ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
▪ “ከባለትዳሮች መካከል ግማሽ የሚያህሉት ‘በገንዘብ ጉዳይ እምነት እንደሚያጎድሉ፣’ ማለትም ስላወጡት ወጪ ለትዳር ጓደኛቸው እንደሚዋሹ አምነዋል።” —ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል፣ ዩናይትድ ስቴትስ
▪ “ከግሪክ መሬት ውስጥ 84 በመቶ የሚሆነው በረሃ የመሆን አደጋ የተጋረጠበት ሲሆን 8 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ቀድሞውንም ደርቆአል።”—ካቲሜሪኒ (የእንግሊዝኛ እትም)፣ ግሪክ
▪ በቫኑዋቱ፣ ኦሺኒያ በምትገኘው የቴግዋ ደሴት ላይ ያለችው ላቴኡ የምትባል ትንሽ መንደር በአየር ንብረት መለወጥ ሳቢያ የተለቀቀች የመጀመሪያዋ መንደር ሳትሆን አትቀርም፤ የመንደሯ ነዋሪዎች በሌላ አካባቢ ሰፍረዋል። በመንደሩ ያሉ ቤቶች በተደጋጋሚ “በድንገተኛ ማዕበልና በኃይለኛ ሞገድ የተነሳ ሲጥለቀለቁ ቆይተው ነበር።”—ቫኑዋቱ ኒውስ፣ ቫኑዋቱ
የመቶ ዓመት የዕድሜ ባለጠጎች እየበዙ ነው
ባለንበት ጊዜ 100 ዓመት የሆናቸው የዕድሜ ባለጠጋዎችን ማየት የተለመደ እንደሆነ ኒው ሳይንቲስት መጽሔት ይናገራል። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ 200,000 የሚያህሉ የ100 ዓመት የዕድሜ ባለጠጎች አሉ። በተጨማሪም ይህ መጽሔት እንደሚናገረው ከሆነ ከእነዚህ አረጋውያን መካከል 66ቱ 110 ዓመት ሆኗቸዋል። ኒው ሳይንቲስት መጽሔት ሰዎች ይህን ያህል ረዥም ዕድሜ እንደኖሩ ማረጋገጥ አንዳንድ ጊዜ አስቸጋሪ መሆኑን ቢያምንም “አስተማማኝ መዝገብ ባለመኖሩ በአሁኑ ጊዜ ከ100 ዓመት በላይ የኖሩት ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር 450ም ሊደርስ እንደሚችል” ይናገራል።
ምስጢራዊው ገዳይ ታወቀ
“በአቴና በሚገኝ አንድ ጥንታዊ የመቃብር ጉድጓድ ውስጥ ከተገኘ ጥርስ ላይ የተወሰደ ዲ ኤን ኤ ምርመራ” በዘመኑ የነበረውን ገዳይ በሽታ ለማወቅ እንደረዳ የካናዳው ማክሊንስ መጽሔት ገልጿል። ግሪካዊው ጸሐፊ ቱሲዴዲስ፣ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ፔሎፖኔዥያን ዎር በተሰኘ መጽሐፉ ላይ በ430 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ በአቴንስ አንድ ወረርሽኝ ተከስቶ ብዙ ሕዝብ እንደፈጀ ገልጿል። ይህም ተቀናቃኟ የስፓርታ ከተማ ድል እንድትቀዳጅ እንደረዳት ጠቅሷል። ቱሲዴዲስ የሰጠው ማብራሪያ የወረርሽኙን ምንነት ለማወቅ የሚያስችል አልነበረም። አሁን ግን ተመራማሪዎች፣ የሕመም መንስኤ የሆኑ ተሕዋስያንን በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት በሕይወት ሊያቆይ በሚችለው የጥርስ ውስጠኛ ክፍል ላይ ያደረጉት ምርመራ ምስጢራዊው ገዳይ የአንጀት ተስቦ መሆኑን ለማወቅ እንዳስቻላቸው ተዘግቧል።
ግመል ጋላቢ ሮቦቶች
የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች በፋርስ ባሕረ ሰላጤ አካባቢ በሚገኙ አገሮች በሚዘወተረው የግመል ግልቢያ ውድድር ላይ ልጆች በጋላቢነት እንዲሳተፉ መደረጉን በመንቀፋቸው ይህ ስፖርት ሥጋት ላይ ወድቆ ነበር። ሆኖም ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ግመሎቹ በጥሩ ፍጥነት እንዲጋልቡ ከተፈለገ ጋላቢዎቹ ክብደታቸው ከ27 ኪሎ ግራም በታች መሆን አለበት፤ ይህ ደግሞ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶችም እንኳ ከውድድሩ ውጪ እንዲሆኑ ያደርጋል። ታዲያ መፍትሔው ምንድን ነው? መፍትሔው ሮቦቶች እንዲጋልቡ ማድረግ ነው። በስዊዘርላንድ የሚገኙ የሮቦት ንድፍ አውጪዎች 26 ኪሎ ግራም የሚመዝንና ለየት ባለ የግመል ኮርቻ ላይ መፈናጠጥ የሚችል በሪሞት ኮንትሮል የሚሠራ ሮቦት ሠርተዋል። ግመሉ እንዳይደነብር ሲባል ሮቦቱ የሰው ቅርጽና ድምፅ እንዲኖረው ተደርጓል። በተጨማሪም ሮቦቱ ዘንበል ማለት፣ እንዳይወድቅ ሚዛኑን መጠበቅ፣ አለንጋ መጠቀምና መጋለብ እንዲችል ተደርጎ ተሠርቷል። የግመል ባለቤቶች ሮቦቶቹ ሲጋልቡ ለማየት ጓጉተዋል።
ከ2,000 ዓመታት በኋላ የበቀለ ዘር
በመካከለኛው ዘመን የይሁዳን ምድር የወረሩት የመስቀል ጦረኞች በውበቱ፣ በጥላ ሰጪነቱና በመድኃኒትነቱ ተወዳጅ የነበረውን የጥንቷን ይሁዳ የተምር ዛፍ አጥፍተውት ነበር። አሁን ግን “እስራኤላውያን ዶክተሮችና ሳይንቲስቶች 2,000 ዓመታት ያስቆጠረ የተምር ዘር ለማብቀል ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸዋል” በማለት ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል። “ማቱሳላ የሚል ቅጽል ስም የተሰጠው ይህ ዘር የተገኘው” ሮማውያን በ73 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ድል አድርገው በያዙት ከዓለት ውስጥ ተቦርቡሮ በተሠራ “ማሳዳ የተባለ ምሽግ በተካሄደ ቁፋሮ ነበር።” ዘሩን ያበቀሉት የበረሃማ አካባቢዎች የግብርና ባለሞያ የሆኑት ኢላን ሶለዌ የተባሉ ሴት ሲሆኑ እሳቸው በሰጡት አስተያየት መሠረት ችግኙ አድጎ እስኪያፈራ ድረስ ዓመታት ይፈጃል፤ ይህ የሚሆነውም ችግኙ ሴቴ ከሆነ ብቻ ነው። “ችግኙ ወንዴ ከሆነ ግን ብርቅ ግኝት ብቻ ሆኖ ይቀራል” ብለዋል።