በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በእሾህ መካከል የሚበላ መፈለግ

በእሾህ መካከል የሚበላ መፈለግ

በእሾህ መካከል የሚበላ መፈለግ

በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

እስቲ በደቡብ አፍሪካ የሚገኘውን ኑርስፊልድ ተብሎ የሚጠራ አካባቢ አብረን እንጎብኝ። ይህ ከፊል በረሃማ የሆነ ቦታ ስያሜውን ያገኘው በአካባቢው በብዛት ከሚበቅለው ኑርስ ወይም ዩፎረቢያ የተባለ እሾሃማ የቁልቋል ዝርያ ነው። በአካባቢው የሚኖሩት ገበሬዎች የተለያዩ እንስሳትን ያረባሉ። በተለይ በሥዕሉ ላይ የሚታዩት የአንጎራ ፍየሎች ሞሄር ተብሎ የሚጠራውን ነጭ ሱፍ ስለሚያስገኙ ከፍተኛ ተፈላጊነት አላቸው። ይህ የሱፍ ዓይነት ለስላሳ ሆኖም ጠንካራ የሆነ ፈትል የሚወጣው ሲሆን የተለያዩ የፋሽን አልባሳትን እንዲሁም ምንጣፎችን ለመሥራት ያገለግላል። ይሁን እንጂ እነዚህ እንስሳት በዚህ በድርቅ የተጠቃ አካባቢ በሕይወት መቆየት የሚችሉት እንዴት ነው?

በፍየሎቹ ዙሪያ የምትመለከታቸው ችምችም ብለው የበቀሉ የቁልቋል ተክሎች ለፍየሎቹ በሕይወት መቆየት ወሳኝ ሚና አላቸው። ፍየሎቹ 40 በመቶ የሚሆነውን የክረምት ምግባቸውን የሚያገኙት ዩፎረቢያ ኮይሩለሴንስ ተብሎ ከሚጠራው ከዚህ የቁልቋል ዝርያ ነው። ይሁን እንጂ ፍየሎቹ ቁልቋሉን በሚመገቡበት ወቅት እሾሁ እንዳይወጋቸው መጠንቀቅ አለባቸው። እሾሁን ከግንዱ ላይ በቀንዳቸው እየፈገፈጉ ማርገፍ እየለመዱ ሲሄዱ ቁልቋሉን መመገብ የበለጠ ቀላል ይሆንላቸዋል።

ጥሩ ዝናብ በሚጥልበት ወቅት ፍየሎቹ በቁልቋሎቹ ዙሪያ የሚበቅሉትን ዕፅዋት ይመገባሉ። ይህም ቢሆን ግን አደገኛ ነው። ዩርገን ከሪ የተባሉ አርብቶ አዳሪ ስለ ኑርስፊልድ በጻፉት መጽሐፍ ላይ እንዲህ ይላሉ:- “በቁልቋሉ ስርና መሃል የበቀሉትን ለስላሳ ዕፅዋት ለመመገብ የደፈረ የአንጎራ ፍየል የሚያምረው ጥቅልል ጸጉሩ በእሾሁ ሊያዝና ራሱን ማስለቀቅ ሊያቅተው ይችላል።” ይህ ደግሞ ሞት ሊያስከትልበት ይችላል። አርብቶ አዳሪው እንደሚሉት ፍየሉ በቁልቋሉ የተያዘው “የበጋዋ ፀሐይ በከረረችበት ወቅት ከሆነ ከሁለት ሰዓታት የበለጠ ዕድሜ አይኖረውም።”

አልፎ አልፎ የኑርስፊልድ አካባቢ በከባድ ድርቅ ይጠቃል። በእነዚህ ወቅቶች የኑርስ ቁልቋል ሕይወት አድን ነው። አርብቶ አዳሪዎቹ የማጨጃ ማሽኖቻቸውን በቁልቋሉ ላይ እየነዱ ይከረታትፉታል። ፍየሎቹ በትንንሹ የተከረታተፈውን ቁልቋል ለመመገብ የሚቀላቸው ከመሆኑም በላይ እሾሁ አያሰጋቸውም። የዱር እንስሳትም ከፍየሎቹ ጋር ተቀላቅለው እየተሻሙ ይበላሉ። ከሪ እንዲህ ይላሉ:- “አካባቢው በድርቅ በሚጠቃበት ወቅት ኩዱዎችም [ትልቅ የአጋዘን ዝርያ] ከዚህ ሲሳይ ይቋደሳሉ። ምግብ የማግኘት ጉጉት ለሰው ያላቸውን ፍርሃት አስረስቷቸው ከመንገዱ ብዙም ሳይርቁ ቁልቋሉ በተቆራረጠበት መስክ ላይ ሲመገቡ ማየት ትችላላችሁ።”

ዩፎረቢያ ፌሮክስ ተብሎ የሚጠራ ሌላ የቁልቋል ዝርያ ደግሞ ቁመቱ አጠር ያለ ቢሆንም አካሉ በእሾህ የተሸፈነ ከመሆኑ የተነሳ አብዛኞቹ እንስሳት ለመብልነት የሚያገለግለውን አገዳ ሊደርሱበት አይችሉም። ሆኖም ድርቅን የመቋቋም ኃይል ስላለው ሕይወት አድን ምግብ ነው። ዝናብ በወቅቱ ሳይዘንብ ሲቀር አርብቶ አዳሪዎቹና ሠራተኞቻቸው ችምችም ብለው በበቀሉት ቁልቋሎች መካከል እየተዘዋወሩ እሾሁን በእሳት በመለብለብ ወይም በሌላ መንገድ ያራግፉታል። ይህ በጣም አድካሚ ሥራ ነው። ፊልድ ፕላንትስ ኦቭ ሳውዘርን አፍሪካ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “እሾሁ ተቃጥሎ ከረገፈ በኋላ መንጋው አገዳውን እየተሻማ መብላት ይጀምራል። . . . ስፕሪንግቡክ የተባለው እንስሳም [የአጋዘን ዝርያ ነው] ‘በእሳት የተለበለበውን ቁልቋል’ መመገብ የለመደ ሲሆን ከሰዎች ጋር ከመላመዱ የተነሳ ብዙ ጊዜ . . . ቁልቋሉን የሚለበልበውን ሰው ተጠግቶ ሲበላ ይታያል።”

ፍየሎቹ በቁልቋሎቹ መሃል ተመስገው ሲቀነጣጥቡ ስንመለከት የይሖዋን ልዩ ልዩ ፍጥረታት ለማድነቅ እንገፋፋለን። የኑርስ ቁልቋል ፈጽሞ የማያስጠጋና ለሕይወት የሚያሰጋ ቢመስልም በዚህ በድርቅ የተጠቃ አካባቢ ለብዙ እንስሳት ሕይወት አድን መኖ ነው።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፍየሎቹ 40 በመቶ የሚሆነውን የክረምት ምግባቸውን የሚያገኙት ከዚህ የቁልቋል ዝርያ ነው

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አበባው የፈካ ቁልቋልና አደገኛ እሾሆቹ በቅርበት ሲታዩ