የወተት ማለፊያ ቧንቧ
ንድፍ አውጪ አለው?
የወተት ማለፊያ ቧንቧ
▪ በግ፣ ፍየል ወይም ላም ስትወልድ አይተህ የምታውቅ ከሆነ ግልገሉ ወይም ጥጃው ወዲያውኑ በእግሮቹ ቆሞ የእናቱን ጡት ፍለጋ መሄዱ አስገርሞህ ይሆናል። ሁሉም አጥቢ እንስሳት ልጆቻቸውን የሚመግቡት ወተት ነው። ይሁን እንጂ የበግና የፍየል ግልገልን እንዲሁም ጥጃን የመሳሰሉ የሚያመሰኩ እንስሳት አንድ በጣም የሚያስደንቅ ነገር አላቸው።
እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ የላሞች ጨጓራ አራት ክፍሎች ያሉት ሲሆን እነዚህ ክፍሎች ሣርና ድርቆሽ ለመፍጨት የተለያየ ተግባር ያከናውናሉ። ይሁንና ጥጃዎች የሚመገቡት ወተት ብቻ ስለሆነ ለመፈጨት በእነዚህ ሁሉ ክፍሎች ማለፍ አያስፈልገውም። ስለሆነም አዲስ የተወለደው እንስሳ ጡት በሚጠባበት ጊዜ ወተቱ በቀጥታ ወደ መጨረሻው የጨጓራ ክፍል እንዲያልፍ ልዩ ቧንቧ ይከፈታል።
የመጀመሪያው የጨጓራ ክፍል ለመድቀቅ አስቸጋሪ የሆኑ ምግቦች በባክቴሪያ ተብላልተው የሚፈጩበት ስለሆነ ወተቱ ወደዚህ ክፍል ቢገባ ጥጃው በሆድ ሕመም ሊሠቃይ ይችላል። ምግብ በሚብላላበት ክፍል ወተት ቢገባ በእንስሳው ሆድ ውስጥ ጋዝ ይፈጠራል። አዲስ የተወለደ ጥጃ ደግሞ ይህንን ጋዝ ማስወጣት አይችልም። ስለሆነም የሚያመሰኩ እንስሳት ጡት በሚጠቡበት ጊዜም ይሁን ከባልዲ ላይ ወተት በሚጠጡበት ጊዜ ወደ መጀመሪያው የጨጓራ ክፍል የሚያስገባው ቧንቧ ወዲያውኑ ይዘጋል።
የሚያስደንቀው ነገር ጥጃው ውኃ በሚጠጣበት ጊዜ የሚከሰተው ሁኔታ ከዚህ የተለየ መሆኑ ነው። መኖ መመገብ በሚጀምርበት ጊዜ የሚያስፈልጉት ባክቴሪያዎችና ሌሎች ረቂቅ ሕዋሳት በጨጓራው የመጀመሪያ ክፍል ውስጥ መራባት እንዲችሉ ጥጃው ብዙ ውኃ መጠጣት ያስፈልገዋል። ምንም እንኳ ወተት በቀጥታ የሚሄደው ወደ ጨጓራው የመጨረሻ ክፍል ቢሆንም ውኃ ግን የሚገባው መፈጨት የሚያስፈልጋቸው ምግቦች ወደሚገቡበት የመጀመሪያው የጨጓራ ክፍል ውስጥ ነው። አስደናቂ የሆነው የወተት ማለፊያ ቧንቧ የሚያገለግለው ለወተት ብቻ ነው!
ታዲያ ምን ይመስልሃል? የወተት ማለፊያው ቧንቧ በአጋጣሚ የተገኘ ነው? ወይስ ድንቅ ችሎታ ያለው ፈጣሪ ሥራ ነው?
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል/ሥዕላዊ መግለጫ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ወተቱ በጥጃው ጨጓራ ውስጥ ያሉትን የመጀመሪያ ሦስት ክፍሎች አልፎ በቀጥታ ወደ መጨረሻው የጨጓራ ክፍል ይገባል
[ሥዕላዊ መግለጫ]
የወተት ማለፊያ ቧንቧ
1 የመጀመሪያው የጨጓራ ክፍል (Rumen)
2 ሁለተኛው የጨጓራ ክፍል (Reticulum)
3 ሦስተኛው የጨጓራ ክፍል (Omasum)
4 የመጨረሻው የጨጓራ ክፍል (Abomasum)