ብትጣጣሙ የሚከተሉት ሁኔታዎች ሊያጋጥሟችሁ እንደሚችሉ መጠበቅ ይኖርባችኋል፦
-
የማትስማሙባቸው ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ
-
ቅድሚያ የምትሰጧቸው ነገሮች ሁልጊዜ አንድ ዓይነት ላይሆኑ ይችላሉ
-
የሚያስደስቷችሁ ሥራዎች ሁልጊዜ ተመሳሳይ ላይሆኑ ይችላሉ
-
መጀመሪያ ላይ የሚኖራችሁ ዓይነት የፍቅር ስሜት ሁልጊዜ አይኖርም
ከላይ የተዘረዘሩትን የመሰሉ ሁኔታዎች በትዳራችሁ ውስጥ ቢያጋጥሟችሁ የሚያስገርም አይደለም። ይሁን እንጂ እነዚህ ሁኔታዎች እናንተ ካልፈቀዳችሁላቸው በስተቀር ትዳራችሁን ለማፍረስ ምክንያት አይሆኑም። መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር “ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል” እንዲሁም ፍቅር “ፈጽሞ አይከስምም” በማለት እንደሚናገር አስታውሱ።—1 ቆሮንቶስ 13:4, 7, 8
የሕይወት እውነታ፦ ትዳራችሁ እንዲጸና ወይም እንዲፈርስ የሚያደርጉት የሚያጋጥሟችሁ ችግሮች ሳይሆኑ ችግሮቹን የምትፈቱበት መንገድ ነው።—ቆላስይስ 3:13
2. ቃል ኪዳንን ማክበር
አንተና የትዳር ጓደኛህ፣ ምንም ይምጣ ምን አንድ ላይ ለመኖር ከወሰናችሁ የሚያጋጥሟችሁን ያልተጠበቁ ችግሮች መቋቋም ትችላላችሁ።—ማቴዎስ 19:6
አንዳንዶች ቃል ኪዳን መግባት ትዳር ከባድ እንዲሆን ያደርጋል ብለው ይናገሩ ይሆናል። ይሁንና እውነታው ከዚህ ተቃራኒ ነው! ቃል ኪዳን፣ ትዳራችሁ አስተማማኝ እንዲሆን ያደርጋል። ቃል ኪዳን አክባሪዎች ከሆናችሁ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች በሚያጋጥሟችሁ ጊዜ ከትዳር ኃላፊነት ነፃ የምትሆኑበትን መንገድ ከመፈለግ ይልቅ ለችግሩ መፍትሔ ትሻላችሁ።
ለትዳራችሁ ምንጊዜም ታማኝ ሆናችሁ መኖር እንድትችሉ ስለ ትዳር እውን ሊሆኑ የማይችሉ ሐሳቦችን ከመያዝ ይልቅ እውነታውን ማሰብ ያስፈልጋችኋል። በሁለቱ አስተሳሰቦች መካከል ያለውን ልዩነት በምሳሌ ለመመልከት ቀጥሎ የቀረበውን መልመጃ ለመሥራት ሞክር፦
1. ወደፈለግከው ቦታ ለመጓዝ የሚያስችል ነፃ የአውሮፕላን ቲኬት አገኘህ እንበል። የት መሄድ ትፈልጋለህ? ለምን?
ቦታ፦
ምክንያት፦
-
መልክዓ ምድሩ
-
ባሕሉ
-
የአየሩ ጠባይ
-
መዝናኛው
-
ሌላ
2. አሁን ደግሞ፣ የአውሮፕላን ቲኬትህ መሄጃ ብቻ እንደሆነና የምትሄድበት ቦታ ለዘለቄታው መኖሪያህ እንደሚሆን አድርገህ አስብ።
አሁን ምርጫህ ምን ይሆናል?
-
ቦታ፦
-
ወይም
እዚሁ ብኖር ይሻለኛል።
ከላይ በቀረበው መልመጃ ላይ የመጀመሪያውና የሁለተኛው ምርጫህ የተለያየ ሊሆን ይችላል። ምርጫህ ተመሳሳይ ቢሆንም እንኳ ሁለተኛውን ውሳኔ ከማድረግህ በፊት ቆም ብለህ እንደምታስብ የታወቀ ነው። ሁለተኛውን ምርጫ በምታደርግበት ጊዜ የምታስበው ለመዝናናት ወደ ባሕር ዳርቻዎች ወይም ወደ ተራራማ አካባቢዎች እንደሚሄድ ጎብኚ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የአካባቢው ነዋሪ ስትሆን በዚያ ቦታ በዕለታዊ ሕይወትህ የሚያጋጥሙህን አስደሳችም ሆነ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተቀብለህ መኖር እንደሚገባህ ታስባለህ።
ስለ ትዳርም እንደዚህ ዓይነት አመለካከት ሊኖርህ ይገባል። ደግሞም ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ሁኔታዎች ሊለወጡ ይችላሉ። አንተና የትዳር ጓደኛህም እንደምትለወጡ ጥርጥር የለውም። በትዳር ውስጥ ያልጠበቃችሁት ነገር ሊያጋጥማችሁ እንደሚችል የምትጠብቁና ሁኔታዎቹን በተሳካ መንገድ መወጣት የምትችሉ ከሆነ ትዳራችሁ የሰመረ ይሆናል።
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ ነጠላ ከሆንህ በአሁኑ ጊዜ ያልተጠበቁ ነገሮች ሲያጋጥሙህ ሁኔታውን የምታስተናግደው እንዴት ነው?
ወላጆችህን ለምን አትጠይቃቸውም?
አዲስ ተጋቢዎች በነበራችሁበት ወቅት ምን ያልጠበቃችኋቸው አስደሳችና ተፈታታኝ ነገሮች አጋጥመዋችሁ ነበር? እኔ ባገባ ሊያጋጥሙኝ ለሚችሉ ያልተጠበቁ ነገሮች ራሴን ማዘጋጀት የምችለው እንዴት ነው?