ስኬታማ ለመሆን የሚረዱ ስድስት መንገዶች
ስኬታማ ለመሆን የሚረዱ ስድስት መንገዶች
አንድ ሰው እውነተኛ ስኬት አገኘ የሚባለው ከሁሉ በተሻለው የሕይወት መንገድ መጓዝ ሲችል ነው። ይህ መንገድ አምላክ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ተግባራዊ ማድረግንና ለእኛ ካለው ዓላማ ጋር ተስማምቶ መኖርን ይጠይቃል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነቱን ሕይወት ስለሚመራ ሰው ሲናገር “በወራጅ ውሃ ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፣ ቅጠሏም እንደማይጠወልግ ዛፍ ነው፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል [“ይሳካለታል፣” የ1980 ትርጉም]” ይላል።—መዝሙር 1:3
ምንም እንኳ ሁላችንም ፍጽምና የሌለንና ስህተቶች የምንሠራ ብንሆንም በጥቅሉ ሲታይ ሕይወታችን እጅግ ስኬታማ ሊሆን ይችላል! እንዲህ ያለውን ስኬት ለማግኘት ትጓጓለህ? ከሆነ ቀጥሎ የቀረቡት ስድስት የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች እዚህ ግብ ላይ እንድትደርስ ሊረዱህ ይችላሉ፤ እዚህ ግብ ላይ መድረስህ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ትምህርቶች በእርግጥ መለኮታዊ ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ለመሆናቸው ግልጽ ማስረጃ ይሆናል።—ያዕቆብ 3:17
1. ለገንዘብ ተገቢ አመለካከት ይኑርህ
‘የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ሥር ነው፤ አንዳንዶች ባለጠጋ ለመሆን ካላቸው ጉጉት የተነሣ ራሳቸውን በብዙ ሥቃይ ወግተዋል።’ (1 ጢሞቴዎስ 6:10) ችግሩ ያለው በገንዘቡ ላይ እንዳልሆነ ልብ በል። ሁላችንም ራሳችንንም ሆነ ቤተሰቦቻችንን ለመንከባከብ ገንዘብ ያስፈልገናል። ችግሩ ያለው ለገንዘብ ባለን ፍቅር ላይ ነው። በእርግጥም እንዲህ ያለው ፍቅር ገንዘብን የባለቤቱ ጌታ ወይም አምላክ ያደርገዋል።
በመጀመሪያው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ገንዘብ የስኬት ቁልፍ ነው ብለው ሀብትን በጦፈ ስሜት የሚያሳድዱ ሰዎች ጉምን ለመጨበጥ ከመሞከር የማይተናነስ ነገር እያደረጉ ነው። እነዚህ ሰዎች ተስፋ ከመቁረጣቸውም በተጨማሪ ራሳቸውን ለብዙ ችግር ይዳርጋሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ሰዎች ሀብትን በጦፈ ስሜት ሲያሳድዱ ብዙውን ጊዜ ከቤተሰባቸውና ከወዳጆቻቸው ጋር ያላቸውን ዝምድና መሥዋዕት ያደርጋሉ። ሌሎች ደግሞ ከሥራ ጫና ብቻ ሳይሆን ከጭንቀት ወይም ከስጋት የተነሳ እንቅልፍ አጥተው ያድራሉ። መክብብ 5:12 “ጥቂትም ይሁን ብዙ ቢበላ፣ የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው፤ የሀብታም ሰው ብልጽግና ግን እንቅልፍ ይነሣዋል” በማለት ይናገራል።
ገንዘብ ጨካኝ ጌታ ብቻ ሳይሆን አታላይም ጭምር ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ “ሀብት [ስላለው] የማታለል ኃይል” ተናግሯል። (ማርቆስ 4:19 NW) በሌላ አነጋገር፣ ሀብት ደስታ የሚያስገኝ ይመስላል፣ ይሁን እንጂ ደስታ አያስገኝም። ከዚህ ይልቅ የበለጠ የማግኘት ጉጉት ይፈጥራል። መክብብ 5:10 “ገንዘብን የሚወድ፣ ገንዘብ አይበቃውም” ይላል።
በአጭሩ፣ የገንዘብ ፍቅር ለውድቀት የሚዳርግ ከመሆኑም በላይ ውሎ አድሮ ወደ ሐዘንና ብስጭት አልፎ ተርፎም ወደ ወንጀል ይመራል። (ምሳሌ 28:20) ከደስታና ከስኬት ጋር ይበልጥ ቁርኝት ያላቸው ነገሮች ለጋስነት፣ ይቅር ባይነት፣ የሥነ ምግባር ንጽሕና፣ ፍቅርና መንፈሳዊነት ናቸው።
2. የለጋስነት መንፈስ አዳብር
“ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።” (የሐዋርያት ሥራ 20:35 NW) አንድ ሰው አልፎ አልፎ መስጠቱ የደስታ ስሜት የሚፈጥርለት ከሆነ ሁልጊዜ የለጋስነት መንፈስ ማዳበሩ ደስተኛ ሰው እንደሚያደርገው እሙን ነው። እርግጥ ነው፣ ለጋስነት በብዙ መንገዶች ሊገለጽ ይችላል። ከሁሉ የተሻለውና የብዙዎችን አድናቆት የሚያስገኘው የልግስና መንገድ ራስን መስጠት ነው።
ስቲፈን ፖስት የተባሉ ተመራማሪ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ለሌሎች ስለ ማሰብ፣ ስለ ደስታና ስለ ጤንነት የተደረጉት አንዳንድ ጥናቶችን ከመረመሩ በኋላ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ለሌሎች አሳቢነት ማሳየትና ሰዎችን መርዳት ዕድሜ እንደሚያረዝም፣ የደህንነት ስሜትን እንደሚያሻሽል እንዲሁም የመንፈስ ጭንቀት መቀነስን ጨምሮ የተሻለ አካላዊና አእምሯዊ ጤንነት እንደሚያስገኝ ደርሰውበታል።
ከዚህም በላይ አቅማቸው የፈቀደውን ያህል በልግስና የሚሰጡ ሰዎች በመስጠታቸው ምክንያት ለኪሳራ አይዳረጉም። ምሳሌ 11:25 “ለጋስ ይበለጽጋል፤ ሌሎችን የሚያረካም ራሱ ይረካል” ይላል። ከእነዚህ ቃላት ጋር በሚስማማ መልኩ ወሮታ እንዲመለስላቸው ሳይጠብቁ ከልብ በመነጨ ስሜት የሚሰጡ ሰዎች በሌሎች በተለይም በአምላክ ዘንድ አድናቆትና ፍቅር ያተርፋሉ።—ዕብራውያን 13:16
3. በነፃ ይቅር በል
“አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው . . . እርስ በርስ በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ። ይሖዋ በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ።” (ቆላስይስ 3:13 NW) በዛሬው ጊዜ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ይቅር ለማለት ፈቃደኞች አይደሉም፤ እንዲያውም ምሕረት ከማድረግ ይልቅ ለመበቀል ይነሳሳሉ። ይህ ምን ውጤት ያስከትላል? ስድብ ስድብን፣ ዓመፅ ደግሞ ዓመፅን ይወልዳል።
ጉዳቱ በዚህ ብቻ ላያበቃ ይችላል። “ከ18 እስከ 30 ዓመት ዕድሜ ባላቸው ከ4,600 የሚበልጡ ሰዎች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት፣ [አንድ ሰው] በጥላቻ በተሞላ መጠን እንዲሁም ይበልጥ ብስጩና ጨካኝ በሆነ መጠን” ሳንባው እንደሚጎዳ ማሳየቱን በሞንትሪያል ካናዳ የሚታተመው ዘ ጋዜቲ ዘግቧል። እንዲያውም አንዳንዶቹ ጎጂ ውጤቶች ሲጋራ የሚያጨስ ሰው ከሚደርስበት ጉዳት የከፉ ናቸው! በእርግጥም ይቅር ባይነት ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን መርዳት ብቻ ሳይሆን ጥሩ መድኃኒት ጭምር ነው!
ታዲያ ይበልጥ ይቅር ባይ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? ራስህን በሐቀኝነት በመመርመር መጀመር ትችላለህ። አንተስ አንዳንድ ጊዜ ሌሎችን አበሳጭተህ አታውቅም? ይቅርታ ሲያደርጉልህስ ደስ አይልህም? እንግዲያውስ ለሌሎች ይቅርታ በማድረግ ረገድ ለምን ለጋስ አትሆንም? (ማቴዎስ 18:21-35) እንዲህ ለማድረግ ደግሞ ራስን መግዛት በጣም አስፈላጊ ነው። አንዳንዶች የተናደደ ሰው ምንም ዓይነት እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ‘ከአንድ እስከ አሥር ቢቆጥር’ ወይም ሌላ መንገድ ተጠቅሞ የተወሰነ ጊዜ ቢያሳልፍ ንዴቱ እንደሚበርድለት ይናገራሉ። ራስን መግዛት የጥንካሬ ምልክት እንደሆነ አድርገህ ተመልከተው። ምሳሌ 16:32 “ትዕግሥተኛ ሰው ከኃያል ሰው ይሻላል” ይላል። (የ1954 ትርጉም) አንድ ሰው ‘ከኃያል ሰው ከተሻለ’ ስኬታማ ሆኗል ማለት ነው፤ አይደለም እንዴ?
4. የአምላክን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ተከተል
“የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፤ ዐይንን ያበራል።” (መዝሙር 19:8) በአጭር አነጋገር የአምላክ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ለአካላዊ፣ አእምሯዊና ስሜታዊ ጤንነት በጣም ጠቃሚ ናቸው። አደንዛዥ ዕፅ ከመውሰድ፣ ከስካር፣ የፆታ ብልግና ከመፈጸም፣ የብልግና ምሥሎችን ከመመልከትና እነዚህን ከመሳሰሉ ጎጂ ድርጊቶች ይጠብቁናል። (2 ቆሮንቶስ 7:1፤ ቈላስይስ 3:5) እነዚህን ድርጊቶች መፈጸም ወደ ወንጀል ይመራል፣ ለድህነት ይዳርጋል፣ ባልና ሚስት እርስ በርስ እንዳይተማመኑ አልፎ ተርፎም ቤተሰባቸው እንዲፈርስ ያደርጋል፣ ለአእምሮና ለስሜት ቀውስ ይዳርጋል፣ ለበሽታ ያጋልጣል እንዲሁም ሕይወትን በአጭሩ ይቀጫል።
በሌላ በኩል ደግሞ የአምላክን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች በጥብቅ የሚከተሉ ሰዎች ከሌሎች ጋር ጤናማ የሆነ አስተማማኝ ግንኙነት ይኖራቸዋል፤ በተጨማሪም ለራሳቸው ጥሩ ግምት የሚኖራቸው ሲሆን ውስጣዊ ሰላምም ያገኛሉ። አምላክ በኢሳይያስ 48:17, 18 ላይ “የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ፣ መሄድ በሚገባህ መንገድ የምመራህ ነኝ” በማለት ተናግሯል። አክሎም “ትእዛዜን ሰምተህ ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር” ብሏል። አዎን፣ ፈጣሪያችን ለእኛ የሚመኝልን ከሁሉ የተሻለውን ነው። እውነተኛ ስኬት በሚያስገኘው ‘መንገድ ላይ እንድንሄድ’ ይፈልጋል።
5. ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር አሳይ
“ፍቅር . . . ያንጻል።” (1 ቆሮንቶስ 8:1) አንድ ሰው ፍቅር ቢያጣ ሕይወቱ ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት ትችላለህ? ሕይወቱ ባዶና ደስታ የራቀው ይሆንበታል! ክርስቲያን የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ በአምላክ መንፈስ ተመርቶ ‘ለሌሎች ፍቅር ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ፍቅር ከሌለኝ ምንም የማተርፈው ነገር የለም’ በማለት ጽፏል።—1 ቆሮንቶስ 13:2, 3 NW
የተቃራኒ ፆታ ፍቅር የራሱ ቦታ ያለው ቢሆንም እዚህ ላይ የተጠቀሰው ፍቅር ግን ለየት ያለ ነው። ይህ ዓይነቱ ፍቅር አምላክ ባወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚመራ ሲሆን ይበልጥ ጥልቀት ያለውና ዘላቂ ነው። * (ማቴዎስ 22:37-39) ከዚህም በላይ እንዲያው በስሜት ብቻ ሳይሆን በተግባር ጭምር የሚገለጽ ነው። ጳውሎስ ቀጥሎ ይህ ፍቅር ታጋሽና ቸር እንደሆነ ተናግሯል። በተጨማሪም አይመቀኝም፤ አይመካም ወይም አይታበይም። ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ለሌሎች ጥቅም የሚያስብ ከመሆኑም በላይ በቀላሉ አይበሳጭም፤ ከዚህ ይልቅ ይቅር ይላል። እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር ያንጻል። ከዚህም በተጨማሪ ከሌሎች ጋር፣ በተለይም ከቤተሰብ አባሎቻችን ጋር ተስማምተን በመኖር ረገድ ስኬታማ እንድንሆን ይረዳናል።—1 ቆሮንቶስ 13:4-8
ፍቅር ወላጆች ልጆቻቸውን በጣም እንዲወዷቸው ብሎም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ግልጽ የሥነ ምግባር ገደብ እንዲያወጡላቸው ያነሳሳቸዋል። እንዲህ ባለ ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ ልጆች ደህንነት የሚሰማቸው ሲሆን የተረጋጋ የቤተሰብ ሕይወት ይኖራቸዋል፤ ከዚህም በላይ በእርግጥ እንደሚወደዱና እንደሚደነቁ ይሰማቸዋል።—ኤፌሶን 5:33 እስከ 6:4፤ ቈላስይስ 3:20
በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር ጃክ የሚባል ወጣት ያደገው በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በሚመራ ቤተሰብ ውስጥ ነበር። ራሱን ችሎ ከቤት ከወጣ በኋላ ለወላጆቹ የጻፈው ደብዳቤ በከፊል እንዲህ ይላል፦ “ምንጊዜም ጥረቴ ‘መልካም እንዲሆንልህ . . . አባትህንና እናትህን አክብር’ የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ማክበር ነበር። (ዘዳግም 5:16) ደግሞም መልካም ሆኖልኛል። እንዲህ ያለውን ውጤት ማግኘት የቻልኩት ጥብቅ ሆናችሁ በፍቅር ስላሳደጋችሁኝ እንደሆነ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ተገንዝቤያለሁ። ለልፋታችሁና እኔን ስታሳድጉ ላደረጋችሁልኝ ድጋፍ ሁሉ አመሰግናችኋለሁ።” ወላጅ ከሆንክ ይህን የመሰለ ደብዳቤ ቢደርስህ ምን ይሰማህ ነበር? በጣም አትደሰትም?
በተጨማሪም በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራው ፍቅር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው መንፈሳዊ ‘እውነት ጋር ደስ ይሰኛል።’ (1 ቆሮንቶስ 13:6፤ ዮሐንስ 17:) በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፦ በትዳራቸው ውስጥ ችግር ያጋጠማቸው ባልና ሚስት 17በማርቆስ 10:9 ላይ የሚገኙትን “እግዚአብሔር ያጣመረውን ማንም አይለየው” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት ለማንበብ ወሰኑ እንበል። በዚህ ጊዜ ልባቸውን መመርመር ይኖርባቸዋል። በእርግጥ ‘በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ደስ ይሰኛሉ?’ ልክ እንደ አምላክ ትዳርን ቅዱስ አድርገው ይመለከቱታል? ችግራቸውን በፍቅር ለመፍታት የሚያስችላቸውን ጥረት ለማድረግ ፈቃደኞች ናቸው? ከሆነ ትዳራቸው እንዲሳካ ማድረግና በሚያገኙት ውጤት መደሰት ይችላሉ።
6. ለመንፈሳዊ ፍላጎትህ ትኩረት ስጥ
“በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው።” (ማቴዎስ 5:3 NW) ሰዎች፣ ከእንስሳት በተለየ መልኩ መንፈሳዊ ፍላጎት አላቸው። በመሆኑም እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን እንጠይቃለን፦ የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? ፈጣሪ አለ? ስንሞት ምን እንሆናለን? የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን?
በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቅን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ እንደሚሰጥ ተገንዝበዋል። ለምሳሌ ያህል፣ የመጨረሻው ጥያቄ አምላክ ለሰው ዘር ካለው ዓላማ ጋር የተያያዘ ነው። ይህ ዓላማ ምንድን ነው? ዓላማው ምድር አምላክንና እሱ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች የሚወዱ ሰዎች ለዘላለም የሚኖሩባት ገነት እንድትሆን ማድረግ ነው። መዝሙር 37:29 “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” ይላል።
በግልጽ ለማየት እንደምንችለው ፈጣሪያችን ለ70 ወይም ለ80 ዓመት ብቻ ከሚገኝ ጊዜያዊ ስኬት የበለጠ ነገር እንድናገኝ ይፈልጋል። ለዘላለም ስኬታማ እንድንሆን ይፈልጋል! ስለዚህ ስለ ፈጣሪህ ለመማር ጊዜው አሁን ነው። ኢየሱስ “አንተ ብቻ እውነተኛ አምላክ የሆንኸውንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሏል። (ዮሐንስ 17:3) ይህን እውቀት በቀሰምክና በሕይወትህ ውስጥ ተግባራዊ ባደረግክ መጠን “የእግዚአብሔር በረከት ብልጽግናን ታመጣለች፤ መከራንም አያክልባትም” የሚለው ተስፋ እውነት መሆኑን ታረጋግጣለህ።—ምሳሌ 10:22
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.22 በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ወይም “በአዲስ ኪዳን” ውስጥ የሚገኘው “ፍቅር” የሚለው ቃል በአብዛኛው የተተረጎመው አጋፔ ከተባለው የግሪክኛ ቃል ነው። አጋፔ፣ የሞራል ግዴታ እንዳለብን ተሰምቶን ለሌሎች ጥቅም ከልብ በማሰብ የምናሳየው የፍቅር ዓይነት ነው። ይሁን እንጂ አጋፔ ከውስጥ ፈንቅሎ የሚወጣ የመውደድ ስሜት እንጂ ስሜት አልባ አይደለም።—1 ጴጥሮስ 1:22
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ለስኬት የሚረዱ ተጨማሪ መመሪያዎች
▪ ለአምላክ ጤናማ ፍርሃት ይኑርህ። “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው።”—ምሳሌ 9:10
▪ ጓደኞችህን በጥበብ ምረጥ። “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጕዳት ያገኘዋል።”—ምሳሌ 13:20
▪ ከመጠን አትለፍ። “ሰካራሞችና ሆዳሞች ድኾች ይሆናሉ።”—ምሳሌ 23:21
▪ አትበቀል። “ለማንም ክፉን በክፉ አትመልሱ።”—ሮሜ 12:17
▪ ጠንክረህ ሥራ። “ሊሠራ የማይወድ አይብላ።”—2 ተሰሎንቄ 3:10
▪ ወርቃማውን ሕግ ተግባራዊ አድርግ። “ሌሎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር እናንተም አድርጉላቸው።”—ማቴዎስ 7:12
▪ አንደበትህን ተቆጣጠር። “ሕይወትን የሚወድ፣ መልካም ቀኖችን ሊያይ የሚፈልግ፣ ምላሱን ከክፉ . . . ይከልክል።”—1 ጴጥሮስ 3:10
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ፍቅር ፍቱን መድኃኒት ነው
የሕክምና ዶክተርና ደራሲ የሆኑት ዲን ኦርኒሽ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ፍቅር ስናጣ እንታመማለን፣ ፍቅር ስናገኝ ጤናማ እንሆናለን፤ ፍቅር ስናጣ እናዝናለን፣ ፍቅር ስናገኝ እንደሰታለን፤ ፍቅር ስናጣ እንሠቃያለን፣ ፍቅር ስናገኝ እንፈወሳለን። አንድ ሐኪም ለሁሉም በሽታ ፍቱን የሆነ መድኃኒት ቢያገኝ ለበሽተኞቹ እንደሚያዝ የታወቀ ነው። ይህን መድኃኒት ሳያዝ ቢቀር የሞያ ግዴታውን እንዳልተወጣ ተደርጎ ይታያል።”
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
ከተስፋ መቁረጥ ወደ ስኬት
በአንዲት የባልካን አገር የሚኖር ሚላንኮ የተባለ ሰው በአገሩ ውስጥ ጦርነት ሲጀመር ሠራዊቱን ተቀላቀለ። በድፍረት ባከናወነው ጀብዱ የተነሳ ሰዎች የጭካኔ ድርጊት በሚበዛባቸው ፊልሞች ላይ ዋና ገጸ ባሕርይ ሆኖ በሚሠራው ሰው ስም ራምቦ ብለው ይጠሩት ጀመር። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ሚላንኮ በውትድርናው ዓለም ውስጥ በተመለከተው ሙስናና ግብዝነት የተነሳ ግራ ተጋባ። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ይህ ሁኔታ እንደ ስካር፣ ሲጋራ ማጨስ፣ አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ፣ ቁማርና ሴሰኝነት ወደመሳሰሉት ብዙ ጎጂ ልማዶች መራኝ። የሥነ ምግባር አቋሜ በጣም ከማዝቀጡ የተነሳ መውጫ መንገዱ ጠፍቶኝ ነበር።”
ሚላንኮ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ጀመረ። በኋላም አንድ ዘመዱን ሊጠይቅ ሄዶ ሳለ በይሖዋ ምሥክሮች የሚዘጋጀውን አንድ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት እትም አገኘ። በመጽሔቱ ላይ ያነበበውን ነገር ስለወደደው ብዙም ሳይቆይ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ደስታና እውነተኛ ስኬት በሚያስገኘው ጎዳና ላይ እንዲጓዝ ረዳው። ሚላንኮ እንዲህ ብሏል፦ “የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የተለየ ብርታት ስለሰጠኝ ጎጂ ልማዶቼን ሁሉ እርግፍ አድርጌ በመተው ሙሉ በሙሉ ተለወጥኩ። ከዚያም ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ። ድሮ የሚያውቁኝ ሰዎች አሁን ራምቦ ብለው አይጠሩኝም፤ ከዚህ ይልቅ ገራም ሰው ስለሆንኩ ዛክ በሚለው የልጅነት ቅጽል ስሜ ይጠሩኛል።”