በእርግጥ ይህን ያህል ዓመት ኖረዋል?
በእርግጥ ይህን ያህል ዓመት ኖረዋል?
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው አዳም 930 ዓመት እንዲሁም ሴት 912 ዓመት ኖረዋል። ማቱሳላ ደግሞ 969 ዓመት የኖረ ሲሆን አንድ ሺህ ሊሞላ የቀረው 31 ዓመት ብቻ ነበር! (ዘፍጥረት 5:5, 8, 27) በዚያ ዘመን የነበረው የአንድ ዓመት ርዝማኔ ከዛሬው ጋር እኩል ነው ወይስ ያንሳል? ምናልባት አንዳንዶች እንደሚሉት የዚያ ዘመን አንድ ዓመት በዛሬው ጊዜ አንድ ወር ከምንለው ጋር እኩል ይሆን?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙት የዚያ ዘመን ዓመታት ርዝማኔ ከዛሬዎቹ ጋር ተመሳሳይ ነው። እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ ልብ በል። የዚያ ዘመን አንድ ዓመት ርዝመት በዛሬው ጊዜ አንድ ወር ከምንለው ጋር እኩል ቢሆን ኖሮ ቀጥሎ የተገለጹት ሰዎች የልጅ አባት የሆኑት መውለድ በማይችሉበት ዕድሜ ላይ ይሆን ነበር። ለምሳሌ ያህል ቃይናን ልጅ የወለደው ስድስት ዓመት ሳይሞላው ሔኖክና መላልኤል ደግሞ በአምስት ዓመታቸው ነበር ማለት ነው።—ዘፍጥረት 5:12, 15, 21
ከዚህም በላይ የጥንት ሰዎች ታሪካቸው የተገለጸው ቀን፣ ወርና ዓመት እየተጠቀሰ ነው። (ዘፍጥረት 1:14-16፤ 8:13) እንዲያውም ስለ ኖኅ የሚናገረው ዝርዝር ታሪክ አንድ ወር ምን ያህል ርዝመት እንደነበረው ለይተን እንድናውቅ ይረዳናል። ዘፍጥረት 7:11, 24ን ከዘፍጥረት 8:3, 4 ጋር ስናነጻጽረው ከሁለተኛው ወር 17ኛ ቀን አንስቶ እስከ ሰባተኛው ወር 17ኛ ቀን ድረስ ያለው አምስት ወር ወደ ቀን ሲለወጥ 150 ቀን መሆኑን እንረዳለን። ከዚህ መረዳት እንደምንችለው ኖኅ አንድ ወር ያለው 30 ቀናትን ነው፤ አሥራ ሁለት ወራት ደግሞ ተደምረው አንድ ዓመት ይሆናሉ።—ዘፍጥረት 8:5-13 *
ይሁን እንጂ ሰዎች 900 ዓመትና ከዚያ በላይ እንዴት ሊኖሩ ቻሉ? መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ሰዎችን የፈጠረው ለዘላለም እንዲኖሩ እንደሆነና አለፍጽምናና ሞት ወደ ሰብዓዊው ቤተሰብ የገባው በአዳም ኃጢአት ምክንያት መሆኑን ይነግረናል። (ዘፍጥረት 2:17፤ 3:17-19፤ ሮሜ 5:12) ከጥፋት ውኃ በፊት ይኖሩ የነበሩት ሰዎች በዛሬው ጊዜ ከምንገኘው ይልቅ ለፍጽምና ቅርብ ስለነበሩ ረጅም ዓመት ሊኖሩ የቻሉበት ዋነኛ ምክንያት ይህ መሆኑ አያጠራጥርም። ለምሳሌ ያህል፣ ማቱሳላ የኖረው ከአዳም ሰባት ትውልድ በኋላ ነው።—ሉቃስ 3:37, 38
ይሁን እንጂ በቅርቡ ይሖዋ አምላክ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ባፈሰሰው ደም የሚያምኑ ሰዎች በአዳም ምክንያት የመጣባቸው ኃጢአት ሙሉ በሙሉ እንዲወገድላቸው ያደርጋል። “የኀጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው።” (ሮሜ 6:23) አዎን፣ ማቱሳላ የኖረበት 969 ዓመት በጣም አጭር የሚመስልበት ጊዜ ቀርቧል!
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.4 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 2 ገጽ 1214ን ተመልከት።
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ግራፍ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
1000
ማቱሳላ
አዳም
ሴት
900
800
700
600
500
400
300
200
100
በዛሬው ጊዜ የሰው አማካይ ዕድሜ