በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥሩ ውጤት ለማምጣት መኮረጅ ስህተት ነው?

ጥሩ ውጤት ለማምጣት መኮረጅ ስህተት ነው?

ጥሩ ውጤት ለማምጣት መኮረጅ ስህተት ነው?

ተማሪ ነህ? ከሆነ አብረውህ ከሚማሩ ልጆች መካከል ጥሩ ውጤት ለማምጣት ሲሉ የሚኮርጁ እንዳሉ ሳታውቅ አትቀርም። ኩረጃ በጣም እየተስፋፋ የመጣ ችግር ሆኗል። በ2008፣ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ ጆሴፍሰን የተባለ አንድ ተቋም ወደ 30,000 በሚጠጉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ ጥናት አካሂዶ ነበር፤ በጥናቱ ላይ ከተካፈሉት 64 በመቶ የሚሆኑት በዚያ ዓመት በወሰዱት ፈተና ላይ እንደኮረጁ ተናግረዋል። ሆኖም ሌሎች ሰዎች ትክክለኛው አኃዝ ከዚህ እንደሚበልጥ ማለትም ከ75 በመቶ በላይ እንደሚሆን ይገምታሉ።

በአውሮፓም ቢሆን መኮረጅ በተለይም የሌሎች ሰዎችን ሥራ እንደ ራስ አድርጎ ማቅረብ አሳሳቢ እየሆነ የመጣ ችግር ሆኗል። ዲጂተም በተሰኘ በኢንተርኔት የወጣ ጽሑፍ ላይ የሚገኝ አንድ ርዕስ እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዟል፦ “ተማሪዎች የሚያስረክቧቸውን ጽሑፎች እንዲሁም የድህረ ምረቃ ተማሪዎች ማዘጋጀት ያለባቸውን የመመረቂያ ጽሑፎች እንደማንኛውም ሸቀጥ የሚሸጡ ድረ ገጾች መኖራቸው አዲስና አሳሳቢ እየሆነ የመጣ ችግር እንዲፈጠር አድርጓል።”

ይሁንና ኩረጃ ይህን ያህል ሊስፋፋ የቻለው ለምንድን ነው? በእርግጥ ኩረጃ ድርጊቱን የሚፈጽሙ ሰዎችን ይጠቅማቸዋል? አንድ ሰው ሐቀኛ በመሆኑ ምክንያት ዝቅተኛ ውጤት ቢያገኝም እንኳ እንዲህ ማድረጉ ጥቅም አለው?

ኩረጃ በጣም የተስፋፋው ለምንድን ነው?

የሥነ ምግባር እሴቶች እያዘቀጡ መሄዳቸው። አሜሪካን ስኩል ቦርድ ጆርናል የተሰኘ መጽሔት እንዲህ ብሏል፦ “በርካታ የትምህርት ባለሙያዎች፣ ኩረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሄደው ራስ ወዳድ በሆነ ማኅበረሰብ ውስጥ የሥነ ምግባር እሴቶች እያዘቀጡ በመሄዳቸው እንደሆነ ይናገራሉ።” አንዲት ተማሪ በምትማርበት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ጎበዝ ተማሪዎች ተመርጠው በሚማሩባቸው ክፍሎች ውስጥ ያሉትን ልጆች አስመልክታ እንዲህ በማለት በግልጽ ተናግራለች፦ “ሁላችንም . . . ኮርጀናል፤ ምክንያቱም ደህና ትምህርት ቤት ለመግባት ጥሩ ውጤት ማምጣት ያስፈልገናል። ጥሩዎችና መልካም ምግባር ያለን ተማሪዎች ነበርን፤ ሥነ ምግባር የሌለን ሰዎች አልነበርንም። . . . እንዲህ ያደረግነው ጥሩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ገብተን መማር ስለፈለግን ብቻ ነው።” አንዳንድ ወላጆችም እንኳ ይህ ወረርሽኝ “ተጋብቶባቸዋል።” ልጆቻቸው “ተሳክቶላቸው” ለማየት ስለሚጓጉ ኩረጃን ይደግፋሉ፤ አሊያም ልጆቻቸው እንደሚኮርጁ ቢያውቁም እንዳላወቁ ለመምሰል ይሞክራሉ። በዚህም ምክንያት የልጆቹ ሥነ ምግባር ይበልጥ እያሽቆለቆለ ይሄዳል።

እንዲሳካላቸው ግፊት የሚደረግባቸው መሆኑ። ኢንተርናሽናል ሴንተር ፎር አካዳሚክ ኢንተግሪቲ የተባለው ተቋም መሥራች የሆኑት ዶናልድ ማኬብ እንደገለጹት የሚኮርጁ ተማሪዎች ይህን የሚያደርጉት በሐቀኝነት የሚያገኙት ውጤት፣ ሳይያዙ ከሚኮርጁ ተማሪዎች ጋር ሲወዳደር ዝቅተኛ ስለሚሆን አለመኮረጃቸው ጉዳት እንደሚያስከትልባቸው ስለሚሰማቸው ነው።

የቴክኖሎጂ ውጤቶች ኩረጃን ቀላል ማድረጋቸው። ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተማሪዎች በቀላሉና በረቀቀ መንገድ እንዲኮርጁ አስችለዋቸዋል። ተማሪዎቹ የሚያስረክቧቸውን ጽሑፎች አሊያም የቤት ሥራዎቻቸውን መልስ ከኢንተርኔት ላይ ማግኘት እንዲሁም ከሌሎች ጋር መለዋወጥ ይችላሉ። ብዙውን ጊዜ ሲኮርጁ የሚያዙት በጣም ጥቂት በመሆናቸው ሌሎችም እንዲህ ለማድረግ ይደፋፈራሉ።

የሌሎች መጥፎ ምሳሌነት። በትላልቅ የንግድ ድርጅቶች፣ በፖለቲካና በስፖርቱ ዓለም አዋቂዎች ሲያጭበረብሩ መመልከት የተለመደ ነገር ነው፤ አልፎ ተርፎም ወላጆች በቤት ውስጥ ከግብር ወይም ከኢንሹራንስ ጋር በተያያዘ ሲያታልሉ ልጆች ይመለከታሉ። ዘ ቺቲንግ ካልቸር የተባለው መጽሐፍ ደራሲ የሆኑት ዴቪድ ካለሃን “ባለሥልጣናት ወይም እንደ ምሳሌ የሚታዩ ሰዎች ያጭበረብራሉ፤ ይህ ደግሞ ለወጣቶች ማጭበርበር ችግር የለውም የሚል መልእክት እንደሚያስተላልፍ ይሰማኛል” በማለት ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ማታለል ችግር የለውም? ደግሞስ ጥሩ ውጤት ለማግኘት ተብሎ መደረጉ ኩረጃን ትክክል ያደርገዋል?

አንድ ሰው መኮረጅ የሌለበት ለምንድን ነው?

‘የጥሩ ትምህርት ዓላማ ምንድን ነው?’ በማለት ራስህን ጠይቅ። ዓላማው በሥራ ቦታ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለይቶ እንደማወቅና መፍትሔ እንደመፈለግ ላሉ በሕይወት ውስጥ ለሚያጋጥሙ በርካታ ኃላፊነቶች ተማሪዎችን ማዘጋጀት አይደለም? የመኮረጅ ልማድ ያላቸው ተማሪዎች እነዚህን አስፈላጊ ችሎታዎች ሳይማሩ ይቀራሉ። በመሆኑም የማጭበርበር ልማድ የተጠናወታቸው ሰዎች ድክመታቸውን ስለሚደብቁ በተለያዩ የሕይወታቸው ዘርፎች ስኬት ሊያገኙባቸው የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች ያጣሉ።

ከዚህ የከፋው ደግሞ “ገና ከትንሽነታቸው ጀምሮ ችግሮችን ለመፍታት አቋራጭ መንገዶችን የሚጠቀሙ ልጆች ለምሳሌ በትምህርት ቤት የሚኮርጁ፣ ወደ ሥራው ዓለም ሲገቡም ይህን ልማዳቸውን ይዘው ሊመጡ ይችላሉ” በማለት ካለሃን ይናገራሉ። እንዲህ ያሉ ሰዎች ታዋቂ የንግድ ምልክት ከተለጠፈበት ልብስ ወይም የእጅ ሰዓት ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ፤ ምልክቱ እውነተኛ አለመሆኑን ስናውቅ መናደዳችን አይቀርም።

እርግጥ ነው፣ አጭበርባሪዎች ሊደረስባቸውና የእጃቸውን ሊያገኙ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ እንዲያፍሩና እንዲሸማቀቁ ያደርጋቸዋል። በተጨማሪም ከትምህርት ቤት መባረር አሊያም ከዚያ የከፋ ቅጣት ሊደርስባቸው ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል” በማለት በግልጽ ያስጠነቅቃል። (ገላትያ 6:7) ይሁን እንጂ አንድን ሰው ሐቀኛ ለመሆን የሚያነሳሳው ዋነኛ ምክንያት ሲያታልል እንዳይደረስበት ያለው ፍራቻ መሆን የለበትም። ሐቀኛ ለመሆን የሚያነሳሱን ከዚህ የበለጡ ምክንያቶች አሉ።

ሐቀኝነት—ለስኬት የሚያበቃ እውነተኛ ቁልፍ

ጠቢብ የሆኑ ወጣቶች ጥሩ ውጤት ለማግኘት ብቻ ሳይሆን በሕይወታቸው ሙሉ ሊጠቅሟቸው የሚችሉ ባሕርያትን ለማዳበር ይጣጣራሉ። በመሆኑም በትምህርት ቤት ሳሉ ጠንክረው የሚሠሩ ሲሆን ለራሳቸው አክብሮት እንዲኖራቸው የሚያደርጉ የሥነ ምግባር እሴቶችን ለማዳበር ጥረት ያደርጋሉ፤ ይህ ደግሞ ሥራ ሲይዙ በአሠሪዎቻቸው ዘንድ ጥሩ ስም የሚያተርፍላቸው ከመሆኑም በላይ ዘላቂ ደስታ ያስገኝላቸዋል።

እነዚህ የሥነ ምግባር እሴቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን በእነዚህ መመሪያዎች ሕይወታቸውን የሚመሩ ወጣቶችም ጉዳት አይደርስባቸውም። ከዚህ በተቃራኒ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17 እንደሚናገረው “ለማንኛውም መልካም ሥራ በሚገባ በመታጠቅ ሙሉ በሙሉ ብቁ” ይሆናሉ። ሆርሃ የሚባል አንድ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ እንደሚከተለው ብሏል፦ “የክፍሌ ተማሪዎች ምንም ሳይለፉ ጥሩ ውጤት ለማግኘት ስለሚፈልጉ ይኮርጃሉ። እኔ ግን አምላክን ማስደሰት እፈልጋለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ በ⁠ምሳሌ 14:2 ላይ ‘አካሄዱ ቅን የሆነ ሰው እግዚአብሔርን ይፈራል፤ መንገዱ ጠማማ የሆነ ግን ይንቀዋል’ በማለት ይናገራል። ከአምላክ ምንም ነገር መደበቅ እንደማንችል አውቃለሁ። ስለዚህ አልኮርጅም እንዲሁም ሌሎች እንዲኮርጁ አልረዳም።”

ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምተው ለመኖር ጥረት የሚያደርጉ ልጆች ጎበዝ ተማሪ ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ። ይሁን እንጂ በሕይወታቸው ውስጥ ዘላቂ ለሆነ ስኬት ጽኑ መሠረት እየጣሉ ስለሆነ ጥበበኞች ናቸው። (መዝሙር 1:1-3፤ ማቴዎስ 7:24, 25) ከዚህም በላይ የፈጣሪን ሞገስና ድጋፍ እንደሚያገኙ እርግጠኞች መሆን ይችላሉ።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ሊታሰብባቸው የሚገቡ መመሪያዎች

● “እውነት የሚናገሩ ከንፈሮች ለዘላለም ጸንተው ይኖራሉ፤ ሐሰተኛ አንደበት ግን ለቅጽበት ያህል ብቻ ነው።”​—ምሳሌ 12:19

● “ታማኝ ሰው እጅግ ይባረካል።”​—ምሳሌ 28:20

● “መልካምም ይሁን ክፉ፣ ስውር የሆነውን ነገር ሁሉ አንድ ሳይቀር፣ ማንኛውንም ሥራ እግዚአብሔር ወደ ፍርድ ያመጣዋል።”​—መክብብ 12:14

● “በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር [እንመኛለን]።”​—ዕብራውያን 13:18

[በገጽ 26 እና 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተማሪዎች በቀላሉና በረቀቀ መንገድ እንዲኮርጁ አስችለዋቸዋል

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሚኮርጁ ተማሪዎች ታዋቂ የንግድ ምልክት በሐሰት ከተለጠፈበት የእጅ ሰዓት ጋር ይመሳሰላሉ፤ ከላይ ሲታዩ ጥሩ ይመስላሉ