አማራጭ ሕክምናዎች—ተጠቃሚያቸው የተበራከተበት ምክንያት
አማራጭ ሕክምናዎች—ተጠቃሚያቸው የተበራከተበት ምክንያት
አማራጭ ወይም ተጨማሪ የሚባሉት የሕክምና ዓይነቶች የሚጠቀሙባቸው መፈወሻ ዘዴዎች እጅግ ብዙ ናቸው። ብዙዎቹ ናቹሮፓቲ በሚል አጠቃላይ ስያሜ የሚጠሩ ሲሆን ይህም ከተፈጥሮ የተገኙ ነገሮችን ብቻ በመጠቀም ሰውነት ራሱን በራሱ እንዲፈውስ የሚያስችሉትን ሁኔታዎች በማመቻቸት የሚከናወነው ሕክምና ነው። በዚህ ዘርፍ ከሚመደቡት የሕክምና ዓይነቶች መካከል በርካታዎቹ ለብዙ መቶ ዓመታት ሲሠራባቸው የኖሩ ቢሆንም በዘመናዊው ሕክምና ቦታ ተነፍጓቸው ወይም ችላ ተብለው ቆይተዋል።
ለምሳሌ ያህል በነሐሴ 27, 1960 የወጣው ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን እንደገለጸው በሰውነት ላይ ቃጠሎ ሲደርስ በቀዝቃዛ ውኃ ወይም በበረዶ የተነከረ ንጹሕ ጨርቅ ማድረግ “ጥንታዊ ዘዴ ነው። ይሁን እንጂ ሐኪሞችም ሆኑ ተራው ሰው ይህን ዘዴ ችላ ያሉት ይመስላል። ስለዚህ የሕክምና ዘዴ የሚያወሱ ሳይንሳዊ ጽሑፎች በሙሉ በአንድ ድምፅ የሚያወድሱት ቢሆንም ዛሬ በሰፊው የሚሠራበት ዘዴ አልሆነም። አብዛኞቹ ሐኪሞች ምክንያቱ ምን እንደሆነ ሊናገር የሚችል ሰው ባይኖርም ‘የማይሠራበት’ ዘዴ እንደሆነ ይናገራሉ።”
ይሁን እንጂ በቅርብ አሥርተ ዓመታት በቀዝቃዛ ውኃ ወይም በበረዶ የተነከረ ጨርቅ በተቃጠለ አካል ላይ ማድረግ በመደበኛው ሕክምና ድጋፍ እያገኘ የመጣ ዘዴ ሆኗል። በመስከረም 1963 የወጣው ዘ ጆርናል ኦቭ ትራውማ እንዲህ ሲል ዘግቧል:- “ቃጠሎ ሲደርስ ቀዝቃዛ ውኃን እንደ መጀመሪያ ደረጃ ሕክምና የመጠቀም ጠቃሚነት ግንዛቤ ማግኘት የተጀመረው በ1959 እና 1960 ከቀረበው የኦፋግሰንና ሹልማን ሪፖርት በኋላ ነው። ባለፈው ዓመት በዚህ ዘዴ ተጠቅመን በሽተኞችን ስናክም የቆየን ሲሆን ያገኘነው ውጤት አበረታች ነው።”
በቀዝቃዛ ውኃ ማከም በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ለሌላ ችግር የማይዳርግ ከመሆኑም በላይ በቃጠሎ ምክንያት የሚደርሰውን የሕመም ስሜት ያስታግሳል። ውኃን በተለያዩ መንገዶች በመጠቀም የሚሰጠው ኃይድሮቴራፒ የተባለ የሕክምና ዓይነት በአማራጭ ሕክምናዎች ውስጥ የተካተተ ሲሆን ዛሬ ዛሬ የዚህ ሕክምና የተለያዩ ዘርፎች የዘመናዊውን ሕክምና እውቅና አግኝተዋል። *
በተመሳሳይም የአማራጭ ሕክምና ባለሙያዎች በሽታዎችን ለመፈወስ ብዙውን ጊዜ በዕፅዋት ይጠቀማሉ። ይህ ዘዴ በአንዳንድ የምድር ክፍሎች ለብዙ መቶ አልፎ ተርፎም ለብዙ ሺህ ዓመታት ሲሠራበት የኖረ ነው። ለምሳሌ ያህል በሕንድ ዕፅዋትን መጠቀም ዋነኛ ሕክምና ሆኖ ቆይቷል። ዛሬ የአንዳንድ ዕፅዋት ፈዋሽነት የብዙ የጤና ባለሙያዎችን እውቅና ያላገኘበት የዓለም ክፍል የለም ለማለት ይቻላል።
ልብ ሊባል የሚገባው ገጠመኝ
የዕፅዋት ባዮኬሚስትሪ ተማሪ የሆነው ራይካርት ዊልስቶተር ከአንድ መቶ ዓመታት በፊት የ10 ዓመት እድሜ ባለው የቅርብ ጓደኛው በዜፕ ሽዋብ ላይ የደረሰው ሁኔታ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮበታል። ዜፕ እግሩ በኢንፌክሽን በጣም ተጎድቶ ስለነበር ዶክተሩ ሕይወቱን ለማዳን እግሩ መቆረጥ እንዳለበት ወሰነ። የዜፕ ወላጆች ግን ቀዶ ሕክምናውን እስከሚቀጥለው ቀን ጠዋት እንዲዘገይ አደረጉ። በዚህ መሃል ዕፅዋትን በመድኃኒትነት በመጠቀም ጥሩ ስም ያተረፈ አንድ እረኛ ማፈላለግ ጀመሩ። እረኛው አንዳንድ ዕፅዋትን ቀላቅሎ የተቀቀለ እስፒናች እስኪመስሉ ድረስ አልሞ ከፈጫቸው በኋላ ቁስሉ ላይ አደረገለት።
በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ቁስሉ መሻሻል ስላሳየ ቀዶ ሕክምናው እንደገና ለሌላ ጊዜ ተላለፈ። ሕክምናው ቀጠለና ከጊዜ በኋላ ቁስሉ ሙሉ በሙሉ ዳነ። ዊሊስቶተር በጀርመን ሙኒክ
ዩኒቨርሲቲ ኬሚስትሪ ማጥናት ጀመረና ከጊዜ በኋላ በዕፅዋት ውስጥ በሚገኙ ቀለማት በተለይም በክሎሮፊል ላይ ምርምር አድርጎ ስለደረሰባቸው ግኝቶች የኖቤል ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል። በዛሬው ጊዜ ጥቅም ላይ ከዋሉት በፋብሪካ የተመረቱ መድኃኒቶች መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት በከፊልም ይሁን ሙሉ በሙሉ በተፈጥሮ በዕፅዋት ውስጥ ከሚገኙ ኬሚካሎች የተሠሩ ናቸው።ሚዛናዊ የመሆን አስፈላጊነት
ይሁን እንጂ ሕክምናዎችን በተመለከተ ለአንዱ ሰው እንደ ተዓምር የሚቆጠር ውጤት ያስገኘው ሕክምና ለሌላው ሰው ምንም ላይፈይድ እንደሚችል መዘንጋት አይኖርበትም። የማንኛውም ዓይነት ሕክምና ውጤታማነት በበሽታው ዓይነትና ክብደት እንዲሁም በታማሚው አጠቃላይ የጤና ሁኔታና በሌሎችም ብዙ ሁኔታዎች ላይ የተመካ ነው። የጊዜ ጉዳይም ሳይቀር ወሳኝ ሊሆን ይችላል።
የአማራጭ ሕክምና ዘዴዎች ውጤት ብዙውን ጊዜ ከመደበኛው ሕክምና ይልቅ አዝጋሚ ነው። በመሆኑም ታማሚው በጊዜ ምርመራ ተደርጎለት ቢታከም ኖሮ ሊወገድ ይችል የነበረው ሕመም ተባብሶ ይህንን ለማዳን ሲባል ከባድ መድኃኒቶች መውሰድን ምናልባትም ቀዶ ሕክምና ማድረግን ወደሚጠይቅበት ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል። በመሆኑም ምንም ዓይነት አማራጭ የሌለ ይመስል አንድን ዓይነት ሕክምናን ብቻ የሙጥኝ ማለት ጥበብ አይሆንም።
አማራጭ ሕክምና ስለ ጤና ያለው አመለካከት ከመደበኛው ሕክምና ይለያል። ብዙውን ጊዜ ሕክምናው የሚያተኩረው በመከላከል ላይ ሲሆን በግለሰቡ አኗኗርና አካባቢ እንዲሁም እነዚህ ነገሮች በጤናው ወይም በጤናዋ ላይ በሚያሳድሩት ተጽዕኖ ላይ ያነጣጥራል። በሌላ አባባል የአማራጭ ሕክምና ባለሙያዎች የሚያተኩሩት በታወከው አካል ወይም በአንድ የተወሰነ በሽታ ላይ ሳይሆን በሰውዬው አጠቃላይ ሁኔታ ላይ ነው።
አማራጭ ሕክምና ተወዳጅ እንዲሆን ያደረገው ጠንካራ ጎን በተፈጥሮአዊ ነገሮች መጠቀሙና የሕክምናውም ዘዴ ቢሆን ከመደበኛው ሕክምና ይልቅ ቀለል ያለና ብዙም አደጋ የሌለበት ሆኖ መገኘቱ እንደሆነ ግልጽ ነው። በመሆኑም ጉዳት የማያስከትልና ውጤታማ የሆነ ሕክምና የማግኘቱ ፍላጎት እየጨመረ በመሄዱ በሚቀጥለው ርዕስ ጥቂት የአማራጭ ሕክምና ዓይነቶችን አንስተን እንወያያለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.5 የሰኔ 22, 1988 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 25-6ን ተመልከት።