በጭንቀት መዋጤን ለሰው መንገር ይኖርብኛልን?
ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .
በጭንቀት መዋጤን ለሰው መንገር ይኖርብኛልን?
“በጭንቀት ስዋጥ ሰዎች አስቸጋሪ ልጅ እንደሆንኩ አድርገው ሊያስቡ ይችላሉ በሚል በመጀመሪያ ስለጉዳዩ ምንም ነገር አልናገርም። በኋላ ግን እርዳታ ለማግኘት የግድ ለአንድ ሰው መናገር እንዳለብኝ ይሰማኛል።”—የ13 ዓመቱ ኤሌካንድሮ
“በጭንቀት ስዋጥ ለጓደኞቼ አልነግራቸውም። ብነግራቸውም መሳለቂያ ከማድረግ በቀር ምንም ሊፈይዱልኝ እንደማይችሉ ይሰማኛል።”—የ13 ዓመቱ ኤርቱሮ
ሁሉም ሰው ማለት ይቻላል አልፎ አልፎ የሚያስጨንቀው ነገር አያጣም። * ይሁን እንጂ ገና ወጣት ስለሆንህና በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ተሞክሮ ስለሌለህ በሕይወትህ በሚያጋጥሙህ ችግሮች በቀላሉ በጭንቀት ልትዋጥ ትችላለህ። ወላጆችህ፣ ጓደኞችህና መምህራንህ የሚጠብቁብህ ነገር፤ ጉርምስና የሚያስከትላቸው አካላዊና ስሜታዊ ለውጦች፤ ወይም በጥቃቅን ድክመቶችህ ምክንያት የሚሰማህ የተስፋ መቁረጥ ስሜት፤ እነዚህ ሁሉ በጭንቀት እንድትዋጥ ሊያደርጉህ ይችላሉ።
በጭንቀት በምትዋጥበት ጊዜ ምስጢርህን የምትነግረው አንድ ሰው ማግኘት ጥሩ ነው። “ስላስጨነቀኝ ነገር ለሰው ካልተናገርኩ የምፈነዳ ይመስለኛል” በማለት የ17 ዓመቷ ቤትሪስ ተናግራለች። የሚያሳዝነው ግን ብዙ ወጣቶች ችግሮቻቸውን ለሰው ከመንገር ይልቅ ዝም ማለትን ስለሚመርጡ ቀስ በቀስ ሳይታወቃቸው በተስፋ መቁረጥ ማጥ ውስጥ ይገባሉ። የማድሪድ የሕክምና ማዕከል ፕሮፌሰር የሆኑት ማሬያ ዲ ኪሰስ ሜርዶሚንጎ ራሳቸውን የመግደል ሙከራ የሚያደርጉት ወጣቶች ብዙውን ጊዜ ከባድ የብቸኝነት ስሜት የሚሰማቸው እንደሆኑ ተናግረዋል። ራስን የመግደል ሙከራ አድርገው ከሞት የተረፉ ብዙ ወጣቶች የሚያዋዩትና ምስጢራቸውን የሚያካፍሉት አንድም የበሰለ ሰው አለማግኘታቸውን ተናግረዋል።
አንተስ? ሐዘንና ትካዜ ሲሰማህ የምታዋየው ሰው አለህ? ከሌለህስ ለማን ልታካፍለው ትችላለህ?
ከወላጆችህ ጋር ተነጋገር
በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ኤሌካንድሮ በጭንቀት ሲዋጥ ምን እንደሚያደርግ እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “እናቴ ከሕፃንነቴ ጀምሮ በቅርብ ትደግፈኝ ስለነበር ስጨነቅ ለእርሷ እነግራታለሁ። እርሷም በራሴ እንድተማመን ትረዳኛለች። አባቴም ከእኔ ጋር የሚመሳሰሉ ተሞክሮዎች ስላሉት እርሱንም ሄጄ አነጋግረዋለሁ። በጭንቀት መዋጤን ለሰው ካልተናገርኩ የባሰ መጥፎ ስሜት ይሰማኛል።” የ11 ዓመቱ ሮዶልፎ እንዲህ በማለት ያስታውሳል:- “አንዳንድ ጊዜ መምህራችን ሲያንቋሽሸኝና ሲነቅፈኝ በጣም ስለማዝን ወደ መጸዳጃ ቤት ሄጄ አለቅሳለሁ።
በኋላ ግን ሁኔታውን ለእናቴ ስነግራት ለችግሬ መፍትሄ እንዳገኝ ረዳችኝ። ለእርሷ ባልነግራት ኖሮ ይበልጥ አዝን ነበር።”ከወላጆችህ ጋር ልብ ለልብ ተግባብተህ ስለመነጋገር አስበህበት ታውቃለህ? ምናልባት ችግሬን ሙሉ በሙሉ አይረዱልኝም ብለህ ታስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሁኔታው እንደዚያ ነውን? በአሁኑ ጊዜ ያሉት ወጣቶች የሚያጋጥሟቸውን ሁሉንም ችግሮች ሙሉ በሙሉ ላይረዷቸው ይችሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ በምድር ላይ ካለው ከማንኛውም ሰው ይበልጥ አንተን በደንብ የሚያውቁህ ወላጆችህ አይደሉምን? ኤሌካንድሮ እንዲህ ይላል:- “አንዳንድ ጊዜ ወላጆቼ ጭንቀቴን መጋራትና ስሜቴን መረዳት ያዳግታቸዋል።” ይሁን እንጂ እንዲህ በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል:- “ችግር ሲያጋጥመኝ እነርሱን ማነጋገር እንደምችል አውቃለሁ።” ብዙውን ጊዜ ወጣቶች ወላጆቻቸው እነርሱ ከጠበቁት በላይ ችግራቸውን የሚረዱላቸው ሆነው ያገኟቸዋል! በእድሜ ስለሚበልጡህና በሕይወታቸውም ብዙ ተሞክሮ ስላካበቱ ጠቃሚ ምክር ሊለግሱህ ይችላሉ። ይህ በተለይ ወላጆችህ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ልምድ ያላቸው ከሆኑ እውነት ነው።
ቀደም ብላ የተጠቀሰችው ቤትሪስ “ከወላጆቼ ጋር ስነጋገር ማበረታቻና ችግሮቼን ለመፍታት የሚያስችል ተግባራዊ መፍትሔ አገኛለሁ” በማለት ተናግራለች። እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስ ለወጣቶች “ልጄ ሆይ፣ የአባትህን ትእዛዝ ጠብቅ፣ የእናትህንም ሕግ አትተው፤ የወለደህን አባትህን ስማ፣ እናትህም ባረጀች ጊዜ አትናቃት” የሚል ምክር መስጠቱ ተገቢ ነው።—ምሳሌ 6:20፤ 23:22
እርግጥ፣ ከወላጆችህ ጋር የማትቀራረብ ከሆነ ምሥጢርህን ለእነርሱ መንገሩ ሊከብድህ ይችላል። ዶክተር ካታሊና ጎንሴሌዝ ፎርቴሴ እንዳሉት ከሆነ ራሳቸውን የመግደል ሙከራ እንዳደረጉ የተናገሩ ወጣቶች ለራሳቸው ያላቸው ግምት ዝቅተኛ እንደሆነና ከወላጆቻቸውም ጋር እንደማይቀራረቡ በሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መካከል የተካሄደው ጥናት አመልክቷል። ከዚህ በተቃራኒ እንዲህ ያለውን ራስን የመግደል ሐሳብ ከማውጠንጠን በአብዛኛው የሚርቁት “ከእናታቸውና ከአባታቸው ጋር ጥሩ ቅርርብ ያላቸው ወጣቶች ናቸው።”
ስለዚህ ከወላጆችህ ጋር ጥሩ ቅርርብ ለመፍጠር ጥረት አድርግ። ከእነርሱ ጋር ዘወትር የመነጋገር ልማድ ይኑርህ። በዕለት ተዕለት ሕይወትህ ስለሚገጥምህ ነገር ንገራቸው። ጥያቄዎች ጠይቃቸው። እንዲህ የመሰሉት ቀለል ያሉ ውይይቶች ከባድ ችግር ሲያጋጥምህ እነርሱን ቀርቦ ማነጋገሩን ቀላል ሊያደርጉልህ ይችላሉ።
ለጓደኛህ አዋየው
ይሁን እንጂ ችግሮችን ለዕድሜ እኩዮችህ ማካፈሉ ይበልጥ አይቀልምን? እርግጥ፣ ልታምናቸው የምትችላቸው ጓደኞች ማግኘቱ ጥሩ ነው። ምሳሌ 18:24 “ከወንድም አብልጦ የሚጠጋጋ ወዳጅ አለ” በማለት ይናገራል። ይሁን እንጂ የዕድሜ እኩዮችህ ሊያዝኑልህና ድጋፍ ሊሰጡህ ቢችሉም ሁልጊዜ የተሻለ ምክር ይሰጡሃል ማለት አይደለም። ደግሞም በአብዛኛው ከአንተ የበለጠ የሕይወት ተሞክሮ የላቸውም። ሮብዓምን ታስታውሳለህ? በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይኖር የነበረ ንጉሥ ነው። ተሞክሮ ያላቸው የጎለመሱ ወንዶች የሰጡትን ምክር ከመስማት ይልቅ የዕድሜ እኩዮቹን ማዳመጥ መረጠ። ውጤቱስ ምን ሆነ? ውድቀት! ሮብዓም የአብዛኛውን ሕዝብ ድጋፍና የአምላክን ሞገስ አጥቷል።—1 ነገሥት 12:8-19
ምሥጢርን ለዕድሜ እኩዮች በመንገር በኩል ያለው ሌላው ችግር ምሥጢር የመጠበቁ ጉዳይ ነው። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ኤርቱሮ እንዲህ ብሏል:- “ብዙ የማውቃቸው ልጆች ሐዘን ሲሰማቸው ለጓደኞቻቸው ይነግሯቸዋል። ሆኖም ትንሽ ቆይቶ ጓደኞቻቸው እነርሱ የነገሯቸውን ነገር አንድም ሳያስቀሩ ለሌሎች በመንገር ማሾፊያ ያደርጓቸዋል።” የአሥራ ሦስት ዓመቷ ገብሪኤላ ተመሳሳይ ነገር ደርሶባታል። እንዲህ ብላለች:- “አንድ ቀን ጓደኛዬ የእኔን የግል ምሥጢር ዝክዝክ አድርጋ ለሌላ ጓደኛዋ እንደምትነግራት ተገነዘብኩ። ስለዚህ ከአሁን ወዲህ እርሷን አላምናትም። አዎን፣ በእኔ ዕድሜ ከሚገኙት ልጆች ጋር እነጋገራለሁ። ሆኖም ለሌሎች ቢነግሩብኝ እጎዳለሁ ብዬ የማስባቸውን ነገሮች ለእነርሱ ከመንገር እቆጠባለሁ።” ስለዚህ እርዳታ በምትፈልግበት ምሳሌ 25:9) እንዲህ ያለው ሰው ደግሞ ከአንተ በዕድሜ የሚበልጥ እንደሚሆን እሙን ነው።
ወቅት ‘የሌላውን ሰው ምሥጢር የማይገልጥ’ ሰው ማግኘትህ አስፈላጊ ነው። (ስለዚህ የወላጆችህን ድጋፍ ማግኘት የማትችል ከሆነ ምሥጢርህን የምታካፍለው ጓደኛ ማግኘትህ ጥሩ ነው። ይሁን እንጂ ምሥጢርህን የምትነግረው ሰው የሕይወት ተሞክሮ ያለውና የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚያውቅ ስለመሆኑ እርግጠኛ ሁን። በአካባቢህ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ይህንን ብቃት የሚያሟሉ እንደሚኖሩ ምንም ጥርጥር የለውም። የ16 ዓመቷ ሊሊያኔ እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “ምሥጢሬን ለአንዳንድ ክርስቲያን እህቶቼ ማካፈሌ ጠቅሞኛል። በዕድሜ ከእኔ ስለሚበልጡ የሚሰጡኝ ምክር ጥሩ ነው። አሁን ጓደኞች ሆነናል።”
በችግሩ ምክንያት መንፈሳዊነትህ መጎዳት ጀምሮ ከሆነስ? ምናልባት ከመጠን በላይ በጭንቀት ከመዋጥህ የተነሳ መጸለይንና የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብን ችላ ማለት ጀምረህ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ በያዕቆብ 5:14, 15 ላይ የሚከተለውን ምክር ይሰጣል:- “ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል።” በአካባቢህ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ተስፋ የቆረጡትንና በመንፈሳዊ የታመሙትን ሰዎች በመርዳት ረገድ ልምድ ያላቸው ሽማግሌዎች አሉ። እነርሱን ለማነጋገር ነፃነት ይሰማህ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያሉት ሰዎች “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ” ሊሆኑ እንደሚችሉ ይናገራል።—ኢሳይያስ 32:2
“በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ”
ይሁን እንጂ ከሁሉ የተሻለው የእርዳታ ምንጭ “የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” ነው። (2 ቆሮንቶስ 1:3) ስታዝንና ስትጨነቅ በፊልጵስዩስ 4:6, 7 ላይ የሚገኘውን ምክር ተከተል። “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” ይሖዋ በማንኛውም ጊዜ አንተን ለማዳመጥ ዝግጁ ነው። (መዝሙር 46:1፤ 77:1) እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ አእምሮህን ከጭንቀት ነፃ ለማድረግ የሚያስፈልግህ ጸሎት ብቻ ሊሆን ይችላል።
አልፎ አልፎ ሐዘን ወይም ጭንቀት ከተሰማህ ሌሎች ብዙ ወጣቶችም ልክ እንዳንተው እንደሚሰማቸው ፈጽሞ አትዘንጋ። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያሉት ስሜቶች ወዲያው ይጠፋሉ። ይሁን እንጂ እስከዚያው ድረስም ቢሆን ብቻህን አትሰቃይ። በጭንቀት መዋጥህን ሌላ ሰው እንዲያውቅ አድርግ። ምሳሌ 12:25 “ሰውን የልቡ ኀዘን ያዋርደዋል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል” በማለት ይናገራል። ይህንን የሚያበረታታ “መልካም ቃል” ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? የሚያስፈልግህን ማጽናኛና እርዳታ ሊሰጥህ ለሚችል ተሞክሮ፣ እውቀትና አምላካዊ ጥበብ ላለው ሰው በመናገር ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.5 ትካዜው ረዘም ላለ ጊዜ ከቆየብህ ምናልባት ከባድ ስሜታዊ ወይም አካላዊ ቀውስ እንዳለ የሚጠቁም ሊሆን ስለሚችል አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋል። “የመንፈስ ጭንቀትን ለማስወገድ በሚደረገው ውጊያ አሸናፊ መሆን” በሚል ርዕስ የዚህ መጽሔት ተጓዳኝ በሆነው መጠበቂያ ግንብ 4-111 ላይ የወጣውን ትምህርት ተመልከት።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ከወላጆቼ ጋር ስነጋገር ማበረታቻና . . . ተግባራዊ መፍትሔ አገኛለሁ”
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አብዛኛውን ጊዜ ለአንተ ምክር ለመስጠት ከሁሉ የተሻለ ሁኔታ የሚኖራቸው የዕድሜ እኩዮችህ ሳይሆኑ አምላካዊ ፍርሃት ያላቸው ወላጆችህ ናቸው