በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

ኢየሱስ በምድር ላይ እንደኖረ የሚያሳይ ማስረጃ

ኢየሱስ በምድር ላይ እንደኖረ የሚያሳይ ማስረጃ

ሀብት ወይም ሥልጣን አልነበረውም። ሌላው ቀርቶ የራሴ የሚለው መኖሪያ ቤት እንኳ አልነበረውም። ሆኖም ትምህርቶቹ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ አሳድረዋል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ክርስቶስ በእርግጥ በምድር ላይ እንደኖረ የሚያሳይ ማስረጃ አለ? በዘመናችን ያሉም ሆነ በጥንት ጊዜ የነበሩ ምሁራን ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ?

  • ማይክል ግራንት የተባለው ስለ ክላሲካል ሲቪላይዜሽን የሚያጠና የታሪክ ምሁር እንዲህ ብሏል፦ “ታሪክን ለሚዘግቡ ሌሎች ጥንታዊ ጽሑፎች የምንጠቀመውን መመዘኛ ለአዲስ ኪዳን ከተጠቀምን፣ (ደግሞም ልንጠቀም ይገባናል) በታሪክ ዘመናት ውስጥ ስለመኖራቸው ምንም ጥያቄ ተነስቶባቸው የማያውቁትን አረማዊ ግለሰቦች ሕልውና ተቀብለን የኢየሱስን ሕልውና አንቀበልም የምንልበት ምንም ምክንያት አይኖርም።”

  • ሩዶልፍ ቡልትማን የተባሉት በአዲስ ኪዳን ላይ ምርምር የሚያደርጉ ፕሮፌሰር እንዲህ በማለት ተናግረዋል፦ “‘ኢየሱስ በእርግጥ በምድር ላይ ኖሯል ወይ?’ የሚለው ጥርጣሬ መሠረተ ቢስ ነው፤ ይህ ሐሳብ ስህተት መሆኑን ለማሳየት ጥረት ሊደረግለት የሚገባ እንኳ አይደለም። ጤነኛ አእምሮ ያለው ማንኛውም ሰው፣ በጥንቱ ፓለስቲና በሚገኘው [የክርስቲያኖች] ማኅበረሰብ አማካኝነት የተጀመረው ታሪካዊ ንቅናቄ መሥራች ኢየሱስ ስለመሆኑ ጥያቄ ሊያነሳ አይችልም።”

  • ዊል ዱራንት የተባሉት የታሪክ ምሁር፣ ጸሐፊና ፈላስፋ እንዲህ ብለዋል፦ “በአንድ ትውልድ ውስጥ የኖሩ ጥቂት ተራ ሰዎች [የወንጌል ጸሐፊዎች] ይህን የመሰለ ኃያልና ማራኪ፣ የላቀ የሥነ ምግባር አቋም ያለው ብሎም ብዙዎች የወንድማማችነት መንፈስ እንዲያሳዩ ማነሳሳት የቻለ ገጸ ባህርይ መፍጠር ከቻሉ፣ ይህ በራሱ በወንጌሎች ውስጥ ከተገለጸው ከየትኛውም ተአምር የበለጠ የሚደንቅ ተአምር ነው።”

  • አልበርት አንስታይን የተባለው በጀርመን የተወለደ አይሁዳዊ የፊዚክስ ሊቅ እንዲህ ብሏል፦ “አይሁዳዊ ብሆንም [የናዝሬቱ ኢየሱስ] ልዩ ባሕርይ በጣም ይማርከኛል።” ኢየሱስን በታሪክ ውስጥ እንደኖረ ሰው አድርጎ ይመለከተው እንደሆነ ሲጠየቅ ደግሞ “ያለምንም ጥርጥር!” ብሎ የመለሰ ሲሆን አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ማንም ሰው ቢሆን የወንጌል መጻሕፍትን ሲያነብ ኢየሱስ እውነተኛ ሰው መሆኑን መገንዘቡ አይቀርም። በእያንዳንዱ ቃል ውስጥ ማንነቱ በግልጽ ይታያል። ይህን ያህል ሕያው የሆነ አፈ ታሪክ ሊኖር አይችልም።”

    “ማንም ሰው ቢሆን የወንጌል መጻሕፍትን ሲያነብ ኢየሱስ እውነተኛ ሰው መሆኑን መገንዘቡ አይቀርም።”—አልበርት አንስታይን

ታሪክ ምን ያሳያል?

ከየትኛውም ጽሑፍ የበለጠ ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት ዝርዝር መረጃ የያዘ ዘገባ የምናገኘው ወንጌሎች ተብለው በሚጠሩት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ውስጥ ነው፤ እነዚህ መጻሕፍት በጸሐፊዎቻቸው ስም የማቴዎስ፣ የማርቆስ፣ የሉቃስ እንዲሁም የዮሐንስ ወንጌል በመባል ይጠራሉ። በተጨማሪም ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች የጻፏቸው በርካታ ጥንታዊ ጽሑፎች ኢየሱስን በስም ጠቅሰው ይናገራሉ።

  • ታሲተስ

    (ከ56-120 ዓ.ም. ገደማ) ታሲተስ ከጥንት ሮማዊ የታሪክ ምሁራን መካከል ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል። ታሲተስ ያሰፈራቸው የታሪክ መዛግብት (አናልስ) ከ14 ዓ.ም. እስከ 68 ዓ.ም. ድረስ ያለውን የሮም ታሪክ ይዘግባሉ። (ኢየሱስ የሞተው በ33 ዓ.ም. ነው።) በ64 ዓ.ም. በሮም ታላቅ እሳት በተነሳበት ወቅት እሳቱን ያስነሳው ንጉሠ ነገሥት ኔሮ እንደሆነ የሚገልጽ ወሬ ይናፈስ እንደነበረ ታሲተስ ዘግቧል። ሆኖም ኔሮ “ወሬውን ለማስቆም” ሲል እሳቱን ያስነሱት ክርስቲያኖች እንደሆኑ መግለጹን ታሲተስ ጽፏል። ታሲተስ በመቀጠል እንዲህ ብሏል፦ “[ክርስቲያን የሚለው ስም] መገኛ የሆነው ክሪስቱስ በገዥው በጴንጤናዊው ጲላጦስ ቃል በጢባሪዮስ ዘመን በሞት እንዲቀጣ [ተደርጓል]።”—አናልስ XV, 44

  • ስዊቶኒየስ

    (ከ69 ዓ.ም. ገደማ–122 ዓ.ም. በኋላ) ይህ ሮማዊ የታሪክ ምሁር ላይቭስ ኦቭ ዘ ሲዛርስ በተባለው ጽሑፉ ላይ በመጀመሪያዎቹ 11 የሮም ንጉሠ ነገሥታት የግዛት ዘመን ወቅት የተከናወኑትን ነገሮች ዘግቧል። ስለ ቀላውዴዎስ የሚናገረው ክፍል በሮም በሚገኙ አይሁዳውያን መካከል ስለተከሰተ ሁከት ይጠቅሳል፤ ሁከቱ የተነሳው ከኢየሱስ ጋር በተያያዘ በተነሳ ውዝግብ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም። (የሐዋርያት ሥራ 18:2) ስዊቶኒየስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “አይሁዳውያኑ በክሬስቱስ [ክሪስቱስ] ቆስቋሽነት ያለማቋረጥ ረብሻ ይፈጥሩ ስለነበር እርሱ [ክላውዲየስ] ከሮም አስወጣቸው።” (ዘ ዲፋይድ ክላውዲየስ XXV, 4) ስዊቶኒየስ፣ ኢየሱስ ረብሻ እንደቀሰቀሰ መናገሩ ሐሰት ቢሆንም በሕይወት የኖረ ሰው መሆኑን አልካደም።

  • ትንሹ ፕሊኒ

    (ከ61-113 ዓ.ም. ገደማ) ደራሲና የቢቲንያ (የአሁኗ ቱርክ) አስተዳዳሪ የነበረው ይህ ሮማዊ፣ በአውራጃው በሚገኙ ክርስቲያኖች ላይ ምን እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ለመጠየቅ የሮም ንጉሠ ነገሥት ለሆነው ለትራጃን ደብዳቤ ጽፎ ነበር። ፕሊኒ፣ ክርስቲያኖች እምነታቸውን እንዲክዱ ለማስገደድ እንደሞከረና ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆኑትን ደግሞ እንዳስገደለ ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “እኔ የምለውን እየደገሙ [ለአረማውያን] አማልክት የጸለዩ እንዲሁም የወይን ጠጅና ዕጣን በማቅረብ ለምስልህ . . . አምልኮ ያቀረቡ ብሎም በክርስቶስ ላይ የስድብ ቃል ለመናገር ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን ነፃ መልቀቅ ተገቢ እንደሆነ ተሰምቶኛል።”—ፕሊኒ—ሌተርስ፣ ጥራዝ X, XCVI

  • ፍላቪየስ ጆሴፈስ

    (ከ37-100 ዓ.ም. ገደማ) ይህ አይሁዳዊ ካህንና የታሪክ ምሁር፣ አይሁዳዊ ሊቀ ካህናት የሆነውና በፓለቲካው ዓለም ተደማጭነት የነበረው ሐና “የሳንሄድሪንን [የአይሁዳውያንን ከፍተኛ ሸንጎ] ዳኞች ሰብስቦ፣ ክርስቶስ እየተባለ የሚጠራው የኢየሱስ ወንድም የሆነውን ያዕቆብን . . . በፊታቸው እንዳቀረበው” ዘግቧል።—ጁዊሽ አንቲኩዊቲስ XX, 200

  • ታልሙድ

    ታልሙድ የሚባሉት ከሦስተኛው እስከ ስድስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ የተሰባሰቡ የረቢዎች ጽሑፎች ናቸው፤ ይህ ጽሑፍ ኢየሱስ በሕይወት የኖረ ሰው መሆኑን ጠላቶቹም እንኳ እንደሚያረጋግጡ ያሳያል። ታልሙድ ላይ የሰፈረ አንድ ሐሳብ እንዲህ ይላል፦ “በፋሲካ በዓል . . . ላይ የናዝሬቱ የሹ [ኢየሱስ] ተሰቀለ”፤ ይህ ደግሞ በታሪክ የተረጋገጠ እውነታ ነው። (ባቢሎኒያን ታልሙድ፣ ሳንሄድሪን 43a፣ ሙኒክ ኮዴክስ፤ ዮሐንስ 19:14-16ን ተመልከት።) በሌላ ቦታ ላይ ደግሞ ታልሙድ “እንደ ናዝሬቱ ሰው በሕዝብ ፊት ራሱን የሚያዋርድ ልጅ ወይም ተማሪ አይኑረን” ይላል፤ ‘የናዝሬቱ ሰው’ የሚለው አጠራር ብዙ ጊዜ ኢየሱስን የሚያመለክት ነው።—ባቢሎኒያን ታልሙድ፣ ቤራኮት 17b፣ የግርጌ ማስታወሻ፣ ሙኒክ ኮዴክስ፤ ሉቃስ 18:37ን ተመልከት።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ ማስረጃ

ወንጌሎች ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት ሲዘግቡ በወቅቱ የነበሩ ሰዎችን፣ ቦታዎችንና ክንውኖቹ የተፈጸሙበትን ጊዜ ጨምሮ ዝርዝር መረጃ ይሰጡናል፤ እነዚህ ነገሮች አንድ ታሪክ እውነተኛ መሆኑን የሚያሳዩ መሥፈርቶች ናቸው። ሉቃስ 3:1, 2 ላይ የሚገኘውን ዘገባ እንደ ምሳሌ መመልከት እንችላለን፤ ይህ ዘገባ፣ ስለ ኢየሱስ መምጣት ያበሰረው መጥምቁ ዮሐንስ የተባለ ሰው አገልግሎቱን የጀመረበትን ትክክለኛ ጊዜ ለማወቅ ያስችለናል።

“ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው።”—2 ጢሞቴዎስ 3:16

ሉቃስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ጢባርዮስ ቄሳር በነገሠ በ15ኛው ዓመት፣ ጳንጥዮስ ጲላጦስ የይሁዳ አገረ ገዢ፣ ሄሮድስ የገሊላ አውራጃ ገዢ፣ ወንድሙ ፊልጶስ ደግሞ የኢጡርያስና የጥራኮኒዶስ አውራጃ ገዢ፣ ሊሳኒዮስ የአቢላኒስ አውራጃ ገዢ በነበሩበት ጊዜ እንዲሁም ቀያፋና የካህናት አለቃው ሐና በነበሩበት ዘመን የአምላክ ቃል በምድረ በዳ ወደነበረው ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ መጣ።” ይህ የማያሻማና ዝርዝር የሆነ መረጃ ‘የአምላክ ቃል ወደ ዮሐንስ የመጣው’ በ29 ዓ.ም. እንደሆነ በእርግጠኝነት ለማወቅ ያስችለናል።

ሉቃስ በስም የጠቀሳቸውን እነዚህን ሰባት የታወቁ ሰዎች የታሪክ ምሁራንም በሚገባ ያውቋቸዋል። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ተቺዎች ጳንጥዮስ ጲላጦስ እና ሊሳኒዮስ በእርግጥ በሕይወት የኖሩ ሰዎች ስለመሆናቸው ጥያቄ ያነሱበት ወቅት ነበር። ሆኖም እነዚህ ተቺዎች መደምደሚያ ላይ ለመድረስ ትንሽ ቸኩለዋል። ጲላጦስን እና ሊሳኒዮስን በስም የሚጠቅሱ ጥንታዊ ጽሑፎች የተገኙ ሲሆን ይህም የሉቃስ ዘገባ ትክክል እንደሆነ ያሳያል። *

ይህን ማወቃችን ለውጥ ያመጣል?

ኢየሱስ፣ ዓለም አቀፍ መስተዳድር ስለሆነው ስለ አምላክ መንግሥት ለሰዎች አስተምሯል

ኢየሱስ በእርግጥ በምድር ላይ የኖረ ሰው የመሆኑ ጉዳይ የሚያሳስበን የኢየሱስ ትምህርቶች አስፈላጊ በመሆናቸው ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ሰዎች ደስተኛና አርኪ ሕይወት መምራት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አስተምሯል። * በተጨማሪም ኢየሱስ፣ የሰው ልጆች ‘የአምላክ መንግሥት’ ተብሎ በሚጠራ ዓለም አቀፍ መስተዳድር ሥር እውነተኛ ሰላም አግኝተው ያለ ስጋት የሚኖሩበት ጊዜ እንደሚመጣ ተናግሯል።—ሉቃስ 4:43

‘የአምላክ መንግሥት’ የሚለው መጠሪያ ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም አምላክ መላዋን ምድር የሚያስተዳድረው በዚህ መንግሥት አማካኝነት ነው። (ራእይ 11:15) ኢየሱስ ለተከታዮቹ በሰጠው የጸሎት ናሙና ላይ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ . . . መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ . . . በምድርም ላይ ይፈጸም” ብሎ መናገሩ ይህን እውነታ ያሳያል። (ማቴዎስ 6:9, 10) የአምላክ መንግሥት ለሰው ልጆች ምን በረከቶችን ያመጣል? እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት፦

  • ጦርነትና የእርስ በርስ ግጭት ይቀራል።መዝሙር 46:8-11

  • ስግብግብነትንና ሙስናን ጨምሮ ክፋት ጨርሶ ይወገዳል፤ ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎችም ይጠፋሉ።መዝሙር 37:10, 11

  • የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች አስደሳችና ፍሬያማ ሥራ ይኖራቸዋል።ኢሳይያስ 65:21, 22

  • ምድር ከደረሰባት ጉዳት ሙሉ በሙሉ አገግማ የተትረፈረፈ ሰብል ትሰጣለች።መዝሙር 72:16፤ ኢሳይያስ 11:9

አንዳንድ ሰዎች፣ እነዚህ ተስፋዎች እንዲሁ ምኞት ብቻ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ይሁንና ከንቱ ምኞት የሚሆነው፣ በሰው ልጆች ጥረት ያሉብን ችግሮች እንደሚወገዱ መተማመን አይደለም? እስቲ አስበው፦ በትምህርት እንዲሁም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ አስደናቂ እድገት ቢኖርም በዛሬው ጊዜ ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ሲያስቡ ከፍተኛ ስጋትና ፍርሃት ይሰማቸዋል። ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጭቆና እንዲሁም በሃይማኖት ምክንያት የሚደርስ ስደት ብሎም ስግብግብነትና ሙስና በየዕለቱ የምናየው ነገር ነው። በእርግጥም፣ የሰዎች አገዛዝ ስኬታማ ሊሆን አለመቻሉ በግልጽ የሚታይ እውነታ ነው!—መክብብ 8:9

በመሆኑም ኢየሱስ በእርግጥ በምድር ላይ እንደኖረ ማወቅ በቁም ነገር ልናስብበት የሚገባ ነገር ነው። * ሁለተኛ ቆሮንቶስ 1:19, 20 እንደሚናገረው “አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች የቱንም ያህል ብዙ ቢሆኑም በእሱ [በክርስቶስ] አማካኝነት ‘አዎ’ ሆነዋል።”

^ አን.23 ሊሳኒዮስ ተብሎ የሚጠራን የአራተኛው ክፍል ገዢ ወይም ‘የአውራጃ ገዢ’ ስም የያዘ ጽሑፍ ተገኝቷል። (ሉቃስ 3:1 የግርጌ ማስታወሻ) ይህ ሰው ሉቃስ በተናገረው ወቅት ላይ የአቢላኒስ ገዢ ነበር።

^ አን.25 ከማቴዎስ ምዕራፍ 5 እስከ 7 ላይ የሚገኘውና ብዙውን ጊዜ የተራራው ስብከት በመባል የሚታወቀው ትምህርት ለዚህ ግሩም ምሳሌ ነው።

^ አን.32 ስለ ኢየሱስና ስላስተማራቸው ትምህርቶች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት www.jw.org/am ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች > የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው የሚለውን ዓምድ ተመልከት።