የወጣቶች ጥያቄ
‘ምነው አፌን በቆረጠው!’ ብለህ ታውቃለህ?
ይህ ርዕስ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ይረዳሃል
አንዳንድ ጊዜ ተገቢ ያልሆነ ነገር የምትናገረው ለምንድን ነው?
አምልጦህ ብትናገር ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
አንደበትህን መግራት የምትችለው እንዴት ነው?
“አብዛኛውን ጊዜ አንደበቴን በመቆጣጠር ረገድ ይሳካልኛል፤ አንዳንድ ጊዜ ግን አምልጦኝ አንድ ነገር እናገርና ከዚያ በኋላ የምገባበት ይጠፋኛል!”—ቼስ
“አንዳንድ ጊዜ ሁሉም ሰው በልቡ ቢያስበውም ማንም ለመናገር ያልደፈረውን ጉዳይ እኔ ፍርጥርጥ አደርገዋለሁ። . . . በኋላ ላይ ግን ስቅቅ እላለሁ።”—አሊስ
ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው?
ቁልፍ ጥቅስ፦ “በንግግሩ የማይሳሳት፣ እርሱ . . . ፍጹም ሰው ነው።” (ያዕቆብ 3:2 የ1980 ትርጉም) የዚህ ጥቅስ ፍሬ ነገር ምንድን ነው? አንደበቱን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር የሚችል ማንም የለም። አኔት * የተባለች ወጣት፣ ያሰበችውን ነገር እንዳመጣላት የምትናገርበት ጊዜ እንዳለ ገልጻለች፤ ብዙ ሰዎች እንደ እሷ ይሰማቸዋል።
እውነተኛ ታሪክ፦ “አንዲት ጓደኛዬ እኔ የማልጠቀምባቸውን አንዳንድ ልብሶች ልትወስዳቸው እንደምትፈልግ ነገረችኝ። እኔም ቆም ብዬ ሳላስብ ‘ልክሽ የሚሆኑ አይመስለኝም’ አልኳት። እሷም ‘እንዴ? አንቺ ትወፍሪያለሽ ማለትሽ ነው?’ አለችኝ።”—ኮሪን
ቀጥሎ የቀረቡት ሐሳቦች አንተም አንዳንድ ጊዜ ‘ምነው አፌን በቆረጠው!’ የምትልበት ሁኔታ የሚያጋጥምህ ለምን እንደሆነ ለማወቅ ይረዱሃል፦
● ድክመትህን ለይተህ እወቅ።
․․․․․ ስናደድ መናገር ይቀናኛል
․․․․․ ሳላስብ መናገር ይቀናኛል
․․․․․ ሳላዳምጥ መናገር ይቀናኛል
․․․․․ ሌላ ․․․․․
ምሳሌ፦ “ከልክ በላይ የመቀለድ ችግር አለብኝ፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሰዎች የተናገርኩትን ነገር በተሳሳተ መንገድ ይረዱታል።”—አሌክሲስ
● አብዛኛውን ጊዜ አፍህ ላይ እንደመጣልህ የምትናገረው ከእነማን ጋር ስትሆን እንደሆነ ለይተህ እወቅ።
․․․․․ ከወላጆችህ
․․․․․ ከወንድምህ ወይም ከእህትህ
․․․․․ ከጓደኛህ
․․․․․ ሌላ ․․․․․
ምሳሌ፦ “የሚያሳዝነው ነገር በንግግሬ ብዙውን ጊዜ የምጎዳው በጣም የምወዳቸውን ሰዎች ነው” በማለት የ20 ዓመቷ ክሪስቲን ተናግራለች። “ይህ የሚሆነው ከእነሱ ጋር ስሆን ዘና ስለምልና ለንግግሬ ያን ያህል ስለማልጨነቅ ይመስለኛል።”
አምልጦህ ብትናገር ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
ቁልፍ ጥቅስ፦ “ሰላም የሚገኝበትን . . . ነገር ለማድረግ የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናድርግ።” (ሮም 14:19) ይህን ምክር መከተል የሚቻልበት አንዱ መንገድ ይቅርታ መጠየቅ ነው።
እውነተኛ ታሪክ፦ “እናቴ የሞተችው ገና የአሥር ወር ሕፃን እያለሁ ሲሆን ከአባቴም ጋር ጨርሶ አንገናኝም ነበር፤ በመሆኑም ያሳደጉኝ አክስቴና ባሏ ናቸው። የ10 ወይም የ11 ዓመት ልጅ እያለሁ የብቸኝነት ስሜት የተሰማኝና እናቴ በመሞቷ በጣም የተበሳጨሁበት ጊዜ ነበር፤ በወቅቱ የሆነ ሰው ላይ ንዴቴን ለመወጣት ሰበብ ነበር የምፈልገው። በዚህም ምክንያት አክስቴ ጠርታኝ አንድ ነገር እንዳግዛት ስትጠይቀኝ መነጫነጭ ጀመርኩ፤ በመጨረሻም ‘አልወድሽም፣ አንቺኮ እናቴ አይደለሽም!’ ብዬ ጮኽኩባት። አክስቴም ክው ብላ ቀረች። ከዚያም ወደ መኝታ ቤቷ ሄዳ በሩን ዘጋችው፤ ውስጥ ሆና ስታለቅስ ይሰማኝ ነበር። በሁኔታው በጣም አዘንኩ። አክስቴ ያሳደገችኝ ከመሆኑም ሌላ ከእኔ ስትል የማትሆነው ነገር አልነበረም፤ እኔ ግን በጣም ጎዳኋት። በኋላ ላይ የአክስቴ ባል ስለ ሁኔታው አንስቶ አነጋገረኝ፤ እንዲሁም አንደበትን ለመቆጣጠር የሚረዱ ጥቅሶችን አሳየኝ። ከዚያ በኋላ አክስቴን ከልብ ይቅርታ ጠየቅኋት። ጥፋተኛ መሆኔን አምኜ መቀበል ነበረብኝ።”—ካረን
ይቅርታ መጠየቅን ከባድ ሊያደርግብህ የሚችል አንድ ምክንያት ከዚህ በታች ጻፍ፦
․․․․․
ይቅርታ መጠየቅህ ጥሩ ስሜት እንዲሰማህ ሊያደርግ የሚችለው ለምንድን ነው?
․․․․․
ፍንጭ፦ በምሳሌ 11:2 እና በማቴዎስ 5:23, 24 ላይ የሚገኙትን ሐሳቦች ልብ በል።
እርግጥ ነው፣ መጀመሪያውኑ ሌሎችን የሚያሳዝን ነገር ላለመናገር መጠንቀቅ በኋላ ይቅርታ ከመጠየቅ ይቀላል። ታዲያ ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
አንደበትህን መግራት የምትችለው እንዴት ነው?
ቁልፍ ጥቅስ፦ “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየና ለቁጣ የዘገየ መሆን አለበት።” (ያዕቆብ 1:19) ይህን ምክር ተግባራዊ እንድታደርግ የሚረዱህ አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦች ቀጥሎ ቀርበዋል።
ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ጥቅሶች አንብብና ከሐሳቦቹ ጋር አዛምድ።
መክብብ 7:9 □
1 “ራስህን ያለ ልክ ከፍ አድርገህ አትመልከት፤ እንዲህ ከሆነ ሌሎች በሚናገሩት ነገር በቀላሉ አትጎዳም።”—ዳኔት
2 “ከቤት ወጥቼ በእግሬ ዞር ዞር እላለሁ። ይህም ለተወሰነ ጊዜ ብቻዬን ለመሆን አጋጣሚ ስለሚሰጠኝ ንዴቴ ቀስ በቀስ ይበርድልኛል።”—ብሪኤል
3 “ትንሽ ልጅ ሳለሁ ያልተስማማሁበትን ነገር ሁሉ መናገር እንዳለብኝ ስለሚሰማኝ በሆነ ባልሆነው እከራከር ነበር። አሁን ግን ነገሮችን ችላ ብዬ ማለፍ እንደሚሻል ተምሬያለሁ።”—ሲልያ
4 “አንድ ሰው እየጮኸብህ አንተ ግን መልስ የማትሰጥ ከሆነ ሰውየው ሲሰለቸው ትቶህ ይሄዳል። ስለዚህ ታጋሽ ሁን፤ በእሳቱ ላይ ነዳጅ አትጨምርበት።”—ኬረን
5 “አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ያበሳጩኛል። በዚህ ጊዜ ያበሳጨኝን ሰው ምን እንደምለው አብሰለስላለሁ። ቆየት ብዬ ግን ልናገር ያሰብኩት ነገር ምን ያህል ፍሬ ቢስ እንደሆነ እገነዘባለሁ። ከዚህ የተማርኩት ነገር መልስ ለመስጠት መቸኮል እንደሌለብኝ ነው።”—ቻርልስ
www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚለው ዓምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን በእንግሊዝኛ ማግኘት ይቻላል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.10 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
አሊስ—አንድ ነገር ከመናገሬ በፊት ራሴን እንዲህ ብዬ እጠይቃለሁ፦ ‘መናገሬ ጥቅም ይኖረዋል? የምናገረው ነገር፣ አብሮኝ ያለው ሰው ምን እንዲሰማው ያደርጋል?’ ልትናገሩት ያሰባችሁት ነገር ስለሚፈጥረው ስሜት እርግጠኞች ካልሆናችሁ ዝም ብትሉ ይሻላል።
ቼስ—አንድ ነገር መናገር ስፈልግ አብረውኝ ባሉት ሰዎች ላይ ስለሚፈጥረው ስሜት ለማሰብ እሞክራለሁ። እያደግሁ ስሄድ አንደበቴን በመቆጣጠር ረገድ እየተሻሻልኩ እንደሆነ ይሰማኛል። ከዚህ ቀደም ያጋጠሙን ነገሮች እንደሚያስተምሩን ግልጽ ነው።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ወላጆችህን ለምን አትጠይቃቸውም?
ፍጹም የሆነ ሰው ስለሌለ ያዕቆብ እንደተናገረው “ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለን።” ወላጆችህ አንደበታቸውን ለመግራት ምን ያህል ጥረት ማድረግ እንዳስፈለጋቸው ጠይቃቸው።—ያዕቆብ 3:2
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“የጥርስ ሳሙናን አንዴ ካወጣኸው በኋላ መመለስ አትችልም። በንግግር ረገድም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አንዴ አምልጦን የሚያስቀይም ነገር ከተናገርን ልንመልሰው አንችልም።”—ጄምስ