ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
“መጽሐፍ ቅዱስ በየዓመቱ በአሜሪካ በከፍተኛ ሁኔታ የሚሸጥ መጽሐፍ መሆኑ የሚያስገርም ሐቅ ነው። ይህ የሆነው ቀድሞውንም 90 በመቶ በሚሆኑ ቤተሰቦች ውስጥ ቢያንስ አንድ መጽሐፍ ቅዱስ እያለ ነው፤ . . . በየዓመቱ ወደ 25 ሚሊዮን ገደማ መጽሐፍ ቅዱሶች ይሸጣሉ።”—ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል፣ ዩናይትድ ስቴትስ
“በመላው ዓለም በየዓመቱ 4.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በእባብ በመነደፋቸው ምክንያት ጉዳት ይደርስባቸዋል፤ ከእነዚህ መካከል ቢያንስ ወደ 100,000 የሚጠጉት የሚሞቱ ሲሆን 250,000 የሚያህሉት ደግሞ የአካል ጉዳተኞች እንደሚሆኑ ግምታዊ ሐሳቦች ይጠቁማሉ።”—ዩኒቨርሲቲ ኦቭ ሜልቦርን፣ አውስትራሊያ
“በ2008 በየቀኑ 210 ቢሊዮን [የሚሆኑ] የኢሜይል መልእክቶች ተልከዋል።”—ኒው ሳይንቲስት፣ ብሪታንያ
የጎዳና ላይ ሁካታ የማስታወስ ችሎታን ያዛባል
“ሰዎች፣ መኝታ ቤታቸው በመኪና ወይም በባቡር መንገድ ዳር አሊያም በአውሮፕላን ማረፊያ አጠገብ ከሆነ ጫጫታ እያለ መተኛት ቢችሉም እንኳ የቆየን ነገር ማስታወስና አዳዲስ ነገሮችን መማር አስቸጋሪ ሊሆንባቸው ይችላል።” እንዲህ ብለው የተናገሩት በኔዘርላንድስ በሚገኘው የነርቭ ሕክምና ሳይንስ ተቋም ውስጥ የሚሠሩት አይስብራንድ ቫንደርቨርፍ የተባሉ ሰው ናቸው። አንድ ሰው እንቅልፍ ማጣቱ በማስታወስና በመማር ችሎታው ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል፤ ይሁን እንጂ ዴ ፎልክስክረንት የተሰኘው የደች ጋዜጣ እንደሚናገረው አንድ ሰው “ከእንቅልፉ . . . ባይነቃም እንኳ በከባድ እንቅልፍ ውስጥ እያለ የተወሰነ የሚረብሽ” ነገር ካጋጠመው ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ለማስታወስ ወሳኝ የሆነው ሂፖካምፐስ የሚባለው የአንጎል ክፍል በተገቢው መንገድ እንዲሠራ ከተፈለገ አንድ ሰው “ውጥረት በሚፈጥሩ እንደ ድምፅና መብራት ባሉ ነገሮች” ሳይረበሽ በደንብ መተኛት ይኖርበታል።
ርችቶች በመተንፈሻ አካላት ላይ የሚያስከትሉት ችግር
ርችቶች ሲተኮሱ ለሚያያቸው ሰው በጣም አስደናቂ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ይሁን እንጂ ወደ ከባቢ አየር የሚለቋቸው ንጥረ ነገሮች ለጤንነትህ አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ብዙ ርችቶች የተለያዩ ቀለማትን እንዲፈነጥቁ ሲባል የብረት ጨው (ሜታል ሶልትስ) እንዲኖራቸው ይደረጋል፤ ለምሳሌ ቀይ ቀለም እንዲኖረው ስትሮንቲየም፣ አረንጓዴ ቀለም እንዲኖረው ደግሞ ባሪየም ይገባበታል። ለአዲስ ዓመት ከሚተኮሱ ርችቶች በፊትና በኋላ በተወሰዱ የበረዶ ናሙናዎች ላይ ጥናት ያደረጉ የኦስትሪያ ተመራማሪዎች በበረዶው ውስጥ የሚገኘው የባሪየም ይዘት መጠን በ500 እጥፍ እንደጨመረ ደርሰውበታል። አንድ ሰው በባሪየም መመረዙ የአየር መተላለፊያው ቱቦ እንዲጠብ ስለሚያደርግ ከርችት የሚወጣውን ጭስ ወደ ሰውነት ማስገባት እንደ አስም ያሉትን የመተንፈሻ አካል ችግሮች ሊያባብስ እንደሚችል ተመራማሪዎች ይናገራሉ።
በነፋስ የሚንቀሳቀሱ ሞተሮች የሌሊት ወፎችን እየገደሉ ነው
ካናዳ ውስጥ በአልበርታ ከተማ የሌሊት ወፎች በነፋስ በሚንቀሳቀሱ ሞተሮች ሥር ሞተው መገኘታቸውን ሳይንቲፊክ አሜሪካን የተሰኘው መጽሔት ዘግቧል። የሌሊት ወፎች የድምፅን ሞገድ የመለየትና የበረራ አስደናቂ ችሎታ እያላቸው እንኳ ሞተው መገኘታቸው ተመራማሪዎችን ግራ አጋብቷቸዋል። ይሁን እንጂ ተመራማሪዎች ሞተው ከተገኙት የሌሊት ወፎች መካከል 92 በመቶ የሚያህሉት በውስጣቸው ደም ፈስሶ እንደነበር ደርሰውበታል፤ ይህ ደግሞ በቀላሉ የሚጎዳውን የሌሊት ወፍ የመተንፈሻ አካል በነፋስ የሚንቀሳቀሱ ሞተሮች የፈጠሩትን የአየር ግፊት መቋቋም ስላልቻለ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል። እነዚህ ሞተሮች በሰዓት እስከ 200 ኪሎ ሜትር ይሽከረከራሉ። በዋነኝነት ጉዳት የሚደርስባቸው የሌሊት ወፍ ዓይነቶች ነፍሳትን የሚመገቡትና ከቦታ ወደ ቦታ የሚፈልሱት የሌሊት ወፎች ናቸው፤ በመሆኑም በነፋስ የሚንቀሳቀስ ሞተር ሥነ ምኅዳሩን እንዳያፋልስ ተፈርቷል።