በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንድ የኬሚካል ፋብሪካ በፈነዳ ጊዜ

አንድ የኬሚካል ፋብሪካ በፈነዳ ጊዜ

አንድ የኬሚካል ፋብሪካ በፈነዳ ጊዜ

ፈረንሳይ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

መስከረም 21 ቀን 2001 ኒው ዮርክ በሚገኘው የዓለም ንግድ ማዕከል ላይ ጥቃት ከተሰነዘረ ከአሥር ቀን በኋላ በደቡባዊ ምዕራብ ፈረንሳይ በቱሉዝ መንደር በአንድ የኬሚካል ፋብሪካ ላይ የደረሰ ከባድ አደጋ አካባቢውን አወደመ። ለ ፕዋ የተባለ አንድ የፈረንሳይ ጋዜጣ ይህን አደጋ “ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በፈረንሳይ አገር ታይቶ የማያውቅ ከባድ የኢንዱስትሪ አደጋ” በማለት ጠርቶታል።

ሦስት ሺህ ኩንታል የሚያህል ማዳበሪያ ፈንድቶ 50 ሜትር ስፋትና 15 ሜትር ጥልቀት ያለው ትልቅ ጉድጓድ ፈጥሯል። በፍንዳታውና ፍንዳታው በፈጠረው ትኩሳትና ንዝረት ምክንያት 30 ሰዎች ሲሞቱ ከ2, 200 በሚበልጡ ሰዎች ላይ የመቁሰል አደጋ ደርሷል። ሁለት ሺህ የሚያህሉ ቤቶች ሲወድሙ በ8 ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ በሚገኙ ሌሎች 27, 000 ቤቶች ላይ ጉዳት ደርሷል። ሰዎች አደጋውን ያደረሱት አሸባሪዎች እንደሆኑ አድርገው በማሰባቸውና ከፋብሪካው መርዛማ ጋዝ በመውጣቱ በከፍተኛ ፍርሃት ተውጠው ነበር።

በርካታ የይሖዋ ምሥክሮችም በፍንዳታው ምክንያት አካላዊና ሌላ ዓይነት ጉዳት ደርሶባቸዋል። የእምነት ባልደረቦቻቸው በክርስቲያናዊ ፍቅር ተገፋፍተው ወዲያው ደርሰውላቸዋል። (ዮሐንስ 13:​34, 35) የሚከተለው ሪፖርት ስለተደረገው አጣዳፊ እርዳታ ይገልጻል።

“ከሕንጻው የቀረ አንድም ነገር አልነበረም”

ኩዲር በዚሁ ፋብሪካ ይሠራ የነበረ ሲሆን ከአደጋው በሕይወት ተርፏል። በፍንዳታውና ከሕንጻው በሚወነጨፈው ፍርስራሽ ምክንያት ራሱን ስቶ ከመውደቁም በላይ አገጩና ብራኳው ተሰብሯል። ከፋብሪካው አጠገብ በሚገኝ ሕንጻ ውስጥ ይሠራ የነበረው ባንዣማም 3 ሜትር ያህል ተወርውሮ ከግድግዳ ጋር ተጋጭቷል። የተወረወሩ የመስተዋት ስብርባሪዎች ብዙ ቦታ ላይ የቆራረጡት ሲሆን ቀኝ ዓይኑም በመወጋቱ የማየት ችሎታውን አጥቷል። “ቢሮ ወንበሬ ላይ ባለመኖሬ እድለኛ ነኝ። በወንበሬና ጠረጴዛዬ ላይ 600 ኪሎ ግራም የሚመዝን ጡብ ተከምሯል” በማለት ተናግሯል።

ከፋብሪካው 200 ሜትር ያህል ርቆ በሚገኝ ትምህርት ቤት የሚያስተምረው አላን ፋብሪካው በፈነዳበት ጊዜ ፎቶ ኮፒ ያነሳ ነበር። እንዲህ ይላል:- “ከጥቂት ብረቶች በቀር ከሕንጻው የቀረ አንድም ነገር አልነበረም። ግድግዳውም ሆነ ጣሪያው ወድሟል። የመስተዋት ፍንጥርጣሪዎች መትተውኝ ነበር። ፊቴ ደም በደም ሆኗል። ፊቴ ላይ በዱላ የተደበደብኩ ያህል ነበር።” አላን አንድ ዓይኑ ማየት የተሳነው ሲሆን በፍንዳታው ምክንያት የመስማት ችሎታውንም አጥቷል።

በፍጥነት የቀረበ እርዳታ

በአደጋው በተነኩ 11 የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ሽማግሌዎች በተቻላቸው ፍጥነት እያንዳንዱን የጉባኤ አባል ጠይቀው የደረሰባቸውን አደጋና ጉዳት አጣሩ። ወዲያው ፈቃደኛ ሠራተኞች የባሰ ጉዳት ወደደረሰባቸው አባላት ተላኩ። ፈቃደኛ ሠራተኞቹም 60 በሚያህሉ የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶች ላይ ጉዳት እንደደረሰ ከማጣራታቸውም በላይ 10 ለሚያህሉ ቤተሰቦች መጠለያ አዘጋጅተዋል። በተጨማሪም ሁለት የመንግሥት አዳራሾችን ጠግነዋል። ከዚህም በላይ የኢንሹራንስ ክፍያ የሚያገኙበትን ተግባራዊ እርዳታ አበርክተዋል።

ካተሪንና ሚሸል የሚኖሩት ከፋብሪካው ፊት ለፊት ነበር። ፍንዳታው በደረሰበት ጊዜ ካተሪን በመኪናዋ ወጣ ብላ ነበር። እንዲህ በማለት ትገልጻለች:- “በመጀመሪያ እንደ ምድር መናወጥ የመሰለ ነገር ተሰማን። ከጥቂት ሰኮንዶች በኋላ ፍንዳታውን ሰማን። ከዚያም ጭሱ ወደላይ ሲወጣ አየን። ወደ ጎረቤቶቼ መንዳት ጀመርኩ። በውጊያ ቀጠና ውስጥ የገባን መስሎ ነበር የተሰማን። ሁሉም ቤቶች ፈርሰዋል፣ የሱቅ መስኮቶች ተሰባብረዋል። ሰዎች በየጎዳናው ይሯሯጣሉ። ሌሎች ደግሞ መንገድ ላይ ተቀምጠው ወይም ተኝተው ይጮሀሉ እንዲሁም ያለቅሳሉ። የቤታችን መስኮቶች፣ ብረቶቹ ሳይቀሩ ተገንጥለው የወደቁ ሲሆን በቤቱ ላይ የቀረ በር አልነበረም። ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በአፋጣኝ መጥተው ረዱን። ከሰዓት በኋላ ከጉባኤው የመጡ ወንድሞችና እህቶች ባልዲና መጥረጊያ ይዘው በመምጣት ካጸዱልን በኋላ መስኮቶቹን በፕላስቲክ ሸፈኑልን።”

አላንና ሊልያንም የሚኖሩት ከፋብሪካው አጠገብ ነበር። ፍንዳታው ቤታቸውን አውድሞባቸዋል። “ሁሉ ነገር ደቅቋል” ይላል አላን። “ግድግዳዎቹና የወለሉ ንጣፎች ተሰነጣጥቀዋል። መስኮቶቹ፣ በሮቹና የቤቱ ዕቃዎች በሙሉ ተሰባብረዋል። የቀረ አንድም ነገር አልነበረም። ክርስቲያን ወንድሞቻችን ወዲያው ደረሱልንና ረዱን። የኛን አፓርተማ ካጸዱልን በኋላ በሕንጻው ውስጥ የሚገኙ ሌሎች አፓርተማዎችን በማጽዳት እርዳታ አበረከቱ። ይህን የሚያህሉ ሰዎች ሊረዱን መምጣታቸው ጎረቤቶቻችንን በጣም አስደንቋቸዋል።” ፍንዳታው በደረሰበት ዕለት ጠዋት አላን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው ደውሎ ጠርቶት ስለነበር ወደዚያው ሄዶ ነበር። ሊልያን ደግሞ ለአንድ ጉዳይ ወጥታ ነበር። በዚህ ምክንያት ፍንዳታው በደረሰበት ጊዜ ሁለቱም ቤት አልነበሩም።

የይሖዋ ምሥክሮች እርዳታ ይሰጡ የነበረው ለጉባኤው አባላት ብቻ አልነበረም። እርስ በርሳቸው ከተረዳዱ በኋላ የጎረቤቶቻቸውን አፓርተማዎች በማጽዳትና የተሰባበሩ መስኮቶችን በመጠገን እርዳታ አበርክተዋል። ጎረቤቶቹ በጣም ከማመስገናቸውም በላይ ለተሰጣቸው እርዳታ ምንም ዓይነት ክፍያ ባለመጠየቃቸው በጣም ተገርመዋል።

በተጨማሪም በደረሰው አደጋ ስፋት ተደናግጠው የሚይዙት የሚጨብጡት ለጠፋቸው የአካባቢው ባለ ሥልጣናት እርዳታ ሰጥተዋል። ምሥክሮቹ ትምህርት ቤቶችንና ሌሎች የሕዝብ መገልገያ ሕንጻዎችን አጽድተዋል። በአንድ አካባቢ ባለ ሥልጣናት የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ፈቃደኛ ሠራተኞችን ልከው ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ የችግሩን መጠን አጣርተው እንዲያሳውቋቸው አድርገዋል።

መንፈሣዊ እርዳታ መስጠት

ፍንዳታው በደረሰበት አካባቢ ከሚኖሩ ምሥክሮች መካከል ብዙዎቹ ከቁሳዊ እርዳታ በተጨማሪ መንፈሣዊ እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋቸው ነበር። በመሆኑም ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና የየጉባኤው ሽማግሌዎች በአደጋው የተጎዱትን ወንድሞችና እህቶች በሙሉ ተዘዋውረው ጠይቀዋል። ይህም ምስጋና የሚቸረው እርዳታ ነበር። ካተሪን “ሽማግሌዎቹ ተረባርበው ረዱን። ሊያጽናኑንና ሊያበረታቱን መጡ። እንደ እውነቱ ከሆነ ከቁሳዊው እርዳታ ይበልጥ ያስፈልገን የነበረው ይህ ነበር” ብላለች።

ከአደጋው በኋላ በአጣዳፊ ሁኔታ ተግባር ላይ የዋለውን ክርስቲያናዊ ፍቅር የተመለከቱ አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች የሰጧቸው ጥሩ አስተያየቶች አሉ። ከባድ ጉዳት የደረሰበት አንድ ምሥክር “ነገ የሚሆነውን ጨርሶ አናውቅም። እያንዳንዱ ቀን የመጨረሻው ቀናችን እንደሆነ አድርገን በማሰብ ዘወትር ማገልገል ይኖርብናል” ብሏል። (ያዕቆብ 4:​13-15) ሌላ ምሥክር “ይህ ሁሉ ከማንኛውም ቁሳዊ ነገር ጋር ተገቢ ያልሆነ ቁርኝት መፍጠር እንደሌለብን እንድንገነዘብ ረድቶናል። በእርግጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር በይሖዋ ሕዝቦች መካከል መገኘት ነው።”

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ባንዣማ እና ኩዲር

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አላን

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቱሉዝ፣ በፍንዳታው ማግስት

[ምንጭ]

© LE SEGRETAIN PASCAL/CORBIS SYGMA

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አላን እና ሊልያን