በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ባለጸጋ ለመሆን ቆርጦ መነሳት ሊጎዳህ የሚችለው እንዴት ነው?

ባለጸጋ ለመሆን ቆርጦ መነሳት ሊጎዳህ የሚችለው እንዴት ነው?

ባለጸጋ ለመሆን ቆርጦ መነሳት ሊጎዳህ የሚችለው እንዴት ነው?

ከ850 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ሕዝብ በረሃብ አለንጋ እየተገረፈ ባለበት በዚህ ዓለም ውስጥ በጣም ሀብታም መሆን ችግር ሊያስከትል ይችላል ብሎ ማሰብ ይከብድ ይሆናል። ይሁን እንጂ ባለፈው ርዕሰ ትምህርት ላይ የተጠቀሰው ጥቅስ ጎጂ እንደሆነ ያስጠነቀቀው ገንዘብን ወይም ሀብትን ሳይሆን የገንዘብ ፍቅርን እና ባለጸጋ ለመሆን ቆርጦ መነሳትን እንደሆነ ልብ ብለሃል? ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ዋነኛ ግባቸው ሀብታም መሆንና ገንዘብ የሚገዛቸውን ነገሮች ሁሉ ማግኘት በሚሆንበት ጊዜ ምን ሊያጋጥም ይችላል? እስቲ በመጀመሪያ ይህ ዓይነቱ አካሄድ እንደዚህ ባሉት ሰዎች ልጆች ላይ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ እንመልከት።

በልጆች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ

በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር አንድ ልጅ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ በቴሌቪዥን የሚተላለፉ 40,000 የንግድ ማስታወቂያዎችን እንደሚመለከት ይገመታል። በዚህ ላይ ደግሞ ልጆች በሱቆችና በጓደኞቻቸው ቤቶች ውስጥ የሚያዩአቸውን የቪዲዮ ጨዋታዎች፣ ዘመናዊ የሙዚቃ ማጫወቻዎች፣ የኮምፒውተር ፕሮግራሞችና በታዋቂ ዲዛይነሮች የተዘጋጁ በውድ ዋጋ የሚሸጡ ፋሽን ልብሶች እንዲሁም ከዚህ ጋር በተያያዘ ለወላጆቻቸው የሚያቀርቧቸውን ጥያቄዎች ለማሰብ ሞክር። አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው የፈለጉትን ሁሉ ያሟሉላቸዋል። ለምን?

ወላጆች፣ እነርሱ ራሳቸው ልጆች ሳሉ በቅንጦት ስላላደጉ ልጆቻቸው ምንም ነገር እንደቀረባቸው ሳይሰማቸው እንዲያድጉ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። ሌሎች ወላጆች ደግሞ ልጆቹ የፈለጉትን ነገር ሁሉ ለማሟላት ፈቃደኛ ካልሆኑ ልጆቻቸው እንዳይጠሏቸው ይፈራሉ። በቦልደር ከተማ ኮሎራዶ፣ ዩ ኤስ ኤ የሚገኙ ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው ወላጆች ዘወትር እየተገናኙ የመፍትሔ ሐሳቦችን የሚለዋወጡበትን ማኅበር ከመሠረቱት ሰዎች አንዷ፣ ወላጆች “የልጆቻቸው የቅርብ ጓደኛ ለመሆንና ልጆቹ ተደስተው ለማየት ይፈልጋሉ” በማለት ተናግረዋል። ሌሎች ወላጆች ከመጠን በላይ በሥራ ተጠምደው ከልጆቻቸው ጋር ለመሆን ባለመቻላቸው ይህን ሁኔታ ለልጆቻቸው ብዙ ስጦታ በመስጠት ለማካካስ ይሞክራሉ። ከዚህም ሌላ ሳምንቱን ሙሉ በሥራ ተወጥረው የቆዩ ወላጆች፣ ልጆቹ ለሚያቀርቡት ጥያቄ “አይሆንም” የሚል መልስ ቢሰጡ ይህን ተከትሎ የሚመጣው ንዝንዝ ስለሚታያቸው ልጆቹ የፈለጉትን ገዝተው መገላገል እንደሚሻል ይሰማቸዋል።

ይሁን እንጂ ልጆቻቸው የጠየቁትን ሁሉ የሚሰጡ ወላጆች፣ ልጆቻቸውን እየጠቀሟቸው ነው ወይስ እየጎዷቸው? የሚገርመው ነገር ከተሞክሮ መመልከት እንደሚቻለው ተሞላቅቀው ያደጉ ልጆች አባታቸውንና እናታቸውን ይበልጥ በመውደድ ፈንታ ምስጋና ቢስ ይሆናሉ። በጣም ለምነው ላገኙት ስጦታም እንኳን አድናቂዎች አይደሉም። የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑ አንዲት ሴት “ልጆች የጠየቁትን ሁሉ ወዲያውኑ ሲያገኙ፣ በብዙ ልመና ያገኙትን ነገር አብዛኛውን ጊዜ ከሁለት ሳምንት በኋላ እንደሚጥሉት ተመልክቻለሁ” ብለዋል።

ተሞላቅቀው ያደጉ ልጆች በኋላ ላይ ምን ይሆናሉ? ኒውስዊክ መጽሔት በገለጸው መሠረት ጥናቶች እንደሚያሳዩት እንደነዚህ ያሉ ልጆች ካደጉ በኋላ “የኑሮን ውጣ ውረድ ለመቋቋም የማይችሉ” ይሆናሉ። የሚፈልጉትን ነገር ለማግኘት ተግቶ መሥራትን ስላልተማሩ አብዛኞቹ በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታቸውና በትዳራቸው ውስጥ ስኬታማ መሆን ያቅታቸዋል፤ ከዚያ በኋላም በገንዘብ ረገድ የወላጆቻቸው ጥገኛ ሆነው ይቀራሉ። በተጨማሪም ለስጋትና ለመንፈስ ጭንቀት የተጋለጡ ሊሆኑ ይችላሉ።

ከዚህ ለመመልከት እንደምንችለው የሚያስፈልጋቸውን ነገር የሚነፈጉት ተሞላቅቀው ያደጉ ልጆች ናቸው። የሥራን ጥቅም የመማርም ሆነ ለራሳቸው ጥሩ ግምት እንዲኖራቸው የማድረግ አጋጣሚ ተነፍጓቸዋል፤ እንዲሁም አስተዳደጋቸው ባሏቸው ጠንካራ ውስጣዊ ባሕርያት መተማመን እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል። የሥነ አእምሮ ሐኪም የሆኑት ጄሲ ኦኔል የተባሉ ሴት “ልጆች የፈለጉትን ነገር በፈለጉት ጊዜ ማግኘት እንደሚችሉ የምታስተምሯቸው ከሆነ ሕይወታቸው በሐዘን የተሞላ እንዲሆን መሠረት እየጣላችሁ ነው” በማለት አስጠንቅቀዋል።

በአዋቂዎች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ

ባለትዳር ከሆናችሁ “የቱንም ያህል ረዥም ዘመን አብራችሁ ብትኖሩ ወይም ምንም ያህል ገንዘብ ቢኖራችሁ፣ በገንዘብ ምክንያት ልትጋጩ ትችላላችሁ” በማለት ሳይኮሎጂ ቱደይ የተሰኘው መጽሔት ዘግቧል። መጽሔቱ አክሎም “አንድ ባልና ሚስት በገንዘብ ረገድ የሚገጥማቸውን አለመግባባትና ቅሬታ የሚፈቱበት መንገድ ትዳራቸው ዘላቂ መሆን አለመሆኑን ሊጠቁም ይችላል” ብሏል። ገንዘብንና ቁሳዊ ነገሮችን ከፍ አድርገው የሚመለከቱ ባልና ሚስት ትዳራቸው ለችግር የተጋለጠ እንደሆነ ግልጽ ነው። በእርግጥም 90 በመቶ በሚሆኑት ፍቺዎች ውስጥ ጎልቶ የሚታየው ችግር ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ጭቅጭቅ እንደሆነ ይገመታል።

ሆኖም ባልና ሚስቱ አብረው ቢኖሩም እንኳ በገንዘብና ገንዘብ በሚያስገኘው የቅንጦት ኑሮ ላይ የሚያተኩሩ ከሆነ ጥሩ ግንኙነት ላይኖራቸው ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ዕዳ ያለባቸው ባልና ሚስት ላጋጠማቸው ገንዘብ ነክ ጭንቀት አንዱ ሌላውን ተጠያቂ በማድረግ በቀላሉ የሚቆጡና ግልፍተኞች ሊሆኑ ይችላሉ። በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ ባልና ሚስቱ ትኩረታቸው ሁሉ በግል ንብረቶቻቸው ላይ ስለሚሆን ከትዳር ጓደኛቸው ጋር የሚያሳልፉትና የሚጫወቱበት ጊዜ ሊያጡ ይችላሉ። አንደኛው ወገን ውድ ዕቃ ገዝቶ ከትዳር ጓደኛው በሚደብቅበት ጊዜስ ምን ያጋጥማል? እንዲህ ማድረግ አንዳቸው ለሌላው ግልጽ አለመሆንን፣ የጥፋተኝነት ስሜትና አለመተማመን የሚያስከትል ሲሆን እነዚህ ነገሮች ደግሞ ትዳሩን ይሸረሽሩታል።

ባለትዳር ሆኑም አልሆኑ፣ አንዳንድ ሰዎች ሕይወታቸውን ቃል በቃል ለፍቅረ ነዋይ ሰውተዋል። በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች የምዕራባውያንን የቅንጦት አኗኗር ለመከተል የሚያደርጉት ጥረት ባስከተለባቸው ውጥረት ምክንያት ራሳቸውን የመግደል ሙከራ አድርገዋል። በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር አንድ ሰው ሚስቱን፣ የ12 ዓመት ወንድ ልጁንና በመጨረሻም ራሱን የገደለ ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ ገንዘብ ነክ ችግር ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

እርግጥ ነው፣ ብዙዎቹ ሰዎች ሀብትን በማሳደድ ምክንያት አይሞቱም። ሆኖም ባለጸጋ ለመሆን በሚያደርጉት ጥረት ተውጠው በሕይወት ውስጥ እውነተኛ እርካታ ሳያገኙ እንዲሁ ሲደክሙ ይኖራሉ። እንደዚሁም ከሥራቸው ወይም ከገንዘብ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥማቸው ውጥረት፣ መሥራት እስኪያቅታቸው ድረስ እንዲጨነቁና እንቅልፍ እንዲያጡ እንዲሁም በከባድ ራስ ምታት ወይም የሆድ ዕቃ ቁስለት እንዲሠቃዩ ካደረጋቸው በሕይወታቸው ደስተኞች አይሆኑም፤ እነዚህ የጤና ችግሮች የአንድን ሰው ዕድሜ ሊያሳጥሩት ይችላሉ። ደግሞም አንድ ሰው ቅድሚያ በሚሰጣቸው ነገሮች ረገድ ለውጥ ማድረግ እንዳለበት የኋላ ኋላ ቢገነዘብ እንኳ ሁኔታው ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ እንደሚባለው ሊሆንበት ይችላል። የትዳር ጓደኛውን አመኔታ መልሶ ላያገኝ ይችላል፤ እንዲሁም ልጆቹ ስሜታቸው ተጎድቶና የራሱ ጤንነትም ተቃውሶ ይሆናል። ምናልባት ከእነዚህ ጉዳቶች ውስጥ አንዳንዶቹን መጠገን የሚቻል ቢሆንም እንኳ ይህን ለማድረግ በጣም ብዙ ልፋት ይጠይቃል። በእርግጥም እንዲህ ዓይነት ሰዎች ‘ራሳቸውን በብዙ ሥቃይ ወግተዋል።’—1 ጢሞቴዎስ 6:10

አንተ የምትፈልገው ምንድን ነው?

አብዛኞቹ ሰዎች ደስተኛ ቤተሰብ፣ ጥሩ ጤንነት፣ ትርጉም ያለው ሥራና ያለ ችግር ለመኖር የሚያስችል በቂ ገንዘብ እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ። እነዚህን አራት ነገሮች በሙሉ ለማግኘት ሚዛንን መጠበቅ ያስፈልጋል፤ አንድ ሰው ዋነኛ ትኩረቱ በገንዘብ ላይ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ይህ ሚዛን ይዛባል። ብዙ ሰዎች ወደ ትክክለኛው ጎዳና ለመመለስ አነስተኛ ክፍያ የሚያስገኝ ሥራ መያዝ፣ አነስ ባለ ቤት ውስጥ መኖር፣ መኪና አለመያዝ ወይም በማኅበረሰቡ ውስጥ ቀደም ሲል ከነበራቸው ባነሰ ደረጃ መኖር ያስፈልጋቸው ይሆናል። ታዲያ ላቅ ያሉ ሥነ ምግባራዊ እሴቶች እንዲኖሯቸው ሲሉ የቅንጦት ኑሯቸውን መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኞች የሚሆኑት ስንቶቹ ናቸው? አንዲት ሴት ‘እነዚህ ሁሉ የቅንጦት ዕቃዎች እንደማያስፈልጉኝ አውቃለሁ፤ ይሁን እንጂ ያለ እነርሱ መኖር በጣም ይከብደኛል!’ በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች። ሌሎች ደግሞ የቅንጦት ኑሯቸውን ለመተው ቢፈልጉም ይህን ለማድረግ የመጀመሪያዎቹ መሆን አይፈልጉም።

አንተስ እንዴት ነህ? ገንዘብና ቁሳዊ ነገሮች ተገቢ ቦታቸውን እንዲይዙ ማድረግ የምትችልበት መንገድ አግኝተህ ከሆነ ልትመሰገን ይገባሃል። በሌላ በኩል ግን፣ የኑሮ ደረጃህ ብዙ ጊዜ የሚጠይቅ በመሆኑ ምክንያት ይህን ርዕሰ ትምህርት የምታነብበው በጥድፊያ ነው? አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ደኅንነታቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ቁሳዊ ነገሮችን መቀነስ እንዳለባቸው ከሚሰማቸው ሰዎች መካከል ነህ? እንግዲያውስ ፍቅረ ነዋይ በቤተሰብህ ውስጥ ጉዳት የሚያስከትልበት አጋጣሚ ከመፈጠሩ በፊት በቁርጠኝነት እርምጃ ውሰድ። በዚህ ገጽ ላይ ያለው ሣጥን ቁሳዊ ነገሮችን መቀነስ ስለምትችልበት መንገድ ጥቂት የመንደርደሪያ ሐሳቦችን ያቀርባል።

ለቁሳዊ ነገሮች ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ ለእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ጥቅም ይኖረዋል። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች ሌላም የሚያሳስባቸው ነገር አለ፤ ይኸውም ቁሳዊ ነገሮች ከአምላክ ጋር ባላቸው ዝምድና ውስጥ ጣልቃ እንዲገቡባቸው አይፈልጉም። ፍቅረ ነዋይ የአንድን ሰው መንፈሳዊ ጤንነት አደጋ ላይ ሊጥለው የሚችለው እንዴት ነው? ይህ እንዳይሆን መከላከል የሚቻለውስ እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ይህን ያብራራል።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ተሞላቅቀው ያደጉ ልጆች ብዙውን ጊዜ ምስጋና ቢሶች ናቸው፤ ለምነው ያገኟቸውን ዕቃዎችም ብዙም ሳይቆዩ ይጥሏቸዋል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ሚዛንን ጠብቆ መኖር

ቁሳዊ ሀብትን ለመቀነስ ቆራጥ መሆንና ጥንቃቄ የተሞላበት ዕቅድ ማውጣት ያስፈልጋል። አንዳንዶች በዚህ ረገድ ጠቃሚ ሆነው ያገኟቸው የመፍትሔ ሐሳቦች ከዚህ በታች ቀርበዋል።

የግል ሁኔታህን ገምግም። መግዛትህን ልታቆም ወይም ልታስወግዳቸው የምትችላቸው ነገሮች አሉ? ሳያስፈልግህ ልብሶችና የቤት ዕቃዎችን መግዛት ልትተው ትችላለህ? ለስላሳ መጠጦችን ወይም የታሸገ ውኃ አሊያም የሙዚቃ ካሴቶችና ሲዲዎችን መግዛትህን መቀነስ ትችላለህ?

ለተወሰነ ጊዜ ኑሮህን በማቅለል ሞክረው። ኑሮህን ይበልጥ ማቅለሉ የተሻለ መሆኑን ከተጠራጠርክ ለስድስት ወር ወይም ለአንድ ዓመት ያህል እንዲህ በማድረግ ለምን አትሞክረውም? ገንዘብና ንብረት በማሳደድ የጠፋው ጊዜ በእርግጥ ይበልጥ ደስተኛ አድርጎህ ወይም ደስታህን ቀንሶብህ እንደሆነ አረጋግጥ።

ኑሮን ስለማቅለል ቤተሰብህ በሚያደርገው ውይይት ውስጥ ልጆችህም እንዲገቡበት አድርግ። እንዲህ ከሆነ እነርሱም ድጋፍ ሊሰጡህ ይችላሉ፤ ደግሞም አንድ ነገር እንዲገዛላቸው ጠይቀውህ መግዛት እንደማትችል መግለጽ በሚኖርብህ ወቅት መልስ መስጠት ቀላል ይሆንልሃል።

ለልጆችህ መጠነኛ የኪስ ገንዘብ ስለ መስጠት አስብበት። ልጆቹ የተሰጣቸውን ገንዘብ አጠራቅመው የሚፈልጉትን ለመግዛት ወይም ደግሞ የፈለጉትን ነገር ላለመግዛት ይወስኑ ይሆናል፤ በዚህ መንገድ ትዕግሥትንና ያላቸውን ነገር በአድናቆት መያዝን ይማራሉ። በተጨማሪም እንዴት ውሳኔ ማድረግ እንደሚቻል ይሠለጥናሉ።

በቁጠባ ለመኖር የሚያስችሉህን ዘዴዎች ተማር። የምትገዛውን ነገር ዋጋ አመዛዝነህ በቅናሽ መግዛት ልመድ። ባጀት አውጣ። ወደ ሥራ ስትሄድም ሆነ ልጆችህን ትምህርት ቤት ስታደርስ ከተለያዩ ሰዎች ጋር አንድ ላይ ተሰባስቦ በአንድ መኪና የመሄድ ልማድ አዳብር። በኤሌክትሪክ ወይም በጋዝ አጠቃቀምህ ረገድ ቆጣቢ ሁን። መጻሕፍትን ከመግዛት ይልቅ ከቤተ መጻሕፍት ተዋስ። የሞባይል ስልክ ካርድ ፍጆታህን ለመቀነስ ሞክር። አላስፈላጊ የትራንስፖርት ወጪዎችን ቀንስ (የምትችል ከሆነ በእግርህ ተጓዝ)። ቤት ተከራይተህ የምትኖር ከሆነ በሥራ ቦታህ አካባቢ ለመከራየት ሞክር። ልጆችህ ለቤትህ ቅርብ በሆነ ትምህርት ቤት እንዲማሩ አድርግ። የምግብ ሸቀጦችን በትንሽ በትንሹ ከመግዛት ይልቅ በርከት አድርገህ ግዛ። አዘውትረህ ከቤት ውጭ ከመመገብ ይልቅ ቤትህ ምግብ የማብሰል ልማድ ይኑርህ። ፍራፍሬዎችን ጨምሮ ለሰውነት ጠቃሚ የሆኑ ምግቦችን በመመገብ የሕክምና ወጪዎችህን መቀነስ ትችላለህ።

ቀለል ያለ አኗኗር በመምራት ያተረፍከውን ጊዜና ጉልበት ጠቃሚ ለሆነ ነገር አውለው። ኑሮህን ቀላል ያደረግኸው ብዙ ቁሳዊ ነገሮች እንዲኖሩህ ስላልፈለግህ ብቻ ሳይሆን ከቤተሰብህና ከጓደኞችህ ጋር ጊዜ እንደማሳለፍ ለመሳሰሉት በሕይወትህ ውስጥ ይበልጥ ቅድሚያ ለምትሰጣቸው ጉዳዮች ጊዜ ለማግኘት እንደሆነ አስታውስ። ታዲያ ይህን እያደረግህ ነው?

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ባለጸጋ ለመሆን ቆርጦ መነሳት በጋብቻ ውስጥ ውጥረት እንዲሰፍን ሊያደርግ ይችላል