በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሆድ ዕቃን የሚቆጣጠረው የነርቭ ሥርዓት (በሰማያዊ ቀለም የሚታየው) የተመገብነው ምግብ ከሚያልፍባቸው የሰውነት ክፍሎች ጋር አብሮ የተሠራ ነው

ሆዳችን ውስጥ “ሁለተኛ አንጎል” አለ?

ሆዳችን ውስጥ “ሁለተኛ አንጎል” አለ?

‘ስንት አንጎል አለህ?’ ተብለህ ብትጠየቅ ምን መልስ ትሰጣለህ? “አንድ” ብለህ ከመለስክ ትክክል ነህ። ይሁንና በሰውነትህ ውስጥ ሌሎች የነርቭ ሥርዓቶችም ይገኛሉ። ከእነዚህ የነርቭ ሥርዓቶች መካከል አንዱ በጣም ውስብስብ ከመሆኑ የተነሳ አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት “ሁለተኛው አንጎል” በማለት ይጠሩታል። ይህ የነርቭ ሥርዓት ሆድ ዕቃን የሚቆጣጠረው የነርቭ ሥርዓት (enteric nervous system) ሲሆን የሚገኘው በጭንቅላታችን ውስጥ ሳይሆን በሆዳችን አካባቢ ነው።

ሰውነታችን የተመገብነውን ምግብ ወደ ኃይል ለመቀየር ትልቅ ቅንጅትና ሥራ ይጠይቅበታል። በመሆኑም አንጎላችን ከምግብ መፈጨት ሥርዓት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን የሆድ ዕቃን ለሚቆጣጠረው የነርቭ ሥርዓት እንዲሰጥ ተደርጎ መሠራቱ ተገቢ ነው።

የሆድ ዕቃን የሚቆጣጠረው የነርቭ ሥርዓት የአንጎልን ያህል ባይሆንም በጣም ውስብስብ ነው። ይህ የነርቭ ሥርዓት በሰዎች ውስጥ ከ200 እስከ 600 ሚሊዮን ከሚያክሉ የነርቭ ሴሎች የተዋቀረ ነው። ውስብስብ የሆነው ይህ የነርቭ ሴሎች አውታር፣ ምግብ ከሚፈጭባቸው የሰውነታችን ክፍሎች ጋር አብሮ የተሠራ ነው። የሳይንስ ሊቃውንት፣ ምግብ የሚፈጭበትን ሥርዓት የመቆጣጠሩ ሥራ የሚከናወነው በአንጎል ውስጥ ቢሆን ኖሮ ይህን ሥራ የሚያከናውኑት ነርቮች በጣም ወፍራም መሆን ያስፈልጋቸው እንደነበር ይናገራሉ። ዘ ሰከንድ ብሬይን የተባለው መጽሐፍ “[ምግብ የሚፈጭበት ሥርዓት] ራሱን በራሱ እንዲቆጣጠር ተደርጎ መሠራቱ ይበልጥ አስተማማኝና አመቺ” እንደሆነ ይናገራል።

የኬሚካል ውህደት የሚካሄድበት ቦታ

የተመገብነው ምግብ እንዲፈጭ ትክክለኛው የኬሚካል ውህድ በትክክለኛው ጊዜ መመረትና ወደ ትክክለኛው ቦታ እንዲደርስ መደረግ አለበት። የዚህ ኬሚካላዊ ሂደት ውስብስብነት በጣም አስደናቂ ነው። ለአብነት ያህል፣ የአንጀት ግድግዳ በተመገብነው ምግብ ውስጥ የትኞቹ ኬሚካሎች እንደሚገኙ መለየት የሚችሉ ሴሎች አሉት። ይህ መረጃ የሆድ ዕቃን የሚቆጣጠረው የነርቭ ሥርዓት የተመገብነውን ምግብ ከሰውነታችን ጋር መዋሃድ ወደሚችልበት ደረጃ ለመቀየር የሚያስፈልጉትን ኢንዛይሞች ለይቶ እንዲልክ ያስችለዋል። በተጨማሪም የሆድ ዕቃን የሚቆጣጠረው የነርቭ ሥርዓት የምግቡን አሲድነትና ሌሎች ኬሚካላዊ ባሕርያት ይቆጣጠራል፤ በዚያ ላይ ተመሥርቶም የተመገብነውን የምግብ ዓይነት ለመፍጨት የሚያስፈልጉትን ኢንዛይሞች ያስተካክላል።

የተመገብነው ምግብ፣ በምግብ መፈጨት ሥርዓት ውስጥ የተለያዩ ሂደቶችን እያለፈ የሚሄድበት መንገድ በጣም አስገራሚ ነው፤ ይህን ሂደት በዋነኝነት የሚቆጣጠረው ደግሞ የሆድ ዕቃን የሚቆጣጠረው የነርቭ ሥርዓት ነው። “ሁለተኛው አንጎል” የተመገብነው ምግብ በሚያልፍባቸው የሰውነት ክፍሎች ግድግዳ ላይ የሚገኙት ጡንቻዎች እንዲኮማተሩ በማድረግ ምግቡ በእነዚህ የሰውነት ክፍሎች ውስጥ እንዲያልፍ ያደርጋል። ይህን የሚያደርገው ጡንቻዎቹ የሚኮማተሩበትን መጠንና ፍጥነት እንደ ሁኔታው በመቀያየር ነው።

የሆድ ዕቃን የሚቆጣጠረው የነርቭ ሥርዓት፣ ሰውነታችንን ከጎጂ ሕዋሳትም ይከላከላል። አብዛኛውን ጊዜ የምንመገበው ምግብ ጎጂ የሆኑ ባክቴሪያዎች ይኖሩታል። በእርግጥም የሰውነታችን በሽታ ተከላካይ ሕዋሳት ወሳኝ ክፍል ከሆኑት ሊምፎሳይት ሴሎች መካከል ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆኑት በሆዳችን ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው ተገቢ ነው! በተመገብነው ምግብ ውስጥ ጎጂ ባክቴሪያዎች በብዛት የሚገኙ ከሆነ ይህ የነርቭ ሥርዓት ምግቡ በሚያልፍባቸው የሰውነት ክፍሎች ውስጥ ያሉት ጡንቻዎች በኃይል እንዲኮማተሩ በማድረግ የመረዘን ነገር በትውከት ወይም በተቅማጥ አማካኝነት እንዲወጣ ያደርጋል።

ጥሩ የመልእክት ልውውጥ

የሆድ ዕቃን የሚቆጣጠረው የነርቭ ሥርዓት ከአንጎል ውጭ ራሱን ችሎ ሥራውን የሚያከናውን ሊመስል ይችላል፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በሁለቱ የነርቭ ማዕከሎች መካከል የማያቋርጥ የመልእክት ልውውጥ ይደረጋል። ለምሳሌ ያህል፣ የሆድ ዕቃን የሚቆጣጠረው የነርቭ ሥርዓት መቼ መብላት እንዳለብንና ምን ያህል መብላት እንዳለብን ለአንጎላችን የሚነግሩትን ሆርሞኖች በመቆጣጠር ረገድ የሚጫወተው ሚና አለ። በዚህ የነርቭ ሥርዓት ውስጥ ያሉት ሴሎች ስንጠግብ ይህን የሚጠቁም መልእክት ለአንጎላችን ይልካሉ፤ ከልክ በላይ ከበላን ደግሞ የማቅለሽለሽ ስሜት እንዲሰማን ሊያደርጉ ይችላሉ።

ይህን ርዕስ ከማንበብህ በፊትም እንኳ በሆድ ዕቃህና በአንጎልህ መካከል የሆነ ግንኙነት እንዳለ ሳትገምት አትቀርም። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ምግቦችን ስትመገብ ጥሩ ስሜት እንደሚሰማህ አስተውለሃል? ይህ የሚሆነው እንዲህ ያሉ ምግቦችን በምትመገብበት ወቅት የሆድ ዕቃህን የሚቆጣጠረው የነርቭ ሥርዓት ለአንጎልህ ‘የደስታ መልእክት’ ስለሚልክና አንጎልህም በምላሹ ጥሩ ስሜት እንዲሰማህ ስለሚያደርግ እንደሆነ አንዳንድ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ሰዎች ውጥረት ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርጉ ምግቦችን የሚመገቡት ለዚህ ሊሆን ይችላል። የሳይንስ ሊቃውንት የሆድ ዕቃን የሚቆጣጠረው የነርቭ ሥርዓት ሰው ሠራሽ በሆነ መልኩ እንዲህ ዓይነቱን መልእክት እንዲልክ በማድረግ የመንፈስ ጭንቀትን ማከም ይቻል እንደሆነ ለማወቅ ምርምር እያደረጉ ነው።

በአንጎላችንና ምግብ እንዲፈጭ በሚያደርጉት የሰውነታችን ክፍሎች መካከል ግንኙነት እንዳለ የሚያሳይ ሌላ ማስረጃም መጥቀስ እንችላለን፤ ለምሳሌ አንድ ሰው በጣም ሲጨንቀው ሆዱን ሊቆርጠው ይችላል። ይህ የሚሆነው አንጎላችን ውጥረት ውስጥ በሚሆንበት ጊዜ የሆድ ዕቃችንን የሚቆጣጠረው የነርቭ ሥርዓት፣ ደም ወደ ሆድ ዕቃችን እንዳይሄድ ስለሚያደርግ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ውጥረት ውስጥ ስንሆን የማቅለሽለሽ ስሜት ሊሰማን ይችላል፤ እንዲህ ያለ ስሜት የሚሰማን አንጎላችን የሆድ ዕቃችንን ለሚቆጣጠረው የነርቭ ሥርዓት መልእክት በመላክ የሆድ ዕቃችን የተለመደ እንቅስቃሴውን እንዲቀይር ስለሚያደርገው ነው።

የሆድ ዕቃህን የሚቆጣጠረው የነርቭ ሥርዓት አንዳንድ ጊዜ “ሁለተኛው አንጎል” ተብሎ የሚጠራ ቢሆንም ሊያስብልህ ወይም ምን ውሳኔ ማድረግ እንዳለብህ ሊጠቁምህ አይችልም። በሌላ አባባል ይህ የነርቭ ሥርዓት እንደ አንጎል ሊቆጠር አይችልም። የሒሳብ ስሌት እንድትሠራ፣ ሙዚቃ እንድታቀናብር ወይም የቤት ሥራህን እንድትሠራ ሊረዳህ አይችልም። ይሁንና አስደናቂ የሆነው የዚህ የነርቭ ሥርዓት ውስብስብነት ሳይንቲስቶችን ማስደመሙን ቀጥሏል፤ ያውም ሳይንቲስቶች ስለዚህ የነርቭ ሥርዓት የሚያውቁት በጣም ጥቂቱን ብቻ ነው ሊባል ይችላል። ስለዚህ በቀጣዩ ጊዜ ምግብ ስትመገብ የምትመገበውን ምግብ ባሕርይ ከመለየት፣ አስፈላጊውን መረጃ ከማሰባሰብ እንዲሁም መልእክት ከማስተላለፍ ጋር በተያያዘ ምግብ በሚፈጭባቸው የሰውነትህ ክፍሎች ውስጥ ምን ያህል የተቀናጀ ሥራ እንደሚከናወን ለአፍታ ቆም ብለህ ለማሰብ ሞክር!