የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎችን መጫወት ይኖርብኛል?
የወጣቶች ጥያቄ
የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎችን መጫወት ይኖርብኛል?
የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች (የቪዲዮ ወይም የኮምፒዩተር ጌሞች) ለመዝናኛነት ብቻ ታስበው የሚዘጋጁ የረቀቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አይደሉም። እውነት ነው፣ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች ችሎታህን ይፈታተናሉ፤ እንዲሁም የመሰላቸትን ስሜት ይቀንሱልሃል። ይሁንና ከዚያም ያለፈ ጠቀሜታ አላቸው። እንደዚህ ያሉ ጨዋታዎችን መጫወት ለነገሮች ፈጣን ምላሽ የመስጠት ችሎታህን የሚያዳብርልህ ከመሆኑም ሌላ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ትኩረት የመሰብሰብ ችሎታን ያሻሽላል። እንዲያውም አንዳንዶቹ የሒሳብና የማንበብ ችሎታህን ያሳድጉልህ ይሆናል። ከዚህም በላይ በቅርቡ የወጣው አዲስ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታ በትምህርት ቤት ውስጥ ዋነኛ የመወያያ ርዕስ መሆኑ አይቀርም። በመሆኑም ይህንን ጨዋታ ተጫወትክ ማለት ከጓደኞችህ ጋር የምታወራው ነገር አገኘህ ማለት ነው።
እርግጥ ነው፣ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎችን መጫወት ይፈቀድልህ እንደሆነና እንዳልሆነ የሚወስኑት ወላጆችህ ናቸው። (ቈላስይስ 3:20) እንድትጫወት ከፈቀዱልህ ግን አስደሳችና ከሥነ ምግባር አኳያ ጥሩ የሆኑ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎችን መምረጥ ይኖርብሃል። ይሁን እንጂ እነዚህን ጨዋታዎች ስትመርጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ የሚያስፈልግህ ለምንድን ነው?
የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች መጥፎ ገጽታ አላቸው!
የአሥራ ስድስት ዓመቱ ብራያን “የኮምፒውተር ጨዋታዎች አስደሳችና የሚወደዱ ናቸው” ብሏል። ይሁን እንጂ ሁሉም የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች ጥሩ እንዳልሆኑ አንተም ሳታውቅ አትቀርም። ብራያን እንዲህ ሲል እውነታውን ሳይሸሽግ ተናግሯል:- “በገሃዱ ዓለም ቢሆን ለከፍተኛ ችግር ስለሚዳርጉህ በጭራሽ የማታደርጋቸውን ነገሮች ጌም ስትጫወት ግን ልታደርጋቸው ትችላለህ።” እነዚህ ጨዋታዎች የሚያበረታቱህ ምን ዓይነት ባሕርይ እንዲኖርህ ነው?
መዝሙር 11:5፤ ገላትያ 5:19-21፤ ቈላስይስ 3:8) አንዳንዶቹ ጨዋታዎች መናፍስታዊ ድርጊቶችን ጥሩ እንደሆኑ አድርገው ያቀርባሉ። የአሥራ ስምንት ዓመቱ አድሪያን ታዋቂ በሆነ በአንድ ጌም ላይ “አደገኛ ዕፆችን የሚወስዱ ሰዎች፣ በወሮበላ ቡድኖች መካከል የሚደረጉ ጦርነቶች፣ በግልጽ የሚታዩ ከጾታ ጋር የተያያዙ ነገሮች፣ አሰቃቂ የዓመጽ ድርጊቶችና ደም መፋሰስ የሞላባቸው ዘግናኝ ትእይንቶች እንደሚታዩና ጸያፍ ንግግር እንደሚደመጥ” ገልጿል። በየጊዜው የሚወጣው አዲስ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታ ደግሞ ቀደም ሲል ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ይበልጥ ማራኪ ይሆናል። የ19 ዓመቱ ጄምስ፣ ከእነዚህ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች ውስጥ በጣም ታዋቂ የሆኑትን በኢንተርኔት አማካኝነት ከሌላ ሰው ጋር መጫወት እንደሚቻል ይናገራል። ይህ ደግሞ የኮምፒውተር ጨዋታ አጨዋወትን ወደ አዲስ የእድገት ደረጃ አሸጋግሮታል። ጄምስ “ቤትህ ቁጭ ብለህ በኮምፒውተር አማካኝነት በሌላው የዓለም ክፍል ከሚገኙ ሰዎች ጋር መፎካከር ትችላለህ” ብሏል።
በርካታ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች የሥነ ምግባር ብልግናን፣ ጸያፍ ንግግርንና ዓመጽን በግልጽ የሚያበረታቱ ሲሆን እነዚህን ድርጊቶች ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ያወግዛቸዋል። (ተጫዋቾች አንድን ገጸ ባሕርይ ወክለው የሚጫወቱባቸው የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች በጣም ተወዳጅ እየሆኑ መጥተዋል። እነዚህን ጨዋታዎች የሚጫወቱት ሰዎች፣ የሰው፣ የእንስሳ ወይም የሁለቱም ድብልቅ የሆነ ገጸ ባሕርይ መፍጠር ይችላሉ። በሺህ የሚቆጠሩ ሌሎች ተጨዋቾች ባሉበት በዚህ የኮምፒውተር ዓለም ውስጥ ሱቆች፣ መኪኖች፣ ቤቶች፣ የጭፈራና የዝሙት አዳሪ ቤቶች ይገኛሉ። በሌላ አነጋገር በገሃዱ ዓለም ውስጥ ያሉት ነገሮች ሁሉ ይገኙበታል። እነዚህን ጨዋታዎች በኢንተርኔት የሚጫወቱ ሰዎች ኮምፒውተር በፈጠራቸው ገጸ ባሕርያት አማካኝነት እየተጫወቱ መልእክት መለዋወጥም ይችላሉ።
በዚህ የኮምፒውተር ዓለም ውስጥ ምን ነገሮች ይከናወናሉ? አንድ ጋዜጠኛ እንደሚከተለው ሲል ተናግሯል:- “ሰዎች በገሃዱ ዓለም ውስጥ በጭራሽ የማያደርጓቸውን ወይም ሊያደርጓቸው የማይችሏቸውን ድርጊቶች ይፈጽማሉ። የጾታ ብልግናም ሆነ ዝሙት አዳሪነት የተለመዱ ነገሮች ናቸው።” ጥቂት የኮምፒውተር ቁልፎችን በመጫን ብቻ ተጫዋቾቹ በኮምፒውተሩ አማካኝነት የፈጠሯቸው ገጸ ባሕርያት የጾታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ ማድረግ የሚችሉ ሲሆን እነሱ ደግሞ ስለ ጾታ ግንኙነት መልእክት መለዋወጥ ይችላሉ። በተጨማሪም፣ ይህ ገሃዱን ዓለም እንዲመስል ተደርጎ የተሠራ የኮምፒውተር ዓለም “በወንጀለኞች፣ በማፊያዎች፣ ዝሙት አዳሪ በሚያገናኙ ደላላዎች፣ በማጅራት መቺዎች፣ በአጭበርባሪዎችና በነፍሰ ገዳዮች የተሞላ” እንደሆነ ኒው ሳይንቲስት መጽሔት ዘግቧል። ሌላ መጽሔት ደግሞ እንዲህ ሲል ሪፖርት አድርጓል:- “በዚህ ዙሪያ ጥናት የሚያደርጉ ባለሙያዎች እነዚህ ጨዋታዎች አስገድዶ እንደ መድፈርና ልጆች እንዲመስሉ ተደርገው የተፈጠሩ ገጸ ባሕርያትን በጾታ እንደ ማስነወር ያሉ በገሃዱ ዓለም ውስጥ ሕገወጥ የሆኑ ድርጊቶች የሚፈጸሙባቸው መሆናቸው ስጋት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።”
ምርጫህ ለውጥ ያመጣል?
ዓመጽ የሚንጸባረቅባቸውንና የጾታ ብልግና በግልጽ የሚታይባቸውን የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች የሚጫወቱ ሰዎች “ማንም ሰው እስካልተጎዳ ድረስ ምን ችግር አለው? ይሄ እኮ የእውነት አይደለም፤ ጨዋታ ነው” ይሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ እንዲህ ባለው የተሳሳተ አስተሳሰብ አትታለል!
መጽሐፍ ቅዱስ “ሕፃን እንኳ ጠባዩ ንጹሕና ቅን መሆኑ፣ ከአድራጎቱ ይታወቃል” ይላል። (ምሳሌ 20:11) ዓመጽና መጥፎ ሥነ ምግባር የሚታይባቸውን የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች አዘውትረህ የምትጫወት ከሆነ ንጹሕና ቅን አስተሳሰብ አለህ ሊባል ይችላል? ዓመጽ የሚበዛባቸውን መዝናኛዎች የሚመለከቱ ሰዎች ጠበኞች የመሆን አጋጣሚያቸው እንደሚጨምር ጥናቶች በተደጋጋሚ አሳይተዋል። ኒው ሳይንቲስት በቅርቡ እንደዘገበው “የቪዲዮ ጨዋታዎች ተጫዋቾቹን ተመልካቾች ብቻ ሳይሆን ተሳታፊዎችም ስለሚያደርጉ ከቴሌቪዥን የበለጠ ተጽዕኖ ያሳድራሉ።”
ዓመጽ ወይም የሥነ ምግባር ብልግና የሚታይባቸውን የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች ለመጫወት መምረጥ በራድዮአክቲቭ ዝቃጭ የመጫወት ያህል ነው። ዝቃጩ የሚያደርሰው አደጋ ወዲያውኑ የሚታይ ባይሆንም ውሎ አድሮ ጉዳት ማስከተሉ አይቀርም። እንዴት? ከፍተኛ መጠን ላለው የራድዮአክቲቭ ጨረር መጋለጥ በጨጓራና በአንጀት ግድግዳ ላይ ጉዳት ያደርሳል፤ ይህም በአንጀት ውስጥ የሚገኙት ባክቴሪያዎች ወደ ደም እንዲገቡ ስለሚያደርግ ለበሽታ ይዳርጋል። በተመሳሳይም የጾታ ግንኙነት በግልጽ የሚታዩባቸውንና አሰቃቂ የዓመጽ ድርጊቶች የሚፈጸሙባቸውን የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች መጫወት ‘ሕሊናህን’ የሚጎዳው ከመሆኑም ባሻገር ሥጋዊ ምኞቶች አስተሳሰብህንና ድርጊትህን እንዲቆጣጠሩት ያደርጋል።—ኤፌሶን 4:19፤ ገላትያ 6:7, 8
ምን ዓይነት የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎችን ብመርጥ ይሻላል?
ወላጆችህ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች እንድትጫወት የሚፈቅዱልህ ከሆነ የትኞቹን መምረጥ እንዳለብህ ማወቅ
የምትችለው እንዴት ነው? በመጫወት የምታሳልፈው ጊዜ ምን ያህል መሆን እንዳለበት ለመወሰንስ ምን ሊረዳህ ይችላል? ራስህን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ጠይቅ:-▪ የማደርገው ምርጫ ይሖዋን ያሳዝነዋል? ለመጫወት የምትመርጠው የኤሌክትሮኒክ ጨዋታ አምላክ ስለ አንተ በሚኖረው ስሜት ላይ ለውጥ ያመጣል። መዝሙር 11:5 “እግዚአብሔር ጻድቁንና ኀጥኡን ይመረምራል፤ ዐመፃን የሚወዱትን ግን፣ ነፍሱ ትጠላቸዋለች” ይላል። የአምላክ ቃል በመናፍስታዊ ድርጊቶች የሚካፈሉ ሰዎችን አስመልክቶ ሲናገር “እነዚህን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው” ይላል። (ዘዳግም 18:10-12) የአምላክ ወዳጆች መሆን ከፈለግን በመዝሙር 97:10 ላይ የሚገኘውን “እግዚአብሔርን የምትወዱ ክፋትን ጥሉ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል።
▪ የምጫወተው ኤሌክትሮኒክ ጨዋታ በአስተሳሰቤ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው? “ይህንን ጨዋታ መጫወቴ ‘ከዝሙት ለመሸሽ’ የማደርገውን ጥረት ቀላል ያደርግልኛል ወይስ ያከብድብኛል?” ብለህ ራስህን ጠይቅ። (1 ቆሮንቶስ 6:18) የጾታ ስሜትን የሚያነሳሱ ሥዕሎችን እንድታይ ወይም መልእክቶችን እንድትለዋወጥ የሚያደርጉ ኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች አእምሮህ ትክክል፣ ንጹሕና በጎ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር አይረዱህም። (ፊልጵስዩስ 4:8) የ22 ዓመት ወጣት የሆነችው ኤሚ እንዲህ ትላለች:- “በርካታ ኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች እንደ ዓመጽ፣ ጸያፍ ንግግርና የጾታ ብልግና ላሉ ነገሮች ደንታ ቢስ እንድትሆን የሚያደርጉህ ሲሆን በሌሎቹ የሕይወት ዘርፎች በሚያጋጥሙህ ፈተናዎች እንድትሸነፍ ሊያደርጉህ ይችላሉ። የምትጫወታቸውን ኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች በጥንቃቄ መምረጥ ይኖርብሃል።”
▪ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎችን በመጫወት ምን ያህል ጊዜ አሳልፋለሁ? የ18 ዓመቷ ዲቦራ “የኮምፒውተር ጨዋታዎች በሙሉ መጥፎ አይመስሉኝም። ሆኖም ብዙ ጊዜ ሊወስዱና ሱስ ሊሆኑ ይችላሉ።” ምንም ጉዳት የላቸውም የሚባሉት የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች እንኳ በጣም ብዙ ጊዜ ሊወስዱ ይችላሉ። እነዚህን ጨዋታዎች በመጫወት የምታጠፋውን ጊዜ ጽፈህ በመያዝ ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑ ሌሎች እንቅስቃሴዎች ላይ ከምታሳልፈው ጊዜ ጋር አወዳድረው። እንዲህ ማድረግህ ቅድሚያ ልትሰጣቸው የሚገቡህን ነገሮች እንድታስቀድም ይረዳሃል።—ኤፌሶን 5:15, 16
መጽሐፍ ቅዱስ መላ ሕይወትህ በጥናትና በሥራ ብቻ የተጠመደ መሆን አለበት አይልም። ከዚህ ይልቅ “ለመሣቅም ጊዜ አለው፤ . . . ለጭፈራም ጊዜ አለው” ሲል ይነግረናል። (መክብብ 3:4) ‘ጭፈራ’ የሚለው ቃል መጫወትን ብቻ ሳይሆን አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግንም የሚጨምር መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። ታዲያ የእረፍት ጊዜህን ኮምፒውተር ላይ ተተክለህ ከማሳለፍ ይልቅ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ በሚጠይቁ ጨዋታዎች በመካፈል ለምን አታሳልፈውም?
በጥበብ ምረጥ
ኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎችን መጫወት፣ በተለይ ደግሞ ጎበዝ ተጫዋች ከሆንክ አስደሳች እንደሚሆንልህ ግልጽ ነው። የምትጫወተውን ጨዋታ በጥበብ መምረጥ የሚኖርብህም ለዚህ ነው። ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ:- ‘በትምህርት ቤት ጥሩ ውጤት የማመጣው በየትኞቹ የትምህርት ዓይነቶች ነው?’ በአብዛኛው በጣም በምትወዳቸው የትምህርት ዓይነቶች አይደለም? እንዲያውም አንድን ትምህርት ይበልጥ በወደድከው መጠን የዚያኑ ያህል ያንን ትምህርት መማር ያስደስትሃል። አሁን ደግሞ ራስህን እንደሚከተለው በማለት ጠይቅ:- ‘በጣም የምወደው የኤሌክትሮኒክ ጨዋታ የትኛው ነው? ይህ ጨዋታስ ምን ዓይነት ሥነ ምግባር ያስተምረኛል?’
አንድ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታ ጥሩ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ለመወሰን እንዲረዳህ፣ መጫወት የምትፈልገውን የእያንዳንዱን የኤሌክትሮኒክ ጨዋታ ዓላማና ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የምትጠቀምባቸውን ዘዴዎች በአጭሩ ለመጻፍ ሞክር። ስለ ጨዋታው የጻፍካቸውን ነገሮች በዚህ ርዕስ ውስጥ ከተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር አስተያያቸው። ከዚያም የኤሌክትሮኒክ ጨዋታው ጥሩ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ወስን።
አንድን የኤሌክትሮኒክ ጨዋታ ጓደኞችህ ስለተጫወቱት ብቻ ከመጫወት ይልቅ የራስህን ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል ጥንካሬ ይኑርህ። ከሁሉም በላይ ደግሞ “ጌታን ደስ የሚያሰኘውን ፈልጉ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ አድርግ።—ኤፌሶን 5:10
www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask . . .” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች
▪ አንድ ጓደኛህ ዓመጽ ወይም የሥነ ምግባር ብልግና የሚንጸባረቅበት የኤሌክትሮኒክ ጨዋታ እንድትጫወት ቢጋብዝህ ምን ትለዋለህ?
▪ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎችን መጫወት ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ እንቅስቃሴዎች የምታውለውን ጊዜ እንዳይሻማብህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ዓመጽ ወይም የሥነ ምግባር ብልግና የሚታይባቸውን የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች ለመጫወት መምረጥ በራድዮአክቲቭ ዝቃጭ የመጫወት ያህል ነው። ዝቃጩ የሚያደርሰው አደጋ ወዲያውኑ የሚታይ ባይሆንም ውሎ አድሮ ጉዳት ማስከተሉ አይቀርም።
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎችን የምትጫወተው ምን ያህል ነው?
□ አልፎ አልፎ
□ በሳምንት አንዴ
□ በየቀኑ
አንድ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታ እየተጫወትክ ምን ያህል ጊዜ ታሳልፋለህ?
□ ጥቂት ደቂቃዎች
□ አንድ ሰዓት ወይም ከዚያ ላነሰ ጊዜ
□ ከሁለት ሰዓት በላይ
በጣም የምትወደው ምን ዓይነት የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎችን ነው?
□ የመኪና ውድድር
□ ስፖርታዊ ጨዋታዎች
□ የጦር መሣሪያ እንደያዝክ ሆነህ የምትጫወታቸውን
□ ሌላ
መጫወት የለብኝም ብለህ የምታስበውን የኤሌክትሮኒክ ጨዋታ ስም ጻፍ:-
․․․․․․․․․․
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ለወላጆች የተሰጠ ማሳሰቢያ
ቀደም ሲል የቀረበውን ርዕስ ካነበብክ በኋላ በዛሬው ጊዜ ያሉት የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች አንተ ወጣት በነበርክበት ወቅት ከምታውቃቸው ጨዋታዎች በጣም የተለዩ መሆናቸውን ትገነዘብ ይሆናል። ወላጅ እንደመሆንህ መጠን ልጅህ እነዚህ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች ሊያስከትሉ የሚችሉትን አደጋ እንዲያውቅና ከእነዚህ አደጋዎች እንዲጠበቅ መርዳት የምትችለው እንዴት ነው?
የኤሌክትሮኒክ ጨዋታ ኢንዱስትሪን በጥቅሉ ማውገዝ ወይም እንዲህ ያሉ ጌሞች ጊዜ ከማባከን ሌላ ምንም ጥቅም የላቸውም ብሎ በደፈናው መናገር የሚፈይደው ነገር የለም። ሁሉም ጌሞች መጥፎ እንዳልሆኑ አስታውስ። ይሁን እንጂ ሱስ ሊያስይዙና ጊዜ ሊያባክኑ ይችላሉ። በመሆኑም ልጅህ እንዲህ ያሉትን ጨዋታዎች በመጫወት ምን ያህል ጊዜ እንደሚያሳልፍ ለማወቅ ጥረት አድርግ። በተጨማሪም ልጅህ መጫወት የሚወደው የትኞቹን ጨዋታዎች እንደሆነ ለማስተዋል ሞክር። እንዲያውም ልጅህን እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ልትጠይቀው ትችላለህ:-
▪ የክፍል ጓደኞችህ በጣም የሚወዱት የኤሌክትሮኒክ ጨዋታ የትኛውን ነው?
▪ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታው ምን ዓይነት ነው?
▪ ይህ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታ ተወዳጅ የሆነው ለምን ይመስልሃል?
ልጅህ አንተ ከጠበቅኸው በላይ ስለ ኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች እንደሚያውቅ ታስተውል ይሆናል! ምናልባትም አንተ መጥፎ ናቸው የምትላቸውን ጨዋታዎች ተጫውቶ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠመህ ለመቆጣት አትቸኩል። እንዲያውም ይህን አጋጣሚ ልጅህ የማስተዋል ችሎታውን እንዲያዳብር ለመርዳት ልትጠቀምበት ትችላለህ።—ዕብራውያን 5:14 NW
ልጅህ እንዲህ ዓይነት የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎችን መጫወት የሚያስደስተው ለምን እንደሆነ እንዲያስተውል አንዳንድ ጥያቄዎች ጠይቀው። ለምሳሌ ያህል፣ እንዲህ ብለህ ልትጠይቀው ትችላለህ:-
▪ ይህን የኤሌክትሮኒክ ጨዋታ እንድትጫወት ስላልተፈቀደልህ ከጓደኞችህ የተለየህ እንደሆንክ ይሰማሃል?
ቀደም ሲል በቀረበው ርዕስ የመጀመሪያ ገጽ ላይ እንደተገለጸው ወጣቶች አንድን የኤሌክትሮኒክ ጨዋታ የሚጫወቱት ከክፍል ጓደኞቻቸው ጋር የሚያወሩት ነገር ለማግኘት ብለው ሊሆን ይችላል። ልጅህ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታውን የተጫወተበት ምክንያት ይህ ከሆነ፣ ጉዳዮን የምትይዝበት መንገድ ዘግናኝ ዓመጽና የጾታ ብልግና የሚታይበትን ጌም የሚወድ ቢሆን ኖሮ ከምትይዝበት መንገድ የተለየ እንደሚሆን ግልጽ ነው።—ቈላስይስ 4:6
ይሁን እንጂ ከአንድ የኮምፒውተር ጨዋታ ውስጥ ልጅህን በጣም የሚስበው መጥፎ የሆነው ገጽታ ቢሆንስ? አንዳንድ ወጣቶች ቶሎ ብለው በኮምፒውተሩ ላይ የሚያዩት አሰቃቂ ነገር ምንም ተጽዕኖ እንደማያሳድርባቸው ለማሳመን ይጥሩ ይሆናል። ‘ኮምፒውተር ላይ አደረግሁት ማለት በእውንም አደርገዋለሁ ማለት አይደለም’ ይላሉ። የአንተም ልጅ እንዲህ የሚሰማው ከሆነ በገጽ 20 ላይ የተጠቀሰው መዝሙር 11:5 የያዘውን ቁም ነገር እንዲያስተውል እርዳው። በጥቅሱ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው አንድ ሰው የአምላክን ሞገስ እንዲያጣ የሚያደርገው ዓመጸኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ዓመጽን መውደዱም ጭምር ነው። ይህ መመሪያ የጾታ ብልግናን ወይም በአምላክ ቃል ውስጥ የተወገዘን ሌላ መጥፎ ምግባር በተመለከተም ይሠራል።—መዝሙር 97:10
አንዳንድ ተመራማሪዎች የሚከተሉትን ሐሳቦች ያቀርባሉ:-
▪ ልጆች የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎችን እንደ መኝታ ክፍል ባሉ ሌሎች ሰዎች ሊያዩአቸው በማይችሉ ቦታዎች እንዲጫወቱ አትፍቀዱ።
▪ ገደብ አብጁ። (ለምሳሌ ያህል፣ ልጃችሁ የቤት ሥራውን ሳይጨርስ ወይም እራት ሳይበላ አሊያም ደግሞ ሌላ አስፈላጊ ነገር ሳያደርግ ኤሌክትሮኒክ ጨዋታ መጫወት እንደማይችል ልትነግሩት ትችላላችሁ።)
▪ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግን የሚጠይቁ ሌሎች ጨዋታዎች ያላቸውን ጠቀሜታ ጎላ አድርጋችሁ ግለጹላቸው።
▪ ልጆቻችሁ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎችን ሲጫወቱ ተመልከቱ፤ እንዲያውም አንዳንዴ አብራችኋቸው ብትጫወቱ ጥሩ ነው።
እርግጥ ነው፣ መዝናኛን በተመለከተ ልጆችህን በነፃነት መምከር እንድትችል አንተ ራስህ ጥሩ ምሳሌ ሆነህ መገኘት አለብህ። በመሆኑም ‘የምመለከታቸው የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና ፊልሞች ምን ዓይነት ናቸው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ለራስህ ሲሆን አቋምህን የምታላላ ለልጆችህ ጊዜ ግን ጥብቅ ለመሆን የምትሞክር ከሆነ ራስህን እያታለልክ ነው፤ ልጆችህም ሁኔታውን ማወቃቸው አይቀርም!