ጥሩ ምክር ለማግኘት ጥረት አድርጉ
1
ጥሩ ምክር ለማግኘት ጥረት አድርጉ
አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ወላጆች ለመጀመሪያ ጊዜ ልጅ ወልደው ሲያቅፉ የተዘበራረቀ ስሜት ሊሰማቸው ይችላል። በብሪታንያ የሚኖር ብሬት የተባለ አንድ አባት “ጥልቅ የሆነ ደስታና የመገረም ስሜት ተሰምቶኝ ነበር” በማለት ይናገራል። “ሆኖም ከባድ ኃላፊነት እንደተጣለብኝና ይህንንም ለመወጣት ዝግጁ እንዳልሆንኩ ተሰምቶኝ ነበር” ብሏል። በአርጀንቲና የምትኖር ሞኒካ የተባለች አንዲት እናት ደግሞ “ትንሿ ልጄ የሚያስፈልጓትን ነገሮች ማሟላት እችል ይሆን? የሚለው ጥያቄ አስጨንቆኝ ነበር። ‘ስታድግ ኃላፊነት የሚሰማት ሰው እንድትሆን የሚያስፈልጋትን ሥልጠና መስጠት እችል ይሆን?’ ብዬ አሰብኩ” ትላለች።
የእነዚህን ወላጆች ደስታና ስጋት ትረዳላቸዋለህ? በእርግጥም ማንኛውም ሰው ከሚያከናውናቸው በጣም አድካሚና ትዕግሥት አስጨራሽ ቢሆኑም የኋላ ኋላ ግን የሚያረኩ ብሎም የሚክሱ ተግባሮች አንዱ ልጅ ማሳደግ ነው። አንድ አባት እንደተናገረው “ልጃችሁን ለማሳደግ አጋጣሚ የምታገኙት አንድ ጊዜ ብቻ ነው።” ወላጆች የልጆቻቸውን ጤንነት በመጠበቅና ደስተኞች እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ከሚጫወቱት ከፍተኛ ሚና አንጻር፣ ጥሩ ወላጅ ለመሆን የሚረዳችሁን አስተማማኝ ምክር ማግኘት በጣም እንደሚያስፈልጋችሁ ይሰማችሁ ይሆናል።
ተፈታታኝ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሁሉም ሰው ስለ ልጆች አስተዳደግ ምክር መስጠት የሚችል ይመስላል። ቀደም ባሉት ጊዜያት አዳዲስ ወላጆች ልጆቻቸውን የሚያሳድጉት የወላጆቻቸውን ምሳሌ በመከተል አሊያም ደግሞ በሃይማኖታዊ እምነታቸው መሠረት ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን በበርካታ አገሮች የቤተሰብ ትስስር እየላላ ሲሆን ሃይማኖትም ኃይሉን እያጣ ነው። በመሆኑም ብዙ ወላጆች የልጆችን አስተዳደግ በተመለከተ ምክር የሚሹት በዚህ መስክ ከተሰማሩ ባለሙያዎች ነው። እነዚህ ባለሙያዎች ከሚሰጧቸው ምክሮች አንዳንዶቹ ትክክለኛ በሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። በሌሎች ሁኔታዎች ግን የባለሞያዎቹ ምክር እርስ በርሱ የሚጋጭ ከመሆኑም በላይ ብዙም ሳይቆይ ጊዜ እንዳለፈበት ተደርጎ ሊታይ ይችላል።
መፍትሔው ምንድን ነው? ከማንም በላይ ስለ ልጆች አስተዳደግ የሚያውቀው አካል የሚሰጠውን ምክር ተቀበሉ፤ እሱም የሰብዓዊ ሕይወት ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 17:26-28) የይሖዋ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ ወላጅ ለመሆን የሚረዳችሁን ቀጥተኛ ምክርና ተግባራዊ ልታደርጓቸው የምትችሏቸውን ምሳሌዎች ይዟል። ይሖዋ “እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ” በማለት ቃል ገብቷል።—መዝሙር 32:8
አምላክ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ደስተኛ እንዲሆኑ አድርገው ለማሳደግ የሚረዳቸው ምን ምክር ይሰጣቸዋል?
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ።”—ምሳሌ 3:5