በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታላቅ ሳይንሳዊ ሚስጥር ተፈታ

ታላቅ ሳይንሳዊ ሚስጥር ተፈታ

ታላቅ ሳይንሳዊ ሚስጥር ተፈታ

በ1901 ጠላቂ ዋናተኞች በግሪክ የአንዲኪቲራ ደሴት አጠገብ ሰጥሞ የተገኘን መርከብ በሚመረምሩበት ወቅት ከፍተኛ ዋጋ ያለው አንድ ነገር አገኙ። ሰጥሞ የተገኘው መርከብ የእብነበረድና የነሐስ ቅርጻ ቅርጾችን እንዲሁም ከብር የተሠሩ ሳንቲሞችን ጭኖ ከጴርጋሞን የተነሳ የጥንቷ ሮም የንግድ መርከብ ነበር። ተመራማሪዎቹ ያገኟቸውን ሳንቲሞች በመመልከት ለመገመት እንደቻሉት መርከቡ የሰጠመው ወደ ሮም በመጓዝ ላይ ሳለ ከ85 እስከ 60 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባለው ጊዜ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም።

የተገኙት ቅርሶች ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በአቴንስ፣ ግሪክ በሚገኘው ብሔራዊ የአርኪኦሎጂ ሙዚየም ውስጥ ተቀምጠዋል። ይሁን እንጂ በ2005 ተመራማሪዎችን ወደ ሙዚየሙ እንዲመጡ ያደረጓቸው በመርከቧ ውስጥ የተገኙት ቅርጻ ቅርጾችና ሳንቲሞች አይደሉም። ትኩረታቸው ያረፈው የጫማ ካርቶን በሚያህል የእንጨት ሣጥን ውስጥ ተቀምጦ በተገኘው የነሐስ መሣሪያ ላይ ነበር። የአንዲኪቲራ መሣሪያ ተብሎ የተጠራው ይህ ዕቃ፣ በአሁኑ ጊዜ ሰዎች የጥንቱ ሥልጣኔ ስለደረሰባቸው ሳይንሳዊ ግኝቶች የነበራቸውን ግምት አጠራጣሪ አድርጎታል። ይህ ቅርስ “ከጥንቱ ዓለም ከተገኙት ሁሉ እጅግ የተራቀቀ መሣሪያ” ተብሎ ተጠርቷል።

ይህ መሣሪያ ምንድን ነው? ይህን ያህል ትልቅ ቦታ የተሰጠውስ ለምንድን ነው?

ሚስጥራዊ ዕቃ

ሣጥኑ ከባሕሩ በወጣበት ጊዜ በጣም ዝጎና የተለያዩ ነገሮች ዝቃጭ ተጋግሮበት ነበር። ባሕር ውስጥ ከሰጠመ 2,000 ዓመታት ሊሞላ የተቃረበው ይህ ሣጥን አረንጓዴ ድንጋይ መስሎ ነበር። መርከቧ ስትገኝ መጀመሪያ የብዙዎችን ትኩረት የሳቡት ቅርጻ ቅርጾቹ ስለነበሩ ይህን ሚስጥራዊ ዕቃ ዞር ብሎ ያየው አልነበረም።

አንድ ግሪካዊ አርኪኦሎጂስት በ1902 ዕቃውን ሲመረምረው መሣሪያው ተፈታቶ ነበር። ተስተካክለው የተቆረጡ ባለ ሦስት ማዕዘን ጥርሶች ያሏቸው መጠናቸው የተለያየ ሽክርክሪቶች ነበሩ። መሣሪያው ሲታይ ሰዓት ይመስል የነበረ ቢሆንም ሰዓት በስፋት ጥቅም ላይ የዋለው ከዛሬ 700 ዓመት ገደማ በፊት እንደሆነ ስለሚታመን እንዲህ ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ አይመስልም።

የአንዲኪቲራውን መሣሪያ በተመለከተ የተጻፈ አንድ ርዕሰ እንዲህ ይላል፦ “በጥቅሉ ሲታይ ታሪክ ጸሐፊዎች [ከ2,000 ዓመታት በፊት የኖሩት ግሪኮች] እንደዚህ በጥንቃቄ የተቆረጡ ጥርሶች ያሉት መሣሪያ ይኖራቸዋል ብለው አያስቡም፤ ከብረት ተቆርጠው ውስብስብ በሆነ መንገድ በቡድን የተደራጁት የማሽኑ ጥርሶች ከአንድ ዘንግ ጋር ተያይዘው ንዝረትን ከአንዱ የመሣሪያው ክፍል ወደ ሌላው ማስተላለፍ ይችላሉ።” መሣሪያው፣ በአንድ ወቅት በሰፊው ይሠራበት ከነበረው አስትሮለብ የተባለ የሕዋ አካላትን አቀማመጥ መሠረት በማድረግ አቅጣጫን ለማወቅ የሚያስችል መሣሪያ ጋር እንደሚመሳሰል ታስቦ ነበር።

ያም ሆኖ፣ ጥርሶቹ እጅግ የተራቀቁ በመሆናቸው መሣሪያው 2,000 ዓመት ዕድሜ ያለው ሊሆን እንደማይችል ብዙዎች ይናገራሉ። ስለዚህ መሣሪያው ሰጥሞ ከተገኘው ጥንታዊ መርከብ ውስጥ የወጣ አይደለም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰው ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ምሑር ዕቃው ስፊር ኦቭ አርክሚዲስ የሚባለው በአፈ ታሪክ የሚነገርለት መሣሪያ ሊሆን ይችላል የሚል ሐሳብ አቅርበው ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት የኖረው ሲሴሮ እንደገለጸው ይህ መሣሪያ፣ የፀሐይንና የጨረቃን እንዲሁም ያለ አጉሊ መነፅር እርዳታ በዓይናችን ልናያቸው የምንችላቸውን የአምስቱን ፕላኔቶች እንቅስቃሴ ማሳየት የሚችል ሞዴል (ፕላኒተሪየም) ነው። ይሁን እንጂ መሣሪያው አስትሮለብ ማለትም የሕዋ አካላትን አቀማመጥ መሠረት በማድረግ አቅጣጫን ለማወቅ የሚያስችል ዕቃ ላለመሆኑ ግልጽ ማስረጃ ማግኘት ስላልተቻለ በርካታ ምሑራን በመርከቧ ውስጥ የተገኘው ይህ ቅርስ አስትሮለብ ነው ወደሚል ድምዳሜ ደርሰዋል።

ጥልቀት ያለው ተጨማሪ ምርመራ ተካሄደ

በ1958 ዴሪክ ዴ ሶላ ፕራይስ የተባለው ሰው በዚህ መሣሪያ ላይ ጥናት አካሄደ፤ ይህ ሰው የፊዚክስ ምሑር የነበረ ቢሆንም በኋላ ግን የታሪክ ፕሮፌሰር ሆኗል። ፕራይስ፣ መሣሪያው ከዚያ ቀደም የተከናወኑ ወይም ወደፊት የሚፈጸሙ ሥነ ፈለካዊ ክስተቶችን ለማስላት የሚያገለግል እንደነበር አመነ፤ ለምሳሌ ጨረቃ ሙሉ ሆና የምትታይበትን ጊዜ ለማወቅ ያስችላል። በመሣሪያው ላይ ባለው የነሐስ ጎማ ላይ የተቀረጹት ጽሑፎች ልክ እንደ ቀን መቁጠሪያ ቀናትን፣ ወራትንና የዞዲያክ ምልክቶችን እንደሚያመለክቱ ተገነዘበ። ፕራይስ፣ በአንድ ወቅት መሣሪያው የሰማይ አካላት በተለያዩ ወቅቶች የሚኖራቸውን አቅጣጫ የሚያመለክቱ የሚሽከረከሩ ቀስቶች እንደነበሩት ገመተ።

ፕራይስ፣ ትልቁ ሽክርክሪት የፀሐይን እንቅስቃሴ ለማሳየት ያገለግል እንደነበረና አንዱ ዙር ምድር ፀሐይን ለመዞር የሚወስድባትን የአንድ ዓመት ጊዜ እንደሚያመለክት ተረዳ። ከመጀመሪያው ሽክርክሪት ጋር የተያያዘ አንድ ሌላ ሽክርክሪት የጨረቃን እንቅስቃሴ የሚያመለክት ከሆነ በሁለቱ ሽክርክሪቶች ላይ ያሉት ጥርሶች ሬሾ የጥንት ግሪካውያን ጨረቃ በምድር ዙሪያ ስለምታደርገው ዙረት የነበራቸውን ጽንሰ ሐሳብ የሚያንጸባርቅ መሆን አለበት።

በ1971 ፕራይስ መሣሪያውን በራጅ መረመረው። የተገኘው ውጤት የእሱን ንድፈ ሐሳብ የሚደግፍ ነበር። መሣሪያው ውስብስብ የሥነ ፈለክ ስሌት ለመሥራት የሚያገለግል ነበር። ፕራይስ የመሣሪያውን አሠራር የሚያሳይ ግምታዊ የሥዕል መግለጫ ያዘጋጀ ሲሆን ግኝቱን በ1974 አሳተመው። እንደሚከተለው በማለት ጽፏል፦ “ይህን የመሰለ መሣሪያ የትም አልተገኘም። . . . በግሪካውያን ዘመን ስለነበረው ሳይንስና ቴክኖሎጂ ከምናውቀው አንጻር እንዲህ ዓይነት መሣሪያ በዚያ ዘመን ሊኖር አይችልም ብለን እናስብ ነበር።” በዚያን ጊዜ የፕራይስ ሥራ የሚገባውን ያህል አድናቆት አልተቸረውም። ይሁን እንጂ ሌሎች ምርምሩን ቀጠሉበት።

ተጨማሪ መረጃ ተገኘ

በ2005 በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሱት ተመራማሪዎች መሣሪያውን ከሁሉም አቅጣጫ የሚያሳይ የራጅ ምስል ለማግኘት ካት ስካን በሚባለው ዘመናዊ መሣሪያ አማካኝነት መረመሩት። እነዚህ ጥናቶች ይህ መሣሪያ እንዴት ይሠራ እንደነበረ ተጨማሪ መረጃ ሰጥተዋል። በመሣሪያው የሚጠቀም ሰው እጀታውን ሲያዞር ቢያንስ ቢያንስ 30 የሚያህሉ እርስ በርስ የተጠላለፉ ባለ ጥርስ ሽክርክሪቶች በሣጥኑ የፊት ለፊት ክፍልና በስተጀርባ የሚገኙትን ሦስት የነሐስ ጎማዎች ያንቀሳቅሷቸዋል። ይህም በየአራት ዓመት ከሚደረጉት የኦሎምፒክና በመላው ግሪክ የሚካሄዱ ሌሎች ጨዋታዎች ጋር በተያያዘ ሊከሰቱ የሚችሉ ግርዶሾችን ጨምሮ ሥነ ፈለካዊ ዑደቶችን ለመተንበይ ያስችል ነበር። እነዚህ ጨዋታዎች ብዙውን ጊዜ ዘመንን ለማስላት እንደ መሠረት ሆነው ያገለግሉ ነበር።

እንዲህ ያለው መረጃ ይህን ያህል አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው? ለዚህ አያሌ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። ገበሬዎች መቼ መዝራት እንዳለባቸው እንዲያውቁ ለሚረዳቸው የቀን አቆጣጠር መሠረት ሆነው የሚያገለግሉት ፀሐይና ጨረቃ ስለነበሩ ለጥንት ሕዝቦች የሥነ ፈለክ ጥናት አስፈላጊ ነበር። መርከበኞችም አቅጣጫቸውን ለማወቅ የሚጠቀሙት በከዋክብት ነበር። የግሪካውያን ማኅበራዊ ሕይወት ለየት ካሉ የሥነ ፈለክ ክስተቶች ጋር የተሳሰረ ነበረ። እንዲህ ዓይነቱ ሥነ ፈለካዊ መረጃ አስፈላጊ የሆነበት ሌላም ምክንያት አለ።

“በጥንቶቹ ባቢሎናውያን ዘንድ ግርዶሾች መጥፎ ገድን የሚያመለክቱ ናቸው ተብሎ ስለሚታመን ግርዶሾችን አስቀድሞ መተንበይ በጣም አስፈላጊ ነበር” በማለት በአንዲኪቲራው መሣሪያ ምርምር ፕሮጀክት ተካፋይ የሆኑት ማርቲን አለን ጽፈዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “መሣሪያው በመግዛት ላይ ለነበሩት ባለሥልጣኖች ተገዢዎቻቸውን ለመቆጣጠር እንደሚያስችላቸው ፖለቲካዊ መሣሪያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። እንዲያውም ስለዚህ መሣሪያ የምናውቀው ነገር እጅግ አናሳ ሊሆን የቻለበት አንዱ ምክንያት ወታደራዊ ወይም ፖለቲካዊ ሚስጥር ስለነበረ እንደሆነ የሚገልጹም አሉ።”

መሣሪያው የሚነግረን ምንም ይሁን ምን፣ ረጅም ዘመናት ያስቆጠረውን የባቢሎናውያን እውቀት መሠረት አድርጎ ያደገው የጥንቷ ግሪክ የሥነ ፈለክና ሒሳብ ጥናት ከምናስበው በላይ የተራቀቀ እንደነበር የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ኔቸር የተሰኘው መጽሔት ጉዳዩን እንደሚከተለው በማለት ይገልጸዋል፦ “ጥንታዊው የአንዲኪቲራ መሣሪያ፣ በዘመናት ሁሉ ሲወርድ ሲዋረድ ስለመጣው ቴክኖሎጂ የነበረንን ግምት አጠራጣሪ የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ ስለ ታሪክ ተጨማሪ መረጃ ይሰጠናል።”

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የሠራው ማን ነው?

የአንዲኪቲራው መሣሪያ በዓይነቱ ብቸኛው ሊሆን አይችልም። ማርቲን አለን እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “መሣሪያው በስህተት የተሠራ ክፍል እንዳለው የሚጠቁም ምንም ማስረጃ የለም። የመሣሪያው ክፍሎች በሙሉ በዓላማ የተሠሩ ናቸው። መሣሪያውን የሠራው ሰው በሚሠራበት ወቅት ንድፉን እንዳሻሻለው የሚያመለክቱ ትርፍ ቀዳዳዎች ወይም ጥቅም ላይ የማይውሉ ክፍሎች በመሣሪያው ላይ አልተገኙም። ይህም ከዚያ ቀደም በርካታ የዚህ ዓይነት መሣሪያዎችን ሠርቶ ነበር ወደሚል መደምደሚያ ያደርሳል።” ታዲያ ይህን መሣሪያ የሠራው ማን ነው? ሌሎቹ ምርቶቹስ የት ደረሱ?

በቅርቡ በመሣሪያው ላይ በተደረገው ምርምር ግርዶሾችን ለመተንበይ በሚረዳው የነሐስ ጎማ ላይ የወሮች ስም ተገኝቷል። የወሮቹ ስሞች ከቆሮንቶስ የመነጩ እንደሆኑ ተረጋግጧል። ይህም ተመራማሪዎቹ፣ መሣሪያውን ሠርተው ይጠቀሙበት የነበሩት አንድ ዓይነት ባሕል ያላቸው ሰዎች ናቸው ወደሚል ድምዳሜ እንዲደርሱ አስችሏቸዋል። ኔቸር የተሰኘው ሳይንሳዊ መጽሔት እንዲህ ይላል፦ “ይህን መሣሪያ ይጠቀሙበት የነበሩት በግሪክ ሰሜናዊ ምዕራብ ወይም በስራኩስ፣ ሲሲሊ ባሉት የቆሮንቶስ ቅኝ ግዛቶች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ሳይሆኑ አይቀሩም፤ በስራኩስ የሚኖሩ ሰዎች ይጠቀሙበት ከነበረ ደግሞ በአርክሚድስ ዘመን ይሠራበት ነበር ማለት ነው።”

ሌሎች ተመሳሳይ መሣሪያዎች ያልተገኙት ለምንድን ነው? “ነሐስ ጠቃሚ የብረት ዓይነት ከመሆኑም በላይ ሰዎች አንድን የነሐስ ዕቃ ቅርጹን እየለዋወጡ የተለያዩ ነገሮችን ለመሥራት ሊያውሉት ይችላሉ” በማለት ማርቲን አለን ጽፈዋል። “በመሆኑም በጥንት ዘመን የተሠሩ የነሐስ ዕቃዎች እምብዛም አይገኙም። እንዲያውም ታሪካዊ ጠቀሜታ ካላቸው የነሐስ ዕቃዎች መካከል ብዙዎቹ የተገኙት እንደገና ጨፍልቀው ሊሠሯቸው የሚፈልጉ ሰዎች ሊያገኟቸው በማይችሉበት በባሕር ውስጥ ነው።” አንድ ተመራማሪ “ይህን መሣሪያ ብቻ ልናገኘው የቻልነው ብረትን ጨፍልቀው የሚሠሩ ሰዎች ሊደርሱ በማይችሉበት ሥፍራ ስለነበረ ነው” በማለት ተናግረዋል።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የአንዲኪቲራው መሣሪያ የሚሠራበት መንገድ

1. የፊት ለፊቱ የነሐስ ጎማ ጨረቃ በተለያዩ ወቅቶች የሚኖራትን ቅርጽ እንዲሁም የፀሐይንና የጨረቃን አቅጣጫ ያመለክት ነበር፤ ከዚህም ሌላ በፀሐይ የዘመን አቆጣጠር መሠረት ቀንና ወርን እንዲሁም በዞዲያክ ኅብረ ከዋክብት መሠረት የፀሐይን (እና የሚታዩትን ፕላኔቶች) እንቅስቃሴ ያሳይ ነበር

2. መሃለኛው የነሐስ ጎማ ጨረቃ ምድርን ለመዞር የሚፈጅባትን ቀናት መሠረት ያደረጉ ወሮችን፣ ምድር ፀሐይን ለመዞር የሚፈጅባትን ቀናት መሠረት ያደረጉ ዓመታትንና በመላው ግሪክ የሚደረጉ ጨዋታዎችን ለማወቅ ያስችል ነበር

3. የኋለኛው የነሐስ ጎማ የፀሐይንና የጨረቃን ግርዶሾች ይተነብይ ነበር

[ሥዕሎች]

ከፊት ለፊት ሲታይ

ከኋላ በኩል ሲታይ

[ምንጭ]

ሁለቱም ፎቶዎች፦ ©2008 Tony Freeth/Antikythera Mechanism Research Project (www.antikythera-mechanism.gr)

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኋለኛው ክፍል ሊኖረው የሚችለው መልክ

[ምንጭ]

©2008 Tony Freeth/Antikythera Mechanism Research Project (www.antikythera-mechanism.gr)

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ሁሉም ፎቶዎች፦ ©2005 National Archaeological Museum/Antikythera Mechanism Research Project (www.antikythera-mechanism.gr)