በአክብሮት መጠሪያዎች መጠቀም ተገቢ ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
በአክብሮት መጠሪያዎች መጠቀም ተገቢ ነው?
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ዕለታዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን በሚያከናውኑበትና ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች በሚሰብኩበት ወቅት ከበርካታ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ይገናኙ ነበር። ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ ከፍተኛ ሥልጣን ነበራቸው። የኢየሱስ ተከታዮች እርስ በርሳቸው ሲጠራሩ በሌሎች የሕይወታቸው ዘርፎች ያላቸውን ሥልጣን በሚያመለክቱ የክብር ስሞች አይጠቀሙም ነበር። በዚያን ጊዜ በሥልጣን ላይ የነበሩ ሌሎች ሰዎች ግን በክብር ስሞች መጠራታቸው የተለመደ ነበር። የሮም ንጉሠ ነገሥት “አውግስጦስ” ተብሎ ይጠራ የነበረ ሲሆን ትርጉሙም “ግርማዊ” ማለት ነው።—የሐዋርያት ሥራ 25:21 የ1954 ትርጉም
ታዲያ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመንግሥት ባለሥልጣናት ፊት ሲቀርቡ በአክብሮት መጠሪያዎች ይጠቀሙ ነበር? እኛስ በአክብሮት መጠሪያዎች መጠቀም ይኖርብናል?
እናከብራቸዋለን እንጂ ድርጊታቸውን አንደግፍም
ሐዋርያው ጳውሎስ “ለእያንዳንዱ የሚገባውን ስጡ፤ . . . ክብር ለሚገባውም ክብርን ስጡ” በማለት የእምነት አጋሮቹን መክሯቸዋል። (ሮሜ 13:7) ይህ ደግሞ ባለሥልጣናትን በክብር ስማቸው መጥራትን ይጨምራል። በዛሬው ጊዜም አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ‘ክቡር’ እንደሚለው ባሉ የአክብሮት መጠሪያዎች መጥራት የተለመደ ነው። ይሁን እንጂ አንዳንዶች፣ ‘አንድ ሰው የሚያስከብር ምግባር እንደሌለው እየተሰማኝ ግለሰቡን በዚህ መንገድ እንዴት ልጠራው እችላለሁ?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል።
በርካታ የመንግሥት ባለሥልጣናት ኃላፊነታቸውን በሚገባ የሚወጡ ቢሆኑም እምነት የሚጣልባቸው ሁሉም አይደሉም። ያም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ ‘ስለ ጌታ ብለን’ ለነገሥታትና ለገዥዎች እንድንገዛ አጥብቆ ያሳስበናል። (1 ጴጥሮስ 2:13, 14) በመሆኑም አንድ ሰው በሥልጣን ላይ እንዲቀመጥ የፈቀደለት አምላክ መሆኑን መገንዘባችን ግለሰቡን እንድናከብረውና ተገቢ በሆነው የአክብሮት ስም እንድንጠራው ሊያነሳሳን ይገባል።—ሮሜ 13:1
አንድን ባለሥልጣን በክብር ስሙ መጥራት እንዳለብንና እንደሌለብን የሚወስነው የግለሰቡ ምግባር አይደለም። እንዲሁም አክብሮት እንድንሰጠው የሚያደርገን ምግባሩ አይደለም። አንድን ባለሥልጣን በአክብሮት ስሙ መጥራታችን ምግባሩን እንደምንደግፍ አያሳይም። ሐዋርያው ጳውሎስ በአንድ ወቅት ያጋጠመው ሁኔታ ለዚህ ምሳሌ ይሆነናል።
ጳውሎስ በአክብሮት መጠሪያዎች የተጠቀመው እንዴት ነበር?
ሐዋርያው ጳውሎስ በሐሰት ተወንጅሎ ኢየሩሳሌም ውስጥ ከታሰረ በኋላ የይሁዳ ገዥ በሆነው ፊልክስ ፊት ቀረበ። ፊልክስ የሐዋርያት ሥራ 24:26
ጥሩ ምግባር የነበረው ሰው አልነበረም። ሮማዊው ታሪክ ጸሐፊ ታሲተስ እንደገለጸው ፊልክስ “ምንም ዓይነት ቅጣት ሳይደርስበት የፈለገውን ክፉ ድርጊት መፈጸም እንደሚችል ያስብ ነበር።” ለእሱ ትልቁ ነገር ጉቦ መቀበል እንጂ ፍትሕ ማስፈን አልነበረም። ያም ቢሆን ግን ጳውሎስ በእስር ቤት በቆየባቸው ሁለት ዓመታት ለዚህ አገረ ገዥ አክብሮት አሳይቷል። ፊልክስ ከጳውሎስ ጉቦ ለመቀበል ተስፋ በማድረግ በየጊዜው እያስጠራ ያነጋግረው ነበር፤ ጳውሎስ ጉቦ ባይሰጠውም በዚህ አጋጣሚ ተጠቅሞ ሰብኮለታል።—ፊስጦስ በፊልክስ ምትክ አገር ገዥ በሆነበት ወቅት በቂሳሪያ ሆኖ የጳውሎስን ጉዳይ ተመለከተ። ፊስጦስ በአይሁድ መሪዎች ዘንድ መወደድ ስለፈለገ የጳውሎስ ጉዳይ በኢየሩሳሌም እንዲታይ ሐሳብ አቀረበ። ሆኖም ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ፍትሕ እንደማያገኝ ስላወቀ የሮም ዜጋ መሆኑ ባስገኘለት መብት በመጠቀም “ወደ ቄሳር ይግባኝ ብያለሁ” በማለት ተናገረ።—የሐዋርያት ሥራ 25:11
ፊስጦስ ጳውሎስ የተከሰሰበትን ጉዳይ ለቄሳር እንዴት እንደሚያስረዳ ግራ ገብቶት እያለ ዳግማዊ ንጉሥ አግሪጳ፣ ፊስጦስን ለመጎብኘት መጣ፤ ንጉሡም የጳውሎስን ጉዳይ ለማየት እንደሚፈልግ ገለጸ። በማግስቱ፣ ንጉሡ በከፍተኛ መኰንኖችና በከተማይቱ ታላላቅ ሰዎች ታጅቦ በታላቅ ክብር ወደ መሰብሰቢያው አዳራሽ ገባ።—የሐዋርያት ሥራ 25:13-23
ጳውሎስ እንዲናገር ሲፈቀድለት ንግግሩን የጀመረው “ንጉሥ” በሚለው የአክብሮት መጠሪያ በመጠቀም ሲሆን አግሪጳ የአይሁድን ልማድና ክርክር በሚገባ እንደሚያውቅም ገልጿል። (የሐዋርያት ሥራ 26:2, 3) በወቅቱ አግሪጳ ከእህቱ ጋር በማመንዘር አሳፋሪ ድርጊት እንደሚፈጽም በሰፊው ይወራ ነበር፤ ጳውሎስ ንጉሡ ጥሩ ሥነ ምግባር እንደሌለው ያውቅ እንደነበር ጥርጥር የለውም። ያም ቢሆን ጳውሎስ ለንጉሡ የሚገባውን አክብሮት ሰጥቶታል።
ጳውሎስ የመከራከሪያ ነጥቡን እያቀረበ እያለ ፊስጦስ “ጳውሎስ ሆይ፤ አእምሮህን ስተሃል” አለው። ጳውሎስ እንዲህ በመባሉ ከመበሳጨት ይልቅ አገረ ገዥውን “ክቡር ፊስጦስ ሆይ” ብሎ በመጥራት በእርጋታ መልስ ሰጥቶታል። (የሐዋርያት ሥራ 26:24, 25) ጳውሎስ ለአገረ ገዥው የሚገባውን ክብር አሳይቶታል። ይሁን እንጂ እነዚህ ምሳሌዎች አንድ ጥያቄ ያስነሳሉ:- ለባለሥልጣናት ልናሳይ የሚገባን አክብሮት ገደብ አለው?
አንጻራዊ የሆነ አክብሮት
ሮሜ 13:1 (NW) እንደሚጠቁመው የመንግሥት ባለሥልጣናት ያላቸው ሥልጣን አንጻራዊ ነው፤ ጥቅሱ “ባለሥልጣናት አንጻራዊ ሥልጣናቸውን ያገኙት ከአምላክ” እንደሆነ ይገልጻል። በመሆኑም ለመንግሥት ባለሥልጣናት የምንሰጠው ክብርም አንጻራዊ ነው። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንደሚከተለው በማለት በተናገረበት ወቅት ሌሎችን በአክብሮት ስም መጥራት የሌለብን መቼ እንደሆነ ጠቁሟል:- “እናንተ ግን ‘መምህር’ ተብላችሁ አትጠሩ፤ አስተማሪያችሁ አንድ ብቻ ሲሆን፣ እናንተ ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁና። በሰማይ ያለ አንድ አባት ስላላችሁ፣ በምድር ማንንም ‘አባት’ ብላችሁ አትጥሩ። መምህራችሁ [“መሪያችሁ፣” NW] አንዱ ክርስቶስ ስለሆነ፣ ‘መምህር [“መሪ፣” NW]’ ተብላችሁ አትጠሩ።”—ማቴዎስ 23:8-10
እንግዲያው፣ ባለሥልጣናትን በተገቢው የአክብሮት ስም በመጥራት ረገድ ሊኖር የሚገባውን ገደብ የሚወስነው የአክብሮት መጠሪያው ሃይማኖታዊ መሆኑ ወይም አለመሆኑ ነው። ጳውሎስ የመንግሥት ባለሥልጣናትን እንድናከብር የሰጠው ምክር እነዚህ ባለሥልጣናት ሃይማኖታዊ የአክብሮት መጠሪያ በሚኖራቸው ጊዜ በዚህ መጠሪያ መጠቀምን አይጨምርም። ቅዱሳን መጻሕፍት የሚሰጡትን ምክር የሚከተል ሰው እነዚህን ባለሥልጣናት ያከብራቸዋል። ያም ቢሆን ግለሰቡ “የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ” የሚለውን መመሪያ መታዘዝ ስላለበት በመጽሐፍ ቅዱስ በሠለጠነ ሕሊናው በመመራት በማንኛውም ሃይማኖታዊ መጠሪያ ከመጠቀም ይቆጠባል።—ማቴዎስ 22:21
ይህን አስተውለኸዋል?
▪ የኢየሱስ ተከታዮች ለመንግሥት ባለሥልጣናት ምን አመለካከት ነበራቸው?—ሮሜ 13:7
▪ ሐዋርያው ጳውሎስ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ባነጋገረበት ጊዜ በአክብሮት መጠሪያዎች ተጠቅሟል?—የሐዋርያት ሥራ 25:11፤ 26:2, 25
▪ ኢየሱስ በምን ዓይነት የአክብሮት መጠሪያዎች መጠቀም እንደሌለብን ገልጿል?—ማቴዎስ 23:8-10
[በገጽ 20, 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጳውሎስ፣ አግሪጳን ማን ብሎ ጠርቶታል?