5ኛው ቁልፍ—ራስህንም ሆነ ቤተሰብህን ቀስቅስ
5ኛው ቁልፍ—ራስህንም ሆነ ቤተሰብህን ቀስቅስ
“አስተዋይ ሰው ሥራውን በዕውቀት ያከናውናል።” (ምሳሌ 13:16) ለጤና በሚረዱ መሠረታዊ እውቀቶች ራስህን ማስታጠቅህ አንተም ሆንክ ቤተሰብህ የተሻለ ጤንነት ለማግኘት አስፈላጊውን ማስተካከያ እንድታደርጉ ሊያነሳሳችሁ ይችላል።
◯ መማርህን ቀጥል። በብዙ አገሮች የሕዝብና የግል ተቋማት በጤና ነክ ጉዳዮች ዙሪያ የትምህርት ፕሮግራም ያላቸው ሲሆን ጽሑፎችንም ይሰጣሉ። እነዚህን አጋጣሚዎች በመጠቀም ጤንነትህን ማሻሻልና ራስህን ከአደጋ መጠበቅ ስለምትችልባቸው መሠረታዊ መንገዶች መማር ትችላለህ። አእምሮህን ክፍት በማድረግ ቀላል ማስተካከያዎችን ለማድረግ ፈቃደኛ ሁን።
የምትማራቸውና ተግባራዊ የምታደርጋቸው ጥሩ ልማዶች ለልጆችህና ለልጅ ልጆችህም ሊጠቅሟቸው ይችላሉ። ወላጆች ለጤና ከሚጠቅም አመጋገብ፣ ከንጽሕና፣ ከእንቅልፍ ልማድ፣ ከአካል ብቃት እንቅስቃሴና በሽታን ከመከላከል ጋር በተያያዘ ጥሩ ምሳሌ ሲሆኑ ልጆቻቸውም መጠቀማቸው አይቀርም።—ምሳሌ 22:6
◯ ሌላ ምን የሚያስፈልግ ነገር አለ? ጤናማ አኗኗር ለመመሥረት ብሎም ያንን ጠብቆ ለመኖር እንዲህ ማድረጉ ጥቅም እንደሚያስገኝ ማወቅ ብቻ አይበቃም። ሥር የሰደዱ መጥፎ ልማዶችን ማስወገድ እልህ አስጨራሽ ሲሆን ቀላል የሚባሉትን ማስተካከያዎች እንኳ ለማድረግ ብዙውን ጊዜ ብርቱ ግፊት ሊጠይቅ ይችላል። አንዳንድ ሰዎች አንድ ልማድ ከባድ በሽታና ሞት ሊያስከትልባቸው እንደሚችል ቢያውቁም ጥሩ ነው ብለው የሚያምኑበትን እርምጃ ለመውሰድ ላይነሳሱ ይችላሉ። ታዲያ ምን ሊያነሳሳቸው ይችላል? እነዚህ ሰዎች እንደማናችንም ሁሉ በሕይወታቸው ከፍ አድርገው የሚመለከቱት ዓላማ ወይም ግብ ሊኖራቸው ያስፈልጋል።
የትዳር ጓደኛሞች እርስ በርስ እየተረዳዱ ለመኖር ምንጊዜም ጤናማና ጠንካራ መሆን ያስፈልጋቸዋል። ወላጆች ልጆቻቸውን መደገፍና ማሠልጠን የምንጊዜም ፍላጎታቸው ነው። ትልልቅ ልጆችም በዕድሜ እየገፉ ያሉ ዘመዶቻቸውን መንከባከብ ያስፈልጋቸዋል። በዚህ ላይ ደግሞ ማንም ሰው ቢሆን ለማኅበረሰቡ በረከት እንጂ ሸክም መሆን አይፈልግም። እነዚህ ሁሉ ለሌሎች ፍቅርና አሳቢነት ማሳየት የሚጠይቁ ናቸው።
አንድን ሰው የበለጠ የሚገፋፋው ምክንያት ግን ለፈጣሪው ያለው አድናቆትና ፍቅር ነው። በአምላክ የሚያምኑ ሰዎች እሱ የሰጣቸውን ውድ የሕይወት ስጦታ በክብር የመያዝ ልባዊ ፍላጎት አላቸው። (መዝሙር 36:9) ጤነኞች ከሆንን አምላክን ይበልጥ ማገልገል እንችላለን። የራስን ጤንነት ለመንከባከብ ከዚህ የላቀ ሊገፋፋ የሚችል ምክንያት አይኖርም።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ መከተል በሚያስገኘው ጥቅም ተደሰት