የምድር የወደፊት ዕጣ በማን እጅ ነው?
የምድር የወደፊት ዕጣ በማን እጅ ነው?
“የምድር ሙቀት መጨመር እስከ ዛሬ አጋጥሞን የማያውቅ ትልቅ ፈተና እንዲጋረጥብን አድርጓል” በማለት ናሽናል ጂኦግራፊክ የተሰኘው መጽሔት በጥቅምት 2007 እትሙ ላይ አበክሮ ገልጿል። መጽሔቱ እንደሚናገረው ይህን ፈተና በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት ከፈለግን “በአፋጣኝና በቆራጥነት መንቀሳቀስ እንዲሁም በማኅበረሰብም ሆነ በሰው ዘር ደረጃ እምብዛም አንጸባርቀን የማናውቀውን ብስለት ማሳየት” ያስፈልገናል።
ታዲያ ሰዎች ይህን ችግር ለመፍታት እንዲህ ያለ ብስለት ማሳየት ይችሉ ይሆን? ለዚህ እንቅፋት የሚሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ፤ ከእነዚህ መካከል ግዴለሽነት፣ ስግብግብነት፣ ድንቁርናና የራስን ጥቅም ብቻ የማሳደድ አባዜ ይገኙበታል። ከዚህም በላይ በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች ውስጥ ብዙዎች ሀብትን ለማካበት መሯሯጣቸው እንዲሁም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከፍተኛ የኃይል ፍጆታ የሚጠይቀውን አኗኗራቸውን መለወጥ አለመፈለጋቸው ሌላው እንቅፋት ነው።
በጥንት ዘመን የኖረ አንድ የአምላክ ነቢይ ከሥነ ምግባር፣ ከማኅበራዊ ሁኔታና ከአስተዳደር ጋር የተያያዙ ችግሮችን የመፍታት አቅማችንን በሚመለከት ትክክለኛውን አስተያየት ሰጥቷል። እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “የሰው ሕይወት በራሱ እጅ እንዳልሆነች፣ አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል ዐውቃለሁ።” (ኤርምያስ 10:23) የሰው ልጅ ያስመዘገበው አሳዛኝ ታሪክ የእነዚህን ቃላት ትክክለኛነት ያረጋግጣል። በዛሬው ጊዜ በሳይንስና በቴክኖሎጂው መስክ ጉልህ እድገት ያስመዘገብን ብንሆንም ቀደም ሲል አስበናቸው የማናውቃቸው አደጋዎች ተጋርጠውብናል። ታዲያ ነገ የተሻለ ቀን እንደሚመጣ ምን ያህል እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
የአየር ንብረት መዛባትንና ሌሎች ጎጂ ሁኔታዎችን ስለ ማስወገድ ብዙ እንደተባለ ባይካድም የተሠራው ግን ጥቂት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በ2007 ኖርዝ ዌስት ፓሴጅ የተባለው መተላለፊያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመርከቦች ክፍት በሆነ ጊዜ መንግሥታት ምን አደረጉ? ኒው ሳይንቲስት የተሰኘው መጽሔት በርዕሰ አንቀጹ ላይ “መንግሥታት ተጨማሪ ነዳጅና ጋዝ ለማውጣት የሚያስችላቸውን ቁራጭ ቦታ ለማግኘት በሚያሳፍር ሁኔታ ሽሚያ ጀመሩ” በማለት ለዚህ ጥያቄ መልስ ሰጥቷል።
ወደ 2,000 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ተገቢ ያልሆነ ነገር ከመፈጸማቸው የተነሳ ‘ምድርን የሚያጠፉበት’ ደረጃ ላይ እንደሚደርሱ በትክክል ተንብዮአል። (ራእይ 11:18) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ዓለማችን ተፈላጊው ግብ ላይ ለመድረስ የሚያስችል ጥበብና ኃይል ያለው መሪ እንዲሁም ለሥልጣኑ የሚገዙለት ዜጎች ያስፈልጓታል። ታዲያ አንድ የፖለቲካ መሪ ወይም ሳይንቲስት ምንም ያህል ቅንና ብልህ ቢሆን እንዲህ ያለውን ሚና መጫወት ይችላል? መጽሐፍ ቅዱስ “በገዦች አትታመኑ፤ ማዳን በማይችሉ ሥጋ ለባሾችም አትመኩ” በማለት መልሱን ይሰጠናል።—መዝሙር 146:3
የምድር የወደፊት ዕጣ የወደቀው በአምላክ እጅ ነው!
በዓለም ላይ የተጋረጡትን ችግሮች በተሳካ ሁኔታ መፍታት የሚችል አንድ መሪ አለ። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን መሪ አስመልክቶ የሚከተለውን ትንቢት ተናግሯል:- “የእግዚአብሔር መንፈስ፣ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፣ የምክርና የኀይል መንፈስ፣ የዕውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል። . . . ለድኾች በጽድቅ ይፈርዳል፤ . . . በከንፈሩም እስትንፋስ ክፉዎችን ይገድላል።”—ኢሳይያስ 11:2-5
ታዲያ ይህ መሪ ማን ነው? በፍቅር ተነሳስቶ ሕይወቱን ለእኛ ሲል መሥዋዕት ካደረገው ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ማንም ሊሆን አይችልም። (ዮሐንስ 3:16) አሁን ኃያል መንፈሳዊ አካል የሆነው ኢየሱስ በምድር ላይ እንዲገዛ አምላክ ሥልጣንና ኃይል ሰጥቶታል።—ዳንኤል 7:13, 14፤ ራእይ 11:15
ኢየሱስ ብቃት እንዲኖረው አስተዋጽኦ ያደረገው አንደኛው ነገር ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ስለ አምላክ የፍጥረት ሥራዎች ያካበተው ሰፊ እውቀት ነው። እንዲያውም ሕልቆ መሳፍርት ከሌለው ዘመን በፊት አምላክ ግዑዙን ጽንፈ ዓለም በፈጠረበት ጊዜ ኢየሱስ የእሱ “ዋና ባለሙያ [“ሠራተኛ፣” የ1954 ትርጉም]” ነበር። (ምሳሌ 8:22-31) እስቲ አስበው፣ ምድርና በውስጧ ያሉት ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሲፈጠሩ ከፍተኛ እገዛ ያበረከተው ኢየሱስ፣ የሰዎች ግዴለሽነት ያስከተለውን ጉዳት በመሻር ረገድ ዋነኛውን ሚና ይጫወታል።
የክርስቶስ ተገዢዎች የሚሆኑትስ እነማን ናቸው? እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን የሚያውቁና ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ገዢያቸው አድርገው የሚታዘዙ ገርና ጻድቅ የሆኑ ሕዝቦች ናቸው። (መዝሙር 37:11, 29፤ 2 ተሰሎንቄ 1:7, 8) ኢየሱስ፣ እነዚህ ሰዎች ወደ ገነትነት የምትለወጠውን ‘ምድር እንደሚወርሱ’ ተናግሯል።—ማቴዎስ 5:5፤ ኢሳይያስ 11:6-9፤ ሉቃስ 23:43
ታዲያ አንተ የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች ሲፈጸሙ ለማየት ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ኢየሱስ ራሱ መልሱን ሲሰጥ “አንተ ብቻ እውነተኛ አምላክ የሆንኸውንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሏል።—ዮሐንስ 17:3
አዎን፣ ፕላኔታችን አደጋ የተደቀነባት ትመስላለች፤ ይሁን እንጂ ወደፊትም የሰው ዘር መኖሪያ በመሆን እንደምትቀጥል ምንም ጥርጥር የለውም። ከዚህ ይልቅ አደጋ የተደቀነባቸው ለአምላክ ፍጥረት ንቀት ማሳየታቸውን የሚቀጥሉና ኢየሱስ ክርስቶስን ለመታዘዝ አሻፈረኝ የሚሉ ሰዎች ናቸው። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን እውቀት እንድትቀስም ያበረታቱሃል።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ከሳይንስ አቅም በላይ የሆነ ችግር
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጉዳት እንደሚያስከትልባቸው በሚገባ ቢያውቁም ደስታ ለማግኘት በሚል ሰበብ ዕፅ በመውሰድ፣ የአልኮል መጠጥ ያላግባብ በመጠጣትና ትንባሆ በማጨስ አእምሯቸውንና አካላቸውን ይጎዳሉ። እነዚህ ሰዎች ሕይወትን ከአምላክ የተገኘ ቅዱስ ስጦታ እንደሆነ አድርገው አይመለከቱትም። (መዝሙር 36:9፤ 2 ቆሮንቶስ 7:1) የሚያሳዝነው ነገር፣ ምድርን ለብልሽት ከዳረጓት ነገሮች አንዱ እንዲህ ያለው አምላክ የለሽ አመለካከት ነው።
ታዲያ መፍትሔው ምንድን ነው? መፍትሔው ሳይንስና ትምህርት ነው? በጭራሽ። ችግሩ ሰዎች መንፈሳዊነት ስለጎደላቸው የመጣ በመሆኑ መፍትሔውን ለማግኘት መንፈሳዊነትን ማዳበር የግድ ነው። መጽሐፍ ቅዱስም ይህንኑ ሐቅ ያረጋግጣል። መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች በምድር ላይ ‘ጉዳት ወይም ጥፋት የማያደርሱበት’ ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ ይሰጣል፤ ምክንያቱም ‘ውሃ ባሕርን እንደሚሸፍን፣ ምድር ሁሉ ይሖዋን በማወቅ ትሞላለች።’—ኢሳይያስ 11:9
[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቶስ በሚገዛበት ወቅት ጻድቃን መላዋን ምድር ገነት በማድረጉ ሥራ ይካፈላሉ