የጥናት ርዕስ 40
እውነተኛ ንስሐ ምንድን ነው?
“እኔ የመጣሁት ኃጢአተኞች ንስሐ እንዲገቡ ለመጥራት [ነው]።”—ሉቃስ 5:32
መዝሙር 36 ልባችንን እንጠብቅ
ማስተዋወቂያ a
1-2. በንጉሥ አክዓብና በንጉሥ ምናሴ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? የትኞቹን ጥያቄዎችስ እንመልሳለን?
በጥንት ዘመን የኖሩ ሁለት ነገሥታትን ታሪክ እንመልከት። አንደኛው ንጉሥ ይገዛ የነበረው አሥሩን ነገድ ባቀፈው የእስራኤል መንግሥት ላይ ሲሆን ሌላኛው ንጉሥ ደግሞ ይገዛ የነበረው ሁለቱን ነገዶች ባቀፈው የይሁዳ መንግሥት ላይ ነበር። ሁለቱ ነገሥታት የኖሩት በተለያየ ዘመን ላይ ቢሆንም የሚያመሳስላቸው ብዙ ነገር አለ። ሁለቱም በይሖዋ ላይ ዓምፀዋል፤ እንዲሁም የይሖዋ ሕዝብ ኃጢአት እንዲፈጽም አድርገዋል። ሁለቱም በጣዖት አምልኮ ተካፍለዋል፤ እንዲሁም ነፍስ አጥፍተዋል። ሆኖም በእነዚህ ሁለት ሰዎች መካከል አንድ ልዩነት አለ። አንደኛው እስከ ዕድሜው መጨረሻ ድረስ መጥፎ አካሄድ መከተሉን ቀጥሏል። ሁለተኛው ግን ንስሐ ገብቷል፤ ለፈጸማቸው ከባድ ኃጢአቶችም ይቅርታ ተደርጎለታል። እነዚህ ነገሥታት እነማን ናቸው?
2 እነዚህ ነገሥታት፣ የእስራኤል ንጉሥ የነበረው አክዓብና የይሁዳ ንጉሥ የነበረው ምናሴ ናቸው። በእነዚህ ሁለት ሰዎች መካከል ያለው ልዩነት፣ ወሳኝ ርዕሰ ጉዳይ የሆነውን ንስሐን በተመለከተ ብዙ ትምህርት ይሰጠናል። (ሥራ 17:30፤ ሮም 3:23) ንስሐ ምንድን ነው? አንድ ሰው ንስሐ መግባቱ የሚታየውስ እንዴት ነው? እኛም ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ ይሖዋ ይቅር እንዲለን እንፈልጋለን። በመሆኑም የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማወቃችን አስፈላጊ ነው። መልሱን ለማግኘት የእነዚህን ሁለት ነገሥታት ታሪክ እንመረምራለን። በተጨማሪም ከእነሱ ታሪክ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመለከታለን። ከዚያም ኢየሱስ ስለ ንስሐ የሰጠውን ትምህርት እንመለከታለን።
ከንጉሥ አክዓብ ታሪክ ምን እንማራለን?
3. አክዓብ ምን ዓይነት ንጉሥ ነበር?
3 አክዓብ አሥሩን ነገድ ያቀፈው የእስራኤል መንግሥት ሰባተኛ ንጉሥ ነበር። አክዓብ የሲዶና ንጉሥ ልጅ የሆነችውን ኤልዛቤልን አግብቶ ነበር፤ ሲዶና ከእስራኤል በስተ ሰሜን የምትገኝ ሀብታም አገር ነበረች። ይህ ትዳር ለእስራኤል ብሔር ሀብት አስገኝቶ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ብሔሩ ከይሖዋ ጋር ያለው ዝምድና ይበልጥ እንዲበላሽ አድርጓል። ኤልዛቤል የባአል አምላኪ ነበረች፤ እንዲሁም ይህን አስጸያፊ ሃይማኖት እንዲያስፋፋ አክዓብን ገፋፍታዋለች፤ የባአል አምልኮ የቤተ መቅደስ ዝሙት አዳሪነትንና ልጆችን መሥዋዕት ማድረግን ያካትት ነበር። ኤልዛቤል ሥልጣን ላይ በነበረችበት ዘመን፣ ሁሉም የይሖዋ ነቢያት ሕይወታቸው አደጋ ውስጥ ነበር። በርካታ የይሖዋ ነቢያትን አስገድላለች። (1 ነገ. 18:13) አክዓብም “ከእሱ በፊት የነበሩት ሁሉ ከፈጸሙት የከፋ ድርጊት በይሖዋ ፊት” ፈጽሟል። (1 ነገ. 16:30) አክዓብና ኤልዛቤል የፈጸሙት ኃጢአት ከይሖዋ እይታ አላመለጠም። ይሖዋ ሁሉንም ነገር ተመልክቷል። ያም ቢሆን ይሖዋ መሐሪ ስለሆነ ሕዝቡ ቅጣት ሳይመጣባቸው በፊት አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ ለማስጠንቀቅ ነቢዩ ኤልያስን ላከላቸው። አክዓብና ኤልዛቤል ግን ማስጠንቀቂያውን ለመስማት አሻፈረን አሉ።
4. በአክዓብ ላይ የተላለፈው ፍርድ ምን ነበር? አክዓብስ ይህን ሲሰማ ምን አደረገ?
4 በመጨረሻም የይሖዋ ትዕግሥት ተሟጠጠ። ኤልያስን በመላክ በአክዓብና በኤልዛቤል ላይ ፍርድ አስተላለፈ። ፍርዱ መላው ቤተሰባቸው እንደሚደመሰስ የሚገልጽ ነበር። አክዓብ፣ ኤልያስ የተናገረውን ነገር ሲሰማ በጣም ደነገጠ! የሚገርመው ያ ትዕቢተኛ ሰው ‘ራሱን አዋረደ።’—1 ነገ. 21:19-29
5-6. አክዓብ እውነተኛ ንስሐ እንዳልገባ የሚያሳየው ምንድን ነው?
5 አክዓብ በዚያ ወቅት ራሱን ያዋረደ ቢሆንም ከዚያ በኋላ ያደረገው ነገር ንስሐው እውነተኛ እንዳልነበር ያሳያል። የበዓል አምልኮን ከግዛቱ ለማስወገድ ጥረት አላደረገም። የይሖዋን አምልኮ ለማስፋፋትም አልሞከረም። አክዓብ እውነተኛ ንስሐ አለመግባቱ በሌሎች መንገዶችም ታይቷል።
6 ከጊዜ በኋላ አክዓብ የይሁዳ ንጉሥ የሆነውን ኢዮሳፍጥን ከሶርያውያን ጋር በሚያደርገው ውጊያ አብሮት እንዲሄድ ጠይቆት ነበር። ጥሩ ንጉሥ የነበረው ኢዮሳፍጥም በመጀመሪያ የይሖዋን ነቢይ እንዲጠይቁ ሐሳብ አቀረበ። መጀመሪያ ላይ አክዓብ ሐሳቡን በመቃወም እንዲህ አለ፦ “በእሱ አማካኝነት ይሖዋን ልንጠይቅ የምንችልበት አንድ ሰው ይቀራል፤ ሆኖም ስለ እኔ መጥፎ ነገር ብቻ እንጂ መልካም ነገር ፈጽሞ ስለማይተነብይ በጣም እጠላዋለሁ።” በኋላ ላይ ግን ነቢዩ ሚካያህን ጠየቁ። እንደተጠበቀው የአምላክ ነቢይ በአክዓብ ላይ መጥፎ ነገር እንደሚደርስበት ተነበየ! በዚህ ጊዜ ክፉው ንጉሥ አክዓብ የይሖዋን ምሕረት ከመለመን ይልቅ ነቢዩን እስር ቤት አስገባው። (1 ነገ. 22:7-9, 23, 27) ንጉሡ የይሖዋን ነቢይ ቢያሳስረውም ትንቢቱ እንዳይፈጸም ማድረግ አልቻለም። በጦርነቱ አክዓብ ተገደለ።—1 ነገ. 22:34-38
7. አክዓብ ከሞተ በኋላ ይሖዋ ስለ እሱ ምን ብሏል?
7 አክዓብ ከሞተ በኋላ ይሖዋ ስለዚህ ሰው ያለውን አመለካከት ገልጿል። ጥሩው ንጉሥ ኢዮሳፍጥ ከጦርነቱ በሰላም ከተመለሰ በኋላ ይሖዋ ነቢዩ ኢዩን በመላክ፣ ከአክዓብ ጎን በመቆሙ ተግሣጽ ሰጠው። የይሖዋ ነቢይ ለኢዮሳፍጥ እንዲህ አለው፦ “ለክፉ ሰው እርዳታ መስጠት ይገባሃል? ይሖዋን የሚጠሉትንስ መውደድ ይገባሃል?” (2 ዜና 19:1, 2) እስቲ አስበው፦ አክዓብ ከልቡ ንስሐ የገባ ቢሆን ኖሮ ነቢዩ፣ አክዓብ ይሖዋን የሚጠላ ክፉ ሰው እንደሆነ አይገልጽም ነበር። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አክዓብ በመጠኑ ተጸጽቶ የነበረ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ንስሐ አልገባም።
8. ከአክዓብ ታሪክ ስለ ንስሐ ምን እንማራለን?
8 ከአክዓብ ታሪክ ምን እንማራለን? አክዓብ በቤተሰቡ ላይ ስለሚመጣው ጥፋት ኤልያስ ሲነግረው መጀመሪያ ላይ ራሱን አዋርዶ ነበር። ይህ ጥሩ እርምጃ ነው። ሆኖም ከዚያ በኋላ ያደረጋቸው ነገሮች ከልቡ ንስሐ እንዳልገባ ያሳያሉ። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ንስሐ መግባት ጊዜያዊ የሆነ የጸጸት ስሜት ከማሳየት ያለፈ ነገርን ሊያካትት ይገባል። እስቲ አሁን ደግሞ እውነተኛ ንስሐ ምን ማለት እንደሆነ የሚያሳይ ሌላ ምሳሌ እንመልከት።
ከንጉሥ ምናሴ ታሪክ ምን እንማራለን?
9. ምናሴ ምን ዓይነት ንጉሥ ነበር?
9 ከ200 ዓመታት ገደማ በኋላ ምናሴ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ። ምናሴ የፈጸመው ኃጢአት ከአክዓብም ሳይብስ አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እሱ ሲናገር “ይሖዋን ያስቆጣው ዘንድ በእሱ ፊት በጣም ብዙ መጥፎ ነገሮችን ሠራ” ይላል። (2 ዜና 33:1-9) ምናሴ ለባዕድ አማልክት መሠዊያዎችን አቁሟል፤ ይባስ ብሎም ቅዱስ በሆነው የይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ የማምለኪያ ግንድ አቁሟል! ይህ የማምለኪያ ግንድ የመራባት አምላክን የሚወክል ጣዖት ሳይሆን አይቀርም። ምናሴ አስማተኛ፣ ሟርተኛና መተተኛ ሆኖ ነበር። በተጨማሪም “እጅግ ብዙ ንጹሕ ደም አፍስሷል።” በጭካኔ ከገደላቸው ሰዎች መካከል ለሐሰት አማልክት መሥዋዕት እንዲሆኑ ‘ለእሳት አሳልፎ የሰጣቸው የገዛ ልጆቹ’ ይገኙበታል።—2 ነገ. 21:6, 7, 10, 11, 16
10. ይሖዋ ለምናሴ ተግሣጽ የሰጠው እንዴት ነው? እሱስ ምን አደረገ?
10 እንደ አክዓብ ሁሉ ምናሴም ልቡን በማደንደን ይሖዋ በነቢያቱ አማካኝነት የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ለመስማት ፈቃደኛ አልሆነም። በመጨረሻም “ይሖዋ [በይሁዳ ሕዝብ ላይ] የአሦርን ንጉሥ ሠራዊት አለቆች አመጣባቸው፤ እነሱም ምናሴን በመንጠቆ ያዙት፤ ከመዳብ በተሠሩ ሁለት የእግር ብረቶች አስረው ወደ ባቢሎን ወሰዱት።” ምናሴ በባዕድ አገር ታስሮ በነበረበት ወቅት፣ ስለፈጸማቸው ኃጢአቶች ቆም ብሎ ማሰብ ጀመረ። “በአባቶቹም አምላክ ፊት ራሱን እጅግ አዋረደ።” ግን በዚህ ብቻ አልተወሰነም። “ሞገስ እንዲያሳየው አምላኩን ይሖዋን ለመነ።” እንዲያውም “ወደ እሱ አጥብቆ ጸለየ።” ያ ክፉ ሰው ለውጥ እያደረገ ነበር። ይሖዋን እንደ “አምላኩ” አድርጎ መመልከት ጀመረ፤ እንዲሁም ሳያሰልስ ወደ እሱ ጸለየ።—2 ዜና 33:10-13
11. በ2 ዜና መዋዕል 33:15, 16 መሠረት ምናሴ እውነተኛ ንስሐ መግባቱን ያሳየው እንዴት ነው?
11 ከጊዜ በኋላ ይሖዋ የምናሴን ጸሎት መለሰለት። ይሖዋ የምናሴ ልብ መለወጡን ካቀረባቸው ጸሎቶች ተመልክቷል። በመሆኑም ይሖዋ፣ ምናሴ ምሕረት ለማግኘት ያቀረበውን ጸሎት በመስማት ወደ ዙፋኑ መለሰው። ምናሴም እውነተኛ ንስሐ መግባቱን ለማሳየት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ አደረገ። ምናሴ አክዓብ ያላደረገውን ነገር አድርጓል። ምግባሩን አስተካክሏል። የሐሰት አምልኮን ለማጥፋት ከፍተኛ ጥረት ያደረገ ከመሆኑም ሌላ እውነተኛውን አምልኮ አስፋፍቷል። (2 ዜና መዋዕል 33:15, 16ን አንብብ።) ምናሴ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ለቤተሰቡ፣ ለመኳንንቱ እንዲሁም ለሕዝቡ መጥፎ ምሳሌ የነበረ ከመሆኑ አንጻር ለውጥ ለማድረግ ድፍረትና እምነት እንደጠየቀበት ጥርጥር የለውም። ምናሴ በሕይወቱ መጨረሻ ላይ፣ የሠራቸውን መጥፎ ነገሮች ለማስተካከል ጥረት አድርጓል። ምናሴ በልጅ ልጁ በኢዮስያስ ላይ ጥሩ ተጽዕኖ አሳድሮ መሆን አለበት፤ ኢዮስያስም በጣም ጥሩ ንጉሥ ሆኗል።—2 ነገ. 22:1, 2
12. ከምናሴ ታሪክ ስለ ንስሐ ምን እንማራለን?
12 ከምናሴ ታሪክ ምን እንማራለን? ምናሴ ራሱን አዋርዷል፤ ግን በዚህ ብቻ አልተወሰነም። ምሕረት ለማግኘት ይሖዋን ለምኗል። እንዲሁም አካሄዱን ቀይሯል። የሠራቸውን መጥፎ ነገሮች ለማስተካከል ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። በተጨማሪም ይሖዋን ለማምለክና ሌሎችም እንደዚያ እንዲያደርጉ ለመርዳት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ አድርጓል። የምናሴ ታሪክ፣ በጣም ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ ሰዎችም ተስፋ እንዳላቸው ያሳያል። ይህ ታሪክ ይሖዋ አምላክ ‘ጥሩ እና ይቅር ለማለት ዝግጁ’ እንደሆነ የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ነው። (መዝ. 86:5) እውነተኛ ንስሐ የሚገቡ ሰዎች ይቅር ይባላሉ።
13. ስለ ንስሐ ያገኘነውን ወሳኝ ትምህርት በምሳሌ አስረዳ።
13 ምናሴ በፈጸመው ኃጢአት ከመጸጸት ያለፈ ነገር አድርጓል። ይህም ስለ ንስሐ አንድ ወሳኝ ትምህርት ይሰጠናል። አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ ዳቦ ለመግዛት ዳቦ ቤት ሄድክ እንበል። ሆኖም ሻጩ፣ ዳቦ ሳይሆን ዱቄት ሰጠህ። የፈለግከውን እንዳገኘህ ይሰማሃል? እንደማይሰማህ የታወቀ ነው። ሻጩ፣ ዳቦ ለመጋገር ዱቄት የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ቢነግርህስ? ይህም ቢሆን አጥጋቢ መልስ አይደለም። በተመሳሳይም ይሖዋ ኃጢአተኞች ንስሐ እንዲገቡ ይፈልጋል። ኃጢአተኛው በኃጢአቱ ከተጸጸተ ይህ ጥሩ እርምጃ ነው። ይህ ስሜት የንስሐ ወሳኝ ክፍል ነው፤ ሆኖም ንስሐ ማለት መጸጸት ማለት ብቻ አይደለም። ታዲያ ሌላስ ምን ያስፈልጋል? ኢየሱስ ከተናገረው ልብ የሚነካ አንድ ምሳሌ ብዙ ትምህርት እናገኛለን።
እውነተኛ ንስሐ የሚገለጸው በምንድን ነው?
14. በኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው አባካኙ ልጅ የንስሐን መንገድ እንደጀመረ ያሳየው እንዴት ነው?
14 ኢየሱስ በሉቃስ 15:11-32 ላይ ስለ አባካኙ ልጅ የሚገልጸውን ልብ የሚነካ ምሳሌ ተናግሯል። አንድ ወጣት በአባቱ ላይ ዓመፀ፤ ከዚያም ከቤት ወጥቶ “ወደ ሩቅ አገር ተጓዘ።” በዚያም ሥነ ምግባር የጎደለውና ልቅ የሆነ ሕይወት መምራት ጀመረ። ሆኖም ችግር ውስጥ ሲገባ፣ ስለሠራቸው ስህተቶች በጥሞና ማሰብ ጀመረ። በአባቱ ቤት በነበረበት ወቅት ሕይወቱ በጣም የተሻለ እንደነበር ተገነዘበ። ኢየሱስ እንዳለው ወጣቱ ‘ወደ ልቦናው ተመለሰ።’ በመሆኑም ወደ ቤቱ በመመለስ የአባቱን ምሕረት ለመለመን ወሰነ። ወጣቱ፣ ምን ያህል ከባድ ስህተት እንደሠራ መገንዘቡ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። ግን ይህ ብቻውን በቂ ነው? አይደለም። ወጣቱ እርምጃ መውሰድ ነበረበት!
15. በኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው አባካኙ ልጅ ንስሐ መግባቱን ያሳየው እንዴት ነው?
15 አባካኙ ልጅ ለሠራው ስህተት ከልቡ ንስሐ መግባቱን አሳይቷል። ረጅሙን መንገድ ተጉዞ ወደ ቤቱ ተመልሷል። ከዚያም አባቱን ሲያገኘው እንዲህ አለው፦ “በአምላክና በአንተ ላይ በደል ፈጽሜአለሁ። ከእንግዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም።” (ሉቃስ 15:21) ወጣቱ በዚህ መንገድ ከልቡ መናዘዙ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ማደስ እንደሚፈልግ ያሳያል። በተጨማሪም ድርጊቱ የአባቱን ስሜት እንደጎዳው ተገንዝቧል። እንዲሁም የአባቱን ሞገስ መልሶ ለማግኘት ሲል ከፍተኛ ጥረት ለማድረግ ፈቃደኛ ነበር፤ እንዲያውም ከአባቱ ቅጥር ሠራተኞች እንደ አንዱ እንዲቆጠር ጠይቋል። (ሉቃስ 15:19) ይህ ምሳሌ ልብ የሚነካ ታሪክ ብቻ አይደለም። የጉባኤ ሽማግሌዎች ከባድ ኃጢአት የፈጸመ አንድ የእምነት ባልንጀራቸው እውነተኛ ንስሐ መግባት አለመግባቱን በሚገመግሙበት ጊዜ ከዚህ ምሳሌ ለምናገኘው ትምህርት ትኩረት ሊሰጡት ይገባል።
16. ሽማግሌዎች አንድ ክርስቲያን እውነተኛ ንስሐ መግባቱን ማወቅ ከባድ ሊሆንባቸው የሚችለው ለምንድን ነው?
16 ከባድ ኃጢአት የፈጸመ አንድ ክርስቲያን እውነተኛ ንስሐ መግባቱን ማወቅ ለሽማግሌዎች ቀላል አይደለም። ለምን? ሽማግሌዎች ልብ ማንበብ አይችሉም፤ ስለዚህ ወንድማቸው ለፈጸመው ኃጢአት ያለውን አመለካከት ሙሉ በሙሉ እንደቀየረ ለማወቅ የሚያስችል በግልጽ የሚታይ ማስረጃ ያስፈልጋቸዋል። አንዳንድ ጊዜ አንድ ሰው በኃጢአት ከመዘፈቁ የተነሳ፣ ጉዳዩን የሚመለከቱት ሽማግሌዎች ግለሰቡ እውነተኛ ንስሐ መግባቱን ማመን ሊከብዳቸው ይችላል።
17. (ሀ) አንድ ሰው በፈጸመው ኃጢአት ማዘኑን መግለጹ ብቻውን እውነተኛ ንስሐ እንደገባ የሚያረጋግጥ አለመሆኑን የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ። (ለ) በ2 ቆሮንቶስ 7:11 ላይ እንደተገለጸው እውነተኛ ንስሐ ከሚገባ ሰው ምን ይጠበቃል?
17 አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንድ ወንድም ለዓመታት ምንዝር ሲፈጽም ኖሯል እንበል። የሽማግሌዎችን እርዳታ ከመጠየቅ ይልቅ ኃጢአቱን ከባለቤቱ፣ ከጓደኞቹ እንዲሁም ከሽማግሌዎች ደብቋል። በመጨረሻም ኃጢአቱ ተጋለጠ። ግለሰቡ፣ ሽማግሌዎች ምንዝር መፈጸሙን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዳላቸው ሲነግሩት ኃጢአቱን አመነ፤ እንዲያውም በድርጊቱ በጣም ያዘነ ይመስላል። ግን ይህ እውነተኛ ንስሐ መግባቱን ያሳያል? ጉዳዩን የሚመለከቱት ሽማግሌዎች ግለሰቡ በድርጊቱ ማዘኑን ማየታቸው ብቻ ንስሐ ገብቷል ብለው ለመደምደም በቂ እንደማይሆንላቸው ግልጽ ነው። ይህ ሰው ኃጢአት የፈጸመው ድንገት ተሳስቶ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ለበርካታ ዓመታት የክፋት አካሄድ ሲከተል ቆይቷል። ከዚህም ሌላ ኃጢአቱ የታወቀው ግለሰቡ በራሱ ተነሳሽነት ተናዝዞ ሳይሆን ሌላ ሰው አጋልጦት ነው። በመሆኑም ሽማግሌዎች የግለሰቡ አስተሳሰብ፣ ስሜትና ድርጊት ሙሉ በሙሉ መቀየሩን የሚያሳይ ማስረጃ ያስፈልጋቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 7:11ን አንብብ።) ግለሰቡ አስፈላጊውን ለውጥ እንዲያደርግ ረዘም ያለ ጊዜ ሊያስፈልገው ይችላል። በመሆኑም ሽማግሌዎቹ ይህ ሰው ለተወሰነ ጊዜ ከክርስቲያን ጉባኤ እንዲወገድ የመወሰናቸው አጋጣሚ ሰፊ ነው።—1 ቆሮ. 5:11-13፤ 6:9, 10
18. አንድ የተወገደ ሰው እውነተኛ ንስሐ ማሳየት የሚችለው እንዴት ነው? ይህስ ምን ውጤት ያስገኛል?
18 ከጉባኤ የተወገደ አንድ ግለሰብ እውነተኛ ንስሐ መግባቱን ለማሳየት አዘውትሮ በስብሰባዎች ላይ መገኘት እንዲሁም የሽማግሌዎችን ምክር በመከተል አዘውትሮ መጸለይ እና መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ይኖርበታል። በተጨማሪም ወደ ኃጢአት ከመሩት ነገሮች ለመራቅ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለበት። ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ለማደስ በርትቶ ከሠራ ይሖዋ ሙሉ በሙሉ ይቅር እንደሚለው እንዲሁም ሽማግሌዎች ወደ ጉባኤው እንደሚመልሱት እርግጠኛ መሆን ይችላል። እርግጥ ነው፣ ሽማግሌዎች አንድ ኃጢአተኛ ከልቡ ንስሐ መግባቱን ለማረጋገጥ በሚሞክሩበት ወቅት የእያንዳንዱ ሰው ሁኔታ የተለያየ እንደሆነ ከግምት ያስገባሉ። ስለዚህ ጉዳዩን በጥንቃቄ ይመረምራሉ እንዲሁም ግለሰቡ ወደ ጉባኤ መመለስ እንዲችል ከሚጠብቁበት ነገር ጋር በተያያዘ ከልክ በላይ ጥብቅ ላለመሆን ጥረት ያደርጋሉ።
19. እውነተኛ ንስሐ መግባት ምን ይጠይቃል? (ሕዝቅኤል 33:14-16)
19 እስካሁን እንደተመለከትነው እውነተኛ ንስሐ መግባት ለፈጸምነው ኃጢአት ይቅርታ ከመጠየቅ ያለፈ ነገርን ያካትታል። አስተሳሰባችንን እና ልባችንን ሙሉ በሙሉ መቀየር እንዲሁም ንስሐ መግባታችንን በተግባር ማሳየት ይኖርብናል። ይህም መጥፎ አካሄዳችንን መተውንና ከኃጢአታችን ተመልሰን ይሖዋን የሚያስደስት አካሄድ መከተልን ይጨምራል። (ሕዝቅኤል 33:14-16ን አንብብ።) አንድ ኃጢአተኛ ከምንም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ማስተካከል ነው።
ኃጢአተኞች ንስሐ እንዲገቡ መጥራት
20-21. ከባድ ኃጢአት የፈጸመን ሰው መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?
20 ኢየሱስ ከአገልግሎቱ ወሳኝ ገጽታዎች አንዱ ምን እንደሆነ ሲናገር “እኔ የመጣሁት ኃጢአተኞች ንስሐ እንዲገቡ ለመጥራት [ነው]” ብሏል። (ሉቃስ 5:32) እኛም እንዲህ የማድረግ ፍላጎት ሊኖረን ይገባል። አንድ የቅርብ ወዳጃችን ከባድ ኃጢአት እንደፈጸመ አወቅን እንበል። ምን ማድረግ ይኖርብናል?
21 የጓደኛችንን ኃጢአት ለመሸፋፈን ብንሞክር እሱን እንጎዳዋለን እንጂ አንጠቅመውም። ደግሞም ይሖዋ ሁሉንም ነገር ስለሚመለከት ኃጢአቱን ለመሸፈን የምናደርገው ጥረት አይሳካም። (ምሳሌ 5:21, 22፤ 28:13) ለጓደኛህ ሽማግሌዎች ሊረዱት እንደሚፈልጉ አስታውሰው። ጓደኛህ ኃጢአቱን ለሽማግሌዎች ለመናዘዝ ፈቃደኛ ካልሆነ አንተ ራስህ ጉዳዩን ለሽማግሌዎች መናገር ይኖርብሃል፤ ይህም ጓደኛህን ለመርዳት ከልብህ እንደምትፈልግ ያሳያል። ምክንያቱም ጓደኛህ ከይሖዋ ጋር ያለው ዝምድና አደጋ ላይ ወድቋል።
22. በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
22 ይሁንና አንድ ሰው ለረጅም ጊዜ ከባድ ኃጢአት ሲፈጽም በመቆየቱ ሽማግሌዎች ይህ ሰው እንዲወገድ ቢወስኑስ? ይህን ውሳኔ ማድረጋቸው ግለሰቡን በምሕረት እንዳልያዙት ያሳያል? በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ይሖዋ ምሕረት በሚንጸባረቅበት መንገድ ለኃጢአተኞች ተግሣጽ የሚሰጠው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን፤ እኛም የእሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።
መዝሙር 103 እረኞች—ስጦታ የሆኑ ወንዶች
a እውነተኛ ንስሐ መግባት ሲባል ለፈጸምነው ኃጢአት ይቅርታ መጠየቅ ማለት ብቻ አይደለም። ይህ ርዕስ የንጉሥ አክዓብን፣ የንጉሥ ምናሴን እንዲሁም ኢየሱስ የጠቀሰውን የአባካኙን ልጅ ምሳሌ በመጠቀም እውነተኛ ንስሐ ምን እንደሆነ ያስገነዝበናል። በተጨማሪም ሽማግሌዎች ከባድ ኃጢአት የፈጸመ የእምነት ባልንጀራቸው ንስሐ መግባት አለመግባቱን ሲገመግሙ የትኞቹን ነገሮች ግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለባቸው ያብራራል።