ወንዶች ሴቶችን የሚደበድቡት ለምንድን ነው?
ወንዶች ሴቶችን የሚደበድቡት ለምንድን ነው?
አንዳንድ ጠበብት እንደሚሉት ከሆነ በትዳር ጓደኞቻቸው የሚገደሉት ሴቶች ቁጥር በሌሎች ሰዎች ከሚገደሉት ሴቶች ጠቅላላ ቁጥር ሳይበልጥ አይቀርም። በትዳር ጓደኛ ላይ የሚፈጸመውን በደል ማስቀረት የሚቻልበትን መንገድ ለመሻት በርካታ ጥናቶች ተካሂደዋል። ሚስቱን የሚደበድበው ምን ዓይነት ወንድ ነው? የልጅነት ሕይወቱ ምን ይመስላል? ይጠናኑ በነበረበት ወቅት የኃይለኛነት ባሕርይ ይንጸባረቅበት ነበር? ለሚሰጠው የሕክምና እርዳታ ምን ዓይነት ምላሽ ይሰጣል?
ሚስቶቻቸውን የሚደበድቡ ወንዶች ሁሉ አንድ ዓይነት እንዳልሆኑ ጠበብት መገንዘብ ችለዋል። በአንደኛው ጽንፍ ያለው ወንድ ለዘብ ያለ ነው። መሣሪያ የማይጠቀም ከመሆኑም በላይ በትዳር ጓደኛው ላይ በደል የመፈጸም ልማድ የለውም። የኃይል ድርጊት ለመፈጸም የሚነሳሳው አልፎ አልፎ ሲሆን ለእንዲህ ዓይነቱ ድርጊት የሚገፋፉት በሕይወቱ ውስጥ የሚያጋጥሙት ሁኔታዎች ሊሆኑ ይችላሉ። በሌላው ጽንፍ ያለው ወንድ ደግሞ ሚስቱን የመደብደብ ሥር የሰደደ ልማድ የተጠናወተው ሰው ነው። በሚስቱ ላይ የሚያደርሰው በደል ቀጣይነት ያለው ከመሆኑም በላይ እምብዛም የጸጸት ስሜት አያድርበትም።
ይሁን እንጂ ሚስቶቻቸውን የሚደበድቡ ወንዶች ሁኔታ የሚለያይ መሆኑ በሴቶች ላይ የሚፈጸመው አንዳንዱ ድብደባ ብዙም አሳሳቢ አይደለም ሊያሰኝ አይችልም። እንዲያውም የትኛውም ዓይነት አካላዊ በደል ጉዳት ብሎም ሞት ሊያስከትል ይችላል። በመሆኑም አንድ ወንድ ሚስቱን የሚደበድበው አልፎ አልፎ መሆኑና የሌላውን ያህል የከፋ ጉዳት የማያደርስ መሆኑ ከተጠያቂነት ነፃ ሊያደርገው አይችልም። “ተቀባይነት ያለው” የድብደባ ዓይነት የለም። ይሁንና አንድ ወንድ በቀሪው የሕይወት ዘመኑ ሊንከባከባት ቃል ገብቶ የወሰዳትን ሚስቱን እንዲደበድብ የሚያነሳሱት ነገሮች ምን ሊሆኑ ይችላሉ?
ከቤተሰብ ጋር ያለው ትስስር
አካላዊ በደል የሚፈጽሙት ብዙዎቹ ወንዶች ራሳቸው በእንዲህ ዓይነት ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ መሆናቸው ምንም አያስገርምም። በትዳር ጓደኞች ላይ የሚፈጸመውን በደል ከሁለት አሥርተ ዓመታት በላይ ሲያጠኑ የቆዩት ማይክል ግሮች “ሚስቶቻቸውን የሚደበድቡ አብዛኞቹ ወንዶች ‘ከጦርነት ቀጣናዎች’ በማይለዩ ቤቶች ውስጥ ያደጉ ናቸው” ሲሉ ጽፈዋል። “በሕፃንነታቸውና በልጅነታቸው ያደጉበት ቤት ‘ዕለት ተዕለት’ ስሜታዊና አካላዊ በደል የሚፈጸምበትና ጥላቻ የነገሠበት ነበር።” አንዲት ባለሙያ እንዳሉት ከሆነ እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ እያየ ያደገ ወንድ “አባቱ ለሴቶች ያለው ንቀት ገና በልጅነቱ ሊጋባበት ይችላል። ልጁ አንድ ወንድ ምንጊዜም ሴቶችን በቁጥጥሩ ሥር ማድረግ እንዳለበትና ይህን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ በማስፈራራት፣ ጉዳት በማድረስና በማዋረድ እንደሆነ ይማራል። በተጨማሪም በአባቱ ዘንድ ተቀባይነት
ለማግኘት የተሻለው መንገድ አባቱ የሚያደርገውን ማድረግ እንደሆነ ይማራል።”መጽሐፍ ቅዱስ የአንድ ወላጅ ጠባይ በልጁ ላይ በጎም ይሁን መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል በግልጽ ይናገራል። (ምሳሌ 22:6፤ ቆላስይስ 3:21) እርግጥ አንድ ወንድ ያደገበት ቤተሰብ ሁኔታ ሚስቱን ለመደብደብ ሰበብ ሊሆነው ባይችልም ይህ የጠበኛነት መንፈስ ዘሩ የት እንደተዘራ ለመገንዘብ ሊረዳ ይችላል።
የባሕል ተጽዕኖ
በአንዳንድ አገሮች ሴትን መደብደብ ተቀባይነት ያለው አልፎ ተርፎም ያለ ነገር እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። የተባበሩት መንግሥታት ያወጣው አንድ ሪፖርት “ብዙዎቹ ኅብረተሰቦች ባል ሚስቱን የመደብደብ ወይም የማስፈራራት መብት አለው የሚል ሥር የሰደደ እምነት አላቸው” ሲል ገልጿል።
እንዲህ ያለው በደል ተቀባይነት በማያገኝባቸው አገሮችም እንኳን ብዙዎቹ ግለሰቦች የኃይለኛነት ጠባይ ያዳብራሉ። አንዳንድ ወንዶች በዚህ ረገድ ያላቸው ጭፍን አስተሳሰብ እጅግ ያስገርማል። የደቡብ አፍሪካው ዊክሊ ሜይል ኤንድ ጋርዲያን እንደሚለው ከሆነ በኬፕ ባሕረ ገብ መሬት የተካሄደው ጥናት በትዳር ጓደኞቻቸው ላይ በደል እንደማይፈጽሙ ከተናገሩት ወንዶች መካከል አብዛኞቹ ሴትን መምታት ተቀባይነት እንዳለውና ይህ እንደ ኃይል ድርጊት ተደርጎ ሊታይ እንደማይችል መናገራቸውን አመልክቷል።
እንዲህ ዓይነቱ የተዛባ አስተሳሰብ ብዙውን ጊዜ የሚጀምረው በልጅነት እንደሆነ የታወቀ ነው። ለምሳሌ ያህል በብሪታንያ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከ11 እስከ 12 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙት ወንዶች ልጆች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት አንዲት ሴት አንድን ወንድ በምታበሳጨው ጊዜ ቢመታት አግባብ ነው የሚል እምነት አላቸው።
ለመደብደብ ምክንያት አይሆንም
ከላይ የተዘረዘሩት ነጥቦች በትዳር ጓደኛ ላይ በደል እንዲፈጸም የሚያደርጉ ሁኔታዎችን ግልጽ ለማድረግ ሊረዱ ይችላሉ። ሆኖም ድርጊቱን ለመፈጸም ሰበብ ሊሆኑ አይችሉም። ኤፌሶን 5:28-30
በአጭሩ፣ የትዳር ጓደኛን መደብደብ በአምላክ ፊት ከባድ ኃጢአት ነው። በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚከተለውን እናነባለን:- “ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፣ ነገር ግን . . . ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት፣ ይመግበዋል ይከባከበውማል።”—መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ የነገሮች ሥርዓት “የመጨረሻ ቀኖች” ውስጥ ብዙዎች “በሌሎች ላይ በደል የሚፈጽሙ፣” “የተፈጥሮ ፍቅር የሌላቸው” እና “ጨካኞች” እንደሚሆኑ ከረጅም ጊዜ በፊት ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-3፤ ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል ) በትዳር ጓደኞች ላይ የሚፈጸመው በደል እየተስፋፋ መሄዱ በዚህ ትንቢት ላይ በተጠቀሰው ዘመን እንደምንኖር የሚያሳይ አንድ ምልክት ነው። ይሁን እንጂ አካላዊ በደል የሚደርስባቸውን ሰዎች ለመርዳት ምን ሊደረግ ይችላል? የትዳር ጓደኛቸውን የሚደበድቡ ሰዎች ይህን ጠባያቸውን ሊለውጡ ይችሉ ይሆን?
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ሚስቱን የደበደበ ግለሰብ የማያውቀውን ሰው ከደበደበ ግለሰብ እኩል ወንጀለኛ ነው።”—ዌን ሜን ባተር ዊሜን
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የወንድ ትምክህተኝነት ዓለም አቀፋዊ ችግር
እንግሊዝኛ ተናጋሪው ዓለም “ማቺዝሞ” የሚለውን ቃል ከላቲን አሜሪካ ወርሷል። ይህ ቃል የወንድ እብሪተኝነትን የሚያመለክት ሲሆን ወንዶች ለሴቶች ያላቸውን የተዛባ አመለካከት ለመግለጽ ይሠራበታል። ይሁንና ቀጥሎ የተገለጹት ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት የወንድ ትምክህተኝነት በላቲን አሜሪካ ብቻ የሚንጸባረቅ ችግር አይደለም።
ግብፅ:- በእስክንድርያ ለሦስት ወራት የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳመለከተው በሴቶች ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ዋናው ምክንያት በቤት ውስጥ የሚፈጸም ጥቃት ነው። የድንገተኛ አደጋ እርዳታ ወደሚሰጡ ተቋማት ከሚሄዱት ሴቶች መካከል 27.9 በመቶ የሚሆኑት በቤት ውስጥ በሚፈጸም ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው።—የአራተኛው የዓለም የሴቶች ጉባኤ 5ኛ ጥናታዊ ዘገባ
ታይላንድ:- ከባንኮክ ወጣ ብሎ በሚገኝ አንድ ትልቅ የመኖሪያ ሰፈር ከሚገኙ ባለትዳር ሴቶች መካከል 50 በመቶ የሚሆኑት በየጊዜው ድብደባ ይደርስባቸዋል።—የሴቶች ጤና የፓስፊክ ክልል ተቋም
ሆንግ ኮንግ:- “በትዳር ጓደኞቻቸው ድብደባ እንደተፈጸመባቸው የሚናገሩ ሴቶች ቁጥር ባለፈው ዓመት ከ40 በመቶ በላይ አሻቅቧል።”—ሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት፣ ሐምሌ 21, 2000
ጃፓን:- በ1995 መጠለያ የሚፈልጉ ሴቶች ቁጥር 4, 843 የነበረ ሲሆን በ1998 ደግሞ ወደ 6, 340 አሻቅቧል። “ከእነዚህ መካከል አንድ ሦስተኛ ገደማ የሚሆኑት ራሳቸውን የሚያስጠጉበት መጠለያ የፈለጉት ጠበኛ በሆኑት ባሎቻቸው ሳቢያ እንደሆነ ገልጸዋል።”—ዘ ጃፓን ታይምስ፣ መስከረም 10, 2000
ብሪታንያ:- “በብሪታንያ በየስድስት ሴኮንዱ በሆነ ቤት ውስጥ የግዳጅ ወሲብ፣ ድብደባ ወይም በስለት የመውጋት ወንጀል ይፈጸማል።” የለንደን ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ክፍል ያወጣው ሪፖርት እንደሚገልጸው ከሆነ “ፖሊስ በየዕለቱ በቤት ውስጥ ጥቃት ከተፈጸመባቸው ሰዎች 1, 300 የስልክ ጥሪ የሚደርሰው ሲሆን ይህም በዓመት ከ570, 000 በላይ ይሆናል። ከእነዚህ መካከል ሰማንያ አንድ በመቶ የሚሆኑት በወንዶች ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ናቸው።”—ዘ ታይምስ፣ ጥቅምት 25, 2000
ፔሩ:- ለፖሊስ ሪፖርት ከሚደረጉት ወንጀሎች መካከል ሰባ በመቶ የሚሆነው በባሎቻቸው በሚደበደቡ ሴቶች ላይ የሚፈጸመውን በደል ይጨምራል።—የሴቶች ጤና የፓስፊክ ክልል ተቋም
ሩስያ:- “በአንድ ዓመት ውስጥ 14, 500 ሩስያውያን ሴቶች በባሎቻቸው የተገደሉ ሲሆን ሌሎች 56, 400 የሚሆኑ ደግሞ በቤት ውስጥ በተፈጸመባቸው ጥቃት የአካል ጉዳተኛ ሆነዋል ወይም ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።”—ዘ ጋርዲያን
ቻይና:- “ቀደም ሲል ያልነበረ ችግር ነው። አሁን ግን በተለይ በከተሞች ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ነው” ሲሉ የቺንግሉን የቤተሰብ ማዕከል ዲሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ቸን ዪዩን ተናግረዋል። “ጎረቤቶች ለማከላከል የሚያደርጉት ጥረት በቤት ውስጥ የሚፈጸመውን ጥቃት እንደ ቀድሞ ሊገታው አልቻለም።”—ዘ ጋርዲያን
ኒካራጉዋ:- “በኒካራጉዋ በሴቶች ላይ የሚፈጸመው በደል በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው። አንድ ጥናት እንዳመለከተው ባለፈው ዓመት ብቻ 52 በመቶ የሚሆኑ ኒካራጓውያን ሴቶች በባሎቻቸው በደል ተፈጽሞባቸዋል።”—የቢ ቢ ሲ ዜና አገልግሎት
[ገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አደጋ ጠቋሚ ምልክቶች
በዩ ኤስ ኤ የሮድ አይለንድ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ በሆኑት ሪቻርድ ጄ ጄልስ መሪነት የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከሆነ ከዚህ ቀጥሎ የተዘረዘሩት ነገሮች በቤት ውስጥ አካላዊም ሆነ ስሜታዊ በደል ሊፈጸም እንደሚችል የሚጠቁሙ ምልክቶች ናቸው:-
1. ሰውየው ቀደም ሲል በሆነ መንገድ በቤት ውስጥ በሚፈጸም በደል ተሳታፊ ከነበረ።
2. ሥራ ከሌለው።
3. የተከለከሉ አደገኛ ዕፆችን ቢያንስ በዓመት ውስጥ አንድ ጊዜ የሚወስድ ከሆነ።
4. ከወላጆቹ ጋር ይኖር በነበረበት ጊዜ አባቱ እናቱን ሲመታ ይመለከት ከነበረ።
5. ሳይጋቡ አብረው የሚኖሩ ከሆነ።
6. ሥራ ቢኖረውም እንኳ ዝቅተኛ ደሞዝ የሚከፈለው ከሆነ።
7. የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያላጠናቀቀ ከሆነ።
8. ከ18 እስከ 30 ዓመት ድረስ ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ከሆነ።
9. ከወላጆቹ አንዱ ወይም ሁለቱም በልጆቻቸው ላይ ኃይል ይጠቀሙ ከነበረ።
10. በከባድ ድህነት ውስጥ የሚኖር ከሆነ።
11. ሰውየውና ሴትየዋ ያደጉበት ባሕል የተለያየ ከሆነ።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቤት ውስጥ የሚፈጸም የኃይል ድርጊት በልጆች ላይ ከባድ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል