እንቅልፍ ቅንጦት ነው ወይስ የግድ አስፈላጊ የሆነ ነገር?
እንቅልፍ ቅንጦት ነው ወይስ የግድ አስፈላጊ የሆነ ነገር?
አንዳንድ ሰዎች እንቅልፍን ምንም ጥቅም የሌለው ጊዜ ማጥፊያ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። እንደዚህ ያሉት ሰዎች በሥራና በማኅበራዊ ጉዳዮች ከልክ በላይ በመጠላለፍ ለእንቅልፍ እጃቸውን የሚሰጡት በጣም በሚደክማቸው ጊዜ ብቻ ነው። በአንጻሩ ደግሞ ሌሊቱን ሙሉ ሲገላበጡ ቢያድሩም እንቅልፍ በዓይናቸው ሳይዞር ሌሊቱ የሚነጋባቸው ሰዎችም አሉ።
አንዳንዶች እንቅልፍ እምቢ ሲላቸው ሌሎች ግን መተኛት ሳይፈልጉ እንቅልፍ የሚጫጫናቸው ለምንድን ነው? እንቅልፍን ማየት የሚኖርብን እንደ ቅንጦት ነው ወይስ የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ነገር? እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ በመጀመሪያ በምንተኛበት ጊዜ በሰውነታችን ውስጥ ምን እንደሚካሄድ መረዳት ይኖርብናል።
የእንቅልፍ ምስጢር
አንድ ሰው እንቅልፍ ጥሎት ራሱን እንዲስት የሚያደርገው ነገር ምን እንደሆነ ገና አልታወቀም። ይሁን እንጂ ተመራማሪዎች እንቅልፍ አንጎል የሚቆጣጠረውና በሰውነታችን ውስጥ ላለው ተፈጥሯዊ ሰዓት የሚታዘዝ የተወሳሰበ ሂደት እንደሆነ አውቀዋል።
ዕድሜያችን እየገፋ ሲሄድ የእንቅልፍ ልማዳችንም እየተለወጠ ይሄዳል። አዲስ የተወለደ ሕፃን በቀን ውስጥ በየመሃሉ እየነቃም ቢሆን በጠቅላላው 18 ሰዓት ያህል ይተኛል። ስለ እንቅልፍ ያጠኑ ምሁራን እንደሚሉት ከሆነ አንዳንድ ትልልቅ ሰዎች በቀን ውስጥ የ3 ሰዓት እንቅልፍ ብቻ ሲበቃቸው ሌሎች ግን እስከ 10 ሰዓት የሚደርስ እንቅልፍ ያስፈልጋቸዋል።
በቅርብ ጊዜ የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው በሰውነታችን ውስጥ ያለው ተፈጥሯዊ ሰዓት የሚለያይ መሆኑ አንዳንድ ወጣቶች ጧት ጧት ከአልጋቸው ውስጥ ለመውጣት የሚቸገሩበትን ምክንያት እንድንረዳ ያስችለናል። በወጣትነት ወቅት ባዮሎጂያዊው ሰዓት ስለሚለወጥ ወጣቶች አምሽቶ መተኛትና አርፍዶ መነሳት እንዲመርጡ ያደርጋቸዋል። ይህ የእንቅልፍ መጓተት የተለመደ ሲሆን ከአሥራዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ጀምሮ እየጠፋ ይሄዳል።
ይህ ተፈጥሯዊ ሰዓት በኬሚካላዊ ንጥረ ነገሮች ቁጥጥር የሚደረግበት ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ታውቀዋል። ከእነዚህም አንዱ ሜላቶኒን የሚባለው ሆርሞን ሲሆን እንቅልፍ እንቅልፍ የማለትን ስሜት እንደሚቀሰቅስም ይታመናል። ሜላቶኒን የሚመነጨው አንጎል ውስጥ ሲሆን አንዳንድ ሳይንቲስቶች ልንተኛ ስንል ሰውነታችን የምግብ ማዋሃድ ሥራውን እንዲቀንስ የሚያደርገው ይህ ንጥረ ነገር እንደሆነ ያምናሉ። ሜላቶኒን በሰውነታችን ውስጥ ሲሰራጭ የሰውነታችን ሙቀትና ወደ አንጎላችን የሚገባው የደም መጠን ይቀንሳል፤ ጡንቻዎቻችንም ቀስ በቀስ እየላሉ ይሄዱና በመጨረሻም ይዝላሉ። ከዚያ በኋላ ሰውየው ወደ ምስጢራዊው የእንቅልፍ ዓለም ሲገባ ምን ይሆናል?
‘የተፈጥሮ ዋነኛ ምግብ’
እንቅልፍ ከወሰደን ከሁለት ሰዓት ገደማ በኋላ ዓይኖቻችን መርገብገብ ይጀምራሉ። ሳይንቲስቶች ስለዚህ ክስተት በቂ እውቀት ማግኘታቸው እንቅልፍን በሁለት መሠረታዊ ክፍሎች እንዲከፍሉት አድርጓቸዋል። እነሱም ፈጣን የዓይን መርገብገብ ያለበትና የሌለበት እንቅልፍ ናቸው። ፈጣን የዓይን መርገብገብ የሌለበት እንቅልፍ ደግሞ በአራት የእንቅልፍ ደረጃዎች ይከፈላል። ጥሩ እንቅልፍ ባለበት ሌሊት ፈጣን የዓይን መርገብገብ ያለበት እንቅልፍ ፈጣን የዓይን መርገብገብ ከሌለበት እንቅልፍ ጋር በመፈራረቅ ብዙ ጊዜ ይከሰታል።
ብዙ ሕልም የሚታየው ፈጣን የዓይን መርገብገብ ባለበት እንቅልፍ ላይ ነው። በዚህ የእንቅልፍ ወቅት የሰውነት ጡንቻዎችም ዘና ስለሚሉ የተኛው ሰው ከእንቅልፉ ሲነቃ ሰውነቱ እንደታደሰ ሆኖ ይሰማዋል። በተጨማሪም አንዳንድ ተመራማሪዎች አዳዲስ እውቀቶች በአእምሯችን ውስጥ በመቀረፅ ከረዥም ጊዜ በፊት ከምናውቃቸው እውቀቶች ጋር የሚዋሃዱት በዚህኛው የእንቅልፍ ክፍል እንደሆነ ያምናሉ።
ከባድ እንቅልፍ ሲወስደን (የዓይን መርገብገብ በሌለበት እንቅልፍ በሦስተኛውና በአራተኛው ደረጃዎች ላይ) የደም
ግፊታችንና የልባችን ምት በጣም ዝቅ ይላሉ። ይህም የደም ዝውውር ሥርዓታችን ዕረፍት እንዲያገኝና የደም ቧንቧዎች በበሽታ እንዳይጠቁ ለመከላከል ይረዳል። በተጨማሪም ዕድገትን የሚቆጣጠሩ ሆርሞኖች ከፍ የሚሉት በዚህ የእንቅልፍ ክፍል ወቅት ነው። እንዲያውም እነዚህ ሆርሞኖች በአሥራዎቹ ዕድሜ በሚገኙ አንዳንድ ወጣቶች ሰውነት ውስጥ ከቀን ይልቅ ማታ ማታ 50 እጥፍ ይመነጫሉ።በተጨማሪም እንቅልፍ በምግብ ፍላጎታችን ላይም ለውጥ የሚያመጣ ይመስላል። ሳይንቲስቶች እንቅልፍ ሼክስፒር እንደተናገረው “ዋነኛ የሕይወት ምግብ” መሆኑን ደርሰውበታል። አንጎላችን የእንቅልፍ ዕጦትን ምግብ እንደማጣት አድርጎ ይተረጉመዋል። አካላችን ምግብ በልተን መጥገባችንን የሚነግረንን ሌፕቲን የሚባለውን ሆርሞን ስንተኛ ያመነጫል። ሳንተኛ ከሚገባው በላይ ከቆየን ሰውነታችን የሚያመነጨው የሌፕቲን መጠን አነስተኛ ስለሚሆን ተጨማሪ ምግብ መብላት ያምረናል። በመሆኑም እንቅልፍ አለመተኛት ተጨማሪ ምግቦች እንድንበላ ስለሚያደርግ ከመጠን በላይ መወፈርን ያስከትላል።—“የቀትር ሸለብታ” የሚለውን ገጽ 6 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።
ለጤንነት በጣም አስፈላጊ ነው
እንቅልፍ የሚሰጠው ጥቅም በዚህ ብቻ አያበቃም። እንቅልፍ ሰውነታችን እርጅናንና ካንሰርን ያመጣሉ ተብለው የሚታሰቡትን ፍሪ ራዲካልስ ተብለው የሚታወቁትን ሞለኪውሎች ለማፍረስ ይረዳል። በቺካጎ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ በተካሄደ አንድ ጥናት ጤነኛ የሆኑ 11 ወጣቶች ለስድስት ቀናት ያህል በየቀኑ ለአራት ሰዓታት ብቻ እንዲተኙ ተደረገ። ከስድስቱ ቀን በኋላ ሰውነታቸው ሥራውን የሚያከናውነው እንደ 60 ዓመት አረጋውያን ሆኖ የተገኘ ከመሆኑም በላይ በደማቸው ውስጥ ያለው የኢንሱሊን መጠን የስኳር በሽታ ካለበት ሰው ጋር የሚተካከል ሆኖ ተገኝቷል። የእንቅልፍ እጦት በሰውነታችን ውስጥ ነጭ የደም ሴሎችና ኮርቲሶል የሚባል ሆርሞን በበቂ መጠን እንዳይመረቱ በማድረግ ኢንፌክሽንና ከደም ዝውውር ጋር የተያያዙ በሽታዎች እንዲከሰቱ ሊያደርግ ይችላል።
ከዚህ ለማየት እንደምንችለው እንቅልፍ የሰውነትንና የአእምሮን ጤና ለመጠበቅ እጅግ አስፈላጊ ነው። ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው ስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የእንቅልፍ ጥናት ማዕከል መሥራች የሆኑት ዊልያም ዳመንት የተባሉ አንድ ተመራማሪ “እንቅልፍ ምን ያህል ዕድሜ እንደምንኖር ከሁሉ የሚበልጥ አመላካች ይመስላል” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በሳኦ ፓውሎ፣ ብራዚል የእንቅልፍ ጥናት ማዕከል ተመራማሪ የሆኑት ዴቦራ ሱሼኪ የተባሉ ሴት “ሰዎች እንቅልፍ በተነፈገው ሰውነት ውስጥ የሚካሄደውን ነገር ቢያውቁ ኖሮ እንቅልፍ ጊዜ ማባከኛ ወይም የሰነፎች ነው ብለው ባልተናገሩ ነበር” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።—ከላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።
ይሁንና ሰውነትን የሚያድሰው ሁሉም ዓይነት እንቅልፍ ነውን? አንዳንድ ሰዎች ሌሊቱን ሙሉ ተኝተው እንቅልፍ ሳይጠግቡ የሚነሱት ለምንድን ነው? ቀጣዩ ርዕስ ለእንቅልፍ መዛባት ምክንያት የሆኑት ዋነኛ ችግሮች ምን እንደሆኑና ጥሩ እንቅልፍ እንዴት ማግኘት እንደምትችል ያብራራል።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የእንቅልፍ ማነስ የሚያስከትላቸው ችግሮች
የአጭር ጊዜ ችግሮች
▪ ድብታ
▪ ድንገተኛ የጠባይ መለዋወጥ
▪ ጊዜያዊ የመርሳት ችግር
▪ ሥራ የመፍጠር፣ የማቀድና የማከናወን ችሎታ ማጣት
▪ በትኩረት የመከታተል ችሎታ ማጣት
የረዥም ጊዜ ችግሮች
▪ ከልክ በላይ መወፈር
▪ ያለዕድሜ ማርጀት
▪ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ድካም
▪ ለኢንፌክሽን፣ ለስኳር በሽታ፣ ለሥርዓተ ልብ ቧንቧ በሽታዎች፣ ለጨጓራና ለአንጀት በሽታዎች መጋለጥ
▪ ሥር የሰደደ የመርሳት ችግር
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የቀትር ሸለብታ
ምሳ ከበላህ በኋላ እንቅልፍ ተጫጭኖህ ያውቃል? ይህ ሌሊት ጥሩ እንቅልፍ ሳትተኛ በመቅረትህ ምክንያት ያጋጠመህ ላይሆን ይችላል። በተፈጥሮ ቀትር ላይ የሰውነት ሙቀት ስለሚቀንስ እንቅልፍ እንቅልፍ የማለት ስሜት መሰማቱ የተለመደ ነገር ነው። በተጨማሪም በቅርቡ የሳይንስ ሊቃውንት እንደደረሱበት አንጎላችን እንድንነቃ የሚያደርግ ሃይፖክሬቲን ወይም ኦሬክሲን የሚባል ፕሮቲን ያመነጫል። በሃይፖክሬቲንና በምግብ መካከል ምን ግንኙነት አለ?
ምግብ በምንበላበት ጊዜ ሰውነታችን መጥገባችንን ለማሳወቅ ሌፕቲን የሚባል ሆርሞን ያመነጫል። ሌፕቲን ግን ሃይፖክሬቲን እንደልብ እንዳይመነጭ ያግዳል። በሌላ አነጋገር በአንጎላችን ውስጥ ብዙ ሌፕቲን ሲኖር በሰውነታችን ውስጥ ያለው የሃይፖክሬቲን መጠን ይቀንሳል፤ ይህም እንቅልፍ እንዲጫጫነን ያደርጋል። በአንዳንድ አገሮች ያሉ ሠራተኞች ምሳ ከበሉ በኋላ ትንሽ ጊዜ ወስደው የሚያሸልቡት በዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ግራፍ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የእንቅልፍ ደረጃዎች
ቀለል ተደርጎ የተዘጋጀ ግራፍ
የእንቅልፍ ደረጃዎች
ንቁ
ፈጣን የዓይን መርገብገብ ያለበት እንቅልፍ
ፈጣን የዓይን መርገብገብ የሌለበት እንቅልፍ
ቀላል እንቅልፍ 1
2
3
ከባድ እንቅልፍ 4
1 2 3 4 5 6 7 8
የእንቅልፍ የጊዜ ርዝመት
[በገጽ 4 እና 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቂ እንቅልፍ መተኛት ሰውነታችንና አእምሯችን ጤናማ እንዲሆን ይረዳል
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እንቅልፍ ስንተኛ ዕድገትን የሚቆጣጠረው ሆርሞን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል