የጥናት ርዕስ 1
መዝሙር 38 ጠንካራ ያደርግሃል
በይሖዋ በመታመን ፍርሃትህን አሸንፍ
የ2024 የዓመት ጥቅስ፦ “ፍርሃት በሚሰማኝ ጊዜ በአንተ እታመናለሁ።”—መዝ. 56:3
ዓላማ
በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከርና ፍርሃታችንን ማሸነፍ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንማራለን።
1. አልፎ አልፎ ፍርሃት የሚሰማን ለምን ሊሆን ይችላል?
ሁሉም ሰው አልፎ አልፎ ፍርሃት ይሰማዋል። እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችን ሙታንን፣ መናፍስትን እንዲሁም የወደፊቱን ጊዜ ከመፍራት ነፃ አውጥቶናል። ያም ቢሆን የምንኖርበት ዘመን እንደ ጦርነት፣ ወንጀልና በሽታ ባሉ “የሚያስፈሩ ነገሮች” የተሞላ ነው። (ሉቃስ 21:11) ከዚህም ሌላ፣ ግፍ የሚፈጽሙብንን ባለሥልጣናትና እውነትን የሚቃወሙ ዘመዶቻችንን ጨምሮ ሰዎችን እንፈራ ይሆናል። አንዳንዶች በአሁኑ ወቅት እያጋጠማቸው ያለውን ወይም ወደፊት ሊያጋጥማቸው የሚችለውን ፈተና በጽናት መቋቋም እንደማይችሉ በማሰብ ይሰጋሉ።
2. ዳዊት ወደ ጌት በሸሸበት ወቅት ምን አጋጠመው?
2 ዳዊት ፍርሃት የተሰማው ጊዜ ነበር። ለምሳሌ ንጉሥ ሳኦል ሊገድለው አስቦ እያሳደደው በነበረበት ወቅት ዳዊት የፍልስጤም ከተማ ወደሆነችው ወደ ጌት ለመሸሽ ወሰነ። ብዙም ሳይቆይ ግን የጌት ንጉሥ የሆነው አንኩስ፣ ዳዊት “አሥር ሺዎችን ገደለ” ተብሎ የተዘፈነለት ኃያል ተዋጊ መሆኑን አወቀ። በዚህ ጊዜ ዳዊት “እጅግ ፈራ።” (1 ሳሙ. 21:10-12) አንኩስ እንዳይገለው ፈርቶ ነበር። ታዲያ ዳዊት ፍርሃቱን ማሸነፍ የቻለው እንዴት ነው?
3. በመዝሙር 56:1-3, 11 መሠረት ዳዊት ፍርሃቱን ማሸነፍ የቻለው እንዴት ነው?
3 በመዝሙር 56 ላይ ዳዊት በጌት ሳለ የተሰማውን ስሜት ጽፏል። ይህ መዝሙር ዳዊት የተሰማውን ፍርሃት በግልጽ ይናገራል፤ ሆኖም ፍርሃቱን ያሸነፈበትን መንገድም ይገልጻል። ዳዊት ፍርሃት በተሰማው ወቅት በይሖዋ ታምኗል። (መዝሙር 56:1-3, 11ን አንብብ።) ደግሞም እምነቱ ክሶታል። በይሖዋ እርዳታ ዳዊት ያልተለመደ ሆኖም ውጤታማ ዘዴ ቀየሰ፤ እንደ እብድ ሆነ። በዚህ ጊዜ አንኩስ ዳዊትን ለመግደል ከማሰብ ይልቅ ከፊቱ እንዲባረርለት ጠየቀ። በመሆኑም ዳዊት ማምለጥ ቻለ።—1 ሳሙ. 21:13–22:1
4. በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።
4 እኛም በይሖዋ በመታመን ፍርሃታችንን ማሸነፍ እንችላለን። ይሁንና በተለይ ፍርሃት በሚሰማን ጊዜ በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው? እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንድ በሽታ እንዳለብህ ቢነገርህ መጀመሪያ ላይ ፍርሃት ይሰማህ ይሆናል። ሆኖም በሐኪምህ የምትተማመን ከሆነ ፍርሃትህ ሊቀንስ ይችላል። የአንተ ዓይነት በሽታ የያዛቸውን ሰዎች በማከም ረገድ ብዙ ልምድ ይኖረው ይሆናል። በጥሞና ስለሚያዳምጥህ ስሜትህን እንደተረዳልህ እርግጠኛ ነህ። ደግሞም በሌሎች ታካሚዎች ላይ ውጤታማ ሆኖ የተገኘ አንድ ሕክምና እንድትከታተል ሐሳብ አቅርቦልሃል። እኛም በተመሳሳይ ይሖዋ ከዚህ በፊት ስላደረገው ነገር፣ አሁን እያደረገ ስላለው ነገር እንዲሁም ወደፊት ስለሚያደርግልን ነገር ማሰባችን በእሱ ላይ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። ዳዊትም ያደረገው ይህንኑ ነው። መዝሙር 56 ላይ ዳዊት በመንፈስ መሪነት የጻፋቸውን ሐሳቦች ስንመረምር አንተም በይሖዋ ላይ ያለህን እምነት ማጠናከርና ፍርሃትህን ማሸነፍ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክር።
ይሖዋ ከዚህ በፊት ምን አድርጓል?
5. ዳዊት ፍርሃቱን ለማሸነፍ በምን ላይ አሰላስሏል? (መዝሙር 56:12, 13)
5 ዳዊት ሕይወቱ አደጋ ላይ በወደቀበት ጊዜ ይሖዋ ከዚያ በፊት ስላደረጋቸው ነገሮች አስቧል። (መዝሙር 56:12, 13ን አንብብ።) ዳዊት በመላው ሕይወቱ እንዲህ የማድረግ ልማድ ነበረው። ለምሳሌ ዳዊት በይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ላይ ያሰላስል ነበር፤ ይህም ይሖዋ ስላለው ገደብ የለሽ ኃይልና ለሰው ልጆች ስላለው ጥልቅ ፍቅር እንዲያስብ አድርጎታል። (መዝ. 65:6-9) ዳዊት፣ ይሖዋ ለሌሎች ሰዎች ባደረገላቸው ነገር ላይም አሰላስሏል። (መዝ. 31:19፤ 37:25, 26) በዋነኝነት ደግሞ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ለእሱ ባደረገለት ነገር ላይ አሰላስሏል። ይሖዋ ዳዊትን ከሕፃንነቱ አንስቶ ደግፎታል እንዲሁም ጠብቆታል። (መዝ. 22:9, 10) ዳዊት በእነዚህ ሐሳቦች ላይ ማሰላሰሉ በይሖዋ ላይ ያለውን እምነት ምንኛ አጠናክሮለት ይሆን!
6. ፍርሃት ሲሰማን በይሖዋ ለመታመን ምን ሊረዳን ይችላል?
6 ፍርሃት ሲሰማህ ‘ይሖዋ ከዚህ በፊት ምን አድርጓል?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። እሱ በፈጠራቸው ነገሮች ላይ አሰላስል። ለምሳሌ ይሖዋ በእሱ መልክ ያልተፈጠሩትንና እሱን የማምለክ ችሎታ የሌላቸውን ወፎችና አበቦች የሚንከባከብበትን መንገድ ‘ልብ ብለን ስንመለከት’ እኛንም እንደሚንከባከበን ያለን እምነት ይጠናከራል። (ማቴ. 6:25-32) ይሖዋ ከዚህ በፊት ለአገልጋዮቹ ያደረገላቸውን ነገርም አስብ። አስደናቂ እምነት ስላሳየ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪክ ልታጠና ወይም በዘመናችን የኖረን አንድ የይሖዋ አገልጋይ ተሞክሮ ልታነብ ትችላለህ። a ከዚህም ሌላ፣ ይሖዋ እስካሁን ባደረገልህ እንክብካቤ ላይ አሰላስል። ወደ እውነት የሳበህ እንዴት ነው? (ዮሐ. 6:44) ጸሎትህን የመለሰልህ እንዴት ነው? (1 ዮሐ. 5:14) የሚወደውን ልጁን መሥዋዕት በማድረጉ በየዕለቱ እየተጠቀምክ ያለኸው እንዴት ነው?—ኤፌ. 1:7፤ ዕብ. 4:14-16
7. ቫኔሳ በነቢዩ ዳንኤል ተሞክሮ ላይ ማሰላሰሏ ፍርሃቷን እንድታሸንፍ የረዳት እንዴት ነው?
7 በሄይቲ የምትኖር ቫኔሳ b የተባለች እህት አስፈሪ ሁኔታ አጋጥሟት ነበር። በአካባቢዋ የሚኖር አንድ ሰው በየቀኑ በመደወልና መልእክት በመላክ ከእሱ ጋር የፍቅር ግንኙነት እንድትጀምር ይወተውታት ነበር። ቫኔሳ ፈቃደኛ አለመሆኗን በግልጽ ነገረችው። ሆኖም ሰውየው በውትወታው ገፋበት፤ ይባስ ብሎም ያስፈራራት ጀመር። ቫኔሳ “በጣም ፈርቼ ነበር” ብላለች። ታዲያ ፍርሃቷን ማሸነፍ የቻለችው እንዴት ነው? ራሷን ከአደጋ ለመጠበቅ ተግባራዊ እርምጃዎችን ወሰደች። አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ፖሊሶችን እንድታነጋግር ረዳት። በተጨማሪም ይሖዋ በጥንት ዘመን አገልጋዮቹን የጠበቃቸው እንዴት እንደሆነ አሰበች። እንዲህ ብላለች፦ “ወደ አእምሮዬ የመጣው የመጀመሪያው ሰው ነቢዩ ዳንኤል ነበር። ዳንኤል ምንም ጥፋት ባይሠራም በተራቡ አንበሶች ወደተሞላ ጉድጓድ ተጥሎ ነበር። ያም ቢሆን ይሖዋ ጠብቆታል። እኔም ይሖዋ ጣልቃ ገብቶ ችግሩን እንዲፈታልኝ ጠየቅኩት። ከዚያ በኋላ ፍርሃቴ ጠፋ።”—ዳን. 6:12-22
ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ ምን እያደረገ ነው?
8. ዳዊት ስለ ምን ጉዳይ እርግጠኛ ነበር? (መዝሙር 56:8)
8 ዳዊት በጌት በነበረበት ወቅት ሕይወቱ አደጋ ውስጥ ቢሆንም ለፍርሃት እጅ አልሰጠም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ በዚያ ወቅት እያደረገለት ባለው ነገር ላይ አተኩሯል። ዳዊት ይሖዋ እየመራውና እየጠበቀው እንደሆነ እንዲሁም ስሜቱን እንደሚረዳለት እርግጠኛ ነበር። (መዝሙር 56:8ን አንብብ።) ከዚህም ሌላ ዳዊት በታማኝነት የሚደግፉትና ተግባራዊ እርዳታ የሚሰጡት እንደ ዮናታንና እንደ ሊቀ ካህናቱ አሂሜሌክ ያሉ ወዳጆች ነበሩት። (1 ሳሙ. 20:41, 42፤ 21:6, 8, 9) ደግሞም ንጉሥ ሳኦል ቢያሳድደውም እንኳ ዳዊት ሕይወቱን ማትረፍ ችሏል። እየደረሰበት ያለውን ፈተና እንዲሁም ይህ ፈተና ያስከተለበትን የስሜት ሥቃይ ይሖዋ በሚገባ እንደሚረዳ እርግጠኛ ነበር።
9. ይሖዋ ስለ እያንዳንዳችን ምን ያስተውላል?
9 ፍርሃት እንዲሰማህ የሚያደርግ ፈተና ሲያጋጥምህ ይሖዋ እየደረሰብህ ያለውን ፈተና ብቻ ሳይሆን ፈተናው ያሳደረብህን ስሜትም እንደሚያስተውል አስታውስ። ለምሳሌ ይሖዋ፣ እስራኤላውያን በግብፅ የደረሰባቸውን በደል ብቻ ሳይሆን የተሰማቸውን ሥቃይም ተመልክቷል። (ዘፀ. 3:7) ዳዊት በመዝሙሩ ላይ ይሖዋ ‘ጉስቁልናውን’ ብቻ ሳይሆን ‘በጭንቀት መዋጡንም’ እንዳየ ገልጿል። (መዝ. 31:7) በተጨማሪም የአምላክ ሕዝቦች መከራ ሲደርስባቸው ጥፋቱ የእነሱ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ አብሯቸው ‘ተጨንቋል።’ (ኢሳ. 63:9) አንተም ፍርሃት በሚሰማህ ጊዜ ይሖዋ ስሜትህን ይረዳልሃል፤ እንዲሁም ፍርሃትህን እንድታሸንፍ ሊረዳህ ይፈልጋል።
10. ይሖዋ በትኩረት እንደሚመለከትህ እንዲሁም የሚያጋጥምህን ማንኛውንም ፈተና ለመቋቋም እንደሚረዳህ እርግጠኛ የሆንከው ለምንድን ነው?
10 ይሁንና አስፈሪ ፈተና በምትጋፈጥበት ወቅት ይሖዋ እየደገፈህ ያለው እንዴት እንደሆነ ማስተዋል ሊከብድህ ይችላል። ስለዚህ እያደረገልህ ያለውን ድጋፍ ለማስተዋል እንዲረዳህ ጠይቀው። (2 ነገ. 6:15-17) ከዚያም የሚከተሉትን ጥያቄዎች አስብባቸው፦ በጉባኤ ስብሰባ ላይ የቀረበ ንግግር ወይም ሐሳብ አበረታቶሃል? አንድ ጽሑፍ፣ ቪዲዮ ወይም ኦሪጅናል መዝሙር ብርታት ሰጥቶሃል? የሚያጽናና ሐሳብ ወይም ጥቅስ ያካፈለህ ሰው አለ? አፍቃሪ ከሆነው የወንድማማች ማኅበራችን እንዲሁም ከሚቀርብልን መንፈሳዊ ምግብ የምናገኘውን እርዳታ አቅልለን እንመለከተው ይሆናል። ያም ቢሆን እነዚህ ዝግጅቶች ከይሖዋ ያገኘናቸው ውድ ስጦታዎች ናቸው። (ኢሳ. 65:13፤ ማር. 10:29, 30) ይሖዋ እንደሚያስብልህ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ናቸው። (ኢሳ. 49:14-16) ልትተማመንበት የሚገባ አምላክ እንደሆነ ዋስትና ይሰጡሃል።
11. አይዳ ፍርሃቷን እንድታሸንፍ የረዳት ምንድን ነው?
11 በሴኔጋል የምትኖር አይዳ የተባለች እህት በፈተና ወቅት ይሖዋ የረዳት እንዴት እንደሆነ ተመልክታለች። አይዳ የመጀመሪያ ልጅ ስለሆነች ወላጆቿ በቂ ገንዘብ አግኝታ ራሷንም ሆነ እነሱን እንድታስተዳድር ይጠብቁባት ነበር። ሆኖም በአቅኚነት ለማገልገል ስትል አኗኗሯን ካቀለለች በኋላ የኢኮኖሚ ችግር አጋጠማት። በዚህ ጊዜ ቤተሰቦቿ ከፍተኛ ትችት ይሰነዝሩባት ጀመር። እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼን መርዳት እንደማልችልና በዚህ የተነሳ ሁሉም ሰው እንደሚጠላኝ ተሰምቶኝ ነበር። እንዲያውም እንዲህ ያለ ችግር እንዲደርስብኝ በመፍቀዱ በይሖዋ ላይ ተማርሬ ነበር።” ከዚያም በስብሰባ ላይ አንድ ንግግር አዳመጠች። እንዲህ ብላለች፦ “ተናጋሪው ልባችንን ያቆሰለው ምንም ይሁን ምን ይሖዋ የሚሰማንን እንደሚያውቅ ገለጸ። የጉባኤ ሽማግሌዎችና ሌሎች የሰጡኝን ምክር በመቀበሌ ቀስ በቀስ ይሖዋ እንደሚወደኝ ድጋሚ መተማመን ቻልኩ። በይሖዋ ላይ ያለኝን እምነት አድሼ በድጋሚ ወደ እሱ መጸለይ ጀመርኩ። ከዚያም የጸሎቶቼን መልስ በማየቴ ውስጣዊ ሰላም አገኘሁ።” ውሎ አድሮ አይዳ አዲስ ሥራ አገኘች፤ ይህ ሥራ ራሷን እያስተዳደረች በአቅኚነት እንድታገለግል ብቻ ሳይሆን ለወላጆቿና ለሌሎችም እንድትተርፍ አስችሏታል። እንዲህ ብላለች፦ “ሙሉ በሙሉ በይሖዋ መታመን እንዳለብኝ ተምሬያለሁ። አሁን አሁን፣ ከጸለይኩ በኋላ ብዙውን ጊዜ ፍርሃቴ ይጠፋል።”
ይሖዋ ወደፊት ምን ያደርጋል?
12. በመዝሙር 56:9 መሠረት ዳዊት ስለ ምን ነገር እርግጠኛ ነበር?
12 መዝሙር 56:9ን አንብብ። ይህ ጥቅስ፣ ዳዊት ፍርሃቱን እንዲያሸንፍ የረዳውን ሌላ ነገር ይገልጻል፤ ሕይወቱ አሁንም አደጋ ውስጥ ቢሆንም ይሖዋ ወደፊት በሚያደርግለት ነገር ላይ አሰላስሏል። ዳዊት፣ ይሖዋ በትክክለኛው ጊዜ እንደሚታደገው እርግጠኛ ነበር። ደግሞም ይሖዋ፣ ዳዊት ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ እንደሚሆን አስቀድሞ ተናግሯል። (1 ሳሙ. 16:1, 13) ዳዊት፣ ይሖዋ የተናገረው ነገር ሁሉ እንደሚፈጸም እርግጠኛ ነበር።
13. ይሖዋ ምን እንደሚያደርግ መተማመን እንችላለን?
13 ይሖዋ ለአንተስ ምን እንደሚያደርግልህ ቃል ገብቷል? እርግጥ ምንም ዓይነት ችግር እንዳይደርስብን ይከላከልልናል ብለን አንጠብቅም። c ያም ቢሆን በዚህ ሥርዓት ውስጥ የሚያጋጥምህ ፈተና ምንም ይሁን ምን ይሖዋ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ያስወግደዋል። (ኢሳ. 25:7-9) ፈጣሪያችን የሞቱትን ለማስነሳት፣ እኛን ለመፈወስ እንዲሁም ተቃዋሚዎቻችንን በሙሉ ለማስወገድ የሚያስችል ኃይል አለው።—1 ዮሐ. 4:4
14. በምን ላይ ማሰላሰል እንችላለን?
14 ፍርሃት በሚሰማህ ጊዜ ይሖዋ ወደፊት በሚያደርገው ነገር ላይ አሰላስል። ሰይጣን ሲጠፋ፣ ክፉዎች ተወግደው በምድር ላይ ጻድቃን ብቻ ሲኖሩ እንዲሁም በየዕለቱ ቀስ በቀስ ወደ ፍጽምና እየተጠጋን ስንሄድ ምን እንደሚሰማህ ለማሰብ ሞክር። በ2014 የክልል ስብሰባ ላይ የቀረበ አንድ ሠርቶ ማሳያ በተስፋችን ላይ ማሰላሰል የምንችለው እንዴት እንደሆነ አሳይቶን ነበር። አንድ አባት 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 በገነት ውስጥ የሚኖረውን ሕይወት የሚገልጽ ቢሆን ኖሮ ምን ይል እንደነበር ከልጆቹ ጋር ይወያያል፦ “በአዲሱ ዓለም እጅግ አስደሳች የሆነ ዘመን እንደሚመጣ ይህን እወቅ። ምክንያቱም ሰዎች ሌሎችን የሚወዱ፣ መንፈሳዊ ሀብት የሚወዱ፣ ልካቸውን የሚያውቁ፣ ትሑቶች፣ አምላክን የሚያወድሱ፣ ለወላጆች የሚታዘዙ፣ የሚያመሰግኑ፣ ታማኝ የሆኑ፣ ለቤተሰባቸው ጥልቅ ፍቅር ያላቸው፣ ለመስማማት ፈቃደኞች የሆኑ፣ ሁልጊዜ ስለ ሌሎች መልካም ነገር የሚያወሩ፣ ራሳቸውን የሚገዙ፣ ገሮች፣ ጥሩ ነገር የሚወዱ፣ ታማኞች፣ እሺ ባዮች፣ ራሳቸውን ዝቅ የሚያደርጉ፣ ሥጋዊ ደስታን ከመውደድ ይልቅ አምላክን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ከልብ ለአምላክ ያደሩ ናቸው፤ ከእነዚህ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ይኑርህ።” በአዲሱ ዓለም ስለሚኖረው ሕይወት ከቤተሰቦችህ ወይም ከእምነት ባልንጀሮችህ ጋር የመወያየት ልማድ አለህ?
15. ታንያ ፍርሃት ቢሰማትም ፍርሃቷን ለማሸነፍ የረዳት ምንድን ነው?
15 በሰሜን መቄዶንያ የምትኖር ታንያ የተባለች እህት ወደፊት በምታገኛቸው በረከቶች ላይ በማሰላሰል ፍርሃቷን ማሸነፍ ችላለች። መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና ወላጆቿ አጥብቀው ይቃወሟት ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “የፈራኋቸው አንዳንድ ነገሮች መድረሳቸው አልቀረም። ከስብሰባ በተመለስኩ ቁጥር እናቴ ትደበድበኝ ነበር። ወላጆቼ የይሖዋ ምሥክር ከሆንኩ እንደሚገድሉኝ ይዝቱብኝ ነበር።” በመጨረሻም ታንያ ከቤት ተባረረች። ታዲያ ምን አደረገች? እንዲህ ብላለች፦ “ንጹሕ አቋሜን ለመጠበቅ መወሰኔ በሚያስገኝልኝ ዘላለማዊ በረከት ላይ አተኩር ነበር። በተጨማሪም በዚህ ሥርዓት ለማጣው ነገር ሁሉ ይሖዋ በአዲሱ ዓለም ውስጥ እንደሚክሰኝ እንዲሁም መጥፎ ነገሮች ሁሉ እንደሚረሱ አሰላስላለሁ።” ታንያ ንጹሕ አቋሟን መጠበቅ ችላለች። ደግሞም በይሖዋ እርዳታ የምትኖርበት ቤት አገኘች። በአሁኑ ወቅት ታንያ ከአንድ ታማኝ ወንድም ጋር ትዳር የመሠረተች ሲሆን ሁለቱም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በደስታ እየተካፈሉ ነው።
ከአሁኑ እምነትህን አጠናክር
16. በሉቃስ 21:26-28 ላይ የተጠቀሱት ክንውኖች ሲፈጸሙ ስንመለከት ደፋር እንድንሆን የሚረዳን ምንድን ነው?
16 በታላቁ መከራ ወቅት አብዛኞቹ ሰዎች ‘ከፍርሃት የተነሳ ይዝለፈለፋሉ።’ የአምላክ ሕዝቦች ግን ደፋርና ልበ ሙሉ ይሆናሉ። (ሉቃስ 21:26-28ን አንብብ።) ለምን? ምክንያቱም ቀድሞውንም በይሖዋ ላይ እምነት አዳብረዋል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ታንያ፣ ያሳለፈችው ተሞክሮ ያጋጠሟትን ሌሎች አስፈሪ ሁኔታዎች ለመቋቋም እንደረዳት ተናግራለች። እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ ወደ በረከት ሊቀይረው የማይችለው ምንም ዓይነት ሁኔታ እንደሌለ ተምሬያለሁ። አንዳንድ ጊዜ ሁኔታው በሌሎች ሰዎች ቁጥጥር ሥር እንዳለ ሊሰማን ይችላል፤ ሆኖም እነሱ መቆጣጠር የሚችሉት ይሖዋ የፈቀደላቸውን ያህል ብቻ ነው። ደግሞም የሚደርስብን ፈተና ከባድ ቢሆንም እንኳ ማለፉ አይቀርም።”
17. የ2024 የዓመት ጥቅስ የሚረዳን እንዴት ነው? (የሽፋኑን ሥዕል ተመልከት።)
17 በዛሬው ጊዜ ፍርሃት የተለመደ ነገር ሆኗል። ሆኖም እንደ ዳዊት ለፍርሃት እጅ ላለመስጠት መምረጥ እንችላለን። የ2024 የዓመት ጥቅስ ዳዊት ለይሖዋ ያቀረበው “ፍርሃት በሚሰማኝ ጊዜ በአንተ እታመናለሁ” የሚለው ጸሎት ነው። (መዝ. 56:3) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ማመሣከሪያ እንደሚገልጸው ዳዊት “ፍርሃቱን ከመመገብ ወይም በችግሮቹ ላይ ከማተኮር ይልቅ በሚታደገው አምላክ ላይ ትኩረት አድርጓል።” በመጪዎቹ ወራት በተለይም አስፈሪ ሁኔታ ሲያጋጥምህ የዓመት ጥቅሳችንን አስታውስ። ይሖዋ ከዚህ በፊት ባደረገው፣ አሁን እያደረገ ባለው እንዲሁም ወደፊት በሚያደርገው ነገር ላይ ጊዜ ወስደህ አሰላስል። እንዲህ ካደረግክ እንደ ዳዊት “በአምላክ እታመናለሁ፤ አልፈራም” ማለት ትችላለህ።—መዝ. 56:4
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
-
ይሖዋ ከዚህ በፊት ባደረገው ነገር ላይ ማሰላሰልህ ፍርሃትህን ለማሸነፍ የሚረዳህ እንዴት ነው?
-
ይሖዋ አሁን እያደረገ ባለው ነገር ላይ ማሰላሰልህ ፍርሃትህን ለማሸነፍ የሚረዳህ እንዴት ነው?
-
ይሖዋ ወደፊት በሚያደርገው ነገር ላይ ማሰላሰልህ ፍርሃትህን ለማሸነፍ የሚረዳህ እንዴት ነው?
መዝሙር 33 ሸክማችሁን በይሖዋ ላይ ጣሉ
a በjw.org የመፈለጊያ ሣጥን ላይ “በእምነታቸው ምሰሏቸው” ወይም “ተሞክሮዎች” ብለህ በመጻፍ እምነት የሚያጠናክሩ ሐሳቦችን ማግኘት ትችላለህ። በJW ላይብረሪ አፕሊኬሽን ላይ ደግሞ “በእምነታቸው ምሰሏቸው” እንዲሁም “የይሖዋ ምሥክሮች የሕይወት ታሪኮች” የሚሉትን ተከታታይ ርዕሶች ተመልከት።
b አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
d የሥዕሉ መግለጫ፦ ዳዊት አንድን ድብ እንዲገድል ይሖዋ ኃይል የሰጠው እንዴት እንደነበር፣ በአሂሜሌክ አማካኝነት ተግባራዊ እርዳታ እየሰጠው ያለው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ወደፊት ንጉሥ እንደሚያደርገው ሲያሰላስል።
e የሥዕሉ መግለጫ፦ በእምነቱ ምክንያት የታሰረ አንድ ወንድም ሲጋራ ማጨሱን እንዲያቆም ይሖዋ የረዳው እንዴት እንደነበር፣ ከወዳጆቹ በሚላኩለት ደብዳቤዎች አማካኝነት እያበረታታው ያለው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ወደፊት በገነት ውስጥ የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጠው ሲያሰላስል።