ሃይማኖትህን መቀየር ስህተት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ሃይማኖትህን መቀየር ስህተት ነው?
አቭታር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስትጀምር የሲክ እምነት ተከታዮች የሆኑት ቤተሰቦቿ በሁኔታው በጣም ተበሳጭተው ነበር። አቭታር እንዲህ ብላለች፦ “በአገራችን አንድ ሰው ሃይማኖቱን ከቀየረ ኅብረተሰቡ ያገልለዋል። ስማችንም እንኳ ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ ነው። ሃይማኖትህን መቀየር ማንነትህን እንደ መካድ የሚቆጠር ከመሆኑም ሌላ እንዲህ በማድረግህ ቤተሰብህን እንደማታከብር ተደርገህ ትታያለህ።”
አቭታር ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክር ሆናለች። ታዲያ ሃይማኖቷን መቀየሯ ስህተት ነበር? ምናልባት አንተም እንደ አቭታር ቤተሰብ ይሰማህ ይሆናል። ሃይማኖትህ ሲወርድ ሲዋረድ ከመጣው የቤተሰብህ ታሪክና ባሕል ጋር በጥብቅ የተቆራኘ በመሆኑ ሃይማኖትን መቀየር ተገቢ እንዳልሆነ ሊሰማህ ይችላል።
እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው ለቤተሰቡ አክብሮት ማሳየቱ አስፈላጊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የወለደህን አባትህን አድምጥ” ይላል። (ምሳሌ 23:22) ይሁንና ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ስለ ፈጣሪያችንና ስለ ዓላማዎቹ የሚገልጸውን እውነት ማግኘት ነው። (ኢሳይያስ 55:6) ታዲያ ይህንን እውነት ማግኘት ይቻላል? ከሆነስ፣ ይህንን እውነት ማግኘትህ ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?
እውነተኛውን ሃይማኖት ፈልጎ ማግኘት
የዓለም ሃይማኖቶች የሚያስተምሩት ትምህርት እርስ በርሱ የሚጋጭ ነው። ከዚህ አንጻር ሁሉም ትምህርቶች እውነተት እንደማይሆኑ ግልጽ ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ‘ለአምላክ ቅንዓት’ ያላቸው በርካታ ሰዎች ቢኖሩም ቅንዓታቸው ‘በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ’ አይደለም። (ሮም 10:2) ይሁንና ሐዋርያው ጳውሎስ በ1 ጢሞቴዎስ 2:4 ላይ እንደገለጸው የአምላክ ፈቃድ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች . . . ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ” ነው። እንዲህ ያለው ትክክለኛ እውቀት ሊገኝ የሚችለው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስን ለመመርመር የሚያነሳሱ አንዳንድ ምክንያቶችን እስቲ እንመልከት። በአምላክ መንፈስ መሪነት የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን የጻፈው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው፤ እንዲሁም ለማስተማር . . . ይጠቅማል።” (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) እውነትን ለማግኘት ምርምር በምታደርግበት ወቅት፣ መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ መጽሐፍ መሆኑን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን መርምር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት የታሪክ ዘገባዎች ትክክለኛ መሆናቸውንና ትንቢቶቹ ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸውን እንዲሁም በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያለው ጥበብ ወደር የማይገኝለት መሆኑን በመመርመር የአምላክ ቃል እውነት መሆኑን ራስህ ለማረጋገጥ ሞክር።
በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ሁሉም ሃይማኖቶች እንዳልሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፤ ሰዎች የሚሰሙትን ሁሉ ማመን እንደሌለባቸው ከዚህ ይልቅ “በመንፈስ የተነገሩት ቃላት ከአምላክ የመነጩ መሆን አለመሆናቸውን” መመርመር እንደሚያስፈልጋቸው የአምላክ ቃል ይገልጻል። (1 ዮሐንስ 4:1) ለምሳሌ ከአምላክ የሚመነጭ ማንኛውም ትምህርት፣ ዋነኛው የአምላክ ባሕርይ የሆነውን ፍቅርን ጨምሮ ከሁሉም ባሕርያቱ ጋር የሚስማማ መሆን አለበት።—1 ዮሐንስ 4:8
አምላክ፣ እሱን ‘አጥብቀን በመሻት እንድናገኘው’ እንደሚፈልግ መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል። (የሐዋርያት ሥራ 17:26, 27) ፈጣሪያችን እውነትን እንድንፈልግ የሚሻ በመሆኑ ባገኘነው መረጃ ላይ ተመሥርተን የምንወስደው እርምጃ ሃይማኖታችንን እንድንቀይር የሚያደርገን ቢሆንም እንኳ እንዲህ ማድረጋችን ስህተት ሊሆን አይችልም። ይሁንና ሃይማኖታችንን መቀየራችን የሚያስከትላቸውን ችግሮች በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል?
ለቤተሰባችን ታማኝ መሆን ያለብን እስከ ምን ድረስ ነው?
ሰዎች ሃይማኖታቸውን ሲቀይሩ ከዚህ ቀደም ይካፈሉባቸው በነበሩ አንዳንድ የአምልኮ ሥነ ሥርዓቶች ወይም በዓላት ላይ ላለመካፈል ይወስኑ ይሆናል። እንዲህ ያለ እርምጃ መውሰዳቸው ደግሞ ቤተሰባቸውን ሊያስቆጣ እንደሚችል የታወቀ ነው። ኢየሱስ ይህ ሊሆን እንደሚችል ሲገልጽ ለተከታዮቹ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እኔ የመጣሁት ወንድ ልጅን ከአባቱ፣ ሴት ልጅን ከእናቷ እንዲሁም ሙሽሪትን ከአማቷ ለመለያየት ነው።” (ማቴዎስ 10:35) እዚህ ላይ ኢየሱስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በሰዎች መካከል ግጭት እንዲፈጠር የሚያደርግ እንደሆነ መግለጹ ነበር? አይደለም። ኢየሱስ፣ አንድ ሰው ከቤተሰቡ የተለየ እምነት ሲይዝ የቤተሰቡ አባላት ሊቃወሙት እንደሚችሉ እየተናገረ ነበር።
ታዲያ አንድ ሰው ከቤተሰቡ ጋር ላለመጋጨት ሲል ማንኛውንም መሥዋዕትነት መክፈል ይኖርበታል? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ልጆች ለወላጆቻቸው መታዘዝ እንዲሁም ሚስቶች ለባሎቻቸው መገዛት እንዳለባቸው ያስተምራል። (ኤፌሶን 5:22፤ 6:1) ያም ቢሆን አምላክን የሚወዱ ሰዎች ‘ከሰው ይልቅ እሱን እንደ ገዥያቸው አድርገው መታዘዝ’ እንዳለባቸው ይገልጻል። (የሐዋርያት ሥራ 5:29) በዚህም የተነሳ ለአምላክ ታማኝ ለመሆን ስትል አንዳንድ የቤተሰብህን አባላት የማያስደስት ውሳኔ የምታደርግበት ጊዜ ሊኖር ይችላል።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ በትክክለኛና በሐሰተኛ ትምህርቶች መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ ቢያስቀምጥም እያንዳንዱ ሰው በዚህ ረገድ የራሱን ምርጫ እንዲያደርግ አምላክ ነፃነት ሰጥቶታል። (ዘዳግም 30:19, 20) በመሆኑም ማንኛውም ሰው የተሳሳተ እንደሆነ በሚሰማው አምልኮ እንዲካፈል ወይም ከእምነቱና ከቤተሰቡ አንዱን እንዲመርጥ ሊገደድ አይገባም። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የቤተሰብ አባላት እንዲለያዩ ያደርጋል? አያደርግም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ባልና ሚስት ሃይማኖታቸው የተለያየ ቢሆንም እንኳ አብረው እንዲኖሩ ያበረታታል።——1 ቆሮንቶስ 7:12, 13
ፍርሃትን ማሸነፍ
ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ብታጠና ‘የአካባቢዬ ሰዎች ምን ይሉኛል?’ ብለህ ትፈራ ይሆናል። መሪያማ የተባለች አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች፦ “ቤተሰቦቼ፣ ሊያስተዳድረኝ የሚችል ጥሩ ባል ማግኘት እንደማልችል ስለተሰማቸው መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቴን ተቃውመው ነበር።” መሪያማ ግን በይሖዋ አምላክ በመታመን ማጥናቷን ቀጠለች። (መዝሙር 37:3, 4) አንተም እንዲህ ማድረግ ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህ ምን ሊያስከትልብህ እንደሚችል በማሰብ ከመፍራት ይልቅ እንዲህ ማድረግህ በሚያስገኛቸው ጥቅሞች ላይ ትኩረት አድርግ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰዎች የተሻለ ሕይወት እንዲመሩ እንዲሁም ጥሩ ባሕርያትን እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል። ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠኑ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ለቤተሰባቸው ፍቅር ማሳየትን ይማራሉ። እንዲሁም የሌሎችን ስሜት የሚያቆስል ነገር መናገርን፣ አካላዊ ጥቃት መሰንዘርን፣ ከልክ በላይ የአልኮል መጠጥ መጠጣትንና አደገኛ ዕፆችን መውሰድን የመሳሰሉ መጥፎ ልማዶችን እንዲያስወግዱ መጽሐፍ ቅዱስ ይረዳቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 7:1) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰዎች እንደ ታማኝነት፣ ሐቀኝነትና ታታሪ እንደ መሆን ያሉ ግሩም ባሕርያትን እንዲያዳብሩም ያበረታታል። (ምሳሌ 31:10-31፤ ኤፌሶን 4:24, 28) የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች ተግባራዊ ማድረግ የሚያስገኘውን ጥቅም በራስህ ሕይወት መመልከት እንድትችል ለምን መጽሐፍ ቅዱስን አታጠናም?
ይህን አስተውለኸዋል?
▪ ሃይማኖትህን መመርመርህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?—ምሳሌ 23:23፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4
▪ እውነተኛውን ሃይማኖት መለየት የምትችለው እንዴት ነው?—2 ጢሞቴዎስ 3:16፤ 1 ዮሐንስ 4:1
▪ የቤተሰብ ተቃውሞ መጽሐፍ ቅዱስን ከማጥናት ሊያግድህ ይገባል?—የሐዋርያት ሥራ 5:29
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰዎች የተሻለ ሕይወት እንዲመሩ እንዲሁም ጥሩ ባሕርያትን እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መሪያማና ባለቤቷ