ወደ ቼርኖቤል ያደረግነው የአንድ ቀን ጉዞ
ወደ ቼርኖቤል ያደረግነው የአንድ ቀን ጉዞ
ዩክሬን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
ከ20 ዓመታት በፊት በቼርኖቤል የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ላይ የደረሰው አደጋ ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ ነው። በሚያዝያ 26, 1986 በጣቢያው ካሉት አራት የኑክሌር ኃይል ማመንጫዎች መካከል ከአንደኛው የኑክሌር ጨረር አፈትልኮ ወጣ። አብዛኛውን ጊዜ፣ ሰው ሠራሽም ሆኑ የተፈጥሮ አደጋዎች ከተከሰቱ በኋላ አካባቢውን ማጽዳትና መልሶ መገንባት ይቻላል። በቼርኖቤል የደረሰው አደጋ ግን ቶሎ ሊወገድ የማይችል ብክለት ትቶ አልፏል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኃይል ማመንጫው አካባቢ በሚገኙ ከተሞች ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ጥለው የሄዱትን ቤት ለመጎብኘት አንዳንዴም ከጓደኞቻቸውና ከዘመዶቻቸው ጋር ሆነው በየዓመቱ ግንቦት 9 ላይ ወደዚያ ይጓዛሉ። እንዲሁም ለቀብር የሚሄዱባቸው ጊዜያትም አሉ። ሳይንቲስቶችም ጨረሩ ያስከተለውን ጉዳት ለማጥናት አካባቢውን ይጎበኛሉ። ከዚህ በተጨማሪ በዩክሬን የሚገኙ አስጎብኚ ድርጅቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አካባቢውን ለአንድ ቀን የማስጎብኘት ሥራ ጀምረዋል።
በሰኔ ወር 2005 ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ በመጀመሪያ ገጹ ላይ ያወጣው ርዕስ በፕሪፔት ከተማ “በአስጎብኚዎች መሪነት” ስለተደረጉ አጭርና “በጤና ላይ ጉዳት የማያስከትሉ” ጉብኝቶች ገልጾ ነበር። * ፕሪፔት 45,000 ገደማ ሰዎች የሚኖሩባት ከኑክሌር ኃይል ማመንጫው 3 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ስትሆን የተቆረቆረችው በ1970ዎቹ ነበር። ይሁን እንጂ በኑክሌር ጣቢያው ከደረሰው አደጋ በኋላ በአቅራቢያው ያሉ ብዙ ከተሞች እንደተተዉ ሁሉ እርሷም ተመሳሳይ እጣ ደርሶባታል። የራዲዮ አክቲቭ ጨረሩ ችግር ስለሚያስከትል ወደ እነዚህ ቦታዎች መሄድ ታግዷል። ፍንዳታው በደረሰበት ወቅት አና እና ቪክቶር ሩድኒክ ወደ ፕሪፔት ከመጡ አንድ ዓመታቸው ነበር። *
ትንሿ የቼርኖቤል ከተማ (የኑክሌር ማመንጫ ጣቢያውም የሚጠራው በዚሁ ስም ነው) ከጣቢያው 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። በቅርቡ የቀድሞ ነዋሪዎቿ በዓመት አንድ ጊዜ እንዲጎበኟት ተፈቅዶላቸዋል። ቼርኖቤል የሩድኒክ ቤተሰብ የትውልድ ቦታ ስለሆነች በዚህ ወቅት ከተማዋን ሊጎበኙ ሄደው ነበር። ከጥቂት ዓመታት በፊት እኔና ባለቤቴ ከእነርሱ ጋር ስላደረግነው ጉብኝት ልንገራችሁ።
ትካዜ ላይ የጣለን ጉብኝት
የዩክሬን ዋና ከተማ የሆነችውን ኪየቭን ለቅቀን ወደ ሰሜን በሚወስደው ዋና መንገድ ጉዞ ጀመርን። መንገዱ ዳር ቤቶች የሚገኙባቸውን ትንንሽ ከተሞች አልፈን ሄድን፤ የቤቶቹ ፊት ለፊት በሚያማምሩ አበባዎች ከማጌጡም በተጨማሪ ነዋሪዎቹ የጓሮ አትክልት አልምተዋል። ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላኛው እስክንደርስ የበቆሎ፣ የስንዴና የሱፍ ማሳ ለዓይን እስኪያታክት ድረስ አካባቢውን ሸፍኖት ይታያል።
አንድ ቦታ ላይ ስንደርስ ግን የምናየው ነገር ሁሉ ድንገት ተቀየረ። መንገድ ላይ የተለጠፈ ምንም ዓይነት ምልክት ባይኖርም አንድ ዓይነት ለውጥ መኖሩን አስተዋልን። በመንገዳችን ላይ የምናገኛቸው ከተሞች አስፈሪ በሆነ ጸጥታ ተውጠዋል። ከጊዜ ወደ ጊዜ እያረጁ የመጡት ቤቶች መስኮታቸው ተሰባብሯል፣ በራቸው ደግሞ እንደተቆለፈ ነው። ግቢያቸው በአረም ተወርሷል፤ አትክልቶቹም የሚንከባከባቸው አጥተዋል።
ከኃይል ማመንጫው በግምት 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው የተከለከለ ቀጣና ገባን። አና “በዚህ አካባቢ የሚገኙ ከተሞች ከፍተኛ መጠን ያለው የራዲዮ አክቲቭ ጨረር አላቸው” በማለት ነገረችን። አክላም “በአካባቢው ከሚገኙ በርካታ ከተሞችና መንደሮች የመጡ 150,000 ሰዎች በቀድሞዋ ሶቪዬት ሕብረት የተለያዩ ከተሞች ወደተዘጋጁላቸው አዳዲስ ቤቶች ለመሄድ የተነሱት ከዚህ ቦታ ነበር” አለች።
ወደፊት እየገፋን ስንሄድ አካባቢውን ከሌላው የዓለም ክፍል የሚለይ ረጅም የሽቦ አጥር ወዳለው ሌላ ቀጣና ደረስን። በአቅራቢያውም
የጉምሩክ ኬላ በሚመስል ከእንጨት በተሠራ ቤት ውስጥ የተቀመጡ ጠባቂዎች ወደዚያ የሚመጡትን መኪናዎች በሙሉ ይቆጣጠራሉ። ከዚያም አንድ ጠባቂ ፓስፖርታችንን ከተመለከተ በኋላ የመኪናችንን ታርጋ መዝግቦ የመግቢያውን በር ከፈተልን።አሁን ወደ አደገኛው ክልል ገብተናል ማለት ነው። ዛፎቹ በለምለም ቅጠላቸው መንገዱ ላይ ጥላቸውን አጥልተዋል። በአእምሮዬ የጠበቅሁት የተቃጠሉ ዛፎችና የጠወለጉ ቁጥቋጦዎች ለማየት ቢሆንም ጥቅጥቅ ብለው የበቀሉ ቁጥቋጦዎች የጫካውን ወለል ሸፍነውታል። ከፊት ለፊታችን በነጭ ጡብ ላይ በሰማያዊ ቀለም የተጻፈ ቼርኖቤል ከተማ መድረሳችንን የሚያሳውቅ ምልክት አየን።
በቼርኖቤል መግቢያ ላይ አንድ የመድኃኒት መሸጫ መደብር ይገኛል። በአንድ ወቅት የቪክቶር እናት እዚህ ትሠራ ነበር። የሥራ ሰዓቱን የሚገልጽ በደንብ የማይታይ ምልክት በቆሸሸው መስኮት ላይ ተለጥፏል። በከተማዋ መሃል ከሚገኘው የመናፈሻ ቦታ አቅራቢያ የባሕል አዳራሽ አለ። አና በዚህ አዳራሽ ውስጥ ከሥራ በኋላ እርሷም ሆነች ሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች በተለያዩ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የሚቀርቡትን ትርኢቶች በማየት ይዝናኑ እንደነበር ነገረችን። እዚሁ አካባቢ ዩክራኢና የሚባለው ፊልም ቤት ይገኛል፤ ልጆች ቀዝቀዝ ያለ አየር ባለው በዚህ ፊልም ቤት ውስጥ ውጭ ካለው ኃይለኛ ሙቀት አምልጠው በቅርቡ የወጡ ፊልሞችን በማየት ይዝናኑ ነበር። ይህ ጨለማ የዋጠው አዳራሽ የሳቅ ድምፅ ከራቀው በጣም ረጅም ጊዜ ሆኖታል። አና እና ቪክቶር ከከተማው መሃል ጥቂት ርቆ ወደሚገኘው የድሮ መኖሪያ ቤታቸው ወሰዱን። ዛፎቹ መንገዱን ስለዘጉብን በዋናው በር በኩል መግባት አልቻልንም፤ በመሆኑም ፊትና ኋላ ሆነን አረሙን አልፈን ወደ ጓሮ በር ሄድን። ይሁንና በወቅቱ ያገኘነው በር የተነደለ ግድግዳ የሚመስል ነበር።
ወደ ውስጥ ስንገባ ሁሉም ነገር እንዳልነበረ ሆኗል። አንድ ሻጋታ የወረሰው ፍራሽ በዛገ የብረት አልጋ ላይ ተጥሏል። ግድግዳው ላይ የተለጠፈው ወረቀት ተቀዳዶ ተንጠልጥሏል። አና በክፍሉ ውስጥ ከተበታተነው ወረቀት መካከል አንድ የቆየ ፎቶ ጎንበስ ብላ አነሳችና ሐዘኔታ በተቀላቀለው ድምፅ “ይህን ቤት ጥለነው ስንሄድ እንደነበረው አገኘዋለሁ ብዬ አስብ ነበር” አለች። አክላም እንዲህ በማለት ተናገረች “ቤታችን እንዲህ ትርኪምርኪ የሞላበት ሆኖ እንዲሁም ንብረታችን ተሠርቆ ማየት እንዴት ያሳዝናል!”
የድሮ ቤታቸውን ለቅቀን ወጣንና ጎዳናውን ይዘን ቁልቁል ወረድን። አንዱ ጥግ ላይ ሰዎች ተሰብስበው ሞቅ ያለ ጭውውት ይዘዋል። ግማሽ ኪሎ ሜትር ያህል እንደ ተጓዝን መንገዱን ጨርሰን ወደ አንድ መናፈሻ ደረስን፤ ከታች ጸጥ ያለ ወንዝ ይታያል። ንፋሱ በአካባቢው ያሉት ዛፎች ያፈሯቸውን ነጫጭ አበቦች ያወዛውዛቸዋል። በ1986 በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጀልባ አካባቢውን ለቅቀው ለመሄድ ወደ ወደቡ የሚወስደውን ጠመዝማዛ ደረጃ በመውረድ ወረፋ ይጠብቁ ነበር።
የሩድኒክ ቤተሰብ በፕሪፔት የሚገኘውን የቀድሞ መኖሪያ ቤታቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኙት ባለፈው ዓመት ነበር። በኑክሌር ጣቢያው ላይ የደረሰውን ፍንዳታ ተከትሎ ከተማዋን ጥለው የሸሹት ከ19 ዓመት በፊት ነበር።
የደረሰው አደጋ ዳግም የሚታሰብበት ጊዜ
በሚያዝያ 2006 በኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያው አደጋ የተከሰተበትን 20ኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር ታቅዷል። ይህ ቀን የሰው ልጅ ልባዊ ጥረት ቢያደርግም እንኳ ያለ አምላክ እርዳታ የምድር ጉዳዮችን በተሳካ መንገድ መምራት እንደማይችል ብዙዎችን መለስ ብለው እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል።—ኤርምያስ 10:23
ባለፈው መስከረም ወር ላይ አደጋው ያስከተለውን ጉዳት የሚያብራራ ሳይንሳዊ ሪፖርት ቀርቦ ነበር። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰጠው ትእዛዝ የተዘጋጀው ይህ ሪፖርት እንዳለው አደጋው መጀመሪያ ላይ 56 ሰዎችን የገደለ ሲሆን ከዚያ አፈትልኮ በሚወጣው ጨረር ምክንያት ውሎ አድሮ ሊሞቱ የሚችሉት ሰዎች ቁጥር ከ4,000 እንደማይበልጥ ተገምቷል። ቀደም ሲል የነበረው ግምታዊ አኃዝ ግን የሟቾቹ ቁጥር ከ15,000 እስከ 30,000 እንደሚደርስ ጠቁሞ ነበር። ኒው ዮርክ ታይምስ በመስከረም 8, 2005 እትሙ ባወጣው ርዕሰ አንቀጽ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ያቀረበው ሪፖርት “የኑክሌር ኃይል ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ለመሸፋፈን የተደረገ ወገናዊነት የሚታይበት ሙከራ ነው ሲሉ በርካታ የተፈጥሮ ጥበቃ ተሟጋች ቡድኖች አውግዘውታል” በማለት ዘግቧል።
ከአደጋው በኋላ ስለ ፈጣሪው ስለ ይሖዋ አምላክ መማር የጀመረው ቪክቶር እንዲህ ብሏል:- “የአምላክ መንግሥት ሲመጣ ይህን መሰሉ አሰቃቂ አደጋ በፍጹም እንደማይኖር ስለምናውቅ በተከሰተው ሁኔታ የደረሰብን ሐዘን ተወግዶልናል። በጣም የምንወደው የቼርኖቤል መኖሪያችንና አቅራቢያው የሚገኘው ገጠራማ አካባቢ አሁን ከደረሰበት ጉዳት ሙሉ በሙሉ አገግሞ የውቢቷ ገነት ክፍል የሚሆንበትን ጊዜ በጉጉት እንጠብቃለን።”
የቼርኖቤል አደጋ ከደረሰ ወዲህ ምድር ላይ የነበረችው የመጀመሪያዋ ገነት ዳግም እንደምትቋቋምና ምድርን በሙሉ እንደምታጠቃልል መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው ተስፋ ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጽኑ እምነት አሳድረዋል። (ዘፍጥረት 2:8, 9፤ ራእይ 21:3, 4) ባለፉት 20 ዓመታት በዩክሬን ብቻ ከ100,000 በላይ ሰዎች ይህን ተስፋ በደስታ ተቀብለዋል! የአምላክን ዓላማ ለማወቅ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች የተገባላቸውን አስደሳች ተስፋ አንተም ለመመርመር እንድትነሳሳ ምኞታችን ነው።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.5 ለጥቂት ጊዜያት የሚቆየው ይህን መሰሉ ጉብኝት ምንም ጉዳት እንደሌለው የተለያዩ ጽሑፎች የሚናገሩ ቢሆንም ንቁ! በግል ወደዚያ የሚደረግን ማንኛውንም ዓይነት ጉዞ አያበረታታም።
^ አን.5 የሚያዝያ 22, 1997 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ከገጽ 12-15ን ተመልከት።
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ለነፍስ አድን ሠራተኞች የቆመ የመታሰቢያ ሐውልት
ይህ ግዙፍ የመታሰቢያ ሐውልት በቼርኖቤል ጉዳት የደረሰበትን አካባቢ በማጽዳቱ ሥራ ለተካፈሉ ሊኪውዴተርስ ተብለው ለተጠሩ ሠራተኞች ክብር የቆመ ነው። እነዚህ ሰዎች እሳቱን አጥፍተዋል፣ በመጨስ ላይ የነበረውን የኑክሌር ማብለያ ደፍነዋል እንዲሁም ብክለት ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮችን አስወግደዋል። የእነዚህ ሠራተኞች ቁጥር ከጊዜ በኋላ ወደ መቶ ሺዎች ደርሶ ነበር። ከፍንዳታው ጋር በተያያዘ ወደ 4,000 የሚጠጉ ሰዎች ሞተዋል ተብሎ የሚገመት ሲሆን ከሟቾቹ መካከል አብዛኞቹ እነዚህ ሠራተኞች ሊሆኑ ይችላሉ።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የቼርኖቤልን ከተማ የሚጠቁመው ምልክትና ፊልም ቤቱ
[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የሩድኒክ ቤተሰብና በቼርኖቤል የሚገኘው ቤታቸው
[በገጽ 16 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ፍንዳታ የደረሰበት ኃይል ማመንጫ፤ በፕሪፔት ከሚገኘው የሩድኒክ መኖሪያ ቤት (ውስጥ ያለው ፎቶ) ወደ ሦስት ኪሎ ሜትር ይርቃል