በፉጨት ማውራት—“ለመነጋገር” የሚያስችል ግሩም ዘዴ
በፉጨት ማውራት—“ለመነጋገር” የሚያስችል ግሩም ዘዴ
ሜክሲኮ የሚገኘው የንቁ! ጸሐፊ እንዳዘጋጀው
በሜክሲኮ በምትገኘው ዋሃካ የተባለች ተራራማ ከተማ ውስጥ የሚኖሩት የማሳቴክ ሕዝቦች የሞባይልም ሆነ ሌላ ዓይነት የስልክ አገልግሎት የላቸውም። ሆኖም ሁለት ኪሎ ሜትር ወይም ከዚያ በላይ ተራርቀውም እንኳ እርስ በርስ መግባባት የሚችሉበት ዘዴ አላቸው፤ ለምሳሌ ያህል፣ በተራራ ላይ በሚገኙት የቡና ማሳዎች ላይ በሚሠሩበት ወቅት በዚህ የመግባቢያ ዘዴ ይጠቀማሉ። ሚስጥሩ ምንድን ነው? የማሳቴክ ሕዝቦች ከረጅም ጊዜ በፊት ከቋንቋቸው ጋር በሚጣጣም ሁኔታ በፉጨት መግባባት የሚችሉበትን ዘዴ ፈጥረዋል። የማሳቴክ ተወላጅ የሆነው ፔድሮ የተባለ ወጣት እንደሚከተለው በማለት ይናገራል፦ “ማሳቴኮ በድምፅ ቃና የሚገለጽ ቋንቋ ነው። ስለዚህ በምናፏጭበት ጊዜ ስንናገር የምንጠቀምበትን ቋንቋ ቃናና ቅላጼ እንኮርጃለን። የምናፏጨውም ያለጣቶቻችን እገዛ በከንፈራችን ብቻ ነው።” *
ፊደንሲዮ የተባለው የፔድሮ ጓደኛ፣ የፉጨት ቋንቋ ያለውን ጠቀሜታ እንደሚከተለው በማለት ገልጿል፦ “በዚህ ቋንቋ የምንጠቀመው በመካከላችን ያለው ርቀት ረጅም ሲሆንና በአብዛኛው አጠር ያሉ ሐሳቦችን ለመግለጽ ስንፈልግ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ አባት ልጁን ቶርቲላ የተባለ ቂጣ እንዲገዛ ላከው እንበል፤ ሆኖም በዚያው ቲማቲም ይዞ እንዲመጣ ሳይነግረው ቀረ። አባትየው ልጁ በጣም ከመራቁ የተነሳ መልእክቱን በቃል መንገር ካልቻለ የሚፈልገውን ነገር በፉጨት ሊነግረው ይችላል።”
አንዳንድ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮችም እርስ በርስ ሐሳብ ለመለዋወጥ በፉጨት ይጠቀማሉ። ፔድሮ እንዲህ ይላል፦ “ገለልተኛ ወደሆኑ አካባቢዎች በምሄድበት ጊዜ አንድ መንፈሳዊ ወንድሜ አብሮኝ እንዲያገለግል ብፈልግ ቤቱ ድረስ መሄድ አያስፈልገኝም። በቀላሉ በፉጨት እጠራዋለሁ።”
አክሎም ፔድሮ እንዲህ ብሏል፦ “‘እየተናገረ’ ያለው ማን መሆኑን ማወቅ እንድንችል እያንዳንዳችን የየራሳችን የሆነ የፉጨት ዘዴ አለን። አብዛኛውን ጊዜ በፉጨት የሚነጋገሩት የማሳቴክ ወንዶች ብቻ ናቸው። አንዲት ሴት የፉጨት ቋንቋ ልታውቅ ሌላው ቀርቶ ቤት ውስጥ ልትጠቀምበት ትችል ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ከማንኛውም ወንድ ጋር ስታወራ በዚህ የመግባቢያ ዘዴ አትጠቀምም። እንዲህ ብታደርግ ነውር እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል።”
በፉጨት መግባባት የሚችሉት ማሳቴኮች ብቻ አይደሉም፤ በቻይና፣ በካናሪ ደሴቶችና በፓፑዋ ኒው ጊኒ የሚኖሩ ሰዎችም በዚህ ዘዴ ይጠቀማሉ። በአብዛኛው እነዚህ ሰዎች የሚኖሩት በተራሮችና ጥቅጥቅ ባሉ ደኖች ውስጥ ነው። እንዲያውም ከ70 በላይ የሚሆኑ የፉጨት ቋንቋዎች እንደሚኖሩ የሚገመት ሲሆን ቢያንስ በ12ቱ ላይ ጥናት ተካሂዶባቸዋል።
በእርግጥም የሰው ልጆች ያላቸው የፈጠራ ችሎታ በጣም ያስደንቃል። ሰዎች ይህን ችሎታ ሐሳባቸውን ለመግለጽ ካላቸው ጽኑ ፍላጎት ጋር ሲያዋህዱት የፈለጉትን ነገር ከመፈጸም ሊያግዳቸው የሚችል ምንም ዓይነት እንቅፋት ያለ አይመስልም!
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.3 አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “ማሳቴኮች የፉጨቱን ፍጥነትና ቅላጼ በመቀያየር እንዲሁም መጠኑን ከፍ በማድረግ በርከት ያሉ ሐሳቦችን መለዋወጥ ችለዋል።”