ኢብን ባቱታ እና በዘመኑ የነበረው ዓለም
ኢብን ባቱታ እና በዘመኑ የነበረው ዓለም
በ1325 አንድ ወጣት ቻይናን፣ ሕንድን፣ ኢንዶኔዥያን፣ ማሊን፣ ፋርስን፣ ሩስያን፣ ሶርያን፣ ታንዛንያን፣ ቱርክንና የአረብ አገሮችን በሙሉ ጨምሮ በዘመኑ ይታወቅ በነበረው ዓለም በጣም ርቀው የሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎችን ያዳረሰ ጉዞውን ለመጀመር በሞሮኮ ከምትገኘው ከታንጂር ተነሳ። ይህ ወጣት አቡ አብደላ ኢብን ባቱታ የሚባል ሲሆን በጠቅላላው 120,700 ኪሎ ሜትሮች ገደማ ተጉዟል፤ የእንፋሎት ሞተሮች ከመሠራታቸው በፊት በነበረው በዚያ ዘመን ይህን የሚያክል ርቀት መጓዝ ተሰምቶ የማያውቅ ነገር ነበር።
ኢብን ባቱታ ታላቁ የእስላም ተጓዥ ተብሎ ከመጠራቱም በላይ በቅድመ ዘመናዊው ዓለም ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ተጓዥ ሆኗል። ይህ ሰው ከ30 ዓመት ጉዞ በኋላ ወደ አገሩ ሲመለስ የተጻፈው ስላደረጋቸው ጉዞዎች የሚገልጸው ማስታወሻ በ14ኛው መቶ ዘመን ስለነበረው አኗኗርና ባሕል በተለይም በመካከለኛው ዘመን ስለነበረው እስላማዊ ዓለም ብዙ እውቀት እንዲገኝ አስችሏል።
ወደ መካ የተደረገ መንፈሳዊ ጉዞ
ኢብን ባቱታ ቅዱስ ስፍራዎችን ለመጎብኘት እንዲሁም የገንዘብ አቅምና ጉልበት ያለው ለአካለ መጠን የደረሰ ማንኛውም ሙስሊም ማድረግ እንደሚጠበቅበት ሁሉ ወደ መካ የሐጅ ጉዞ ለማድረግ ከታንጂር ተነሳ። መካ የምትገኘው ከታንጂር በስተ ምሥራቅ 4,800 ኪሎ ሜትር ርቃ ነበር። አብዛኞቹ ተጓዦች ያደርጉ እንደነበረው ሁሉ ኢብን ባቱታም ራሱን ከአደጋ ለመጠበቅ ከሌሎች ተጓዦች ጋር በቡድን ሆኖ ይጓዝ ነበር።
የኢብን ባቱታ አባት፣ ቃዲ ወይም የአካባቢ ዳኛ ስለነበር ኢብን ባቱታም በታንጂር ከሁሉ የተሻለ ነው የሚባለውን የቃዲ ትምህርት ተከታትሏል። የጉዞ ባልደረቦቹም ይህን ስላወቁ በመንገድ ላይ በመካከላቸው የሚፈጠረውን ማንኛውንም አለመግባባት እንዲዳኝ ሾመውት ነበር።
ወደ እስክንድርያ፣ ካይሮና ላይኛው አባይ
ተጓዦቹ የሰሜን አፍሪካን የባሕር ዳርቻ ተከትለው ወደ ግብፅ አቀኑ። በዚህ ወቅት ኢብን ባቱታ በግብፅ የሚገኘውን ከጥንቱ ዓለም ድንቅ ሥራዎች አንዱ የሆነውን የእስክንድርያ ዝነኛ የወደብ ላይ የመብራት ማማ የማየት አጋጣሚ አግኝቶ ነበር፤ እርግጥ ይህ ማማ በዚያ ጊዜ በከፊል ፈርሶ ነበር። እሱ እንዳለው ካይሮ “በሕንጻዎቿ ብዛት አቻ የሌላት፣ በውበቷና በድምቀቷ ተወዳዳሪ የማይገኝላት፣ መጪውና ሂያጁ የሚገናኝባት፣ ብርቱውና ደካማው በአንድ ላይ የሚኖርባት፣ ሕዝቦቿ እንደ ባሕር ሞገድ የሚተራመሱባት” ከተማ ነበረች። የዚህችን ታላቅ ከተማ ጀልባዎች፣ የአትክልት ቦታዎች፣ መደብሮች፣ ሃይማኖታዊ ስፍራዎችና ባሕሎች በእጅጉ አድንቋል። በሌሎች አካባቢዎች ያደርግ እንደነበረው ሁሉ በግብፅም የሃይማኖት መሪዎችን፣ የምሁራንንና የሌሎች ታዋቂ ሰዎችን ድጋፍ ለማግኘት ሞክሮ የነበረ ሲሆን ይህም ተሳክቶለታል።
ከካይሮ ተነስቶ የአባይን ወንዝ በመከተል ወደ ላይኛው
ግብፅ በተጓዘበት ወቅት ከሃይማኖት ሰዎች፣ ከገዳማትና በዘመኑ በሙስሊም ከተሞች በብዛት ይገኙ ከነበሩት የበጎ አድራጎት ሆስቴሎችና ኮሌጆች ጥሩ መስተንግዶ አግኝቶ ነበር። ሐሳቡ ምድረ በዳውን አቋርጦ ቀይ ባሕር ከደረሰ በኋላ በመርከብ ወደ ምዕራብ አረብያ በመሻገር የነቢዩ መሐመድ መስጊድ ወደሚገኝባት ወደ መዲና፣ ከዚያም ወደ መካ መጓዝ ነበር። ይሁን እንጂ በጦርነት ምክንያት ጉዞው ስለተስተጓጎለ ወደ ካይሮ ተመለሰ።የጉዞ አቅጣጫውን ቀየረ
ኢብን ባቱታ አሁንም መዲናና መካ ለመድረስ ቆርጦ ስለነበረ ወደ ሰሜን ተጉዞ ጋዛ ከደረሰ በኋላ ወደ ኬብሮን፣ ከዚያም የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ መቃብር ይገኝበታል ተብሎ ወደሚታመንበት ቦታ ተጓዘ። ወደ ኢየሩሳሌምና በዚያ ወደሚገኘው ዶም ኦቭ ዘ ሮክ ወደሚባለው የአምልኮ ቦታ እየተጓዘ ሳለ ቤተልሔም ላይ አጭር ቆይታ አድርጎ የነበረ ሲሆን በዚያም ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች ኢየሱስ ለተወለደበት ቦታ የሚሰጡትን ለየት ያለ ሃይማኖታዊ ክብር ተመልክቷል።
ከዚያም ኢብን ባቱታ ወደ ሰሜን ተጉዞ ደማስቆ ከደረሰ በኋላ እውቅ ከሆኑ ሙስሊም ምሁራን ትምህርት የቀሰመ ሲሆን አስተማሪ ለመሆን የሚያስችለውን የምሥክር ወረቀት አግኝቷል። በዚህች ከተማ የሚገኘው የኡማያድ መስጊድ በመላው ዓለም “በውበቱ ተወዳዳሪ የሌለው” መሆኑን ተናግሯል። በከተማዋ የሚገኙ መደብሮች ጌጣጌጥ፣ ልብስ፣ የጽሕፈት መሣሪያ፣ መጻሕፍትና እንደ ብርጭቆ ያሉ ዕቃዎች የሚሸጡ ሲሆን በዚያም “አምስት ወይም ስድስት ምሥክሮችና የጋብቻ ሥነ ሥርዓቶችን እንዲያስፈጽም ከቃዲው ሥልጣን የተሰጠው አንድ ሰው የሚገኝባቸው” መዝገብ ቤቶች ነበሩ። ኢብን ባቱታ ያገባውም እዚያው በደማስቆ ሳለ ነበር። ይሁን እንጂ ድንገት ብቅ ብለው የውኃ ሽታ ሆነው እንደሚቀሩት በርካታ ሚስቶቹና ቁባቶቹ ሁሉ ይህችም ሴት በእሱ ታሪክ ውስጥ ምንም አልተጠቀሰችም።
ኢብን ባቱታ ደማስቆ ላይ ወደ መካ የሐጅ ጉዞ ለማድረግ ከተነሱ መንገደኞች ጋር ተገናኘ። በጉዞ ላይ ሳሉም ከጎሽ ቆዳ ትላልቅ ገንዳዎችን ሠርተው ውኃ ሲያጠራቅሙ የነበሩ ሰዎች ያሉበት አንድ ምንጭ አጠገብ ሲደርሱ አረፉ። ተጓዦቹም ምድረ በዳውን ለማቋረጥ ከመነሳታቸው በፊት ከነዚህ ገንዳዎች ግመሎቻቸውን ውኃ አጠጡ፤ እንዲሁም የውኃ መያዣ አቁማዳቸውን ሞሉ። በመጨረሻም ኢብን ባቱታ መካ ደረሰ። ወደ መካ ካደረጋቸው ሰባት ጉዞዎች መካከል ይህ የመጀመሪያው ነበር። አብዛኞቹ ተጓዦች ሃይማኖታዊውን ሥርዓት ከፈጸሙ በኋላ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። ኢብን ባቱታ ግን አልተመለሰም። ስለእሱ የሕይወት ታሪክ የዘገበ አንድ ጸሐፊ “ጀብዱ መሥራት ስለሚወድ ብቻ” ወደ ባግዳድ ለመሄድ እንደተነሳ ገልጿል።
መላውን ምድር ለማዳረስ ተነሳ
ኢብን ባቱታ በጊዜው የእስልምና ዋና መዲና በነበረችው በባግዳድ ባሉት የሕዝብ የገላ መታጠቢያ ቦታዎች በእጅጉ ተደንቋል። “በእያንዳንዱ የገላ መታጠቢያ ቦታ በርካታ የግል መታጠቢያ ክፍሎች ይገኛሉ” ካለ በኋላ “እያንዳንዱ የግል መታጠቢያ ደግሞ ቀዝቃዛና ሙቅ ውኃ የሚያፈሱ ሁለት ቧንቧዎች የተገጠሙለት የመታጠቢያ ገንዳ አለው” ብሏል። ይህ ወጣት ተግባቢ በሆነ አንድ ጄኔራል አማካኝነት አቡ ሰኢድ ይባል ከነበረው ሱልጣን ጋር ሊተዋወቅ ችሏል። ኢብን ባቱታ ከሱልጣኑ ጋር ሲለያይ ውድ የሆኑ ስጦታዎች ይኸውም አንድ ፈረስና የክብር ልብስ ተሰጥተውት ነበር፤ እንዲሁም የባግዳድ ገዢ ግመሎችና ስንቅ እንዲሰጠው የሚያዝ ደብዳቤ አግኝቶ ነበር።
ኢብን ባቱታ ወደ አረብያና ወደ ፋርስ ባሕረ ሰላጤ ከመሄዱ በፊት የምሥራቅ አፍሪካ ወደቦች ወደሆኑት ወደ ሞቃዲሾ፣ ሞምባሳና ዛንዚባር በመርከብ ተጉዟል። ከጊዜ በኋላም እግረ መንገዱን ስላያቸው ሕዝቦች፣ ባሕሎችና ምርቶች እንዲሁም በሶማሊያ ለነጋዴዎች ስለተደረገው መስተንግዶና በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ዕንቁ ስለሚወጣበት መንገድ ገልጿል፤ በተጨማሪም በየመን ቢተልነት እንደሚታኘክና ኮኮናት እንደሚመረት ተናግሯል። ከዚያ በኋላ ወደ ሕንድ የሚያደርሰውን እጅግ ጠመዝማዛ ጉዞ በመጀመር በግብፅ፣ በሶርያና በአናቶልያ (ቱርክ) አልፎ ጥቁር ባሕርን ከተሻገረ በኋላ በካስፕያን ባሕር ሰሜናዊ ዳርቻ በመዞር በዛሬው ጊዜ ካዛክስታን፣ ኡዝቤኪስታን፣ አፍጋኒስታንና ፓኪስታን ተብለው ወደሚጠሩት አካባቢዎች ወርዷል።
ከሕንድ ወደ ቻይና
ኢብን ባቱታ በሕንድ ለዴልሂው ሱልጣን ቃዲ በመሆን ለስምንት ዓመታት አገልግሏል። ሱልጣኑ ኢብን ባቱታ ከአገር አገር መጓዝ ይወድ እንደነበር ስላወቀ ቶጎን ቴሙር ይባል ለነበረው ሞንጎሊያዊው የቻይና ንጉሠ ነገሥት አምባሳደር እንዲሆን ሾሞ ላከው። እዚያም ሲደርስ “ምርጥ ዝርያ ያላቸውን አንድ መቶ ፈረሶች፣ አንድ መቶ ነጭ ባሮችን፣ የሚጨፍሩና የሚዘፍኑ አንድ መቶ ሕንዳውያን ልጃገረዶችን፣ አንድ ሺህ ሁለት መቶ የተለያዩ ዓይነት ልብሶችን፣ ከወርቅና ከብር የተሠሩ የሻማ መቅረዞችንና ሳህኖችን፣ ልዩ ካባዎችን፣ ባርኔጣዎችን፣ የቀስት ኮሮጆዎችን፣ ሰይፎችን፣ በዕንቁ ያጌጡ ጓንቶችንና አሥራ አምስት ጃንደረቦችን” የሚያካትት ዲፕሎማሲያዊ ስጦታ ለንጉሡ ማቅረብ ነበረበት።
ኢብን ባቱታ ካሊከት በሚባለው የደቡብ ሕንድ ወደብ ወደ ቻይና ሊሄድ ባሰበበት መስመር የሚመላለሱትን ጁንክ የሚባሉ ትላልቅ የንግድ መርከቦች አየ። መርከቦቹ በቀርከሃ ተጠላልፈው የተሠሩ እስከ 12 የሚደርሱ ሸራዎች ያሏቸው ሲሆን 600 መርከበኞችንና 400 ታጣቂዎችን በድምሩ እስከ 1,000 የሚደርሱ የመርከብ ሠራተኞችን ይይዙ ነበር። የመርከበኞቹ ቤተሰቦች የሚኖሩት እዚያው መርከቡ ላይ ሲሆን “በእንጨት ገንዳዎች ላይ ዝንጅብልና ሌሎች አትክልቶች ያበቅሉ” እንደነበረ ኢብን ባቱታ ገልጿል።
ኢብን ባቱታ ያጋጠመው የመርከብ መሰበር አደጋ በቻይና ሊያከናውን ያሰበውን ዲፕሎማሲያዊ ተልእኮ አስተጓጎለበት። በመሆኑም በማልዳይቭስ የአንድ ሙስሊም ገዢ አገልጋይ ሆነ፤ የዚህችን ደሴት ባሕልና ልማድ ለውጪው ዓለም ያስተዋወቀው የመጀመሪያው ሰው እሱ ነበር። ከጊዜ በኋላም ወደ ቻይና መግባት ችሏል። በዚያ ጥሩ ነገሮችን ያየ ቢሆንም ከሃይማኖቱ ጋር በተያያዘ ስሜቱን የሚጎዱ ነገሮችን ተመልክቷል። አንዳንዶች ኢብን ባቱታ ስለ ቻይና የጻፋቸው ነገሮች ብዙ ባለመሆናቸው እንደተናገረው በእርግጥ እዚያ ድረስ መጓዙን ይጠራጠራሉ። ምናልባትም በደቡባዊ ቻይና ከሚገኙት ወደቦች አላለፈ ይሆናል ይላሉ።
ወደ አገሩ እየተመለሰ ሳለ ያጋጠሙት አሳዛኝ ሁኔታዎች
ኢብን ባቱታ ወደ ደማስቆ ሲመለስ ከ20 ዓመት በፊት ትቶት የሄደው ልጁ ከሞተ 12 ዓመት እንዳለፈ እንዲሁም በታንጂር ይኖር የነበረው አባቱ ከሞተ 15 ዓመት እንደሆነው ሰማ። ኢብን ባቱታ ደማስቆ የደረሰው በ1348 ሲሆን በዚህ ወቅት ጥቁር ሞት የተባለው ወረርሽኝ በመካከለኛው ምሥራቅ ብዙ ሰዎችን እያረገፈ ነበር። እንዲያውም በካይሮ በየቀኑ እስከ 21,000 ሰው ይሞት እንደነበር ኢብን ባቱታ ዘግቧል!
ይህ የ45 ዓመቱ ተጓዥ ከአንድ ዓመት በኋላ ሞሮኮ ሲደርስ እናቱ ከጥቂት ወራት በፊት በወረርሽኙ እንደሞተች ሰማ። ከአገሩ ሲወጣ የ21 ዓመት ሰው ነበር። ታዲያ ለ24 ዓመት ያደረገው ጉዞ ጀብደኛ የመሆን ጥማቱን አርክቶለት ይሆን? ያረካለት አይመስልም፤ ምክንያቱም ወዲያው ወደ ስፔን አቀና። ከሦስት ዓመት በኋላ የመጨረሻ ጉዞውን ለማድረግ ይኸውም ወደ ኒጀር ወንዝና ዛሬ ማሊ በመባል በምትታወቀው የአፍሪካ አገር ወደምትገኘው ቶምባክቱ (ቲምቡክቱ) ወደምትባል ከተማ ለመጓዝ ተነሳ።
ገጠመኞቹን በጽሑፍ እንዲያሰፍር ታዘዘ
በሞሮኮ የምትገኘው የፌዝ ሱልጣን ኢብን ባቱታ ስላደረገው ጉዞ ሲያውቅ ገጠመኞቹን በጽሑፍ አስፍሮ ለቤተ መንግሥቱ እንዲሰጥ አዘዘው፤ ኢብን ጁዛይ የተባለ ጸሐፊም ሰጠው። በአረብኛ የተዘጋጀው የጽሑፍ ሥራ ሰፊ ስርጭት ያላገኘ ሲሆን በምዕራቡ ዓለም ቋንቋዎችም መተርጎም የጀመረው በጽሑፍ የሰፈረውን ታሪክ በ19ኛው መቶ ዘመን የነበሩ አውሮፓውያን ምሁራን ካገኙት ወዲህ ነው።
ኢብን ጁዛይ ታሪኩን የፃፈው ተጓዡ በቃል የተረከለትን አሳጥሮ እንደሆነ ይግለጽ እንጂ ጸሐፊው በታሪኩ ላይ አንዳንድ ለውጦችን እንዳደረገ ግልጽ ነው። ቢሆንም ይህ ሥራ ኢብን ባቱታ በጎበኛቸው አገሮች በተለይም በመካከለኛው ዘመን እስላማዊ ዓለም ውስጥ ስለነበረው አኗኗር፣ ባሕል፣ ሃይማኖትና ፖለቲካ ልዩ የሆነ ግንዛቤ አስገኝቷል።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመካከለኛው ዘመን የነበሩ የእስልምና ሃይማኖት የሐጅ ተጓዦችን የሚያሳይ የአል ዋሲቲ የ13ኛው መቶ ዘመን ሥዕል
[የሥዕሉ ምንጭ]
Scala/White Images/Art Resource, NY
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢብን ባቱታ የተጓዘባቸውን አካባቢዎች በከፊል የሚያሳይ የ1375 የካታላን አትላስ
[የሥዕሉ ምንጭ]
Snark/Art Resource, NY