“ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ!” የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ
“ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ!” የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ
▪ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከግንቦት 22-24 በሚካሄደው ስብሰባ የሚጀምሩት በሺህ የሚቆጠሩት የሦስት ቀን የአውራጃ ስብሰባዎች በቀጣዮቹ ወራት በመላው ዓለም ይካሄዳሉ። በኢትዮጵያ ሦስቱንም ቀናት እያንዳንዱ ክፍለ ጊዜ የሚጀምረው 3:20 ላይ በሚደመጥ ሙዚቃ ይሆናል። የዓርብ ዕለት ጭብጥ “ዝግጁ ሁኑ” የሚል ሲሆን በማቴዎስ 24:44 ላይ የተመሠረተ ነው። ሊቀ መንበሩ ንግግር ካቀረበ በኋላ “የአውራጃ ስብሰባዎች ነቅተን እንድንኖር ይረዱናል” እንዲሁም “‘የጊዜና የወቅት’ አምላክ የሆነው ይሖዋ” የሚሉት ንግግሮች ይቀርባሉ። ከዚያም “ነቅተው ይኖሩ የነበሩ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮችን ምሰሉ” የሚል ርዕስ ባለው ሲምፖዚየም ሥር ኖኅ፣ ሙሴ እና ኤርምያስ ነቅተው የኖሩት እንዴት እንደሆነ የሚያብራሩ ንግግሮች ይቀርባሉ። የጠዋቱ ፕሮግራም የሚደመደመው “ይሖዋ ‘ምንጊዜም ነቅተን እንድንጠብቅ’ የሚረዳን እንዴት ነው?” የሚል ርዕስ ባለውና የስብሰባውን ጭብጥ በሚያብራራው ንግግር ነው።
ዓርብ ከሰዓት በኋላ የሚቀርበው የመጀመሪያው ንግግር “‘የመጨረሻ ቀኖችን’ በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው” የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን ከዚያም “‘ቀኑንም ሆነ ሰዓቱን አታውቁም’—ለምን?” እና “መጨረሻው መቅረቡን እወቁ” የሚሉ ንግግሮች ይቀርባሉ። ቀጥሎ ደግሞ “ክርስቲያን ቤተሰቦች ‘ነቅታችሁ ጠብቁ!’” የሚል ርዕስ ያለው ስድስት ንግግሮችን የያዘ ሲምፖዚየም ይቀርባል። የመጀመሪያዎቹ ሦስት ንግግሮች በባሎች፣ በሚስቶችና በልጆች ላይ ያተኮረ ጭብጥ ያላቸው ሲሆን ቀሪዎቹ ሦስት ንግግሮች “ምንጊዜም አጥርቶ የሚያይ ዓይን ይኑራችሁ፣” “መንፈሳዊ ግቦችን ለመከታተል የምታደርጉትን ጥረት ግፉበት” እና “የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁ እንዳይቋረጥ ጥረት አድርጉ” የሚል ርዕስ አላቸው። የከሰዓት በኋላው ክፍለ ጊዜ የሚደመደመው “‘ምንጊዜም በጥንቃቄ እንድናስተውል’ የሚገፋፉን ስንኞች” በሚለው ንግግር ነው።
የቅዳሜው ዕለት ጭብጥ “የማስተዋል ስሜቶቻችሁን ጠብቁ፤ ንቁዎች ሆናችሁ ኑሩ” የሚል ሲሆን በ1 ጴጥሮስ 5:8 ላይ የተመሠረተ ነው። “ሰዎች ‘ከእንቅልፍ እንዲነቁ’ እርዷቸው” በሚል ርዕስ የሚቀርበው ባለ አምስት ክፍል ሲምፖዚየም “አገልግሎታችን ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?፣” “አገልግሎት ላይ ስትሆኑ አስተዋዮች ሁኑ፣” “ችሎታችሁን ለማሻሻል ትኩረት ስጡ፣” “ዘመዶቻችሁን አትርሷቸው!” እና “ምንጊዜም የጥድፊያ ስሜት ይኑራችሁ!” የሚሉ ንግግሮችን የያዘ ነው። ከዚህ ቀጥሎ “ኢየሱስ ነቅቶ በመኖር ረገድ የተወውን ምሳሌ ተከተሉ” እና “በጸሎት ረገድ ንቁዎች ሁኑ” የሚሉ ንግግሮች ከቀረቡ በኋላ የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ጥምቀትን አስመልክቶ በሚቀርብ ንግግር ይደመደማል። ከዚያም ብቃቱን ያሟሉ ሰዎች የጥምቀት ሥነ ሥርዓት ይካሄዳል።
በቅዳሜ ከሰዓት በኋላው ፕሮግራም ላይ “እሳቱ፣” “ጉድጓዱ፣” “ወጥመዱ፣” “አንቆ የሚይዘው ወጥመድ” እና “የሚያደቅቀው ወጥመድ” የሚሉ ንግግሮችን የያዘና “በሰይጣን ወጥመዶች እንዳትያዙ ተጠንቀቁ!” የሚል ርዕስ ያለው ባለ አምስት ክፍል ሲምፖዚየም ይቀርባል። ከዚያም “እስክሞት ድረስ ንጹሕ አቋሜን አላጎድፍም” የሚል ርዕስ ያለው ልዩ ፕሮግራም ይቀርባል። የዕለቱ ፕሮግራም “‘በኋላችሁ ያሉትን ነገሮች’ አትመልከቱ” እና “ነቅቶ መኖር የሚቻልበትን መንገድ ከኢየሱስ ሐዋርያት ተማሩ” በሚሉ ንግግሮች ይደመደማል።
የእሁድ ዕለት ጭብጥ “ጠብቀው፤ . . . ከቶም አይዘገይም” የሚል ሲሆን በዕንባቆም 2:3 ላይ የተመሠረተ ነው። በመጀመሪያ በዕለቱ ጭብጥ ላይ ያተኮረ ንግግር ይቀርባል፤ ከዚያም “ዓይናችሁ ምንጊዜም በማይታዩት ነገሮች ላይ ያተኩር” በሚል ርዕስ የሚቀርበው ሲምፖዚየም የሚከተሉትን ርዕሰ ጉዳዮች ያብራራል፦ “አሥሩ ቀንዶች . . . ጋለሞታይቱን ይጠሏታል፣” “ብሔራት ለይሖዋ እውቅና መስጠት ይኖርባቸዋል፣” “‘እነዚያ መንግሥታት’ ሁሉ ይደቃሉ፣” “ዲያብሎስ ‘ለአንድ ሺህ ዓመት ይታሰራል’፣” “ቤት ይሠራሉ፤ ወይንንም ይተክላሉ፣” “ተኵላና የበግ ጠቦት በአንድነት ይበላሉ፣” ‘አምላክ እንባን ሁሉ ይጠርጋል፣’ ‘በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ ይወጣሉ’ እና “አምላክ ለሁሉም ሁሉንም ነገር ይሆናል”። የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ “በዓለም ላይ ከሚመጣው ጥፋት መትረፍ የምትችሉት እንዴት ነው?” የሚል ርዕስ ባለው የሕዝብ ንግግር ይደመደማል።
እሁድ ከሰዓት በኋላ ልዩ ፕሮግራም የሚቀርብ ሲሆን ይህም ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅ በተናገረው ምሳሌ ላይ የተመሠረተውና “ወንድምህ ሞቶ ነበር አሁን ግን ሕያው ሆኗል” የሚል ርዕስ ያለው ዘመናዊ ድራማ ነው። ከዚያም ሳምንታዊው የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ከቀረበ በኋላ የአውራጃ ስብሰባው “የይሖዋን ቀን በአእምሯችሁ አቅርባችሁ ተመልከቱ!” በሚል ንግግር ይደመደማል።
በስብሰባው ላይ ለመገኘት ከአሁኑ ጀምረው እቅድ ያውጡ። እርስዎ በሚኖሩበት አካባቢ ስብሰባው የት እንደሚካሄድ ለማወቅ በአቅራቢያዎ ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ መሄድ ወይም ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች ደብዳቤ መጻፍ ይችላሉ። በአንዳንድ አገሮች አራት ቀን የሚወስዱ ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ይካሄዳሉ። የመጋቢት 1 መጠበቂያ ግንብ የአውራጃ ስብሰባው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄድባቸውን ቦታዎች ዝርዝር ይዟል።