በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከወንድሞቼና እህቶቼ ጋር ለመስማማት ምን ላድርግ?

ከወንድሞቼና እህቶቼ ጋር ለመስማማት ምን ላድርግ?

የወጣቶች ጥያቄ

ከወንድሞቼና እህቶቼ ጋር ለመስማማት ምን ላድርግ?

ከወንድሞችህና ከእህቶችህ ጋር ያለህን ግንኙነት ስትገመግመው ምን ይመስላል?

․․․․․ በጣም የምንዋደድ ጓደኛሞች ነን

․․․․․ አብዛኛውን ጊዜ እንስማማለን

․․․․․ እንቻቻላለን

․․․․․ ሁልጊዜ እንጣላለን

አንዳንድ ወንድማማቾችና እህትማማቾች በጣም ይቀራረባሉ። ለምሳሌ ያህል፣ 19 ዓመት የሆናት ፈሊሻያ “የ16 ዓመቷ እህቴ ኢሬና በጣም የምወዳት ጓደኛዬ ናት” ብላለች። * የ17 ዓመቷ ካርሊ ደግሞ 20 ዓመት ስለሆነው ወንድሟ ስለ ኤሪክ ስትናገር “በጣም እንስማማለን፤ በፍጹም አንጣላም” ብላለች።

በሌላ በኩል ደግሞ ብዙዎች በመካከላቸው ያለው ግንኙነት ሎረንና ማርላ እንደገለጹት ዓይነት ነው። ሎረን “በሁሉም ነገር እንጨቃጨቃለን። ተራ በሆነ ጉዳይም እንኳ ሳይቀር እንጣላለን” በማለት ተናግራለች። ወይም ደግሞ የ12 ዓመት ልጅ እንደሆነችው እንደ አሊስ ዓይነት ስሜት ይኖርህ ይሆናል፤ አሥራ አራት ዓመት ስለሆነው ስለ ወንድሟ ስትናገር “በጣም ያበሳጨኛል! ክፍሌን በርግዶ ይገባና ሳያስፈቅደኝ ዕቃዎቼን ይወስዳል። ዴኒስ አሁንም ገና እንደ ትንሽ ልጅ ያደርገዋል!” ብላለች።

ወንድምህ ወይም እህትህ የሚያደርጉት ነገር ያበሳጭሃል? እርግጥ ነው፣ በቤተሰቡ ውስጥ ሥርዓት የማስፈን ኃላፊነት ያለባቸው ወላጆችህ ናቸው። ይሁንና ይዋል ይደር እንጂ ከሌሎች ጋር እንዴት ተስማምተህ እንደምትኖር መማር ያስፈልግሃል። ይህን ደግሞ መማር የምትችለው አድገህ ከወላጆችህ ቤት ከመውጣትህ በፊት ነው።

ከወንድምህ ወይም ከእህትህ ጋር ስለተፈጠሩት ግጭቶች ለማሰብ ሞክር። ብዙውን ጊዜ የምትጣሉት በምን ምክንያት ነው? ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ሐሳቦች ተመልከትና አንተን የሚያበሳጭህ ነጥብ ላይ ✔ አድርግ፤ ወይም ስለሚያናድድህ ሁኔታ ጻፍ!

ንብረቶች፦ ወንድሜ ወይም እህቴ ሳያስፈቅዱኝ ዕቃዎቼን ይወስዳሉ።

የባሕርይ አለመጣጣም፦ ወንድሜ ወይም እህቴ ራስ ወዳድ ወይም አሳቢነት የጎደላቸው ናቸው፤ አለዚያም ደግሞ ሕይወቴን ለመቆጣጠር ይሞክራሉ።

ነፃነትን መጋፋት፦ ወንድሜ ወይም እህቴ ሳያንኳኩ ወደ ክፍሌ ይገባሉ፤ ወይም ሳያስፈቅዱኝ የተላኩልኝን የኢሜይል ወይም የጽሑፍ መልእክቶች ያነባሉ።

ሌላ ․․․․․

ወንድምህ ወይም እህትህ አንተን ለመቆጣጠር በመሞከር አለዚያም ነፃነትህን በመጋፋት ሁልጊዜ የሚያናድዱህ ከሆነ ቅሬታ ሊያድርብህ ይችላል። ይሁን እንጂ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “አፍንጫን ሲያሹት እንደሚደማ፣ ቍጣን ማነሣሣትም ጥልን ይፈጥራል” ይላል። (ምሳሌ 30:33) አፍንጫህን ማሸት እንደሚያደማው ሁሉ ቂም መያዝህ በቁጣ እንድትገነፍል ሊያደርግህ ይችላል። ከዚያም ችግሩ ጭራሽ ሊባባስ ይችላል። (ምሳሌ 26:21) ታዲያ ያናደደህ ነገር በቁጣ እንድትገነፍል እንዳያደርግህ መከላከል የምትችለው እንዴት ነው? የመጀመሪያው እርምጃ የችግሩን እውነተኛ መንስኤ ማወቅ ነው።

ድርጊቱ ወይስ መንስኤው?

በወንድማማቾችና እህትማማቾች መካከል የሚፈጠሩት ግጭቶች እንደ ብጉር ናቸው። ብጉር ለዓይን ደስ የማይል ቁስል ቢሆንም መንስኤው ግን ከቆዳው ሥር ያለ ኢንፌክሽን ነው። በተመሳሳይም በወንድማማቾችና እህትማማቾች መካከል የሚነሳ ደስ የማይል ጭቅጭቅ ብዙውን ጊዜ በመካከላቸው ችግር መኖሩን የሚያመለክት ከላይ የሚታይ ማስረጃ ነው።

ብጉርን ልታፈርጠው ትችላለህ። ይሁን እንጂ እንዲህ ማድረግ የሚያስወግደው ምልክቱን ብቻ በመሆኑ ጠባሳ ሊተው ወይም ኢንፌክሽኑን ሊያባብሰው ይችላል። የተሻለው መንገድ ኢንፌክሽኑን በማከም ሌላ ብጉር እንዳይወጣ መከላከል ነው። ከወንድሞችህና ከእህቶችህ ጋር አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ስለዚህ አለመግባባት እንዲፈጠር ምክንያት የሆነውን ነገር ለይተህ ለማወቅ በመጣር ካናደደህ ድርጊት ባሻገር ያለውን የችግሩን መንስኤ መረዳት ትችላለህ። በተጨማሪም “ጥበብ ሰውን ታጋሽ ታደርገዋለች” የሚለውን የጠቢቡን ንጉሥ የሰለሞንን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ትችላለህ።—ምሳሌ 19:11

ለምሳሌ ያህል፣ ቀደም ሲል የተጠቀሰችው አሊስ ስለ ወንድሟ ስለ ዴኒስ ስትናገር “ክፍሌን በርግዶ ይገባና ሳያስፈቅደኝ ዕቃዎቼን ይወስዳል” ብላለች። ያናደዳት ድርጊት ይሄ ነው። ሆኖም እውነተኛው መንስኤ ምን ይመስልሃል? መንስኤው ከአክብሮት ጋር የተያያዘ ነው። *

አሊስ፣ ዴኒስን ጨርሶ ወደ ክፍሏ እንዳይመጣ ወይም ዕቃዎቿን እንዳይነካ በመንገር ችግሩን ለማስወገድ ልትጥር ትችላለች። ይሁን እንጂ ይህ እርምጃ ምልክቱን ብቻ ከማስወገድ ያለፈ ጥቅም አይኖረውም፤ እንዲያውም ሌላ ግጭት ሊያስከትል ይችላል። አሊስ ነፃነቷንና የግል ንብረቷን እንዲያከብርላት ዴኒስን ማሳመን ብትችል ግንኙነታቸው እንደሚሻሻል ጥርጥር የለውም።

አለመግባባቶችን መፍታት ወይም ማስቀረት የሚቻልበትን መንገድ ተማር

እርግጥ ነው፣ ከወንድምህ ወይም ከእህትህ ጋር ባለህ ግንኙነት ለሚፈጠሩ አለመግባባቶች መንስኤ የሆነውን ነገር ለይቶ ማወቅ የመፍትሔው አንድ አካል ብቻ ነው። የተፈጠረውን ግጭት ለመፍታትና ወደፊትም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳይከሰት ለማድረግ ምን እርምጃ መውሰድ ትችላለህ? የሚከተሉትን ስድስት እርምጃዎች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር።

1. በተወሰኑ መሠረታዊ ደንቦች ላይ ተስማሙ። ንጉሥ ሰለሞን “ምክር ሲጓደል ዕቅድ ይፋለሳል” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 15:22) ብስጭትን ለማስቀረት በአንተና በወንድምህ ወይም በእህትህ መካከል ለተፈጠረው ጭቅጭቅ መንስኤ ነው ብለህ ያሰብከውን ነገር መለስ ብለህ አስበው። ሁለታችሁም ልትስማሙባቸውና ችግሩን ከሥረ መሠረቱ ሊያስወግዱ የሚችሉ አንዳንድ ደንቦችን ማውጣት ትችሉ እንደሆነ ተማከሩ። ለምሳሌ ያህል፣ የምትጋጩት በንብረት ከሆነ ደንብ ቁጥር 1 “የሌላ ሰው ንብረት ከመውሰድህ በፊት ሁልጊዜ ፈቃድ ጠይቅ” የሚል ሊሆን ይችላል። ደንብ ቁጥር 2 ደግሞ “ወንድምህ ወይም እህትህ ‘አይሆንም፣ ይህን ዕቃ አላውስህም’ የማለት መብት እንዳላቸው አምነህ ተቀበል” የሚል ሊሆን ይችላል። እነዚህን ደንቦች ስታወጡ “እንግዲህ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም እንደዚሁ ልታደርጉላቸው ይገባል” በማለት ኢየሱስ የሰጠውን ትእዛዝ አስታውሱ። (ማቴዎስ 7:12) በዚህ መንገድ አንተም ሆንክ ወንድምህ ወይም እህትህ ልታከብሯቸው የምትችሏቸውን ደንቦች ማውጣት ትችላላችሁ። ከዚያም ወላጆቻችሁ ስምምነታችሁን እንደሚደግፉት ለማረጋገጥ ከእነሱ ጋር ተነጋገሩበት።—ኤፌሶን 6:1

2. ራስህም ላወጣችሁት ደንብ ተገዛ። ሐዋርያው ጳውሎስ “ታዲያ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርም? አንተ ‘አትስረቅ’ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህ?” በማለት ጽፏል። (ሮም 2:21) ይህን መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ላይ ማዋል የምትችለው እንዴት ነው? ለምሳሌ ያህል፣ ወንድምህ ወይም እህትህ የአንተን ነፃነት እንዲያከብሩ የምትፈልግ ከሆነ አንተም ወደ እነሱ ክፍል ከመግባትህ በፊት በሩን ማንኳኳት ወይም የተላኩላቸውን የኢሜይል ወይም የጽሑፍ መልእክቶች ከማንበብህ በፊት ማስፈቀድ ይኖርብሃል።

3. ለመቆጣት አትቸኩል። ይህ ጥሩ ምክር የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እንደሚገልጸው “ለቁጣ የሚቸኩሉትና ቂም የሚይዙት ሞኞች ብቻ” ናቸው። (መክብብ 7:9 ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርሽን) በቀላሉ የምትቀየም ከሆነ ሕይወትህን መራራ ታደርገዋለህ። አዎ፣ ወንድምህ ወይም እህትህ አንተን የሚያበሳጭ ነገር ሊያደርጉ ወይም ሊናገሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ‘እኔስ ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ነገር አድርጌባቸው አላውቅም?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። (ማቴዎስ 7:1-5) ጄኒ “የ13 ዓመት ልጅ ሳለሁ እኔ የምሰጠው ሐሳብ ከሁሉ የተሻለ እንደሆነና የእኔ ሐሳብ መሰማት እንዳለበት አድርጌ አስብ ነበር። አሁን ደግሞ ታናሽ እህቴ እኔ ይሰማኝ የነበረው ዓይነት ስሜት ይሰማታል። ስለዚህ በምትናገረው ነገር ላለመበሳጨት ጥረት አደርጋለሁ” ብላለች።

4. ይቅር በልና እርሳው። ከባድ የሆኑ አለመግባባቶች ውይይት ሊደረግባቸውና ሊፈቱ ይገባል። ይሁን እንጂ ወንድምህ ወይም እህትህ ስህተት በሠሩ ቁጥር እየጠራህ መጨቃጨቅ ይኖርብሃል? ይሖዋ አምላክ ‘በደልን ንቀህ ለመተው’ ፈቃደኛ ስትሆን ደስ ይለዋል። (ምሳሌ 19:11) የ19 ዓመቷ አሊሰን እንዲህ ብላለች፦ “እኔና እህቴ ሬቸል ብዙውን ጊዜ በመካከላችን የሚፈጠሩትን አለመግባባቶች መፍታት እንችላለን። ሁለታችንም ይቅርታ ለመጠየቅና ለተፈጠረው አለመግባባት መንስኤ ነው ብለን የምናስበውን ነገር ለማስረዳት ዝግጁ ነን። አንዳንድ ጊዜ ችግሩን አንስቼ ከመነጋገሬ በፊት ለቀጣዩ ቀን አሳድረዋለሁ። ብዙውን ጊዜ በማግስቱ ጧት ጉዳዩን መተዉ ቀላል ይሆንልኛል፣ ላነሳውም እንኳ አልፈልግም።”

5. ወላጆቻችሁ እንዲያስታርቋችሁ አድርጉ። አንተና ወንድምህ ወይም እህትህ በአንድ ከበድ ያለ ጉዳይ ላይ የተፈጠረን አለመግባባት መፍታት ካቃታችሁ ወላጆቻችሁ እንድትታረቁ ሊረዷችሁ ይችላሉ። (ሮም 14:19) ይሁንና ያለ ወላጆቻችሁ እርዳታ አለመግባባትን መፍታት መቻላችሁ እውነተኛ ብስለት ያላችሁ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት እንደሆነ አስታውሱ።

6. የወንድምህን ወይም የእህትህን ጥሩ ባሕርያት አድንቅ። ወንድምህ ወይም እህትህ፣ የምታደንቅላቸው ባሕርይ እንደሚኖራቸው የታወቀ ነው። ወንድሞችህና እህቶችህ ካላቸው ባሕርያት መካከል የምታደንቅላቸውን አንድ ባሕርይ በጽሑፍ አስፍር።

ስም የማደንቀው ባሕርይ

․․․․․ ․․․․․

በወንድምህ ወይም በእህትህ ደካማ ጎን ላይ ከማብሰልሰል ይልቅ ያሏቸውን መልካም ባሕርያት እንደምታደንቅ ለእነሱ ለመናገር የሚያስችልህን አጋጣሚ ለምን አትፈልግም?—መዝሙር 130:3፤ ምሳሌ 15:23

የሕይወት እውነታ፦ ራስህን ችለህ ከቤት ስትወጣ አንዳንድ ጊዜ የሚያበሳጩህ ሰዎች ያጋጥሙህ ይሆናል፤ ምናልባትም ሥርዓት ከሌላቸው፣ ደንታ ቢስና ራስ ወዳድ ከሆኑ የሥራ ባልደረቦች ጋር ለመሥራት ልትገደድ ትችላለህ። ስለዚህ አሁን ከቤተሰብህ ጋር በምትኖርበት ጊዜ እንደዚህ ያሉትን ተፈታታኝ ችግሮች እንዴት በሰላም መፍታት እንደምትችል መማርህ ጠቃሚ ነው። አስቸጋሪ ባሕርይ ያለው ወንድም ወይም እህት ካለህ አዎንታዊ ጎኑን ተመልከት። ወንድምህ ወይም እህትህ ለወደፊት ሕይወትህ ጠቃሚ የሆኑ ችሎታዎች እንድታዳብር እየረዱህ ነው ማለት ነው!

መጽሐፍ ቅዱስ የአንድ ሰው ወንድሞች ወይም እህቶች በጣም የሚቀርባቸው ወዳጆቹ የማይሆኑበት ጊዜ ሊኖር እንደሚችል ይገልጻል። (ምሳሌ 18:24) ይሁን እንጂ በወንድሞችህ ወይም በእህቶችህ ‘ቅር ለመሰኘት የሚያስችል’ በቂ ምክንያት በሚኖርህ ጊዜም እንኳ ‘እርስ በርስ ለመቻቻል’ የምትጥር ከሆነ በመካከላችሁ ያለው ወዳጅነት እንዲጠናከር ማድረግ ትችላለህ። (ቆላስይስ 3:13) እንዲህ ካደረግህ ወንድሞችህና እህቶችህ የሚያደርጉት ነገር እምብዛም አያበሳጭህም። አንተም ብትሆን እነሱን ያን ያህል አታበሳጫቸውም!

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.8 አንዳንዶቹ ስሞች ተለውጠዋል።

^ አን.20 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት  ከታች ያለውን ሣጥን ተመልከት።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

በሚያናድዱ ድርጊቶችና በችግሩ መንስኤ መካከል ያለውን ልዩነት መረዳት ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

ከላይ ከተዘረዘሩት ስድስት እርምጃዎች ውስጥ ይበልጥ ልትሠራበት የምትፈልገው የትኛውን ነው?

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

 ትክክለኛውን መንስኤ ለይተህ እወቅ

በወንድማማቾችና እህትማማቾች መካከል ለሚነሱ ጭቅጭቆች መንስኤ የሚሆነውን ነገር ለይተህ የማወቅ ችሎታህን ማዳበር ትፈልጋለህ? ከሆነ ኢየሱስ ከቤተሰቡ ተለይቶ ስለሄደውና በውርስ ያገኘውን ሀብት ስላባከነው ልጅ የተናገረውን ምሳሌ አንብብ።—ሉቃስ 15:11-32

ታላቁ ልጅ ታናሽ ወንድሙ ወደ ቤቱ ተመልሶ ሲመጣ ስሜቱን የገለጸበትን መንገድ ልብ በል። ከዚያም የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ።

ታላቅ ወንድምየውን ያናደደው ድርጊት ምን ነበር?

እንዲህ እንዲሰማው ያደረገው ዋነኛው ምክንያት ምን ይመስልሃል?

አባትየው የችግሩን ዋነኛ መንስኤ ለመፍታት የሞከረው እንዴት ነበር?

ታላቅ ወንድምየው ችግሩን ለመፍታት ምን ማድረግ ያስፈልገው ነበር?

አሁን ደግሞ በቅርቡ ከወንድምህ ወይም እህትህ ጋር ተፈጥሮ ስለነበረ አለመግባባት አስብ። ከዚያም ከዚህ ቀጥሎ ካሉት ጥያቄዎች ጎን መልሶቹን ጻፍ።

ጭቅጭቁን የቀሰቀሰው ነገር ምን ነበር?

የችግሩ ዋነኛ መንስኤ ምን ይመስልሃል?

ችግሩን ለመፍታትና ከዚያ በኋላም ተመሳሳይ አለመግባባቶች እንዳይፈጠሩ ለማድረግ ሁለታችሁም የምትስማሙባቸውን ምን መሠረታዊ ደንቦች ማውጣት ትችላላችሁ?

[በገጽ 28 እና 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

እኩዮችህ ምን ይላሉ?

“ሕይወቴን በሙሉ ከእህቶቼ ጋር ጓደኛሞች እንድንሆን እፈልጋለሁ፤ ስለዚህ ይህን የዕድሜ ልክ ፕሮጀክት አሁኑኑ መጀመር አለብኝ።”

“ብዙ ነገሮችን በቤተሰብ አንድ ላይ ሆነን ስለምንሠራ አንድነት እንዲኖረን ረድቶናል። እንደ ቀድሞው ብዙ አንጨቃጨ ቅም።”

“በአንዳንድ መንገዶች ስንታይ በመካከላችን የብርሃንና የጨለማ ያህል ልዩነት አለ። ያም ሆኖ እህቴ ለእኔ በጣም ልዩ ናት። በምንም ልለውጣት አልፈልግም!”

“ወንድምና እህት ባይኖረኝ ኖሮ ደስ የሚሉኝ ትዝታዎች ሁሉ በንነው ይጠፉ ነበር። ወንድሞችና እህቶች ላላቸው ሁሉ የምመክራቸው ነገር ቢኖር ‘ያላችሁን ነገር አቅልላችሁ አትመልከቱ!’ የሚል ነው።”

[ሥዕሎች]

ቲያ

ቢያንካ

ሳማንታ

ሜርሊን

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በወንድማማቾችና እህትማማቾች መካከል የሚነሱ ጭቅጭቆች እንደ ብጉር ናቸው፤ ብጉርን ለማዳን ምልክቱን ማጥፋት ሳይሆን መንስኤውን ማከም ያስፈልግሃል