ለጥናት የሚረዱ ሐሳቦች
ሥዕል መሣል ለማስታወስ ይረዳል
ብዙዎቻችን ያጠናነውን ነገር ለማስታወስ እንቸገራለን። ይሁንና የኢየሱስን ምሳሌዎች በቀላሉ ማስታወስ እንደሚቻል አስተውለሃል? እነዚህን ምሳሌዎች በምናባችን መሣል እንችላለን፤ ይህም ለማስታወስ ይረዳናል። አንተም የምታጠናውን ነገር በአእምሮህ መሣልህ በተሻለ መንገድ ለማስታወስ ሊረዳህ ይችላል። እንዲህ ለማድረግ የሚረዳህ አንዱ ነገር በምታጠናበት ጊዜ ሥዕሎችን መሣል ነው።
ያገኙትን አዲስ ትምህርት በሥዕል የሚያስቀምጡ ሰዎች ትምህርቱን የማስታወሳቸው አጋጣሚ ሰፊ ይሆናል። እንዲህ ማድረጋቸው ቃላትን ብቻ ሳይሆን ጽንሰ ሐሳቦችንም ለማስታወስ ይረዳቸዋል። ሥዕሉ የግድ የተራቀቀ መሆን አያስፈልገውም፤ ጫር ጫር አድርጎ ማስቀመጥ በቂ ነው። ደግሞም አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ይህ ዘዴ በተለይ ለአረጋውያን ጠቃሚ ነው።
በቀጣዩ የጥናት ፕሮግራምህ ወቅት የተማርከውን ነገር በሥዕል ለማስቀመጥ ለምን አትሞክርም? ከጠበቅከው በላይ ብዙ ነገር ለማስታወስ ይረዳህ ይሆናል!