ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
ዛሬ ነገ ማለትና ጤና
በቫንኩቨር ሳን ጋዜጣ ላይ የተጠቀሰ አንድ ጥናት “ዛሬ ነገ እያሉ ሥራን ማዘግየት ሊያሳምም ይችላል” ይላል። በቅርቡ በቶሮንቶ፣ ካናዳ በተደረገ የአሜሪካ ሥነ እእምሮ ማኅበር ጉባኤ ላይ 200 በሚያክሉ የካናዳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ የተደረገ የጥናት ውጤት “መሥራት ያለባቸውን ሥራ ዛሬ ነገ እያሉ የሚያዘገዩ ሰዎች በዚህ ድርጊታቸው ምክንያት በራሳቸው ላይ ከፍተኛ የሆነ ጭነት ስለሚያስከትሉ ከሌሎቹ የበለጠ ከጭንቀት ጋር ተዛምዶ ባላቸው በሽታዎች እንደሚጠቁ አረጋግጧል። . . . የፈተናው ቀን እየቀረበ ሲመጣ በዛሬ ነገ ባዮቹ ላይ የሚደርሰው ውጥረት እያየለ ይሄዳል። በግድየለሽነት ያሳለፉት ጊዜ በራስ ምታት፣ በወገብ በሽታ፣ በጉንፋን፣ በእንቅልፍ እጦትና በተለያዩ አለርጂዎች ይተካል። ከሌሎቹ የበለጠ በመተንፈሻ አካላት ችግሮች፣ በተለያዩ ኢንፌክሽኖችና ራስ ምታቶች ተጠቅተዋል።”
ቋጥኝ ወጪ ዓሣ!
አንድ የብራዚላውያን የዓሣዎች ባሕርይ አጥኚ የሳይንቲስቶች ቡድን ዳርተር የተባለው የደቡብ አሜሪካ የዓሣ ዝርያ የአምስት ፎቅ ከፍታ ያለውን በውኃ የራሰና የሚያዳልጥ ቋጥኝ ከፏፏቴው ግርጌ አንስቶ ሲወጣ እንደተመለከተ ናቹራል ሂስትሪ መጽሔት ዘግቧል። “አጥኚዎቹ በምሥራቅ ብራዚል በጣም ፈጣን በሆነው የኤስፒሪቶ ሳንቶ ወንዝ ከአራት ሳንቲ ሜትር የማይበልጥ ቁመት ያላት ዓሣ በፏፏቴ የተጥለቀለቀ ገደል የመውጣት ችሎታ እንዳላት ተመልከተዋል።” ዳርተር የተባሉት ዓሦች ሁለቱን ትላልቅ ጥንድ መቅዘፊያዎች በመጠቀም ከፏፏቴው ግርጌ ያለውን አለት ቆንጥጠው ከያዙ በኋላ ቀስ ብለው “ከግራ ወደ ቀኝ እየተንቀሳቀሱና” በየመሐከሉ ዕረፍት እየወሰዱ የ15 ሜትር ከፍታ ያለውን ቋጥኝ ይወጣሉ። “ገለልተኛ በሆኑ ደጋማ አካባቢዎች ብዛታቸው ሳይቀንስ ሊኖሩ የቻሉት በዚህ ልዩ የሆነ ባሕርያቸው ምክንያት ሊሆን ይችላል ብለው ሳይንቲስቶች እንደሚያምኑ” ሪፖርቱ ይገልጻል። ይሁን እንጂ ቋጥኝ የመውጣት ችሎታ ያላቸው ዓሦች ዳርተሮች ብቻ አይደሉም። ትሮፒካል ጎቢስ እና ኤዥያን ሎችስ የተባሉትም ቋጥኝ የመውጣት ችሎታ አላቸው።
ፈጣኖቹ የፈረንሳይ ባቡሮች
በ1867 ከፓሪስ ወደ ማርሴይ የሚደረገው የባቡር ጉዞ 16 ሰዓት ይፈጅ ነበር። በ1960ዎቹ ዓመታትም ቢሆን ሰባት ሰዓት ተኩል ይፈጅ ነበር። በሰኔ 2001 ግን የፈረንሳይ ብሔራዊ ባቡር ድርጅት በሁለቱ ከተሞች መካከል አዲስ ፈጣን የባቡር መስመር ከፈተ። ይህ አዲስ ባቡር በሰዓት 300 ኪሎ ሜትር ፍጥነት ሲኖረው የ740 ኪሎ ሜትሩን ርቀት በሦስት ሰዓት ውስጥ ያጠናቅቃል። ከሊዮ ከተማ በስተደቡብ በሚገኝ የ250 ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ ባቡሮች 500 ድልድዮችን፣ ጠቅላላ ርዝመታቸው 17 ኪሎ ሜትር የሚደርሱ የሚያማምሩ የብረት ድልድዮችንና የ8 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸውን ዋሻዎች ያቋርጣሉ። አስፈላጊ ከሆነ “በሰዓት እስከ 20 የሚደርሱ ባቡሮች በሁለቱም አቅጣጫዎች አለአንዳች ሥጋት ሊጓዙ ይችላሉ” በማለት የፈረንሳዩ ዕለታዊ ጋዜጣ ለ ሞንድ ዘግቧል። በየሦስት ደቂቃ አንድ ባቡር ያልፋል ማለት ነው።
ውጥረት ያለባቸው ሕፃናት
“ልጅነት ከጭንቀትና ከሐሳብ ነጻ የሆነ የመቦረቂያ ጊዜ መሆኑ ቀርቷል” ይላል የሜክሲኮ ሲቲው ኤል ኡኒቨርሳል ጋዜጣ። ባሁኑ ጊዜ አንድ የአሥር ዓመት ልጅ በ1950 አንድ የ25 ዓመት ሰው ይደርስበት ከነበረው ውጥረት ጋር የሚተካከል ውጥረት እንደሚደርስበት ተመራማሪዎች ደምድመዋል። ይህ ውጥረት በአብዛኛው የሚመጣው ከትምህርት ቤትና ወላጆች ወደፊት የተሻለ ኑሮ እንዲኖር ያስችለዋል ብለው ከሚያስቧቸው እንቅስቃሴዎች ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ ተጨማሪ ጭነቶች “በልጁ ጤንነት፣ ዕረፍትና እድገት ላይ ጉዳት ያደርሳሉ” ይላል ጋዜጣው። ሪፖርቱ ወላጆች ልጆቻቸው በዛ ያለ ጊዜ ቤታቸው ማሳለፍ እንዲችሉ ያሉባቸውን ግዴታዎች ደግመው ቢያጤኑ ጥሩ እንደሚሆን አሳስቧል። እንዲህ ሲባል ግን ሙሉውን ከሰዓት በኋላ ሥራ ፈትተው ወይም ቴሌቪዥን ላይ ወይም ኮምፒውተር ላይ ተተክለው ይዋሉ ማለት አይደለም። “ወጣ ብለው ከሌሎች ልጆች ጋር ይጫወቱ፣ ይሯሯጡ፣ ብስክሌታቸውን ይንዱ፣ የተለያዩ ጨዋታዎችን ይጫወቱ ወይም ሥዕል ይሳሉ ማለት ነው።”
የባሕር ሙቀት መጨመር በዱር እንስሳት ላይ ጉዳት ያስከትላል
ሳይንቲስቶች ከአውስትራሊያ በስተ ደቡብ ምዕራብ 4, 600 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኸርድ ደሴት ባደረጉት ጉብኝት ባካባቢው እፅዋትና የዱር እንስሳት ብዛት ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንደደረሰ አስተውለዋል። ዌስት አውስትራሊያን ጋዜጣ “የኪንግ ፔንግዊን፣ የፈር ሲልና የኮርሞርናት ብዛት በጣም ጨምሯል። በአንድ ወቅት በበረዶ ክምር ተሸፍነው የነበሩ አካባቢዎች ዛሬ በእፅዋት ተሸፍነዋል” ሲል ዘግቧል። ኤሪክ ቮህለር የተባሉት የሥነ ሕይወት ምሁር በ1957 በደሴቲቱ በሞላ የነበሩት ጥንድ ፔንግዊኖች ሦስት ብቻ ነበሩ። “አሁን ግን ከ25, 000 የሚበልጡ አሉ” ብለዋል። ቮህለር እንደሚሉት የባሕሩ ሙቀት ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ በሦስት አራተኛ ዲግሪ ሴንቲግሬድ ከፍ ብሏል። አክለውም “ይህ ጭማሪ ብዙ አይምሰል እንጂ እንደምናየው ያለውን ለውጥ በማምጣት ረገድ ግን ከሚበቃ በላይ ነው” ብለዋል። የደሴቲቱ አየር ንብረት እየሞቀ ሄዶ አንዳንድ እፅዋትንና እንስሳትን ሊያኖር ከማይችልበት ደረጃ ላይ ይደርስ ይሆናል በማለት ሥጋታቸውን ገልጸዋል።
‘ሃይማኖት ሁለተኛ ደረጃ ተሰጥቶታል’
በቅርቡ ጎልማሳ በሆኑ የብራዚል ከተማ ድሃ ኗሪዎች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት 67 በመቶ የሚሆኑት ካቶሊኮች እንደሆኑ ቢናገሩም በኢየሱስ፣ በማርያምና በቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረተ ትምህርቶች እናምናለን የሚሉት ግን ከ35 በመቶ እንደማይበልጡ ገልጧል። በየሳምንቱ ቤተ ክርስቲያን ሄደው የሚያስቀድሱት ደግሞ ከዚህ ያነሱ ሲሆኑ እንዲያውም 30 በመቶ ብቻ ናቸው። በብራዚላውያን ጳጳሳት ብሔራዊ ጉባኤ ትእዛዝ የተካሄደው ይህ ጥናት ብዙዎች ከጋብቻ በፊት ስለሚፈጸም ወሲብ (44 በመቶ)፣ ስለ ፍቺ (59 በመቶ)፣ ፈትቶ ስለማግባት (63 በመቶ) እንዲሁም የወሊድ መቆጣጠሪያ ስለመጠቀም (73 በመቶ) ቤተ ክርስቲያኒቱ ከምታስተምረው ትምህርት ጋር አይስማሙም። የሃይማኖት
ምሁር የሆኑት ሴቬሪኖ ቪሴንቴ እንዳሉት ቤተ ክርስቲያን የቀሳውስት ቁጥር ማነሱ፣ በብራዚል የትምህርት ሥርዓት ላይ የነበራት ሥልጣን መመናመኑ፣ ስለ መሠረተ ትምህርቶች የምትሰጠው ማብራሪያ ጥልቀት የሌለው መሆኑ የነበራትን ቦታ እያጣች እንድትሄድ እንዳደረጓት ተናግረዋል። “አዲሱ የካቶሊካውያን ትውልድ እውነት አንፃራዊ ነው በሚል አስተሳሰብ ተኮትኩተው ያደጉ ሲሆኑ ለሃይማኖት የሚሰጡት አስፈላጊነት ሁለተኛ ደረጃ ነው” ብለዋል።በገዛ ቤት ውስጥ የሚያጋጥም አደጋ!
የብሪታንያ የንግድና ኢንዱስትሪ መሥሪያ ቤት ለ1999 ዓመት ባወጣው የሆስፒታል ስታትስቲክስ “በየሳምንቱ በቤት ውስጥ ባጋጠሙ አደጋዎች ምክንያት 76 ሰዎች እንደሞቱና ይህም አኃዝ በመንገድ ላይ በሚከሰት አደጋ ከሞቱት እንደሚበልጥ” የለንደን ዘ ጋርድያን ዘግቧል። በጣም ከተደጋገሙት የሞት ምክንያቶች መካከል “የእጅ መሣሪያዎች፣ ደረጃዎች፣ ምንጣፎችና የፈላ ውኃ ያለባቸው ጀበናዎች ይገኛሉ።” በየዓመቱ ከ3, 000 የሚበልጡ ሰዎች የቆሸሹ ልብሶች የተጠራቀሙበት ቅርጫት አደናቅፏቸው በመውደቅ፣ ከ10, 000 የሚበልጡ ሰዎች ካልሲያቸውን ወይም ጠባብ ሱሪያቸውን ለማጥለቅ ሲሞክሩ በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት፣ ከ13, 000 የሚበልጡ አትክልቶችን ሲያዘጋጁ በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት ሆስፒታል ይገባሉ። ከአንድ መቶ ሺህ የሚበልጡት ጉዳቶች ከአልኮል ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ናቸው። የአደጋዎች መከላከያ ማኅበር ቃል አቀባይ “በሥራ ቦታና በመንገዶች ላይ ጠንቃቆች ነን። እቤታችን ስንሆን ግን እንዘናጋለን። የፈላ ውኃ ያለበትን ጀበና ክዳን ለመክፈት ስትሞክሩ ጀበናውን ከነፈላው ውኃ እግራችሁ ላይ ብትጥሉት ከባድ ጉዳት ሊደርስባችሁ ይችላል” ብለዋል።
ዘመናዊ የባሪያ ንግድ
“በብሪታንያ የሚገኝ የአንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ባልደረባ የሆኑ ሰው በቅርቡ ባደረጉት ምርምር መሠረት በዓለም ዙሪያ ባርነት በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የአሁኑን ያህል የተስፋፋበት ጊዜ የለም” በማለት የለንደኑ ዚ ኢንዲፔንደንት ሪፖርት አድርጓል። በሱሪ የሮሃምፕተን ከተማ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት የኅብረተሰብ ሳይንስ ፕሮፌሰር ኬቨን ቤልዝ “እንዳሰሉት በአሁኑ ጊዜ 27 ሚልዮን የሚሆኑ ሰዎች በባርነት ቀንበር ሥር የሚኖሩ ሲሆን ይህም በሮማ ግዛት ከነበሩት ወይም ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ባሻገር ይሸጡ ከነበሩት ባሮች በልጦ ተገኝቷል” ሲል ጋዜጣው ዘግቧል። በዛሬው ጊዜ ያለው ባርነት ከዛሬ 150 ዓመት በፊት ከነበረው የተለየ ቢሆንም እንኳ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች “የኃይል ድርጊት በሚፈጽሙባቸው ወይም የኃይል ድርጊት እንደሚፈጽሙባቸው በሚዝቱባቸው ሰዎች ቁጥጥር ሥር ያሉ ሲሆን ለሚሰጡትም አገልግሎት ምንም አይከፈላቸውም” በማለት ቤልዝ ተናግረዋል። በአሁኑ ጊዜ በእጅጉ ተስፋፍቶ የሚገኘው የባርነት ዓይነት የኮንትራት ባርነት ሲሆን የተደራጁ ሕገወጥ ቡድኖች ከፍተኛ ደሞዝ የሚያስገኝ ሥራ እንደሚያስይዟቸው ቃል በመግባት ሰዎችን ወደ ውጭ አገር ይልካሉ። ይሁን እንጂ ሠራተኞቹ ወደተባለው አገር ከገቡ በኋላ ለላኳቸው ሰዎች ያለባቸውን ዕዳ ዝቅተኛ የሆነ ሥራ እየሠሩ ለመክፈል ስለሚገደዱ ጉልበታቸው ይበዘበዛል።
አካላዊ እንቅስቃሴ አዘውትሮ ማድረግ የሚያስገኘው ጥቅም
ብዙ ሰዎች አልፎ አልፎ ላባቸው ጠብ እስኪል አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ብዙ ሰዓት በመቀመጥ የቢሮ ሥራ በመሥራት ምክንያት የሚመጣውን ውፍረት፣ የልብ ሕመምና ሌሎች የጤና እክሎች ለመከላከል የሚችሉ ይመስላቸዋል። ይሁን እንጂ አንድ በቅርቡ የተደረገ ጥናት አልፎ አልፎ ብቻ ከሚደረግ ከባድ እንቅስቃሴ ይልቅ አዘውትሮ የሚደረግ መጠነኛ እንቅስቃሴ የአካል ክፍሎችን ተግባራት በማንቀሳቀስ ረገድ የተሻለ መሆኑን እንዳመለከተ የጀርመኑ ሱድ ዶቸ ሳይቱንግ አመልክቷል። የኔዘርላንድ ተመራማሪ የሆኑት ክላስ ዌስተርተርፕ ጥናት የተደረገባቸውን 30 ሰዎች የየደቂቃ የኃይል ፍጆታ ተከታትለዋል። የጥናቱ ውጤት አንድ ሰው “የማይንቀሳቀስባቸውን ጊዜያት በጣም ኃይለኛ በሆነ እንቅስቃሴ ለማካካስ ከሚሞክር ይልቅ” በዕለት ተዕለት ተግባሩ ላይ ተጨማሪ አካላዊ እንቅስቃሴ ቢያደርግ የተሻለ እንደሚሆን አመልክቷል። ሪፖርቱ “በተቻለ መጠን ብዙ ጊዜ መቀመጥና መቆም የሚጠይቁ ሥራዎችን ማፈራረቅ፣ በእግር መሄድ ወይም ብስክሌት መንዳት” ጥሩ እንደሚሆን ሐሳብ ሰጥቷል።