የባሕር ዔሊ አቅጣጫዋን የምታውቅበት መንገድ
ንድፍ አውጪ አለው?
የባሕር ዔሊ አቅጣጫዋን የምታውቅበት መንገድ
● ተመራማሪዎች፣ የባሕር ዔሊዎች ከሚመገቡበት አካባቢ ተነስተው እንቁላል ወደሚጥሉባቸው የባሕር ዳርቻዎች የሚያደርጉት ጉዞ “በእንስሳት ዓለም እጅግ አስደናቂ ከሆኑት ክንውኖች አንዱ” እንደሆነ ገልጸዋል። የእነዚህ እንስሳት ባሕርይ የተመራማሪዎችን ቀልብ ከሳበ በርካታ አሥርተ ዓመታት አልፈዋል።
እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ እንስቷ ዔሊ እንቁላል የምትጥለው ከሁለት እስከ አራት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፤ ዔሊዋ እንቁላል ወደምትጥልበት የባሕር ዳርቻ በመሄድ አሸዋውን ቆፍራ መቶ ያህል እንቁላሎችን አንድ ቦታ ላይ ከጣለች በኋላ ትቀብራቸዋለች። እንቁላሎቹ ከተፈለፈሉ በኋላ ትንንሾቹ ዔሊዎች ወደ ውቅያኖሱ ያመራሉ። ከዚያም በጥቅሉ እስከ 12,900 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን አስገራሚ ጉዞ ይያያዙታል። ከዓመታት በኋላ ለአካለ መጠን የደረሱት እንስት ዔሊዎች፣ እነሱ ራሳቸው ወደተፈለፈሉበት የባሕር ዳርቻ ተመልሰው እንቁላላቸውን ይጥላሉ!
የባሕር ዔሊዎች አቅጣጫቸውን አውቀው የሚጓዙት እንዴት ነው? በዩናይትድ ስቴትስ የኖርዝ ካሮላይና ዩኒቨርሲቲ የባዮሎጂ ባለሙያ የሆኑት ኬነዝ ሎመን፣ ዔሊዎቹ “በውርስ የሚያገኙት የሆነ መግነጢሳዊ ካርታ (ማግኔቲክ ማፕ) ያላቸው ይመስላል” በማለት መናገራቸውን ናሽናል ጂኦግራፊክ ኒውስ ጠቅሷል። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ዔሊዎቹ ያሉበትን ቦታ የሚያውቁት በምድር መግነጢሳዊ መስክ (ማግኔቲክ ፊልድ) አቅጣጫና ኃይል በመጠቀም ሊሆን ይችላል። ይህ አስደናቂ የሆነ ችሎታ እነዚህ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ትናንሽ እንስሳት በአትላንቲክ ውቅያኖስ ዙሪያ የሚያደርጉትን 12,900 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ጉዞ ለመጀመር ይረዳቸዋል፤ ሎመን እንደገለጹት ይህን ረጅም ጉዞ የሚያደርጉት “ሌሎች ዔሊዎችን ሳይከተሉ በራሳቸው ነው።”
ታዲያ ምን ይመስልሃል? የባሕር ዔሊ አቅጣጫዋን አውቃ የመጓዝ ችሎታ እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አስገራሚ እውነታዎች
● እንስቷ ዔሊ እንቁላሎቿን ከጣለችና ከደበቀቻቸው በኋላ ትታቸው ትሄዳለች።
● ጫጩቶቹ የእንቁላሉን ቅርፊት ሰብረው ለመውጣት ካረንክል በሚባል ልዩ ዓይነት ጥርስ ይጠቀማሉ፤ ይህ ጥርስ ጫጩቶቹ ከተፈለፈሉ በኋላ ይወልቃል።
● የባሕር ዔሊዎች 90 በመቶ የሚሆነውን ሕይወታቸውን የሚያሳልፉት ውቅያኖስ ውስጥ ነው።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
© Masa Ushioda/WaterF/age fotostock