ዕድሜዬ የአምላክ ወዳጅ ከመሆን አላገደኝም
ዕድሜዬ የአምላክ ወዳጅ ከመሆን አላገደኝም
ኦላቪ ዮሐንስ ማቲላ እንደተናገሩት
“ስለ ፈጣሪ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት እንደሚቻል አስበው ያውቃሉ?” ይህን ጥያቄ ያቀረበልኝ አንድ የይሖዋ ምሥክር ነበር፤ ጥያቄው በጉዳዩ ላይ ቆም ብዬ እንዳስብ አደረገኝ። በወቅቱ ዕድሜዬ ከ80 ዓመት በላይ ሲሆን በጣም ታዋቂ ከሆኑ በርካታ ሰዎች አልፎ ተርፎም ከፖለቲካ መሪዎች ጋር መተዋወቅ ችዬ ነበር። ይሁን እንጂ በዚህ ዕድሜዬ በእርግጥ አምላክን ማወቅና የእሱ ወዳጅ መሆን እችላለሁ?
የተወለድኩት ጥቅምት 1918 ፊንላንድ ውስጥ በምትገኘው በሃይቪንካአ ከተማ ነው። ከግብርና ጋር የተያያዙ በርካታ ሥራዎችን በመሥራት ቤተሰቤን ማገዝ የጀመርኩት ገና በለጋ ዕድሜዬ ነበር። ቤተሰቤ የቀንድ ከብት፣ ፈረሶች፣ ዶሮና ዝይ ያረባ ነበር። ከልጅነቴ ጀምሮ ቤተሰቤን እረዳ የነበረ መሆኑ ተግቶ መሥራትንና በሥራ መደሰትን እንድማር አድርጎኛል።
በዕድሜ ከፍ እያልኩ ስሄድ ወላጆቼ በትምህርቴ እንድገፋ አበረታቱኝ። ስለዚህ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ የኮሌጅ ትምህርት ለመከታተል ከቤተሰቤ ተለይቼ ሄድኩ። በአትሌቲክስ ስፖርትም እካፈል ስለነበር የፊንላንድ የአትሌቲክስ ማኅበር ሊቀ መንበር ከነበረው ከኡርሃ ኬከነን ጋር ተዋወቅሁ። የሚገርመው ሚስተር ኬከነን በኋላ ላይ የፊንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆነ ሲሆን ቆየት ብሎም የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በመሆን ለ30 ዓመታት አገልግሏል። ሚስተር ኬከነን በእኔ ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል ብዬ በጭራሽ አላሰብኩም ነበር።
ታዋቂነትና ሥልጣን
በ1939 በፊንላንድና በሶቪየት ኅብረት መካከል ጦርነት ፈነዳ። በዚያው ዓመት በኅዳር ወር ላይ በጦር ሠራዊቱ ውስጥ እንዳገለግል ተመለመልኩ። መጀመሪያ ላይ በተጠባባቂ ሠራዊቱ ውስጥ በአሠልጣኝነት ከዚያም የመትረየስ ተኳሽ ቡድን አዛዥ በመሆን አገልግያለሁ። የጦር ግንባሩ የሚገኘው በፊንላንድና በሶቪየት ኅብረት ድንበር መካከል ባለችው በካሪሊያ ነበር። በ1941 ክረምት ላይ በቪቦርግ ከተማ አቅራቢያ ውጊያ እየተካሄደ ሳለ በቦንብ ፍንጣሪ ክፉኛ ስለቆሰልኩ ወደ አንድ ወታደራዊ ሆስፒታል ተወሰድኩ። በደረሰብኝ ጉዳት የተነሳ ተመልሼ በውጊያው መካፈል አልቻልኩም።
መስከረም 1944 ከሠራዊቱ ስሰናበት ወደ ኮሌጅ ትምህርቴ ተመለስኩ። በአትሌቲክስ ስፖርት መካፈሌንም ቀጠልኩ። በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄዱ ውድድሮች ላይ ሦስት ጊዜ ይኸውም ሁለት ጊዜ በዱላ ቅብብል አንድ ጊዜ ደግሞ በመሰናክል ሩጫ ሻምፒዮን መሆን ችያለሁ። በተጨማሪም በቴክኖሎጂና በኢኮኖሚክስ ዲግሪዬን አገኘሁ።
በዚህ መሃል፣ ኡርሃ ኬከነን በፖለቲካው ውስጥ ጉልህ ስፍራ ያለው ሰው ሆኖ ነበር። ሚስተር ኬከነን በ1952 በጠቅላይ ሚኒስትርነት በሚያገለግልበት ወቅት በቻይና ዲፕሎማት ሆኜ እንድሠራ ጠየቀኝ። እዚያ እያለሁ በወቅቱ የቻይና መሪ የነበሩትን ማኦ ሴቱንግን ጨምሮ ከአያሌ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ተዋውቄያለሁ። ሆኖም በቻይና ካገኘኋቸው ሰዎች ሁሉ አስበልጬ የማያት በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ትሠራ የነበረችውን አኒኪ የተባለችን አንዲት ቆንጆ ወጣት ሴት ነበር። በመሆኑ ከአኒኪ ጋር ኅዳር 1956 ተጋባን።
በቀጣዩ ዓመት አርጀንቲና ወደሚገኘው የፊንላንድ ኤምባሲ ተዛወርኩ። እዚያ ሳለን የመጀመሪያዎቹን ሁለት ወንዶች
ልጆቻችን ወለድን። ጥር 1960 ወደ ፊንላንድ ተመለስን። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ሦስተኛዋ ልጃችን ተወለደች።ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ሆኜ ተሾምኩ
የየትኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆኜ ባላውቅም ኅዳር 1963 ፕሬዚዳንት ኬከነን የውጭ ንግድ ሚኒስትር ሆኜ እንዳገለግል ግብዣ አቀረበልኝ። በቀጣዮቹ 12 ዓመታት ስድስት ጊዜ በሚኒስትርነት የተሾምኩ ሲሆን ሁለት ጊዜ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኜ ሠርቻለሁ። በወቅቱ የዓለም ችግሮች በሰው ልጆች ጥረት ሊፈቱ ይችላሉ የሚል ጽኑ እምነት ነበረኝ። ይሁን እንጂ ሰው ምን ያህል የሥልጣን ጥመኛ እንደሆነ በደንብ ለመገንዘብ ጊዜ አልፈጀብኝም። አለመተማመንና ቅናት ጎጂ ውጤት እንደሚያስከትሉ ራሴ ካየሁት ነገር መመሥከር እችላለሁ።—መክብብ 8:9
እርግጥ ነው፣ በቅንነት ተነሳስተው ነገሮችን ለማሻሻል የሚጥሩ ብዙ ሰዎች እንዳሉም ተመልክቻለሁ። ይሁንና ሕዝባቸውን ለማገልገል ከልብ የሚጥሩ መሪዎችም እንኳ ያሰቡት ግብ ላይ ሳይደርሱ ይቀራሉ።
በ1975 ክረምት ላይ በአውሮፓ የደኅንነትና የትብብር ኮንፈረንስ ላይ ለመገኘት 35 የአገር መሪዎች ወደ ሄልሲንኪ መጥተው ነበር። በዚያን ጊዜ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የፕሬዚዳንት ኬከነን የቅርብ አማካሪ ነበርኩ። ስብሰባውን የማደራጀት ኃላፊነት የተሰጠው ለእኔ ሲሆን በኮንፈረንሱ ላይ ከተገኙት ከሁሉም የአገር መሪዎች ጋር የመገናኘት አጋጣሚ አግኝቻለሁ።
በእነዚያ ጥቂት ቀናት ውስጥ ዲፕሎማሲያዊ ብቃቴን የሚፈታተኑ ነገሮች አጋጥመውኛል። ልዑካኑ የሚሰጣቸውን ቦታ ለመቀበል ፈቃደኞች እንዲሆኑ ማግባባት በራሱ እንኳ በጣም አስቸጋሪ ነበር! ያም ሆኖ ኮንፈረንሱና ከዚያ በኋላ የተደረጉት ተከታታይ ስብሰባዎች ለሰብዓዊ መብት መሻሻልና በልዕለ ኃያላን አገሮች መካከል መቻቻል የሰፈነበት ግንኙነት እንዲኖር ለማድረግ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ተሰምቶኝ ነበር።
ለመንፈሳዊ ፍላጎቴ ትኩረት መስጠት ጀመርኩ
በ1983 ጡረታ ስወጣ ሴት ልጄ ወደምትኖርበት ወደ ፈረንሳይ ተዛውረን መኖር ጀመርን። እዚያ እያለን አሳዛኝ ነገሮች አጋጠሙን። ኅዳር 1994 አኒኪ የጡት ካንሰር እንዳለባት ታወቀ። በዚያው ዓመት ደግሞ አንድ ሌላ ችግር አጋጠመኝ፤ የማጭበርበር ድርጊት እንዳለበት ሳላውቅ በአንድ ኢንቨስትመንት ውስጥ ገባሁ። ጥሩ ስም ይዤ ለመኖር ዕድሜዬን ሙሉ ጥረት ሳደርግ ብቆይም በዚህች አንዲት ስህተት የተነሳ መልካም ስሜ ጎደፈ።
የይሖዋ ምሥክሮች ብዙ ጊዜ ያጋጥሙኝ ነበር። ሊያነጋግሩኝ መምጣታቸውን የማደንቅና መጽሔቶቻቸውን የምቀበል ቢሆንም በጣም ሥራ ስለሚበዛብኝ ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ጊዜ አልነበረኝም። በ2000 ላይ ግን በካንሰር ሕመም የምትሠቃየውን ባለቤቴን ለመንከባከብ ይበልጥ ትኩረት መስጠት ጀመርኩ። በ2002 መስከረም ውስጥ አንድ የይሖዋ ምሥክር መጥቶ አነጋገረኝ። እሱም በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኩትን ጥያቄ ጠየቀኝ። እኔም ‘በእርግጥ ስለ አምላክ እውነቱን ማወቅ ይቻላል? የእሱ ወዳጅ መሆንስ የሚቻል ነገር
ነው?’ ብዬ አሰብኩ። አቧራ ሲጠጣ የከረመውን መጽሐፍ ቅዱሴን ፈልጌ በማውጣት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር አዘውትሬ ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይቶችን ማድረግ ጀመርኩ።ሰኔ 2004 ውድ ባለቤቴን በሞት በማጣቴ ብቻዬን ቀረሁ። እርግጥ ነው፣ ልጆቼ ስሜታዊ ድጋፍ አድርገውልኛል። ያም ሆኖ ‘ስንሞት ምን እንሆናለን?’ የሚለው ጥያቄ ያሳስበኝ ነበር። ስለዚህ ጉዳይ ሁለት የሉተራን ቄሶችን ጠይቄ ነበር። እነሱም “ይህ ከባድ ጥያቄ ነው” ከማለት ውጪ የሰጡኝ መልስ አልነበረም። ይሁንና በተናገሩት ነገር አልረካሁም። እኔ ግን ለመንፈሳዊ ነገሮች ያለኝ ፍላጎት ይበልጥ እየጨመረ መጣ።
ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስቀጥል የጓጓሁለትን ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ጀመርኩ። ለምሳሌ ያህል፣ ሞት ከእንቅልፍ ጋር እንደሚመሳሰል እንዲሁም ሙታን ምንም ነገር እንደማያውቁና ተስፋቸው ትንሣኤ አግኝቶ በምድር ላይ ዳግመኛ መኖር እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተረዳሁ። (ዮሐንስ 11:25) ይህን ማወቄ ተስፋ የሰጠኝ ከመሆኑም በላይ በእጅጉ አጽናንቶኛል።
ብዙም ሳይቆይ መጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ በሙሉ አንብቤ ጨረስኩ። ትኩረቴን ከሳቡት ጥቅሶች መካከል አንዱ ሚክያስ 6:8 ሲሆን ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ አይደለምን?” ይህ ጥቅስ የሚያስተላልፈው መልእክት ያልተወሳሰበና ጥበብ ያዘለ መሆኑ ልቤን ማረከው። በተጨማሪም ይሖዋ ምን ያህል አፍቃሪና ፍትሐዊ አምላክ መሆኑን እንድገነዘብ ረዳኝ።
ስለ መጪው ጊዜ ያለኝ ተስፋ
ስለ አምላክ እውነቱን እየተማርኩ ስሄድ እምነቴና በእሱ ላይ ያለኝ የመተማመን ስሜት እያደገ መጣ። ከፈጣሪዬ ጋር እውነተኛ ወዳጅነት መሠረትኩ! ይሖዋ በኢሳይያስ 55:11 ላይ “ከአፌ የሚወጣውም ቃሌ፣ በከንቱ ወደ እኔ አይመለስም፤ ነገር ግን የምሻውን ያከናውናል፤ የተላከበትንም ዐላማ ይፈጽማል” በማለት የተናገረው ሐሳብ ትኩረቴን ሳበው። በእርግጥም አምላክ እስከዛሬ ድረስ የገባቸውን ተስፋዎች ሲፈጽም ኖሯል፤ ወደፊትም ቢሆን እንዲሁ ያደርጋል። ሰብዓዊ መንግሥታት በርካታ ፖለቲካዊ ኮንፈረንሶችን በማካሄድ መፍትሔ ሊያገኙላቸው ያልቻሏቸውን ችግሮች አምላክ ያስወግዳቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ መዝሙር 46:9 “[አምላክ] ከዳር እስከ ዳር ጦርነትን ከምድር ያስወግዳል” ይላል።
በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ በመገኘቴ በእጅጉ ተጠቅሜያለሁ። በዚህ ወቅት፣ የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች መለያ የሆነውን እውነተኛ ክርስቲያናዊ ፍቅር በገዛ ዓይኔ ማየት ችያለሁ። (ዮሐንስ 13:35) ይህ ፍቅር ከብሔራዊ ስሜት እጅግ የላቀና በፖለቲካውና በንግዱ ዓለም ጨርሶ የሌለ ነው።
ከሁሉ የላቀ ውድ መብት
አሁን ዕድሜዬ ከ90 ዓመት በላይ ሲሆን ከይሖዋ ምሥክሮች መካከል እንደ አንዱ መቆጠሬ እስከዛሬ ካገኘኋቸው መብቶች ሁሉ እጅግ የላቀ እንደሆነ ይሰማኛል። መንፈሳዊ ፍላጎቴ ተሟልቶልኛል። ስለ ሕይወት ዓላማና ስለ አምላክ እውነቱን የመማር መብት አግኝቻለሁ።
በዚህ ዕድሜዬም እንኳ በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ንቁ ተሳትፎ ማድረግ በመቻሌ ደስተኛ ነኝ። ምንም እንኳ ከበርካታ ታላላቅ ሰዎች ጋር የተዋወቅኩ እንዲሁም ከባድ ኃላፊነቶችን የተወጣሁ ቢሆንም ፈጣሪ የሆነውን ይሖዋ አምላክን ከማወቅና የእሱ ወዳጅ ከመሆን መብት ጋር የሚወዳደር ምንም ነገር የለም። ይሖዋ ላደረገልኝ ነገር በጣም አመስጋኝ ነኝ፤ እንዲሁም ከእሱ ጋር ‘አብረው ከሚሠሩት’ መካከል አንዱ የመሆን መብት በማግኘቴ እሱን ለማወደስ እገፋፋለሁ። (1 ቆሮንቶስ 3:9) ዕድሜዬ፣ ፈጣሪ ከሆነው ከይሖዋ አምላክ ጋር ወዳጅነት ከመመሥረት አላገደኝም!
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1975 የሄልሲንኪ ኮንፈረንስ ወቅት ከፕሬዚዳንት ኬከነንና ከዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ከፎርድ ጋር
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከፕሬዚዳንት ኬከነንና ከሶቪየት መሪ ከብርዥኔቭ ጋር
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ንቁ ተሳትፎ አደርጋለሁ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Lower left: Ensio Ilmonen/Lehtikuva; lower right: Esa Pyysalo/Lehtikuva