ኤል ኒኞ ምንድን ነው?
ኤል ኒኞ ምንድን ነው?
ወትሮ ደረቅ የነበረው በፔሩ አገር በሊማ አጠገብ የሚገኘው አፑሪማክ ወንዝ ካርሜን የነበራትን ንብረት በሙሉ ጠራርጎ ወሰደ። “ይህ የደረሰው በኔ ላይ ብቻ አይደለም” ትላለች ካርሜን። “በብዙዎቻችን ላይ የደረሰ ነገር ነው።” ወደ ሰሜን እልፍ ብሎ ደግሞ ኃይለኛ ዝናብ በመጣሉ ምክንያት ወትሮ በረሃ የነበረው የሴቹሪያ የባሕር ዳርቻ ተጥለቅልቆ ለአጭር ጊዜ 5, 000 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሐይቅ ሆኖ ነበር። ይህም በፔሩ ከሚገኙት ታላላቅ ሐይቆች በስፋቱ ሁለተኛውን ደረጃ እንዲይዝ አድርጎት ነበር። በሌሎችም የምድር አካባቢዎች የተከሰቱት ታይተው የማይታወቁ ጎርፎች፣ ኃይለኛ የሆኑ አውሎ ነፋሶችና ከባድ ድርቅ፣ ረሃብ፣ ቸነፈርና የደን ቃጠሎ ከማስከተላቸውም በላይ በእህል፣ በንብረትና በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ውድመት አድርሰዋል። የዚህ ሁሉ መንስኤ ምንድን ነው? ብዙዎች ለዚህ ሁሉ መንስኤው ኤል ኒኞ ነው ይላሉ። ለስምንት ወራት ያህል የዘለቀው ኤል ኒኞ የተነሳው በምድር ወገብ አካባቢ ከሚገኘው የፓስፊክ ውቅያኖስ በ1997 መገባደጃ ላይ ነበር።
ታዲያ ኤል ኒኞ ምንድን ነው? የሚከሰተውስ እንዴት ነው? ያስከተለውስ ውጤት ይሄን ያህል ሰፊ አካባቢ የሸፈነ የሆነው ለምንድን ነው? ወደፊት የሚመጣበት ጊዜስ አስቀድሞ በትክክል ሊታወቅና በንብረትና በሕይወት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ቁጥጥር ሊደረግበት ይችላል?
መንስዔው የባሕር መሞቅ ነው
“ኤል ኒኞ ከፔሩ የባሕር ዳርቻ አጠገብ ከሁለት እስከ ሰባት በሚደርሱ ዓመታት ጊዜ ውስጥ እየተፈራረቀ የሚደርስ የባሕር መሞቅ” እንደሆነ ኒውስዊክ መጽሔት ይገልጻል። በፔሩ የባሕር ዳርቻ የሚገኙ የባሕር ተጓዦች እንዲህ ያለውን የባሕር መሞቅ ማስተዋል ከጀመሩ ከመቶ ዓመታት በላይ ሆኗቸዋል። ብዙውን ጊዜ ይህ የባሕር መሞቅ የሚከሰተው በገና ሰሞን አካባቢ በመሆኑ ኤል ኒኞ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ይህም ለሕፃኑ ለኢየሱስ የተሰጠ የስፓንኛ ስያሜ ነው።
በፔሩ የባሕር ዳርቻ አካባቢ የሚገኘው ባሕር መሞቁ በዚህች አገር ላይ የሚዘንበው ዝናብ መጠን እንዲጨምር ምክንያት ይሆናል። በዚህ ምክንያት የሚወርደው ዝናብ ምድረ በዳዎች እንዲለመልሙ እንዲሁም ከብቶች እንዲባዙ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ከዚህም በላይ የዝናቡ መጠን በሚያይልበት ጊዜ በአካባቢው ጎርፍ ይከሰታል። በተጨማሪም ከላይ የሚገኘው ጨዋማ የባሕር ውኃ መሞቁ ለባሕር ፍጥረታት በርካታ ምግብ የያዘው ከታች ያለው ቀዝቃዛ ውኃ ወደ ላይ እንዳይወጣ ያግዳል። በዚህም ምክንያት ብዙ የባሕር ፍጥረታትና አንዳንድ አእዋፍ ምግብ ፍለጋ ወደ ሌላ ቦታ ለመሰደድ ይገደዳሉ። ስለዚህ ኤል ኒኞ የሚያስከትለው ውጤት ቀስ በቀስ ከፔሩ የባሕር ዳርቻ ርቀው ወደሚገኙ አካባቢዎች ሳይቀር ይዳረሳል። *
ነፋስና ውኃ ወለድ
በፔሩ የባሕር ዳርቻ አካባቢ የሚገኘው ውቅያኖስ ሙቀት ባልተለመደ መጠን ከፍ እንዲል ምክንያት የሚሆነው ነገር ምንድን ነው? ይህን ለመረዳት በመጀመሪያ በጣም * በምዕራባዊው የምድር ክፍል በኢንዶኔዢያና በአውስትራሊያ አቅራቢያ የሚገኘው ላይኛው የባሕር ክፍል በፀሐይ በሚሞቅበት ጊዜ ይህ ሙቅና እርጥበት አዘል አየር ወደ ላይ ወደ ከባቢው አየር ስለሚነሳ በባሕሩ ወለል አካባቢ ዝቅተኛ የሆነ የአየር ግፊት ይፈጠራል። ወደ ላይ የተነሳው አየር ይቀዘቅዝና እርጥበቱን ማጣት ስለሚጀምር በአካባቢው ዝናብ ይፈጠራል። ደረቁ አየር በላይኛው ከባቢ አየር ላይ በሚገኙ ነፋሳት ኃይል እየተነዳ ወደ ምሥራቁ የምድር ክፍል ይወሰዳል። ይህ አየር ወደ ምሥራቅ በሚጓዝበት ጊዜ ይበልጥ ስለሚቀዘቅዝና ክብደቱም ስለሚጨምር ወደ ፔሩ እና ኢኳዶር አካባቢ በሚደርስበት ጊዜ ወደ ታች ይዘቅጣል። ይህም በውቅያኖሱ ወለል አካባቢ ከፍተኛ የአየር ግፊት እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል። በተጨማሪም ዝቅተኛ በሆኑ የምድር አካባቢዎች ትሬድ ዊንድስ የሚባሉት ነፋሳት ወደ ምዕራብ ወደ ኢንዶኔዥያ አካባቢ መንፈስ ስለሚጀምሩ ሽክርክሮሹ ሙሉ ዙሩን ያጠናቅቃል።
ግዙፍ የሆነውንና ዎከር ሰርኩሌሽን ተብሎ የሚጠራውን የነፋስ ዑደት እንመልከት። ይህ የነፋስ ሽክርክሮሽ በሐሩር ክልል በምሥራቃዊውና በምዕራባዊው የፓስፊክ ውቅያኖስ መካከል በሚገኘው ከባቢ አየር ላይ የሚከሰት ነው።ትሬድ ዊንድስ የሚባሉት ነፋሳት በሐሩር መስመር አካባቢ በሚገኘው በፓስፊክ ውቅያኖስ የወለል ሙቀት ላይ ለውጥ የሚያስከትሉት እንዴት ነው? ኒውስዊክ እንደሚለው እነዚህ “ነፋሳት በአነስተኛ የውኃ ክምችት ውስጥ አየር ሲነሳ የሚያመጣውን ዓይነት ለውጥ ያስከትላሉ። በምዕራባዊው ፓስፊክ ሙቅ ውኃ እንዲከማች ስለሚያደርጉ በዚያ አካባቢ የሚገኘው የባሕር ወለል በኢኳዶር አካባቢ ከሚገኘው የባሕር ወለል እስከ 60 ሳንቲ ሜትር የሚደርስ ተጨማሪ ከፍታና እስከ 8 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሚደርስ ተጨማሪ ሙቀት ይኖረዋል።” በምሥራቃዊው ፓስፊክ ከሥር የሚገኘው በርካታ ምግብ ያዘለ ቀዝቃዛ ውኃ ወደ ውጭ ተገልብጦ ስለሚወጣ የባሕር ፍጥረታት በብዛት ይራባሉ። በዚህ መንገድ በተለመዱት ዓመታት ወይም ኤል ኒኞ በማይኖርባቸው ዓመታት በምሥራቃዊው ፓስፊክ የሚገኘው የባሕር ወለል ከምዕራባዊው ፓስፊክ የቀዘቀዘ ይሆናል።
ታዲያ ኤል ኒኞ የሚከሰተው በከባቢ አየር ውስጥ ምን ዓይነት ለውጥ ሲፈጠር ነው? ናሽናል ጂኦግራፊክ እንደሚለው “እስከ አሁን ሳይንቲስቶች ሊገነዘቡት ባልቻሉት ምክንያት የተነሳ በየጥቂት ዓመቱ ትሬድ ዊንድስ የሚባሉት ነፋሳት በእጅጉ ይቀንሳሉ አልፎ ተርፎም ከናካቴው እስከ መጥፋት ይደርሳሉ።” እነዚህ ነፋሳት በሚዳከሙበት ጊዜ በኢንዶኔዥያ አቅራቢያ የሚከማቸው ሞቃት ውኃ ወደ ምሥራቅ ስለሚመለስ በፔሩና በሌሎች ምሥራቅ አገሮች የባሕሩ ወለል ሙቀት ከፍ ይላል። ይህ እንቅስቃሴ በተራው በከባቢው አየር ላይ ለውጥ ያስከትላል።
“በሐሩር ክልል በምሥራቃዊው የፓስፊክ ውቅያኖስ አካባቢ የሚፈጠረው ሙቀት የዎከርን የነፋስ ሽክርክሮሽ ከማዳከሙም በላይ በሙቀት መለዋወጥ ምክንያት የሚፈጠረው ከፍተኛ ዝናብ ከምዕራብና ከመካከለኛው የፓስፊክ አካባቢ ወደ ምስራቅ ፓስፊክ አካባቢ እንዲሸሽ ያደርጋል” ይላል አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ። በዚህ መንገድ በሐሩር መሥመር በፓስፊክ ውቅያኖስ አካባቢ በጠቅላላ ያለው የአየር ሁኔታ ይለወጣል።በወንዝ ውስጥ እንደሚገኝ ቋጥኝ
በተጨማሪም ኤል ኒኞ በሐሩር ክልል ካለው ፓስፊክ ውቅያኖስ ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች ሳይቀር የአየር ለውጥ ሊያስከትል ይችላል። እንዴት? የከባቢ አየርን እንቅስቃሴ በመጠቀም ነው። በአንድ አካባቢ የሚደርስ የከባቢ አየር መረበሽ በሌሎች አካባቢዎች የሚያደርሰው ለውጥ በአንድ ወንዝ መሃል የሚገኝ ቋጥኝ በወንዙ ፍሰት ላይ ከሚያስከትለው ለውጥ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ሞቃት በሆነው የሐሩር አካባቢ ውቅያኖስ አናት ላይ የሚፈጠረው ጥቅጥቅ ያለ ዝናብ አዘል ዳመና በወንዝ ውስጥ እንዳለ ቋጥኝ የከባቢውን አየር እንቅስቃሴ ያግዳል። ይህም በሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች የሚኖረውን የአየር ሁኔታ ይነካል።
ኤል ኒኞ ትልቅ ከፍታ ላይ በሚደርስበት ጊዜ በከፍተኛ ፍጥነት የሚጓዙትን ጄት ስትሪምስ የተባሉ የምሥራቅ ነፋሳት ያጠናክራል እንዲሁም ቦታቸውን ያስለቅቃል። በዚህ ከፍታ ላይ የአብዛኞቹን የነፋስ ሞገዶች አካሄድ የሚመሩት እነዚህ ጄት ስትሪምስ የተባሉ ነፋሳት ናቸው። የጄት ስትሪምስ መጠናከርና አቅጣጫ መቀየር የየወቅቱን የአየር ሁኔታ ሊያጠናክር ወይም ሊያዳክም ይችላል። ለምሳሌ ያህል ኤል ኒኞ በሚከሰትባቸው ዓመታት በሰሜናዊ ዩናይትድ ስቴትስ የሚኖረው ክረምት ቀለል ያለ ሲሆን በአንዳንድ ደቡባዊ የዩናይትድ ስቴትስ ክፍሎች ደግሞ ክረምቱ ይበልጥ ቀዝቀዝ ያለና እርጥበት የበዛበት ይሆናል።
ምን ያህል አስቀድሞ መተንበይ ይቻላል?
ነጠላ የባሕር ሞገዶች የሚያስከትሉትን ውጤት ከረጅም ጊዜ በፊት መተንበይ አይቻልም። ኤል ኒኞ የሚያስከትለውን ውጤት ለመተንበይ የሚደረገውስ ጥረት ከዚህ የተለየ ይሆን? አዎን፣ የተለየ ነው። የኤል ኒኞ ትንበያዎች ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆዩ የአየር ሁኔታዎችን የሚገልጹ ሳይሆኑ ለበርካታ ወራት ሰፋ ባሉ የምድር ክፍሎች የሚኖረውን ከተለመደው ውጭ የሆነ የአየር ሁኔታ የሚተነብዩ ናቸው። የአየር ሁኔታ ተመራማሪዎች የኤል ኒኞን ክስተት በመተንበይ ረገድ በተወሰነ ደረጃ ተሳክቶላቸዋል።
ለምሳሌ ያህል፣ ከ1997-98 የደረሰው የኤል ኒኞ ክስተት የተተነበየው በግንቦት ወር 1997 ማለትም የአየሩ ለውጥ ከመከሰቱ ከስድስት ወር በፊት ነበር። በአሁኑ ጊዜ በሐሩር መስመር ቀጣና በሚገኘው የፓስፊክ ውቅያኖስ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በተተከሉት 70 የሚያክሉ ተንሳፋፊ መሣሪያዎች አማካኝነት በውቅያኖሱ ወለል ላይ ያለው የነፋስ ሁኔታና እስከ 500 ሜትር ጥልቀት በሚደርስ የባሕር ክፍል ውስጥ የሚኖረው የሙቀት መጠን ይለካል። በዚህ መንገድ የተገኘው መረጃ በኮምፒዩተር ተሰልቶ ወደፊት የሚኖረው የአየር ሁኔታ ይተነበያል።
ስለ ኤል ኒኞ መከሰት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ለሚደርሰው ለውጥ በቅድሚያ ለመዘጋጀት ያስችላል። ለምሳሌ ያህል ከ1983 ጀምሮ በፔሩ የሚኖሩ ገበሬዎች የኤል ኒኞ ትንበያዎችን በመከታተል እርጥብ አየር የሚስማማቸውን ከብቶችና አትክልቶች ማርባትና መትከል ችለዋል። ዓሣ አጥማጆች ደግሞ ዓሣ ማጥመዳቸውን ትተው ከሞቃት ባሕር ጋር የሚመጡትን ሽሪምፕ የተባሉትን የባሕር ፍጥረታት ወደ ማጥመድ ዞረዋል። አዎን፣ ትክክለኛው ትንበያ የቅድሚያ ዝግጅት ሲታከልበት በኤል ኒኞ ምክንያት የሚደርሰው የሕይወትና የኢኮኖሚ ጉዳት ሊቀንስ ይችላል።
የምድራችንን የአየር ሁኔታ በሚገዙት የተፈጥሮ አሠራሮች ላይ የተደረገው ሳይንሳዊ ምርምር የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን በመንፈስ አነሳሽነት ከ3, 000 ዓመታት በፊት የተናገረው ትክክል መሆኑን አረጋግጧል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ነፋስ ወደ ደቡብ ይሄዳል፣ ወደ ሰሜንም ይዞራል፤ ዘወትር በዙረቱ ይዞራል፣ ነፋስም በዙረቱ ደግሞ ይመለሳል።” (መክብብ 1:6) ዘመናዊው ሰው ስለ አየር ሁኔታ ሊያውቅ የቻለው የነፋሳትን አካሄድና የውቅያኖስን እንቅስቃሴ በማጥናት ነው። ኤል ኒኞን ስለመሳሰሉ የአየር ሁኔታ ለውጦች የሚሰጡትን ማስጠንቀቂያዎች በመስማት የዚህ እውቀት ተጠቃሚዎች እንሁን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.6 በተቃራኒው ላ ኒንኛ (በስፓንኛ “ትንሽ ልጃገረድ” ማለት ነው) የሚለው ስያሜ በደቡብ አሜሪካ ምዕራባዊ የባሕር ዳርቻ በየወቅቱ የሚፈራረቀውን የባሕር መቀዝቀዝ የሚያመለክት ነው። ላ ኒንኛም በአየር ሁኔታ ላይ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ ያስከትላል።
^ አን.8 ይህ የአየር ሽክርክሮሽ ስያሜውን ያገኘው በ1920ዎቹ ዓመታት የዚህን አየር ሁኔታ ባጠናው እንግሊዛዊ ሳይንቲስት ሰር ጊልበርት ዎከር ስም ነው።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የኤል ኒኞ አውዳሚነት ታሪክ
■ 1525:- ኤል ኒኞ በፔሩ መከሰቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመዘገበበት ዓመት ነበር።
■ 1789-93:- ኤል ኒኞ በሕንድ አገር ከ600, 000 ለሚበልጡ ሰዎች መሞት ምክንያት ሲሆን በደቡባዊ አፍሪካም በጣም ከባድ የሆነ ረሃብ እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል።
■ 1982-83:- በዚህ ክስተት ምክንያት በአብዛኛው በሐሩር መሥመር አገሮች ከ2, 000 የሚበልጡ ሰዎች ሲሞቱ 13 ቢልዮን ዶላር የሚገመት ንብረት ወደመ።
■ 1990-95:- በዚህ ወቅት ኤል ኒኞ በተከታታይ ሦስት ጊዜ በመከሰቱ በታሪክ ከተመዘገቡት የኤል ኒኞ ክስተቶች ሁሉ ረዥሙ ክስተት ለመሆን በቃ።
■ 1997-98:- ከማንኛውም ጊዜ ይበልጥ በተሳካ ሁኔታ ኤል ኒኞ ስለሚያስከትለው ጎርፍና ድርቅ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም 2, 100 የሚያክሉ ሰዎች ሲሞቱ በመላው ዓለም ላይ የደረሰው የንብረት ጥፋት እስከ 33 ቢልዮን ዶላር የሚገመት ሆኗል።
[በገጽ 10, 11 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የተለመደው የአየር ሁኔታ
የዎከር ሰርኩሌሽን ዑደት
ኃይለኛ ትሬድ ዊንድስ
የሞቀ የውቅያኖስ ውኃ
ቀዝቃዛ የውቅያኖስ ውኃ
ኤል ኒኞ
ጄት ስትሪምስ አቅጣጫቸውን ይቀይራሉ
ደካማ ትሬድ ዊንድስ
የሞቀው ውኃ ወደ ምሥራቅ ይሄዳል
ከወትሮው የበለጠ ሙቀት ያለው ወይም ደረቅ የሆነ
ከወትሮው ይበልጥ ቀዝቃዛ የሆነ ወይም እርጥበት ያለው
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል/ሥዕላዊ መግለጫ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ኤል ኒኞ
ከላይ ባለው ሉል ላይ የሚታዩት ቀይ ቀለማት ከወትሮው በጣም የበለጠ የባሕር የሙቀት መጠንን የሚያመለክቱ ናቸው
የተለመደው የአየር ሁኔታ
የሞቀው ውኃ በምዕራባዊው ፓስፊክ የሚከማች በመሆኑ ብዙ ምግብ ያዘለው ቀዝቃዛ ውኃ በምሥራቅ በኩል ወደ ላይ ይወጣል
ኤል ኒኞ
ደካማ ትሬድ ዊንድስ የሞቀው ውኃ ወደ ምሥራቅ እንዲመለስ መንገድ የሚከፍቱ በመሆኑ ቀዝቃዛው ውኃ ወደ ባሕሩ ወለል መውጣት ሳይችል ይቀራል
[በገጽ 10, 11 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ፔሩ
በጎርፍ የተጥለቀለቀው የሴቹራ በረሃ
ሜክሲኮ
ሊንዳ የተሰኘው አውሎ ነፋስ
ካሊፎርንያ
የመሬት መንሸራተት
[ምንጮች]
ገጽ 10-11 ከግራ ወደ ቀኝ:- Fotografia por Beatrice Velarde; Image produced by Laboratory for Atmospheres, NASA Goddard Space Flight Center; FEMA photo by Dave Gatley