በአፈር ውስጥ የሚደረግ አስደናቂ ትብብር
ንድፍ አውጪ አለው?
በአፈር ውስጥ የሚደረግ አስደናቂ ትብብር
▪ አንዳንድ የዕፅዋት ዝርያዎችና ባክቴሪያዎች በአፈር ውስጥ በጣም አስደናቂ ትብብር ማድረጋቸው ሕይወት እንዲኖር ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
እስቲ የሚከተለውን አስብ:- ናይትሮጅን ለዕፅዋት እድገትና መራባት የግድ አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ ዕፅዋት ይህን ጋዝ ጥቅም ላይ እንዲያውሉት እንደ አሞኒያ ወዳሉ ሌሎች ንጥረ ነገሮች መለወጥ ይኖርበታል። ባቄላና አተር የመሳሰሉት ሰብሎች ራይዞብያ ከሚባሉት ባክቴሪያዎች ጋር ተቀናጅተው በመሥራት ይህን ተግባር ያከናውናሉ። ሁለት የማይመሳሰሉ ፍጥረታት ለጋራ ጥቅማቸው ሲሉ የሚያደርጉት ይህ ትብብር ሲምባዮሲስ ይባላል።
እነዚህ ተክሎች ልዩ በሆነ ኬሚካል አማካይነት ባክቴሪያዎቹን ወደ ሥሮቻቸው ይስባሉ፤ ባክቴሪያዎቹም ወደ ሥሮቹ ይገባሉ። ናቹራል ሂስትሪ የተሰኘው መጽሔት እንደተናገረው ባክቴሪያዎቹ ከእንስሳት፣ ተክሎቹ ደግሞ ከዕፅዋት የሚመደቡ ቢሆኑም ተባብረው በመሥራት “ናይትሮጅንን የመለወጥ ችሎታ ያለው ሩት ኖዲውል የሚባል አዲስ የሥር እባጭ ያስገኛሉ።” ባክቴሪያዎቹ በአዲሱ መኖሪያቸውና የሥራ ቦታቸው ውስጥ ሆነው ሥራቸውን ማካሄድ ይጀምራሉ። ዋነኛ መሣሪያቸው ናይትሮጂኔዝ የተባለው ልዩ ኤንዛይም ሲሆን በዚህ ኤንዛይም አማካኝነት በአፈር ውስጥ የሚገኘውን ናይትሮጂን ወደ አሞኒያ ይለውጣሉ።
ናቹራል ሂስትሪ እንደገለጸው “በመላዋ ምድር ላይ ያለው ናይትሮጂኔዝ አንድ ላይ ቢጠራቀም . . . ከአንድ ትልቅ ባልዲ ያለፈ መጠን አይኖረውም።” ስለዚህ አንድም ሞለኪዩል መባከን የለበትም! ይሁንና አንድ ችግር አለ። ኤንዛይሙ ለኦክሲጅን ከተጋለጠ ይረክሳል ወይም ኃይሉን ያጣል። ታዲያ መፍትሔው ምንድን ነው? ተክሉ ጎጂ የሆነውን ይህን ኦክሲጅን ማስወገድ የሚችል ልዩ ንጥረ ነገር ይሠራል።
በሩት ኖዲውሉ ዙሪያ ያለው ስስ ሽፋን በባክቴሪያዎቹና በተክሉ መካከል የሚደረገውን የአሞኒያ፣ የስኳርና የሌሎች ንጥረ ነገሮች ልውውጥ ይቆጣጠራል። እንደ ሌሎቹ ዕፅዋት ሁሉ እነዚህ ተክሎችም ውለው አድረው ይሞታሉ። በሚሞቱበት ጊዜ አሞኒያው አፈሩ ውስጥ ይቀራል። በዚህም የተነሳ አንደ ባቄላና አተር የመሳሰሉት ተክሎች “አረንጓዴ ፍግ” ተብለው መጠራታቸው የተገባ ነው።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? በባክቴሪያዎችና በዕፅዋት መካከል የሚፈጸመው እንዲህ ያለው ትብብር እጅግ አስደናቂና ውስብስብ መሆኑ እሙን ነው፤ ይሁንና ለሕይወት አስፈላጊ የሆነውን እንዲህ ያለውን ሥርዓት “የፈለሰፉት” እነሱ ራሳቸው ናቸው ወይስ ንድፍ አውጪ እንዳለ የሚያሳይ ሌላ ማስረጃ ነው?
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሩት ኖዲውል
[በገጽ 25 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]
የዳራ ሥዕል:- © Wally Eberhart/Visuals Unlimited; ሩት ኖዲውል:- © Dr. Jack M. Bostrack/Visuals Unlimited