ወላጆቼ እንድዝናና የማይፈቅዱልኝ ለምንድን ነው?
የወጣቶች ጥያቄ
ወላጆቼ እንድዝናና የማይፈቅዱልኝ ለምንድን ነው?
በአውስትራሊያ የምትኖረው የ17 ዓመቷ አሊሰን * ሰኞ በመጣ ቁጥር ትምህርት ቤት ስትሄድ ጭንቅ ይላታል።
“ሁሉም ቅዳሜና እሁድን እንዴት እዳሳለፉ ያወራሉ” በማለት ትናገራለች። “ከአነጋገራቸው ደስ የሚል ጊዜ ያሳለፉ ይመስላል፤ ስንት ፓርቲ ላይ እንደተገኙ፣ ከስንት ወንድ ጋር እንደተሳሳሙ፣ ሌላው ቀርቶ ፖሊሶችን እንዴት እንደሸወዱ ጭምር ያወራሉ። ሁኔታው በጣም የሚያስፈራ ቢመስልም ደስ ይላል! ቤታቸው የሚገቡት ሊነጋጋ ሲል 11 ሰዓት ላይ ቢሆንም ወላጆቻቸው ምንም አይሏቸውም። እኔ ወደ መኝታዬ በምሄድበት ሰዓት እነሱ ለመዝናናት ይወጣሉ!
“ወደ ሰኞው ሁኔታ ስመለስ የክፍሌ ልጆች ቅዳሜና እሁድ ምን እንዳደረጉ ከነገሩኝ በኋላ የእኔን ይጠይቁኛል። እኔ ደግሞ ምን ሳደርግ ነበር? ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ሄጃለሁ። በአገልግሎት ተካፍያለሁ። ያም ሆኖ የቀረብኝ ነገር እንዳለ ይሰማኛል። ስለዚህ አብዛኛውን ጊዜ ምንም እንዳላደረግሁ እነግራቸዋለሁ። ከዚያም ለምን ከእነሱ ጋር እንዳልሄድኩ ይጠይቁኛል።
“እንደምንም ሰኞን ካለፈች ሁኔታው ይቀልላታል ብላችሁ ታስቡ ይሆናል። ነገር ግን እንደምታስቡት አይደለም። ማክሰኞ ዕለት ደግሞ ሁሉም ስለሚመጣው ቅዳሜና እሁድ ማውራት ይጀምራል! በአብዛኛው እነሱ ሲያወሩ ቁጭ ብሎ ከመስማት ውጪ ሥራ የለኝም ማለት እችላለሁ። የቀረብኝ ነገር እንዳለ ይሰማኛል!”
አንተም ሰኞ ሰኞ ትምህርት ቤት ስትሄድ የሚሰማህ እንዲህ ነው? በውጭ ያሉት ልጆች እንደልባቸው ሲዝናኑ አንተ ግን እንዳትወጣ ወላጆችህ በአንድ ክፍል ውስጥ እንደቆለፉብህ ሊሰማህ ይችላል፤ አሊያም የመጫወቻ ዓይነት በሞላበት የመዝናኛ ስፍራ ገብተህ በአንዱም እንኳ እንዳትጫወት እንደተከለከልክ ይሰማህ ይሆናል። እንዲህ የተሰማህ እኩዮችህ የሚያደርጉትን ነገር ሁሉ ማድረግ ስለምትፈልግ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አልፎ አልፎ መዝናናት ስለምትፈልግ ብቻ ነው አይደል? ለምሳሌ መጪውን ቅዳሜና እሁድ ለማሳለፍ የምትመርጠው በየትኛው መዝናኛ ነው?
◯ ዳንስ
◯ የሙዚቃ ትርዒት
◯ ፊልም
◯ ፓርቲ
◯ ሌላ
መዝናናት እንደሚያስፈልግህ ግልጽ ነው። (መክብብ 3:1, 4) እንዲያውም ፈጣሪህ የወጣትነት ጊዜህን አስደሳች በሆነ መንገድ እንድታሳልፍ ይፈልጋል። (መክብብ 11:9) መቀበል ሊከብድህ ቢችልም ወላጆችህም እንድትዝናና ይፈልጋሉ። ያም ሆኖ ወላጆችህ ሁለት ነገር ያሳስባቸው ይሆናል፦ (1) የምትመርጠው መዝናኛ እና (2) አብረሃቸው የምትውላቸው ልጆች። ደግሞም እነዚህ ነገሮች ቢያሳስቧቸው የሚያስደንቅ አይደለም።
ጓደኞችህ አብረሃቸው ወጣ ብለህ እንድትዝናና ቢጋብዙህና ወላጆችህ እንደሚፈቅዱልህ እርግጠኛ ባትሆንስ? ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቅ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ጥሩም ይሁን መጥፎ ያሉህን አማራጮች እንድታስብባቸውና ውሳኔህ የሚያስከትላቸውን ውጤቶች እንድታመዛዝን መጽሐፍ ቅዱስ ያበረታታሃል። (ዘዳግም 32:29፤ ምሳሌ 7:6-23) ጓደኞችህ አብረሃቸው እንድትዝናና ያቀረቡልህን ግብዣ በተመለከተ ምን አማራጮች አሉህ?
አማራጭ ሀ፦ ሳታስፈቅድ ዝም ብለህ መሄድ።
ይህ አማራጭ ጥሩ መስሎ የታየህ ምናልባት በራስህ ፈቃድ የምትመራ ሰው መሆንህን ለጓደኞችህ ማሳየት ስለምትፈልግ ሊሆን ይችላል። ወይም ከወላጆችህ የበለጠ እንደምታውቅ ስለሚሰማህ አለዚያም የሚያስቡበት መንገድ ስለማይጥምህ ይሆናል።—ምሳሌ 15:5
ውሳኔህ የሚያስከትላቸው ውጤቶች፦ እንዲህ ማድረግህ ለጓደኞችህ አንድ መልእክት ማስተላለፉ አይቀርም፤ አታላይ እንደሆንክ አድርገው ሊያስቡ ይችላሉ። ዛሬ ወላጆችህን ካታለልክ ነገ ጓደኞችህንም ታታልላለህ ማለት ነው። ወላጆችህ ካወቁብህ ደግሞ በጣም ሊያዝኑብህ አልፎ ተርፎም በአንተ ላይ ያላቸውን እምነት ሊያጡና ተጨማሪ ገደብ ሊጥሉብህ ይችላሉ! ዞሮ ዞሮ በወላጆችህ ላይ ዓምፀህ ለመዝናናት መሄድህ ሞኝነት ነው።—ምሳሌ 12:15
አማራጭ ለ፦ ማስፈቀዱንም መሄዱንም ትተህ አርፈህ መቀመጥ።
ይህ አማራጭ ጥሩ መስሎ የታየህ ምናልባት ስለቀረበልህ ግብዣ ስታስብ መዝናኛው አንተ ከምትመራበት የሥነ ምግባር መሥፈርት ጋር የማይስማማ ስለሆነ ወይም ከተጋበዙት መካከል አንዳንዶቹ አብረሃቸው ለመዋል የማትመርጣቸው ዓይነት ልጆች ስለሆኑ ሊሆን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 15:33፤ ፊልጵስዩስ 4:8) በሌላ በኩል ደግሞ ለመሄድ ብትፈልግም ወላጆችህን ማስፈቀድ ትፈራ ይሆናል።
ውሳኔህ የሚያስከትላቸው ውጤቶች፦ ግብዣውን ያልተቀበልከው መሄዱ ጥሩ እንዳልሆነ ስለተሰማህ ከሆነ ለጓደኞችህ መልስ ስትሰጥ ይበልጥ በራስ የመተማመን ስሜት ይኖርሃል። ነገር ግን የማትሄደው ወላጆችህን ለማስፈቀድ ድፍረት ስላጣህ ከሆነ መዝናናት የቀረብህ አንተ ብቻ እንደሆንክ በማሰብ ቤትህ ቁጭ ብለህ ስትብሰለሰል ልትውል ነው።
አማራጭ ሐ፦ መጠየቅና የሚሉትን መስማት።
ይህ አማራጭ ጥሩ መስሎ የታየህ ምናልባት ወላጆችህ በአንተ ላይ ሥልጣን እንዳላቸው ስለምትገነዘብና የእነሱን አመለካከት ስለምታከብር ሊሆን ይችላል። (ቆላስይስ 3:20) አሊያም ወላጆችህን ስለምትወዳቸው ከእነሱ ተደብቀህ በመሄድ ልታስከፋቸው ባለመፈለግህ ይሆናል። (ምሳሌ 10:1) በሌላ በኩል ደግሞ ሐሳብህን ለመግለጽ የሚያስችል አጋጣሚ ስለሚፈጥርልህ ሊሆን ይችላል።
ውሳኔህ የሚያስከትላቸው ውጤቶች፦ ወላጆችህ እንደምትወዳቸውና እንደምታከብራቸው ይሰማቸዋል። በዚያ ላይ ጥያቄህን ምክንያታዊ ሆኖ ካገኙት ሊፈቅዱልህ ይችላሉ።
ወላጆች ላይፈቅዱ የሚችሉበት ምክንያት
ይሁንና ወላጆችህ ባይፈቅዱልህስ? ይህ ሊያበሳጭህ ይችላል። ይሁን እንጂ የወላጆችህን አመለካከት መረዳትህ በመከልከልህ እንዳትበሳጭ ሊረዳህ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ የማይፈቅዱልህ ቀጥሎ ከተዘረዘሩት በአንዱ ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ምክንያቶች ሊሆን ይችላል።
ከአንተ የበለጠ እውቀትና ተሞክሮ ያላቸው መሆኑ። የመምረጥ ዕድል ቢሰጥህ ሕይወት አድን ሠራተኞች በሚገኙበት የባሕር ዳርቻ መዋኘት እንደምትመርጥ የታወቀ ነው። ለምን? ምክንያቱም አብዛኛውን ጊዜ ውኃው ውስጥ መዝናናትህ እንጂ ሊመጣ የሚችለው አደጋ አይታይህ ይሆናል። ሕይወት አድን ሠራተኞቹ ግን አደጋ የሚያስከትሉ ሁኔታዎችን ለመለየት በሚያስችላቸው የተሻለ ቦታ ላይ ይገኛሉ።
በተመሳሳይም ወላጆችህ ከአንተ የተሻለ እውቀትና ተሞክሮ ስላላቸው ለአንተ የማይታዩ አደጋዎችን ሊያስተውሉ ይችላሉ። በባሕሩ ዳርቻ እንዳሉት የሕይወት አድን ሠራተኞች ሁሉ የወላጆችህ ዓላማ እንዳትዝናና እንቅፋት መፍጠር አይደለም። ከዚህ ይልቅ ዓላማቸው ደስታህን ሊያሳጡህ ከሚችሉ አደጋዎች አንተን መጠበቅ ነው።
ለአንተ ያላቸው ፍቅር። ወላጆችህ አንተን ከጉዳት የመጠበቅ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። የሚቻል ሲሆን እንዲፈቅዱልህ፣ የማይሆን ነገር ከሆነ ደግሞ እንዲከለክሉህ የሚያነሳሳቸው ለአንተ ያላቸው ፍቅር ነው። አንድ ነገር ለማድረግ ፈቃድ በምትጠይቃቸው ጊዜ ጥያቄህን ተቀብለው ሊፈቅዱልህና ከዚያ በኋላ የሚመጣውን ውጤት ሊቀበሉ ይችሉ እንደሆነ ከራሳቸው ጋር ይነጋገራሉ። ለራሳቸውም ሆነ ለአንተ እሺ ሊሉ የሚችሉት ምንም ጉዳት እንደማይደርስብህ ለማመን የሚያስችል አጥጋቢ ምክንያት ካገኙ ብቻ ነው።
በቂ መረጃ አለማግኘት። አፍቃሪ ወላጆች የሚመርጡት ‘ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ’ የሚለውን ብሂል መከተል ነው። ጥያቄህን በትክክል መረዳት ካልቻሉ ወይም ጥያቄህን በምታቀርብበት ጊዜ ወሳኝ የሆኑ መረጃዎችን እንደደበቅካቸው ከተሰማቸው ላይፈቅዱልህ ይችላሉ።
ፈቃድ የማግኘትህ አጋጣሚ ሰፊ እንዲሆን ምን ብታደርግ ይሻላል?
አራት ነገሮችን መጥቀስ ይቻላል።
ሐቀኛ ሁን፦ በመጀመሪያ ደረጃእንዲህ እያልክ ራስህን በሐቀኝነት መጠየቅ ይኖርብሃል፦ ‘መሄድ የምፈልግበት ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው? መዝናኛውን ስለምወደው ነው ወይስ በእኩዮቼ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ስለፈለግኩ? ለመዝናናት ከሚሄዱት መካከል የምወደው ሰው ስላለ ነው?’ ለወላጆችህ በምትናገርበት ጊዜም ሐቀኛ ሁን። እነሱም በአንድ ወቅት ወጣቶች የነበሩ ከመሆኑም ሌላ አንተንም በደንብ ያውቁሃል። ስለዚህ ባትነግራቸውም እንኳ ለመሄድ የፈልግክበትን ምክንያት ማወቃቸው አይቀርም። በሐቀኝነት መናገርህ እነሱን የሚያስደስታቸው ሲሆን አንተም ጥበብ ካዘለ ምክራቸው ጥቅም ልታገኝ ትችላለህ። (ምሳሌ 7:1, 2) በሌላ በኩል ደግሞ ሐቀኛ ካልሆንክ በእነሱ ዘንድ ያለህን አመኔታ የምታጣ ከመሆኑም በላይ ፈቃድ የማግኘትህ አጋጣሚም የጠበበ ይሆናል።
ጊዜ ምረጥ፦ ወላጆችህ ሥራ ውለው ገና እቤት ከመግባታቸው ወይም የሚያሳስብ ነገር በገጠማቸው ጊዜ እንዲፈቅዱልህ አትጎትጉታቸው። ይበልጥ ዘና በሚሉበት ጊዜ ቀርበህ ጠይቃቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ቀኑ እስኪደርስ ድረስ መጠበቅ የለብህም፤ ባለቀ ሰዓት በመጠየቅ ቶሎ መልስ እንዲሰጡህ መጎትጎትህ ተገቢ አይደለም። ወላጆችህ የችኮላ ውሳኔ ማድረግ አይፈልጉም። ስለዚህ ቀደም ብለህ ብትጠይቃቸው አሳቢነትህን ያደንቃሉ።
ግልጽ ሁን፦ ጥያቄህን አታድበስብስ። ለማድረግ የፈለግከውን ነገር በትክክል አስረዳቸው። ወላጆች “እኔ እንጃ” የሚለው መልስ አይዋጥላቸውም፤ በተለይ ደግሞ “እነማን ይገኛሉ?” “ኃላፊነት የሚሰማው ትልቅ ሰው ይገኛል?” ወይም “ዝግጅቱ የሚያልቀው በስንት ሰዓት ነው?” ብለው ሲጠይቁህ እንደማታውቅ የምትናገር ከሆነ ስጋት ያድርባቸዋል።
ጥሩ አመለካከት ይኑርህ፦ ወላጆችህን እንደ ጠላት አትያቸው። ከዚህ ይልቅ የቡድንህ አባላት እንደሆኑ አድርገህ ተመልከታቸው፤ ደግሞም ቆም ብለህ ስታስበው ከአንተ ወገን ናቸው። ወላጆችህን እንደ አጋሮችህ አድርገህ የምትመለከታቸው ከሆነ ስትናገር ቆጣ ቆጣ ከማለት የምትቆጠብ ሲሆን እነሱም ተባባሪ ለመሆን ይነሳሳሉ። እምቢ ቢሉህ እንኳ ምክንያታቸውን በአክብሮት ጠይቃቸው። ለምሳሌ ያህል፣ የሙዚቃ ትርዒት ለማየት እንዳትሄድ ቢከለክሉህ ለስጋታቸው ምክንያት የሆነውን ነገር ለይተህ ለማወቅ ጣር። ያሳሰባቸው ምን ይሆን? የዘፋኙ ሁኔታ? በትርዒቱ ቦታ የሚታየው መንፈስ? አብረሃቸው የምትሆናቸው ልጆች ጉዳይ? ወይስ የመግቢያው ዋጋ? ልትጠነቀቅበት የሚገባ ሌላም ጉዳይ አለ፤ “በቃ አትተማመኑብኝም ማለት ነው!” “ሁሉም ልጆች ይሄዳሉ፣” “ጓደኞቼ ወላጆቻቸው ፈቅደውላቸዋል!” እንደሚሉት ያሉ አነጋገሮችን አስወግድ። ውሳኔያቸውን በአክብሮት በመቀበል በሳል ልጅ መሆንህን አሳያቸው። እንዲህ ካደረግህ እነሱም ያከብሩሃል። ደግሞም በሌላ ጊዜ ስትጠይቃቸው በተቻለ መጠን አንተን ለማስደሰት ጥረት እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል።
www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.3 ስሟ ተቀይሯል።
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
“ኃላፊነት የሚሰማኝ ሰው መሆኔን ብዙ ጊዜ በማስመሥከሬ ወላጆቼ እምነት ይጥሉብኛል። ስለ ጓደኞቼ በግልጽ እነግራቸዋለሁ። ከጓደኞቼ ጋር እየተዝናናሁ ሳለ የማይጥመኝ ነገር ካየሁም ትቼ ለመሄድ አልፈራም።”
[ሥዕል]
ኪምበርሊ
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ወላጆችህን ለምን አትጠይቃቸውም?
በዚህ ርዕሰ ትምህርት ውስጥ በተነሱት ጉዳዮች ረገድ ወላጆችህ ምን ሐሳብ እንዳላቸው ለማወቅ ትፈልጋለህ? ብቸኛው መንገድ ጠይቀህ መረዳት ነው! ለመዝናናት ወጣ ብትል ምን ችግር እንዳለው ለማወቅ አመቺ ጊዜ ስታገኝ ከወላጆችህ ጋር ተወያይበት። በዚህ ወቅት ልታነሳው የምትፈልገውን ጥያቄ አስብና ከዚህ በታች ጻፈው።
․․․․․
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በባሕሩ ዳርቻ እንዳሉት ሕይወት አድን ሠራተኞች ሁሉ ወላጆችህም ሊያጋጥምህ ስለሚችል አደጋ አንተን ለማስጠንቀቅ በሚያስችላቸው የተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ