ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
▪ በ2007 በአርክቲክ ባሕር ላይ ያለው የበረዶ ግግር “በሳተላይት ፎቶ መነሳት በጀመረበት ጊዜ ከነበረው መጠን እጅግ በጣም ቀንሷል።” በረዶው በ2005 ሲለካ ከነበረው አነስተኛ መጠን በ23 በመቶ ቀንሶ በአሁኑ ጊዜ 4,280,000 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሆኗል።—ናሽናል ስኖው ኤንድ አይስ ዳታ ሴንተር፣ ዩናይትድ ስቴትስ
▪ ከ100 ዜጎቿ መካከል 90ዎቹ የጦር መሣሪያ እንደታጠቁ የሚነገርላት ዩናይትድ ስቴትስ በዓለም ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሣሪያ የሚገኝባት አገር ሆናለች። “ተራው ሕዝብ የጦር መሣሪያ የታጠቀባት አገር በመሆን ረገድ ሁለተኛውን ደረጃ የያዘችው” ሕንድ ስትሆን “መሣሪያ የታጠቁት ከ100 ሰዎች መካከል 4ቱ ብቻ ናቸው።”—ታይም፣ ዩናይትድ ስቴትስ
▪ በማያሚ፣ ፍሎሪዳ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በ21 ሳምንት ከስድስት ቀኗ የተወለደችው ከ283.5 ግራም የሚያንስ ክብደት ያላት ሕፃን “እስከዛሬ ከተመዘገቡት ያለጊዜያቸው ተወልደው በሕይወት መቆየት የቻሉ ሕፃናት መካከል ትንሿ ሳትሆን” እንደማትቀር ተዘግቧል። “ከተፀነሱ 23 ሳምንት ሳይሞላቸው የሚወለዱና ክብደታቸው ከ400 ግራም በታች የሆኑ ሕፃናት በሕይወት ሊቆዩ እንደማይችሉ ይታመናል።”—ሮይተርስ ኒውስ ሰርቪስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ
ከባሕር የሚገኝ ንጹሕ ውኃ
በኤጅያን ባሕር በሚገኙ ደሴቶች ላይ ያለውን የውኃ እጥረት ለመቅረፍ የግሪክ የሳይንስ ሊቃውንት “ለዓለማችን የመጀመሪያ የሆነውን ራሱን ችሎ የሚሠራ ጨውን ከባሕር ውኃ የሚለይ ተንሳፋፊ የውኃ ማጣሪያ ማሽን” እንደሠሩ የአቴንስ የዜና ወኪል ዘግቧል። በነፋስ ከሚንቀሳቀሱ ሞተሮችና በፀሐይ ከሚሠሩ ባትሪዎች ኃይል የሚያገኘው ይህ ማሽን 300 ለሚያህሉ ሰዎች የዕለት ፍጆታ የሚበቃ ውኃ ማጣራት ይችላል። ይህ ማሽን መጥፎ በሆነ የአየር ሁኔታም እንኳ ያለ አንዳች እንከን የሚሠራ ከመሆኑም ሌላ ከርቀት ሆኖ መቆጣጠርና ወደሚፈለግበት ቦታ ማንቀሳቀስ ይቻላል።
ጥንታዊ አጽሞች ተገኙ
“በሳይቤሪያ ሰሜናዊ ጫፍ ላይ . . . እየጨመረ ያለው የአየር ሙቀት ግግር በረዶውን ስላቀለጠው ለዘመናት ተቀብረው የነበሩ አጽሞች ተገኝተዋል። ከእነዚህ መካከል በአሁኑ ጊዜ የሌሉ ትልልቅ የዝሆን ዝርያዎች እንዲሁም ፀጉራም የሆኑ አውራሪሶችና አንበሶች ይገኙበታል” በማለት በሩሲያ፣ ሳካ ከሚገኘው የቼርስኪ ከተማ ሪፖርት የተደረገው የሮይተር የዜና ዘገባ ይናገራል። አጽም አሰባሳቢዎችም ሆኑ ሳይንሳዊ ተቋማት የሚፈልጓቸውን አጽሞች በእጃቸው ለማስገባት ብዙ ገንዘብ ለመክፈል ፈቃደኞች በመሆናቸው አሳሾች በአካባቢው ሰዎች እየታገዙ ጥሩ ዋጋ የሚያወጡ አጽሞችን ለመፈለግ ጠፍ በሆነው ቀዝቃዛ ምድር ላይ ወዲያ ወዲህ ይላሉ። ዘገባው እንዲህ ይላል:- “ለዘመናት ተጋግሮ የኖረው በረዶ በፍጥነት እየቀለጠ በመሆኑ በአንዳንድ ስፍራዎች . . . በየጥቂት ሜትሮች ርቀት ላይ አግጥጠው የወጡ አጥንቶች ይታያሉ።”
ከኮንትሮባንድ የተወረሰ የአልኮል መጠጥ ለመልካም አገልግሎት ዋለ
እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ የስዊድን የጉምሩክ ባለ ሥልጣናት ከኮንትሮባንድ አዘዋዋሪዎች የወረሱትን የአልኮል መጠጥ “ይደፉት ነበር።” አሁን ግን እንዲህ ዓይነቱ መጠጥ “ለአገሪቱ የሕዝብ መጓጓዣ አገልግሎት የሚወጣውን የነዳጅ ፍጆታ ለመደጎም እያገለገለ” መሆኑን ከስቶክሆልም የተገኘው የአሶሺዬትድ ፕሬስ ሪፖርት ያሳያል። በ2006 የተወረሰው 700,000 ሊትር የሚያህል የአልኮል መጠጥ ወደ ባዮጋዝነት ተለውጦ “አውቶቡሶችን፣ የጭነት መኪኖችንና በባዮጋዝ የሚሠሩ ባቡሮችን ለማንቀሳቀስ ውሏል።” ይህ ነዳጅ “በነፃ የሚገኝ መሆኑ እጅግ ትርፋማ” እንዳደረገው ዘገባው ጠቅሷል። በተጨማሪም ይህን ነዳጅ መጠቀም ስዊድን ከባቢ አየሯን የሚያሞቀውን የጭስ መጠን እንድትቀንስ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
“የዓይነ አፋርነት ወረርሽኝ”
“ኢ-ሜይል፣ በሞባይል ስልኮች የጽሑፍ መልእክት መለዋወጥና አይፖድ ዓለም አቀፍ የሆነ የዓይነ አፋርነት ወረርሽኝ እያስከተሉ” መሆናቸውን የአውስትራሊያው ሰንደይ ቴሌግራፍ ዘግቧል። ሮቢን አብረሃምስ የተባሉት የሥነ ልቦና ሊቅና ተመራማሪ እንደሚሉት ከሆነ በአሁኑ ጊዜ በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ዓይነ አፋር መሆን ከጠቅላላው የዓለም ሕዝብ ግማሽ የሚሆነውን እያጠቃ ሲሆን ይህ አኃዝ ችግሩ ቀደም ሲል ከነበረው በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን ያመለክታል። አብረሃምስ እንዲህ ይላሉ:- “ቴክኖሎጂ የማንፈልጋቸውን ሁኔታዎች ከመጋፈጥ ያዳነን ሲሆን ሰዎች እያደር ራሳቸውን እንዲያገሉ ምክንያት እየሆነ መጥቷል። ሰዎች . . . ከመነጋገር ይልቅ ኢ-ሜይል ማድረግ ወይም በሞባይሎቻቸው የጽሑፍ መልእክት መለዋወጥ ይመርጣሉ።”