ራስን መከላከል ተገቢ የሚሆነው መቼ ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ራስን መከላከል ተገቢ የሚሆነው መቼ ነው?
ሌሊት ተኝተህ ሳለ በድንገት የሆነ ኮሽታ ከእንቅልፍህ ቀሰቀሰህ እንበል። የእግር ኮቴም ተሰማህ። ቤትህን ሰብሮ የገባ ሰው አለ። ልብህ በፍጥነት ይመታል፤ ቀጥለህ ምን ማድረግ እንዳለብህ በፍርሃት ታስባለህ።
ይህ አጋጣሚ በማንም ላይ ሊደርስ የሚችል ነው። ወንጀል ሌላው ቀርቶ የኃይል ድርጊት የታከለበት ወንጀል እንኳ በአንዳንድ አገሮችና በትላልቅ ከተሞች ብቻ የተወሰነ መሆኑ ቀርቶ የትም ቦታ የተለመደ ነገር ሆኗል። ብዙ ሰዎች ወንጀል ይፈጸምብኛል የሚል ስጋት ስላለባቸው የጦር መሣሪያ በመግዛት ወይም ካራቴ በመማር ራሳቸውን ለመከላከል ይጥራሉ። አንዳንድ መንግሥታትም፣ ዜጎቻቸው ራሳቸውን ከወንጀል ለመከላከል የሚያጠቃቸውን ሰው መግደል እንደሚችሉ የሚገልጹ ሕጎችን አውጥተዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል? አንድ ሰው ራሱን ወይም ቤተሰቡን ለመከላከል ሲል ኃይል መጠቀሙ ተገቢ ይሆናል?
አምላክ ዓመጽን ይጠላል
መጽሐፍ ቅዱስ ዓመጽንና ዓመጸኞችን ያወግዛል። መዝሙራዊው ዳዊት፣ ይሖዋ አምላክን በሚመለከት “ዐመፃን የሚወዱትን ግን፣ ነፍሱ ትጠላቸዋለች” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 11:5) አምላክ፣ የራሱ ሕዝብ የነበሩትን ጨምሮ አያሌ የጥንት ብሔራት ዓመጸኞችና ደም አፍሳሾች በመሆናቸው የተነሳ ፍርድ በይኖባቸዋል። (ኢዩኤል 3:19፤ ሚክያስ 6:12፤ ናሆም 3:1) አምላክ ለእስራኤላውያን በሰጠው ሕግ መሠረት አንድ ሰው በግዴለሽነት ነፍስ ማጥፋቱ እንኳ እንደ ከባድ ወንጀል ተደርጎ ይታይ ነበር።—ዘዳግም 22:8
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰዎች በየዕለቱ ሰላምን በመከታተል ጠብ ሊያስነሱ ከሚችሉ ነገሮች እንዲርቁ ይመክራል። አብዛኛውን ጊዜ ግብግብ የሚፈጠረው በንዴት በሚነገሩ የቃላት ምልልሶች ምክንያት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ዕንጨት ምሳሌ 26:20) የረጋ መንፈስ ብዙውን ጊዜ ንዴትን የሚያበርድ ሲሆን ግብግብንም ያስቀራል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ቢቻላችሁስ በበኩላችሁ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” በማለት ጽፏል።—ሮሜ 12:18
ከሌለ እሳት ይጠፋል፤ አሾክሻኪ ከሌለም ጠብ ይበርዳል” በማለት ይናገራል። (ጥቃት ሲሰነዘርብህ
ሰላምን መከታተልህ ጥቃት እንዳይሰነዘርብህ ዋስትና አይሆንህም። በታሪክ ዘመናት ሁሉ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች የዓመጽ ድርጊት ሰለባዎች ነበሩ። (ዘፍጥረት 4:8፤ ኢዮብ 1:14, 15, 17) አንድ ሰው መሣሪያ የታጠቀ ዘራፊ ቢመጣበት ምን ማድረግ ይኖርበታል? ኢየሱስ “ክፉ አድራጊውን ሰው አትቃወሙት” የሚል መመሪያ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 5:39) በተጨማሪም “መጐናጸፊያህን ለሚወስድብህ እጀ ጠባብህን አትከልክለው” ብሏል። (ሉቃስ 6:29) ኢየሱስ፣ ቁሳዊ ንብረትን ለመከላከል ሲባል መሣሪያ መጠቀምን አልደገፈም። ጥበበኛ የሆነ ሰው መሣሪያ የታጠቀ ዘራፊ ቢያጋጥመው ንብረቱን አሳልፎ ላለመስጠት ግብግብ አይገጥምም። በእርግጥም ሕይወት ከማንኛውም ንብረት የበለጠ ውድ ነገር ነው!
በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ግለሰብ ለሕይወቱ የሚያሰጋ ሁኔታ ቢገጥመውስ? አምላክ ለጥንቱ እስራኤል የሰጠው ሕግ በዚህ ረገድ ፍንጭ ይሰጠናል። አንድ ሌባ በቀን ተይዞ ቢገደል፣ ገዳዩ በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ይከሰስ ነበር። ይህም የሆነው ስርቆት በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል ስላልነበረና ቀን ከሆነ ደግሞ ሌባው ማንነቱ ስለሚታወቅ ለፍርድ ሊቀርብ ይችል ስለነበረ ነው። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ቤቱን ሰብሮ የገባውን ግለሰብ በሌሊት ቢገድለው፣ ይህን ያደረገው ግለሰቡ ምን እየሠራ እንዳለና ያሰበው ነገር ምን እንደሆነ በእርግጠኝነት ማወቅ ስለማይችል በመሆኑ ከቅጣት ነፃ ይሆን ነበር። የቤቱ ባለቤት የቤተሰቡ ሕይወት አደጋ ላይ እንደወደቀ ሊያስብና የመከላከል እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ሊሰማው ይችላል።—ዘፀአት 22:2, 3
በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንድ ሰው በራሱ ወይም በቤተሰቡ ላይ አካላዊ ጥቃት ከተሰነዘረበት የመከላከል እርምጃ መውሰድ እንደሚችል ያመለክታል። የተሰነዘረበትን ምት ሊመክት፣ ጥቃት የሚሰነዝረውን ሰው አጥብቆ ሊይዘው ወይም አጥቂውን ለማደናገር አሊያም ጥቃት መሰንዘሩን እንዲያቆም ለማድረግ ሊመታው ይችላል። ዓላማው ጥቃቱን ማስቆም ነው። በዚህ ጊዜ ጥቃት ፈጻሚው ከባድ ጉዳት ቢደርስበት ወይም ቢሞት፣ ሞቱ ድንገተኛ እንጂ ሆን ተብሎ የተደረገ አይደለም።
ከሁሉ የተሻለው የመከላከያ ዘዴ
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሚዛኑን ያልሳተ ራስን የመከላከል እርምጃ መውሰድ ተገቢ የሚሆንባቸው ሁኔታዎች አሉ። ሰዎች ራሳቸውንም ሆነ የሚወዷቸውን ሰዎች ከጥቃትና ሞት ሊያስከትል ከሚችል ጉዳት የመጠበቅ መብት አላቸው። ማምለጥ በማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ ራሳችንን መከላከልን የሚያወግዝ የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ የለም። ያም ሆኖ የጥበብ አካሄድ የሚሆነው ግብግብ ከሚፈጥሩ ሁኔታዎች ለመራቅ የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ነው።—ምሳሌ 16:32
መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወታችን ዘርፍ ሁሉ ‘ሰላምን እንድንፈልግና እንድንከታተል’ ያበረታታናል። (1 ጴጥሮስ 3:11) ይህ በእርግጥም ሰላማዊ ሕይወት ለመኖር የሚረዳ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መመሪያ ነው።
ይህን አስተውለኸዋል?
▪ ከዓመጽ መራቅ ያለብን ለምንድን ነው?—መዝሙር 11:5
▪ ቁሳዊ ንብረቶች እንዳይወሰዱ መከላከልን በተመለከተ የጥበብ አካሄድ የሆነው ነገር ምንድን ነው?—ምሳሌ 16:32፤ ሉቃስ 12:15
▪ አደጋን ለመከላከል የሚረዳን ስለ ጠብ ምን አመለካከት መያዛችን ነው?—ሮሜ 12:18
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንድ ሰው በራሱ ወይም በቤተሰቡ ላይ አካላዊ ጥቃት ከተሰነዘረበት የመከላከል እርምጃ መውሰድ እንደሚችል ያመለክታል