ዕፁብ ድንቅ የሆነው አጽናፈ ዓለም
ዕፁብ ድንቅ የሆነው አጽናፈ ዓለም
ከመቶ ዓመት በፊት ሳይንቲስቶች አጽናፈ ዓለም ሲባል ፍኖተ ሐሊብ የሚባለው የእኛ ጋላክሲ ብቻ እንደሆነ ያምኑ ነበር። ይሁን እንጂ በ20ኛው መቶ ዘመን በሥነ ፈለክ፣ በፊዚክስና በቴክኖሎጂው መስክ የተገኘው ከፍተኛ እድገት አጽናፈ ዓለም ይህ ነው የማይባል ስፋት እንዳለው ለማወቅ አስችሏል። አንዳንዶቹ ግኝቶች ሰው ራሱን በትሕትና ዝቅ እንዲያደርግ የሚያስገድዱ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ከ90 በመቶ በላይ ስለሚሆነው የአጽናፈ ዓለም ክፍል ምንም ነገር እንደማያውቁ ተገንዝበዋል። ከዚህም በላይ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ወደዚህ መደምደሚያ እንዲደርሱ ያደረጓቸው ግኝቶች ሳይንቲስቶች መሠረታዊ የሆኑ የፊዚክስ ሕጎችን በተመለከተ ባላቸው እውቀት ላይ አንዳንድ ጥያቄዎችን እንዲያነሱ አድርገዋቸዋል። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ያሉት ጥያቄዎች አዲስ አይደሉም።
ለምሳሌ ያህል፣ በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ የፊዚክስ ሊቃውንት የብርሃንን ፍጥነት በተመለከተ አንድ እንግዳ ነገር አስተውለው ነበር። የብርሃን ፍጥነት ከአንድ ተመልካች አንጻር ሲታይ ሰውየው የሚጓዝበት ፍጥነት ምንም ይሁን ምን ምንጊዜም በተመሳሳይ ፍጥነት እንደሚጓዝ ተገነዘቡ። ይህ ሐሳብ ምክንያታዊ አይመስልም ነበር! ሆኖም አልበርት አንስታይን በ1905 አንጻራዊነት የተባለውን ንድፈ ሐሳብ ባወጣ ጊዜ ጉዳዩ እንደገና ታየ፤ ይህ ልዩ ንድፈ ሐሳብ ርቀት (ርዝመት)፣ ጊዜና መጠነ ቁስ አንጻራዊ ነገሮች እንደሆኑ የሚገልጽ ነው። በ1907 ደግሞ አንስታይን “በሕይወቴ ውስጥ እጅግ ያስደሰተኝ ሐሳብ” ብሎ የገለጸው አንድ አዲስ ሐሳብ ብልጭ አለለት። በኋላም የአንጻራዊነትን ንድፈ ሐሳብ አዳብሮ በ1916 ለሕትመት አበቃው። አንስታይን ከፍተኛ ለውጥ ባመጣው በዚህ ሥራው ላይ ስበት፣ ቦታና ጊዜ እንዴት በቅንጅት እንደሚሠሩ ከመግለጹም በላይ አይዛክ ኒውተን ባወጣው የፊዚክስ ሕግ ላይ አንዳንድ ማሻሻያዎችን አደረገ።
እየሰፋ የሚሄደው አጽናፈ ዓለም
አንስታይን በወቅቱ ከነበረው ግንዛቤ በመነሳት አጽናፈ ዓለም እየሰፋም ሆነ እየጠበበ የማይሄድ አልፎ ተርፎም ካለበት የማይንቀሳቀስ እንደሆነ አድርጎ ያምን ነበር። ይሁን እንጂ ኤድዊን ሀብል የተባለው አሜሪካዊ የሥነ ፈለክ ተመራማሪ በ1929 አጽናፈ ዓለም እየሰፋ የሚሄድ እንደሆነ የሚያሳይ ማስረጃ አቀረበ።
በተጨማሪም ሀብል፣ ማታ ማታ ሰማይ ላይ ብርሃን የሚፈነጥቁና ደብዘዝ ብለው የሚታዩ አንዳንድ አካላትን ምንነት በተመለከተ ለረዥም ጊዜ ሳይታወቅ የቆየውን ሚስጥር ግልጥልጥ አደረገው፤ እነዚህ አካላት ደመና መስለው ስለሚታዩ ኔቡላ ተብለው ይጠሩ ነበር። ይሁንና እነዚህ ሁሉ ኔቡላዎች የሚገኙት በእኛ ጋላክሲ ውስጥ ነው? ወይስ ብሪታንያዊው የሥነ ፈለክ ተመራማሪ ሰር ዊሊያም ኸርሸል (1738-1822) ከአንድ መቶ ዓመት በፊት እንደተናገረው ከእኛ ጋላክሲ ውጪ?
ሀብል ከእነዚህ የሕዋ አካላት አንዱ የሆነውና በአንድሮሜዳ ኅብረ ከዋክብት ውስጥ የሚገኝው ታላቁ ኔቡላ በምን ያህል ርቀት ላይ እንደሚገኝ ለመገመት ባደረገው ጥረት ይህ ኔቡላ አንድ ሚሊዮን የብርሃን ዓመት ርቆ የሚገኝ ጋላክሲ እንደሆነ ተገነዘበ። እኛ ያለንበት ፍኖተ ሐሊብ ዲያሜትሩ 100,000 የብርሃን ዓመት “ብቻ” መሆኑ ይህ ኔቡላ የሚገኘው ከእኛ ጋላክሲ በጣም ርቆ እንደሆነ ያሳያል። ሀብል ሌሎች ኔቡላዎች በምን ያህል ርቀት ላይ እንደሚገኙ ለመለካት ያደረገው ጥረት አጽናፈ ዓለም * መስክ ሥር ነቀል ለውጥ አምጥቷል።
ይህ ነው የማይባል ስፋት እንዳለው ለመገንዘብ ያስቻለው ከመሆኑም ሌላ በሥነ ፈለክና በኮስሞሎጂከዚያ ብዙም ሳይቆይ ሀብል በርቀት የሚገኙ ጋላክሲዎች ከእኛ እየሸሹ የሚሄዱ መሆናቸውን ማየቱ አጽናፈ ዓለም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ የሚሄድ መሆኑን እንዲገነዘብ አስችሎታል። በተጨማሪም ጋላክሲው እየራቀ በሄደ መጠን የሚሸሽበት ፍጥነት የዚያኑ ያህል እንደሚጨምር አስተዋለ። በዚህ ረገድ የተገኘው ማስተዋል ትናንት የነበረው አጽናፈ ዓለም ከዛሬው ያነሰ እንደሚሆን ያመለክታል። ሀብል አዲስ ግኝቱን በ1929 ለሕትመት ማብቃቱ አጽናፈ ዓለም እንዴት እንደተገኘ ለሚገልጸው ለቢግ ባንግ ንድፈ ሐሳብ መዳበር መንገድ ጠርጓል፤ በቢግ ባንግ ንድፈ ሐሳብ መሠረት አጽናፈ ዓለም የተገኘው ከ13 ቢሊዮን ዓመታት በፊት በጠፈር ውስጥ በተከሰተ ከፍተኛ ፍንዳታ አማካኝነት ነው። ይሁን እንጂ ስለዚህ ጉዳይ እስከ አሁን ድረስ የተሟላ ማብራሪያ ማግኘት አልተቻለም።
የሚሰፋበት ፍጥነት ምን ያህል ነው?
ሀብል ከኖረበት ዘመን ጀምሮ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች አጽናፈ ዓለም እየሰፋ የሚሄድበትን ፍጥነት (“ሀብል ኮንስታንት” ተብሎ ይጠራል) በትክክል ለማወቅ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ፍጥነቱን በትክክል ማወቅ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች አጽናፈ ዓለም እየሰፋ የሚሄድበትን ፍጥነት ማስላት ከቻሉ ይህን ስሌት የአጽናፈ ዓለምን ዕድሜ ለማስላት ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ከዚህም በላይ አጽናፈ ዓለም እየሰፋ የሚሄድበት ፍጥነት የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ የሚጠቁመው ነገር ሊኖር ይችላል። እንዴት? ለምሳሌ ያህል፣ አጽናፈ ዓለም እየሰፋ የሚሄድበት ፍጥነት በጣም አዝጋሚ ከሆነ የኋላ ኋላ የስበት ኃይል አይሎ ሁሉም ነገር በአንድነት ተንኮታኩቶ እንዲጠፋ ሊያደርግ ይችላል! በሌላ በኩል ደግሞ እየሰፋ የሚሄድበት ፍጥነት በጣም ከፍተኛ ከሆነ አጽናፈ ዓለም ለዘላለም እየተለጠጠ ሄዶ በውስጡ ያሉት አካላት ለመገመት በሚያስቸግር መጠን ሊራራቁ ይችላሉ።
አጽናፈ ዓለም የሚሰፋበት ፍጥነት ይበልጥ በትክክል መታወቁ ለአንዳንድ ጥያቄዎች መልስ ያስገኘ ቢሆንም ሌሎች ጥያቄዎችን አስነስቷል፤ እነዚህ ጥያቄዎች ቁስ አካልንና ዋና ዋና የተፈጥሮ ኃይሎችን በተመለከተ በአሁኑ ጊዜ ያለንን ግንዛቤ እንድንጠራጠር የሚያደርጉ ናቸው።
ሚስጥራዊ ኃይልና ሚስጥራዊ ቁስ አካል
በ1998 ተመራማሪዎች ከአንድ የሚፈነዳ ልዩ ኮከብ የሚወጣውን ብርሃን ሲመረምሩ አጽናፈ ዓለም የሚሰፋበት ፍጥነት እየጨመረ እንደመጣ የሚያሳይ ማስረጃ አግኝተዋል! * ሳይንቲስቶቹ መጀመሪያ ላይ ተጠራጥረው የነበረ ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ ሌሎች ተጨማሪ ማስረጃዎችን አገኙ። አጽናፈ ዓለም በፍጥነት እየሰፋ እንዲሄድ የሚያደርገው ምን ዓይነት ኃይል እንደሆነ ለማወቅ ፈልገው ነበር። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይህ ኃይል ስበት የማይበግረው ይመስላል፤ በሌላ በኩል ደግሞ አሁን ካሉት ንድፈ ሐሳቦች ጋር የሚጣጣም አይደለም። ምንነቱ የማይታወቀው ይህ ኃይል ሚስጥራዊ ኃይል መባሉ የተገባ ሲሆን ወደ 75 በመቶ የሚጠጋውን የአጽናፈ ዓለም ክፍል ሊሸፍን ይችላል።
ይሁን እንጂ በቅርቡ የተገኘው ይህ ሚስጥራዊ ኃይል ብቻ አይደለም። ሌላ “ሚስጥራዊ” ነገር መኖሩ የተረጋገጠው በ1980ዎቹ ዓመታት የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ስለተለያዩ ጋላክሲዎች ጥናት ባካሄዱበት ጊዜ ነበር። የእኛን ጨምሮ እነዚህ ጋላክሲዎች የሚሽከረከሩበት ፍጥነት በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ መበታተን የነበረባቸው ይመስላል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው እነዚህ ጋላክሲዎች ሳይበታተኑ እርስ በርስ እንዲሳሳቡ ያደረጋቸው አንድ ዓይነት ቁስ አካል መኖር አለበት። ታዲያ ይህ ቁስ አካል ምንድን ነው? ሳይንቲስቶች ስለዚህ ቁስ አካል ምንም የሚያውቁት ነገር ስለሌለ እንዲሁም ጨረርን ይዞ ስለማያስቀርና ስለማያመነጭ ወይም ስለማያንጸባርቅ ሚስጥራዊ ቁስ አካል ብለው ጠሩት። * ይህ ሚስጥራዊ ቁስ አካል መጠኑ ምን ያህል ነው? ስሌቱ እንደሚያመለክተው 22 በመቶ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆነውን የአጽናፈ ዓለም ክፍል ሊይዝ ይችላል።
እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ በአሁኑ ጊዜ ባለው ግምታዊ ሐሳብ መሠረት ከአጽናፈ ዓለም ውስጥ በውል የሚታወቀው ቁስ አካል 4 በመቶ የሚያህለው ብቻ ነው። የቀረውን የአጽናፈ ዓለም ክፍል የሚሸፍኑት ደግሞ ሁለቱ የማይታወቁት ነገሮች፣ ማለትም ሚስጥራዊ ቁስ አካልና ሚስጥራዊ ኃይል ይመስላሉ። በመሆኑም 95 በመቶ የሚሆነው የአጽናፈ ዓለም ክፍል አሁንም ድረስ ሙሉ በሙሉ ሚስጥር ነው! *
ማቆሚያ የሌለው ምርምር
ሳይንስ ለተለያዩ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ጥረት እያደረገ ነው፤ ሆኖም ለአንድ ጥያቄ የሚገኘው መልስ ሌሎች ብዙ ጥያቄዎችን ይወልዳል። ይህ ሐቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመክብብ 3:11 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ጥልቅ እውቀት የያዘ አነጋገር ያስታውሰናል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “[አምላክ] ሁሉንም ነገር በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ በሰዎችም ልብ ዘላለማዊነትን አኖረ፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያደረገውን ማወቅ አይችሉም።”
እርግጥ ነው፣ ዕድሜያችን አጭር በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ ልንቀስም የምንችለው የተወሰነ እውቀት ብቻ ነው፤ ከዚያም ውስጥ አብዛኛው በግምት ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ውሎ አድሮ ሊለወጥ ይችላል። ይሁን እንጂ አምላክ ታማኝ ለሆኑ ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የመስጠት ዓላማ ስላለው ይህ ሁኔታ በዚህ አይቀጥልም። በዚያን ጊዜ ሰዎች የእሱን የእጅ ሥራ ለዘላለም መመርመርና ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ይችላሉ።—መዝሙር 37:11, 29፤ ሉቃስ 23:43
ስለዚህ አጽናፈ ዓለም ይጠፋል ብለን አንሸበርም። ደግሞም ሳይንስ የደረሰበት እውቀት እጅግ ኢምንት ነው፤ ፈጣሪ ግን ሁሉን ያውቃል።—ራእይ 4:11
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.7 ሥነ ፈለክ፣ ከምድራችን ውጪ ባሉ ግዑዛን አካላትና ቁስ አካላት ላይ የሚደረግ ጥናት ነው። ኮስሞሎጂ ደግሞ የሥነ ፈለክ አንዱ ዘርፍ ሲሆን ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደገለጸው “ስለ አጽናፈ ዓለም አወቃቀርና ዕድገት፣ እንዲሁም በውስጡ ስላሉት ኃይሎች የሚያጠና ሳይንስ ነው።” አክሎም “ኮስሞሎጂስቶች አጽናፈ ዓለም የተሠራው እንዴት እንደሆነ፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በውስጡ ምን እንደተከናወነና ወደፊት ምን እንደሚከናወን ለማወቅ ጥረት ያደርጋሉ” በማለት ገልጿል።
^ አን.13 የሚፈነዱት ከዋክብት 1ኤ ሱፐርኖቫ በመባል የሚታወቁ ሲሆን ለአጭር ጊዜ ይሁን እንጂ የአንድ ቢሊዮን ፀሐዮችን ያህል ድምቀት ሊሰጡ ይችላሉ። የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች እነዚህን ሱፐርኖቫዎች እንደ መለኪያ አድርገው ይጠቀሙባቸዋል።
^ አን.14 ሚስጥራዊ ቁስ አካል መኖሩን በተመለከተ ግምታዊ ሐሳብ የተሰጠው በ1930ዎቹ ዓመታት ሲሆን በትክክል የተረጋገጠው ግን በ1980ዎቹ ዓመታት ውስጥ ነው። በዛሬው ጊዜ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች አንድ የጋላክሲዎች ስብስብ ምን ያህል ሚስጥራዊ ቁስ አካል እንዳለው የሚለኩት፣ በሩቅ ከሚገኝ አካል ላይ የሚፈነጥቀው ብርሃን በከዋክብት ስብስቡ ላይ ሲያርፍ የሚታጠፍበትን መንገድ በመመልከት ነው።
^ አን.15 የያዝነው ዓመት ማለትም 2009 “ዓለም አቀፍ የሥነ ፈለክ ዓመት” ተብሎ የተሰየመ ሲሆን ጋሊሊዮ ጋሊሊ ለጠፈር ምርምር የሚረዳ ቴሌስኮፕ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመበት 400ኛ ዓመት የሚከበረውም በዚህ ዓመት ነው።
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ቀና ብለህ ተመልከት፤ ትሑት እንድትሆን የሚያደርግ ነገር ታያለህ
በጥንት ዘመን የኖረ አንድ የአምላክ አገልጋይ፣ ጥርት ያለውን ሰማይ ማታ ላይ ቀና ብሎ ሲመለከት ከአክብሮት የመነጨ ፍርሃት ያደረበት ሲሆን ይህን ስሜቱን በግጥም መልክ ገልጾታል። መዝሙር 8:3, 4 እንዲህ ይላል፦ “የጣቶችህን ሥራ፣ ሰማያትህን ስመለከት፣ በስፍራቸው ያኖርሃቸውን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን ሳይ፣ በሐሳብህ ስፍራ ትሰጠው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ትጠነቀቅለትም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው?” መዝሙራዊው ሰማዩን ይበልጥ ለመመልከት የሚያስችለው ቴሌስኮፕም ሆነ ልዩ ካሜራ አልነበረውም። ታዲያ እኛ ከመዝሙራዊው ይበልጥ ከአክብሮት የመነጨ ፍርሃት ሊያድርብን አይገባም?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
74 በመቶ ሚስጥራዊ ኃይል
22 በመቶ ሚስጥራዊ ቁስ አካል
4 በመቶ በውል የሚታወቀው ቁስ አካል
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ከጀርባ የሚታየው ፎቶ፦ Based on NASA photo
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ከጀርባ የሚታየው ፎቶ፦ Based on NASA photo