ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
▪ ባለፈው ዓመት፣ ከ15 እስከ 64 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 200 ሚሊዮን ያህል ሰዎች (ከዓለም ሕዝብ መካከል 5 በመቶ የሚሆኑት ማለት ነው) በሕግ የተከለከሉ አደገኛ መድኃኒቶችን ወስደዋል።— በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአደገኛ መድኃኒቶችና ወንጀል ቢሮ፣ በ2005 የተዘጋጀ የዓለም የአደገኛ መድኃኒቶች ሪፖርት
▪ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ በጦር መሣሪያ ወንጀል ሲፈጸም የተመለከተ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ወጣት በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ወንጀል የመፈጸሙ አጋጣሚ በሁለት እጥፍ ያህል ይጨምራል።—ሳይንስ መጽሔት፣ ዩናይትድ ስቴትስ
▪ በሳኦ ፓውሎ፣ ብራዚል በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በአንድ ሆስፒታል ተመርምረው የጡት ካንሰር እንዳለባቸው ከተነገራቸው ሴቶች መካከል 16.8 በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ35 ዓመት በታች ነበር። ካንሰሩ ሥር ከመስደዱ በፊት ከታወቀ እነዚህ ሴቶች 90 በመቶ የመዳን ዕድል ይኖራቸዋል።—ፎያ ኦንላይን፣ ብራዚል
የመሰላቸትን ስሜት መዋጋት
ስለ መሰላቸት የሚያጠኑ ተመራማሪዎች እንዲህ ያለውን ስሜት “ከዘመናችን ዋና ዋና በሽታዎች አንዱ” ብለው እንደሰየሙት ዘ ቫንኩቨር ሰን የተሰኘው ጋዜጣ ይዘግባል። “ከአራት የሰሜን አሜሪካ ነዋሪዎች ውስጥ ሦስቱ በሕይወታቸው አዲስ ነገር ለማየት የሚናፍቁ መሆናቸውን እንደሚናገሩ” አንድ ጥናት ያመለክታል። ጋዜጣው መሰላቸትን ለመዋጋት ያስችላሉ ብሎ ከሚያቀርባቸው የመፍትሔ ሐሳቦች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል:- “ከመሰላቸት ስሜትህ ለመላቀቅ በአኗኗርህ ላይ ለውጥ አድርግ፣” “አዲስ ነገር ተማር፣” “የበጎ ፈቃድ ሠራተኛ ሆነህ ትርጉም ያለው ተግባር” አከናውን፣ “ሰውነትህ እንዲንቀሳቀስ በሚያደርጉ እንደ የእግር ጉዞ ባሉ ተግባሮች ተካፈል” እንዲሁም “አመስጋኝ መሆንን ተማር።”
ዘመናዊ ባርነት
“በዓለም ዙሪያ ቢያንስ 12.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በግዳጅ እንዲሠሩ ይደረጋሉ” በማለት የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት ያቀረበው ጥናት ይዘግባል። ከእነዚህ ውስጥ ከ2.4 ሚሊዮን የሚበልጡት የባሪያ ፍንገላ ሰለባዎች እንደሆኑ ተገምቷል። የግዳጅ ሥራዎች ከሚባሉት ማለትም ሠራተኞች ከፈቃዳቸው ውጪ በኃይል በማስፈራራት እንዲሠሩ ወይም አገልግሎት እንዲሰጡ ከሚገደዱባቸው ሥራዎች መካከል ዝሙት አዳሪነትና ወታደራዊ አገልግሎት እንዲሁም ሠራተኞቹ ቀደም ብለው የተበደሩትን ዕዳ ለመክፈል በተዋዋሉት መሠረት በአነስተኛ ደመወዝ አለዚያም ያለ አንዳች ክፍያ የሚሠሩበት ሁኔታ ይገኙበታል። የዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት ህዋን ሶማቪያ እንደተናገሩት እንዲህ ያለው የግዳጅ ሥራ “የሰዎችን መሠረታዊ መብትና ክብር ያሳጣል።”
በክሪዎል ቋንቋ የተዘጋጀ የመጀመሪያው ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ
“ከዘፍጥረት እስከ ራእይ ያሉትን መጻሕፍት የያዘና በአገሬው ተወላጆች ቋንቋ የተዘጋጀ የመጀመሪያው የአውስትራሊያ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ተጠናቀቀ” በማለት ዘ ሲድኒ ሞርኒንግ ሄራልድ ዘግቧል። በ2007 የሚወጣው አዲሱ የክሪዎል የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ራቅ ብለው በሚገኙት የሰሜን አውስትራሊያ ክልሎች የሚኖሩትን 30, 000 የሚሆኑ አቦርጂኖች የሚጠቅም ነው። “የትርጉም ሥራው ከተጀመረ 27 ዓመት ሆኖታል” በማለት ጋዜጣው ይናገራል። የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት ኅብረት እንደገለጸው “በ2004፣ 22 አዳዲስ የአዲስ ኪዳን ትርጉሞች እንደተዘጋጁ ተመዝግቧል።” በአሁኑ ወቅት መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉም ሆነ በከፊል በ2, 377 ቋንቋዎችና ቀበሌኛዎች ለንባብ በቅቷል።
በቆሙ መኪናዎች ውስጥ ያለው ሙቀት
ፔዲያትሪክስ መጽሔት እንደሚናገረው በ2004 በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በቆሙ መኪናዎች ውስጥ የተተዉ 35 ልጆች በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከመኪናው ውጪ ያለው ሙቀት ከ30 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ ከሆነ በተሽከርካሪው ውስጥ ያለው ሙቀት ወዲያውኑ ከ57 እስከ 68 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሊደርስ እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ። የውጪው ሙቀት 22 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በሆነበት ሰዓትም እንኳ መኪናው ውስጥ ያለው ሙቀት በእጥፍ ያህል ሊጨምር እንደሚችልና የሙቀቱ መጠን እዚህ ደረጃ የሚደርሰውም መኪናው ከቆመ ከ15 እስከ 30 ደቂቃ ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሆነ ተገልጿል። የመኪናው መስኮት 4 ሴንቲ ሜትር ያህል ዝቅ መደረጉ ወይም ሞተሩ ከመጥፋቱ በፊት የመኪናው ማቀዝቀዣ ተከፍቶ መቆየቱ እምብዛም ለውጥ አያመጣም። የርዕሰ አንቀጹ አዘጋጆች ሕዝቡ አደጋውን መገንዘቡ ሕይወትን ለማዳን እንደሚረዳ ያምናሉ።