በእርግጥ ለውጥ እንዲያደርጉ መርዳት ይቻል ይሆን?
በእርግጥ ለውጥ እንዲያደርጉ መርዳት ይቻል ይሆን?
“አንድ ሰው ለውጥ እንዲያደርግ ማንም ሰው ሊያስገድደው አይችልም። ግለሰቡ ራሱ ለውጥ ለማድረግ ውስጣዊ ፍላጎት ሊኖረው ይገባል።”—ቪቭዬን ስተርን፣ ኤ ሲን አጌነስት ዘ ፊውቸር—ኢምፕሪዝንመንት ኢን ዘ ወርልድ።
እስረኞች እውነተኛ ለውጥ እንዲያደርጉ መርዳት የሚቻለው አስፈላጊውን እውቀት እንዲቀስሙና አመለካከታቸውም ሆነ የሥነ ምግባር መመሪያቸው እንዲለወጥ ማድረግ ሲቻል ብቻ ነው። እስረኞችን ለማስተማርና ለመርዳት ጥረት የሚያደርጉ ቅን ልቦና ያላቸው ሰዎች መኖራቸው ምንም ጥርጥር የለውም። እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ለሌሎች በማሰብ ያከናወኑት መልካም ተግባር የብዙ እስረኞችን አድናቆት ሳያገኝ አላለፈም።
አንዳንድ ሰዎች የእስር ቤት ሥርዓት በጥቅሉ የሚለወጥ ባለመሆኑ እስረኞች በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆነው ለውጥ ማድረግ የመቻላቸው አጋጣሚ በጣም የመነመነ ነው በማለት ይከራከሩ ይሆናል። ሰዎችን እስር ቤት መክተት በራሱ አዳዲስ የሥነ ምግባር መመሪያዎችን በውስጣቸው ለመቅረጽ የማያስችል መሆኑ የታመነ ቢሆንም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አንዳንዶች ሕይወታቸውን እንዲለውጡ ረድቷቸዋል። ይህም በግለሰብ ደረጃ ለውጥ እንዲያደርጉ መርዳት እንደሚቻል ያሳያል።
በዛሬው ጊዜ አንዳንድ እስረኞች በመጽሐፍ ቅዱስ እርዳታ ትክክለኛ አስተሳሰብና ምግባር ለማፍራት የሚያስችል ለውጥ እያደረጉ ነው። እንዴት? የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በመከተል ነው:- “የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።” (ሮሜ 12:2) ይህ እየሆነ ያለው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ የሚጫወተው ሚና
እስረኞች ቀደም ሲል ለፈጸሟቸው ድርጊቶች ንስሐ እንዲገቡ በመርዳት ረገድ ሃይማኖት ትልቅ ሚና ሊጫወት ይችላል የሚል እምነት ያላቸው በርካታ ሰዎች አሉ። እርግጥ ከዚህ ጋር የተያያዘው ትልቁ ችግር እስረኛው ከብረት አጥሮች ጀርባ በነበረበት ጊዜ በባሕርይው ላይ ያመጣው ለውጥ እስር ቤቱን ለቅቆ ሲወጣ እልም ብሎ ሊጠፋ የሚችል መሆኑ ነው። አንድ የሕግ ታራሚ ሁኔታውን እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “ብዙ ሰዎች ክርስቶስን የተቀበሉት እዚህ ነው። ከእስር ቤት ሲወጡ ግን ክርስቶስንም እዛው ትተውት ይሄዳሉ!”
ከተሞክሮ መረዳት እንደተቻለው ወንጀለኛው በውስጡ ማለትም በአእምሮውና በልቡ ውስጥ እውነተኛ ለውጥ ማድረግ አለበት። ይህ ደግሞ ቀደም ሲል ለፈጸመው ስህተት ከልብ ንስሐ መግባቱን በሚያሳይ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ፕሮግራም ግለሰቡ አምላክ ስለ ክፋት ያለው አመለካከት ምን እንደሆነና የክፋት ድርጊት ተገቢ ያልሆነው ለምን እንደሆነ እንዲገነዘብ ሊረዳው ይችላል። ይህም በእንዲህ ዓይነቱ ጎዳና መቀጠል እንዳይመርጥ ጠንካራ ምክንያት ሊሆነው ይችላል።
የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በርካታ እስር ቤቶች ውስጥ እንዲህ ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ፕሮግራም እያካሄዱ ሲሆን ግሩም ውጤቶችም አግኝተዋል። (ገጽ 10ን ተመልከት።) “መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሕይወት ዓላማና ወደፊት የሰው ልጆች ስለሚያገኟቸው በረከቶች የሚሰጠውን ሐሳብ ማወቅ የሚያስችል እርዳታ አግኝተናል” ሲል አንድ እስረኛ አስተያየቱን ሰጥቷል። አክሎም “ወደር የማይገኝለት ትምህርት ነው!” ሲል ተናግሯል። ሌላ የሕግ ታራሚ ደግሞ “የምናደርጋቸው ውሳኔዎች አምላክ በሰጠው ምክር ላይ የተመሠረቱ ናቸው። . . . በራሳችን ላይ ለውጥ እያየን ነው። በሕይወት ውስጥ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮች ምን እንደሆኑ አውቀናል” ብሏል።
እርግጥ ነው፣ የለውጥ ሂደቱ አስፈላጊነት በእስር ቤት አጥሮች ውስጥ ብቻ የተወሰነ አይደለም። እስር ቤቶች ለገጠማቸው ቀውስ እውነተኛ መፍትሔ የሚሆነው ለእስር ቤቶች መቋቋም ምክንያት የሆነውን ነገር እንዲወገድ ማድረግ ነው። የበርካታ እስረኞችን ልብ ከነኩት አስደሳች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች መካከል አንዱ አምላክ በሰጠው በሚከተለው ተስፋ ውስጥ ተገልጿል:- “ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉ . . . ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:9, 29
ይህ በሚከናወንበት ጊዜ አፍቃሪ የሆነና ጽኑ አቋም ያለው የማይጠፋ መንግሥት የአምላክን የላቁ መስፈርቶች ያስፈጽማል። ይህ መንግሥት ክርስቲያኖች የሚጸልዩለት በክርስቶስ የሚመራ የአምላክ ሰማያዊ መስተዳድር ነው። (ማቴዎስ 6:10) በዚያ አዲስ ዓለም ውስጥ እያንዳንዱ ነዋሪ የአምላክን የላቁ ሕጎች በመማር ትልቅ ለውጥ ያደርጋል። በዚያን ጊዜ ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ “ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለች።” (ኢሳይያስ 11:9) ውጤቱስ ምን ይሆናል? ሕግ አክባሪ የሆኑት የአዲሱ ዓለም ነዋሪዎች “በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።”—መዝሙር 37:11
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የተስፋ ብርሃን መፈንጠቅ
ፈቃደኛ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች አገልጋዮች ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት በዩ ኤስ ኤ ጆርጅያ ግዛት በሚገኘው የአትላንታ ፌዴራል ወኅኒ ቤት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ስኬታማ የትምህርት ፕሮግራም አካሂደዋል። በእነዚህ ጊዜያት ከ40 በላይ የሚሆኑ እስረኞች የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክር አገልጋዮች እንዲሆኑ መርዳት የተቻለ ሲሆን ሌሎች ከ90 የሚልቁ እስረኞችም ቋሚ ከሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
በቅርቡ ንቁ! መጽሔት የሌሎችን ጥቅም በማስቀደም በዚህ እስር ቤት ውስጥ ሲሠሩ የቆዩ የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎችን አነጋግሮ ነበር።
▪ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አንዳንድ እስረኞች ሕይወታቸውን እንዲለውጡ በማነሳሳት ረገድ እጅግ ውጤታማ የሆነው ለምንድን ነው?
ዴቪድ:- ብዙዎቹ እስረኞች ከልጅነታቸው ጀምሮ ፍቅር የተነፈጉ ናቸው። ስለዚህ አምላክ እንደሚወዳቸው ሲገነዘቡ እንዲሁም ልባቸውን በጸሎት ሲያፈስሱለትና እርሱም ለጸሎታቸው መልስ ሲሰጣቸው እውን ሆኖ ይታያቸዋል። በምላሹም ልባቸው እርሱን ለማፍቀር ይገፋፋል።
ሬይ:- ካስጠናኋቸው እስረኞች አንዱ በልጅነቱ በደል ተፈጽሞበታል። ወደ ይሖዋ እንዲሳብ ያደረገው ነገር ምን እንደሆነ ስጠይቀው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ስትማር ይሖዋ ችግርህን እንደሚረዳ ትገነዘባለህ የሚል መልስ ነበር የሰጠኝ። ይህን መገንዘቡ እንዲህ ዓይነቱ አፍቃሪ አምላክ ያለውን ስብዕና የበለጠ ለማወቅ እንዲነሳሳ አደረገው።
▪ አንዳንድ ሰዎች እስረኞች ወደ ሃይማኖት ፊታቸውን የሚያዞሩት ስውር ዓላማ ስላላቸው ነው። የእስራት ጊዜያቸው እንዲቀነስላቸው ለማድረግ ወይም እንዲሁ ለጊዜ ማሳለፊያ ያህል ብለው ነው ይላሉ። እናንተ ከተሞክሮ ያስተዋላችሁት ነገር ምንድን ነው?
ፍሬድ:- እስረኞቹ ለማጥናት ሲመጡ ስሜታቸውን ለመማረክ አንሞክርም። እንዲሁ መጽሐፍ ቅዱስ ከማስጠናት ሌላ የምናደርገው ነገር የለም። ብዙም ሳይቆይ መጽሐፍ ቅዱስ ከማስተማር ሌላ ምንም የምናደርገው ነገር እንደሌለ ይገነዘባሉ። ከፍርድ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ እርዳታ እንዳደርግላቸው የጠየቁኝ እስረኞች ነበሩ። እንዲህ ያሉትን ጉዳዮች ከእነሱ ጋር አልወያይም። በመሆኑም ወደ ጥናት ቡድኑ መጥተው ረዘም ላለ ጊዜ የሚቀጥሉት መጽሐፍ ቅዱስ የመማር እውነተኛ ፍላጎት ያላቸው ናቸው።
ኒክ:- አንዱ የማስተውለው ነገር አንዳንድ እስረኞች በወኅኒ ቤቱ ውስጥ እያሉ የሚያደርጉት ለውጥ ነው። አንዳንዶቹ የተጠመቁ አገልጋዮች ከመሆናቸውም በላይ ከሌሎች እስረኞች ብዙ ችግር ደርሶባቸዋል። ይህ ለእነሱ በጣም ከባድ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ልባቸውን ባይነካው ኖሮ በእነዚህ ሁኔታዎች ሥር ታማኝ ሆነው ሊቀጥሉ አይችሉም ነበር።
ኢስራኤል:- በጥቅሉ ስለ ይሖዋ ለመማር ጥልቅ ፍላጎት ያላቸው ናቸው። ይህን ፍላጎታቸውንም ስሜት በሚነካ መንገድ ይገልጹታል። ከልብ የመነጨ ፍላጎት መሆኑን መረዳት ትችላለህ።
ጆ:- እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚሆኑት እስረኞች ሕይወታቸው ሊበላሽ የቻለው ለምን እንደሆነ ይገነዘባሉ። በተጨማሪም ሕይወታቸውን መለወጥ የሚችሉበት አጋጣሚ እንዳለ ይገነዘባሉ። የተስፋ ብርሃን ይፈነጥቅላቸዋል። በመሆኑም ይሖዋ የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ የሰጣቸውን ተስፋዎች ፍጻሜ በታላቅ ጉጉት መጠባበቅ ይችላሉ።
▪ የእስር ቤት ሥርዓቱ በራሱ ወንጀለኞችን መለወጥ የማይችለው ለምንድን ነው?
ጆ:- የቅጣት ሥርዓቱ ዓላማ ወንጀለኞች ሕይወታቸውን እንዲለውጡ ማድረግ ሳይሆን ከተቀረው ኅብረተሰብ እንዲገለሉ ማድረግ ነው። ዋናው ችግር ያለው እዚህ ላይ ነው። የእስር ቤት ሥርዓቱ ለእነዚህ ሰዎች ያለው አመለካከት እንቅፋት ይፈጥራል።
ሄንሪ:- የእስር ቤት ሥርዓቱ የወንጀለኞቹን ልብ መለወጥ አይችልም። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ከእስር ቤት ሲወጡ ዳግመኛ ወንጀል መፈጸማቸው አይቀርም።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በርካታ እስረኞች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲማሩ እርዳታ ተደርጎላቸዋል