የመታሰቢያው በዓል ለአንድነታችን አስተዋጽኦ የሚያደርገው እንዴት ነው?
“ወንድሞች በአንድነት አብረው ቢኖሩ ምንኛ መልካም ነው! ምንኛስ ደስ ያሰኛል!”—መዝ. 133:1
1, 2. በ2018 በአምላክ ሕዝቦች መካከል አስደናቂ አንድነት እንዲኖር የሚያደርገው የትኛው ክንውን ነው? እንዲህ የምንለውስ ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)
መጋቢት 31, 2018 ፀሐይዋ ማሽቆልቆል ስትጀምር የአምላክ ሕዝቦችና ፍላጎት ያላቸው በርካታ ሰዎች በየዓመቱ የሚከበረውን የጌታ ራት በዓል ለማክበር ይሰበሰባሉ። በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙት እነዚህ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፀሐይዋ ስትጠልቅ የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ ያከብራሉ። በየዓመቱ ይህ በዓል ሲከበር በፕላኔታችን ላይ ከሚፈጸም ከየትኛውም ክንውን በላቀ መንገድ በአምላክ ሕዝቦች መካከል አስደናቂ አንድነት እንዲኖር ያደርጋል!
2 በዚያ ቀን በመላው ዓለም ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የምድር ነዋሪዎች ይህን ልዩ በዓል ሲያከብሩ ይሖዋ እና ኢየሱስ ምንኛ እንደሚደሰቱ አስቡት። “ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች የተውጣጡ አንድም ሰው ሊቆጥራቸው የማይችል እጅግ ብዙ ሕዝብ . . . ‘መዳን ያገኘነው በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ከአምላካችን እንዲሁም ከበጉ ነው’” በማለት በታላቅ ድምፅ እንደሚጮኹ መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ ተናግሯል። (ራእይ 7:9, 10) የአምላክ ሕዝቦች በየዓመቱ የመታሰቢያውን በዓል በማክበር ለይሖዋና ለኢየሱስ እንዲህ ያለ ውዳሴ የሚያቀርቡ መሆኑ እንዴት የሚያስደስት ነው!
3. በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
3 ይህ ርዕስ ከዚህ በዓል ጋር በተያያዘ ለሚነሱት ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል፦ (1) በግለሰብ ደረጃ ለመታሰቢያው በዓል ዝግጅት ማድረግ እንዲሁም ከበዓሉ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? (2) የመታሰቢያው በዓል ለአምላክ ሕዝቦች አንድነት አስተዋጽኦ የሚያደርገው እንዴት ነው? (3) እያንዳንዳችን ለዚህ አንድነት አስተዋጽኦ ማድረግ የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው? (4) የመታሰቢያው በዓል ለመጨረሻ ጊዜ የሚከበርበት ቀን ይኖር ይሆን? ከሆነስ ይህ የሚሆነው መቼ ነው?
ለመታሰቢያው በዓል መዘጋጀትና ከበዓሉ ጥቅም ማግኘት
4. አቅማችንና ያለንበት ሁኔታ እስከፈቀደ ድረስ በመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
4 በመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት፣ በስብሰባዎች ላይ መገኘት ለይሖዋ የምናቀርበው አምልኮ ክፍል ስለሆነ ነው። ይሖዋ እና ኢየሱስ በዓመት ውስጥ ካሉን ስብሰባዎች ሁሉ ትልቅ ቦታ በሚሰጠው በዚህ ስብሰባ ላይ ለመገኘት እያንዳንዳችን የምናደርገውን ጥረት እንደሚመለከቱ ጥርጥር የለውም። አቅማችንና ያለንበት ሁኔታ ካላገደን በቀር በመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘታችን እንደሚያስደስታቸው የታወቀ ነው። ለስብሰባዎቻችን ትልቅ ቦታ እንደምንሰጥ በተግባር ማሳየታችን፣ ስማችን ይሖዋ ካዘጋጀው “የመታሰቢያ መጽሐፍ” ይኸውም ‘ከሕይወት መጽሐፍ’ ላይ እንዳይፋቅ ከሚያደርጉት በርካታ ምክንያቶች አንዱ ነው፤ ይህ መጽሐፍ ይሖዋ የዘላለም ሕይወት ሊሰጣቸው ያሰባቸውን ሰዎች ስም የያዘ ነው።—ሚል. 3:16፤ ራእይ 20:15
5. ‘በእምነት ውስጥ መሆናችንን ለማረጋገጥ’ ከመታሰቢያው በዓል በፊት ባሉት ሳምንታት ‘ራሳችንን መፈተሽ’ የምንችለው እንዴት ነው?
5 ከመታሰቢያው በዓል በፊት ባሉት ሳምንታት፣ ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ በቁም ነገር ማሰባችንና ስለ ጉዳዩ መጸለያችን ጠቃሚ ነው። (2 ቆሮንቶስ 13:5ን አንብብ።) ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን “በእምነት ውስጥ መሆናችሁን ለማረጋገጥ ዘወትር ራሳችሁን ፈትሹ” ብሏቸዋል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ራሳችንን እንደሚከተለው ብለን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ይሖዋ ፈቃዱን ለመፈጸም የሚጠቀመው በዚህ ድርጅት ብቻ እንደሆነ ከልቤ አምናለሁ? የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበክና ለማስተማር የምችለውን ሁሉ እያደረግኩ ነው? የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ እንደሆነና የሰይጣን አገዛዝ ፍጻሜው እንደቀረበ በእርግጥ አምናለሁ? አኗኗሬስ ይህን ያሳያል? በይሖዋና በኢየሱስ ላይ ምን ያህል ትምክህት አለኝ? ራሴን በወሰንኩበት ወቅት እንደነበረው ሁሉ አሁንም በእነሱ እተማመናለሁ?’ (ማቴ. 24:14፤ 2 ጢሞ. 3:1፤ ዕብ. 3:14) ለእነዚህ ጥያቄዎች በምንሰጠው መልስ ላይ ማሰላሰላችን፣ ማንነታችንን ለማወቅ ዘወትር ራሳችንን ለመመርመር ያስችለናል።
6. (ሀ) የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረጋችን የግድ አስፈላጊ ነው? (ለ) አንድ ሽማግሌ በየዓመቱ ለመታሰቢያው በዓል ዝግጅት የሚያደርገው እንዴት ነው? አንተስ ምን ማድረግ ትችላለህ?
6 ለመታሰቢያው በዓል መዘጋጀት የምንችልበት አንዱ መንገድ፣ የበዓሉን አስፈላጊነት የሚያጎሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርቶችን ማንበብና ባነበብነው ላይ ማሰላሰል ነው። (ዮሐንስ 3:16ን እና 17:3ን አንብብ።) የዘላለም ሕይወት ማግኘት ከፈለግን ስለ ይሖዋ ‘ማወቃችን’ እንዲሁም በአንድያ ልጁ በኢየሱስ ‘ማመናችን’ የግድ አስፈላጊ ነው። ወደ ይሖዋና ወደ ኢየሱስ ለመቅረብ የሚረዱ ርዕሶችን መርጠን ማጥናታችን ለመታሰቢያው በዓል ለመዘጋጀት ይረዳናል። ለረጅም ዓመታት በሽምግልና ያገለገለ አንድ ወንድም የሚጠቀምበትን ዘዴ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይህ ወንድም ስለ መታሰቢያው በዓል እንዲሁም ይሖዋና ኢየሱስ ስላሳዩን ፍቅር የሚያወሱ የመጠበቂያ ግንብ ርዕሶችን ለዓመታት ሲሰበስብ ቆይቷል። ከበዓሉ በፊት ባሉት ሳምንታት እነዚህን ርዕሶች አውጥቶ እንደገና ያነባቸዋል፤ እንዲሁም የመታሰቢያው በዓል ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በጥሞና ያስባል። ስለ መታሰቢያው የሚያወሱ ሌሎች ርዕሶችን ሲያገኝ ደግሞ የሰበሰባቸው ጽሑፎች ውስጥ ያካትታቸዋል። ይህ ሽማግሌ እነዚህን ርዕሶች መለስ እያለ ማጥናቱ እንዲሁም የመታሰቢያውን በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ማንበቡና በዚያ ላይ ማሰላሰሉ በየዓመቱ አዲስ ነገር ለማወቅ አስችሎታል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ለይሖዋና ለኢየሱስ ያለው ፍቅር ከዓመት ዓመት እየጨመረ እንዲሄድ ረድቶታል። አንተም እንዲህ ያለ ጥናት ማድረግህ ለይሖዋና ለኢየሱስ ያለህን ፍቅርና አድናቆት ለማሳደግ ይረዳሃል፤ ይህም ከመታሰቢያው በዓል ይበልጥ ጥቅም ለማግኘት ያስችልሃል።
የመታሰቢያው በዓል ለአንድነታችን የሚያደርገው አስተዋጽኦ
7. (ሀ) የመጀመሪያው የጌታ ራት በተከበረበት ምሽት ላይ ኢየሱስ ምን በማለት ጸልዮ ነበር? (ለ) ይሖዋ ለኢየሱስ ልመና መልስ እንደሰጠ የሚያሳየው ምንድን ነው?
7 የመጀመሪያው የጌታ ራት በተከበረበት ምሽት ላይ ኢየሱስ ለየት ያለ ጸሎት አቅርቦ ነበር፤ እሱና አባቱ ያላቸው ዓይነት አንድነት በተከታዮቹም መካከል እንዲኖር አባቱን ለምኗል። (ዮሐንስ 17:20, 21ን አንብብ።) ይሖዋም ውድ ልጁ ላቀረበው ለዚህ ልመና መልስ ሰጥቷል። የአምላክ ሕዝቦች የሚያደርጓቸው በርካታ ስብሰባዎች ቢኖሩም በመካከላቸው ያለው አንድነት ይበልጥ ጎልቶ የሚታየው በመታሰቢያው በዓል ላይ ነው። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የተለያየ ዜግነትና የቆዳ ቀለም ያላቸው ሰዎች በዓሉን ለማክበር ይሰበሰባሉ። በአንዳንድ አካባቢዎች የተለያየ ዘር ያላቸው ሰዎች ለአምልኮ አንድ ላይ መሰብሰባቸው ያልተለመደ ነው፤ እንዲያውም አንዳንዶች ይህ ተገቢ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። ይሖዋና ኢየሱስ ግን እንዲህ ያለውን አንድነት ሲያዩ በጣም ይደሰታሉ!
8. ይሖዋ አንድነትን በተመለከተ ሕዝቅኤልን ምን ብሎት ነበር?
8 የይሖዋ ሕዝቦች በመካከላቸው እንዲህ ዓይነት አንድነት መኖሩ ያን ያህል አያስገርማቸውም። ይሖዋ ይህ እንደሚሆን አስቀድሞ ትንቢት አስነግሯል። “ለይሁዳ” እና “ለዮሴፍ” ተብሎ የተጻፈባቸው ሁለት በትሮች አንድ እንደሚሆኑ ለነቢዩ ሕዝቅኤል ተነግሮት ነበር። (ሕዝቅኤል 37:15-17ን አንብብ።) በሐምሌ 2016 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣው “የአንባቢያን ጥያቄዎች” እንዲህ የሚል ማብራሪያ ይዟል፦ “ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከተመለሱ በኋላ አንድ እንደሚሆኑ የሚገልጽ ተስፋ ያዘለ መልእክት በነቢዩ ሕዝቅኤል በኩል ተናግሮ ነበር። ይህ ትንቢት፣ በፍጻሜው ዘመን የሚኖሩ የአምላክ ሕዝቦችም አንድ እንደሚሆኑ ይጠቁማል።”
9. በየዓመቱ የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ሲከበር ሕዝቅኤል በትንቢት የገለጸው አንድነት የሚታየው እንዴት ነው?
9 ይሖዋ እንደገና እንዲደራጁና አንድነት እንዲኖራቸው መጀመሪያ የረዳው “ለይሁዳ” በተባለው በትር የተመሰሉትን ቅቡዓን ክርስቲያኖች ነው፤ ይህንንም ያደረገው ከ1919 አንስቶ ነው። “ለዮሴፍ” በተባለው በትር የተመሰሉትና በምድር ላይ የመኖር ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች ከቅቡዓኑ ጋር መተባበር ሲጀምሩ ደግሞ እነዚህ ሁለት ቡድኖች “አንድ መንጋ” ሆኑ። (ዮሐ. 10:16፤ ዘካ. 8:23) ይሖዋ እነዚህን ሁለት በትሮች እንደሚያያይዛቸውና በእጁ ላይ አንድ በትር እንደሚሆኑ ቃል ገብቶ ነበር። (ሕዝ. 37:19) በአሁኑ ወቅት ሁለቱም ቡድኖች በአንድ ንጉሥ ሥር ሆነው ይሖዋን አብረው ያገለግላሉ፤ ንጉሣቸውም በትንቢቱ ላይ “አገልጋዬ ዳዊት” የተባለውና ክብር የተላበሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ሕዝ. 37:24, 25) ቅቡዓን ቀሪዎችና “ሌሎች በጎች” በየዓመቱ የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር አንድ ላይ ሲሰበሰቡ ሕዝቅኤል የገለጸው አስደናቂ አንድነት ጉልህ ሆኖ ይታያል! ይሁን እንጂ ይህን አንድነት ጠብቀን ለማቆየትና ይበልጥ ለማጠናከር እያንዳንዳችን ምን ማድረግ እንችላለን?
ለአንድነታችን አስተዋጽኦ ማድረግ የምንችልባቸው መንገዶች
10. በአምላክ ሕዝቦች መካከል ያለው አንድነት እንዲጠናከር አስተዋጽኦ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
10 በአምላክ ሕዝቦች መካከል ያለው አንድነት እንዲጠናከር አስተዋጽኦ ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ ትሕትናን ማዳበር ነው። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ደቀ መዛሙርቱን፣ ራሳቸውን ዝቅ እንዲያደርጉ መክሯቸው ነበር። (ማቴ. 23:12) ከልባችን ትሑት ከሆንን ዓለም የሚያንጸባርቀውን ራስን ከፍ አድርጎ የመመልከት ዝንባሌ እናስወግዳለን። ትሑት መሆናችን በጉባኤ ውስጥ አመራር ለሚሰጡት እንድንገዛ ያነሳሳናል፤ እንዲህ ያለው የታዛዥነት መንፈስ ጉባኤው አንድነት እንዲኖረው ያደርጋል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ትሑት መሆናችን አምላክን ያስደስተዋል፤ ምክንያቱም “አምላክ ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።”—1 ጴጥ. 5:5
11. በመታሰቢያው በዓል ላይ በሚቀርቡት ቂጣና የወይን ጠጅ ትርጉም ላይ ማሰላሰላችን አንድነታችንን ለማጠናከር አስተዋጽኦ የሚያደርገው እንዴት ነው?
11 አንድነታችንን ለማጠናከር አስተዋጽኦ እንድናደርግ የሚያግዘን ሁለተኛው ነገር፣ በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚቀርቡት ቂጣና የወይን ጠጅ ባላቸው ትርጉም ላይ ማሰላሰላችን ነው። ያልቦካው ቂጣና ቀዩ ወይን ስላላቸው ትርጉም ከመታሰቢያው በዓል በፊት ባሉት ጊዜያት በተለይም በዚያ ልዩ ምሽት ላይ በቁም ነገር ልናስብ ይገባል። (1 ቆሮ. 11:23-25) ቂጣው፣ ኢየሱስ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበውን ኃጢአት የሌለበትን ሥጋውን፣ ወይኑ ደግሞ የፈሰሰውን ደሙን ያመለክታል። ይሁንና ቂጣውና የወይን ጠጁ ምን ትርጉም እንዳላቸው ማወቃችን ብቻ በቂ አይደለም። የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት፣ ይሖዋና ኢየሱስ ታላቅ ፍቅር ያሳዩበት ዝግጅት እንደሆነ እናስታውስ፤ ይሖዋ ለእኛ ሲል ልጁን በመስጠት፣ ኢየሱስ ደግሞ እኛን ለማዳን ሕይወቱን በፈቃደኝነት መሥዋዕት በማድረግ ፍቅራቸውን አሳይተውናል። ይሖዋና ኢየሱስ ባሳዩን ፍቅር ላይ ማሰላሰላችን እኛም በምላሹ እንድንወዳቸው ያነሳሳናል። እኛም ሆንን የእምነት ባልንጀሮቻችን ለይሖዋ ያለን ፍቅር ደግሞ እርስ በርስ የሚያስተሳስረን ከመሆኑም ሌላ አንድነታችንን ያጠናክረዋል።
12. ኢየሱስ ከባሪያዎቹ ጋር ሒሳብ ስለተሳሰበ ንጉሥ የተናገረው ምሳሌ ይሖዋ ይቅር ባይ እንድንሆን እንደሚፈልግ የሚያሳየው እንዴት ነው?
12 አንድነታችን እንዲጠናከር አስተዋጽኦ የምናደርግበት ሦስተኛው መንገድ ሌሎችን በነፃ ይቅር ማለት ነው። የበደሉንን ሰዎች ይቅር ስንል የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላስገኘልን የኃጢአት ይቅርታ አድናቆት እንዳለን እናሳያለን። በማቴዎስ 18:23-34 ላይ የሚገኘውን ኢየሱስ የተናገረውን ምሳሌ ካነበብን በኋላ ራሳችንን እንደሚከተለው ብለን እንጠይቅ፦ ‘ኢየሱስ ያስተማረውን ነገር ተግባራዊ አደርጋለሁ? የእምነት ባልንጀሮቼን እታገሣቸዋለሁ? ስሜታቸውንስ እረዳላቸዋለሁ? የበደሉኝን ሰዎች ይቅር ለማለት ዝግጁ ነኝ?’ እርግጥ ነው፣ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ቅር የሚያሰኙንን ነገሮች በሙሉ በእኩል ደረጃ እንመለከታቸዋለን ማለት አይደለም፤ ፍጹማን ባለመሆናችን አንዳንዶቹን በደሎች ይቅር ማለት በጣም ይከብደን ይሆናል። ያም ሆነ ይህ ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ፣ ይሖዋ ምን እንደሚጠብቅብን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። (ማቴዎስ 18:35ን አንብብ።) ወንድሞቻችን ላደረሱብን በደል ከልባቸው እንደተጸጸቱ እያወቅን ይቅር የማንላቸው ከሆነ ይሖዋም ኃጢአታችንን ይቅር እንደማይለን ኢየሱስ በግልጽ ተናግሯል። ይህ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። ኢየሱስ እንዳስተማረን ሌሎችን ይቅር የምንል ከሆነ አንድነታችንን ጠብቀን ማቆየትና ይበልጥ ማጠናከር እንችላለን።
13. ሰላም ፈጣሪዎች መሆናችን አንድነታችንን ለማጠናከር ምን አስተዋጽኦ ያበረክታል?
13 ሌሎችን ይቅር ስንል፣ ሰላም ፈጣሪዎች መሆናችንን እናሳያለን። ሐዋርያው ጳውሎስ “አንድ ላይ በሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ልባዊ ጥረት አድርጉ” በማለት የሰጠውን ምክር እናስታውስ። (ኤፌ. 4:3) ከሌሎች ጋር ስላለህ ግንኙነት በመታሰቢያው በዓል ሰሞን በተለይ ደግሞ በዓሉ በሚከበርበት ምሽት ላይ ቆም ብለህ አስብ። ‘ቂም የማልይዝ ሰው እንደሆንኩ በግልጽ ይታያል? ሰላምና አንድነት እንዲኖር ለማድረግ ስል ከሚጠበቅብኝ አልፌ ለመሄድ ፈቃደኛ እሆናለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። እነዚህ በመታሰቢያው በዓል ወቅት በጥሞና ልናስብባቸው የሚገቡ ጥያቄዎች ናቸው።
14. “እርስ በርሳችሁ በፍቅር በመቻቻል ኑሩ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
14 አንድነታችን እንዲጠናከር አስተዋጽኦ የምናደርግበት አራተኛው መንገድ ደግሞ የፍቅር አምላክ የሆነውን ይሖዋን በመምሰል ፍቅር ማሳየት ነው። (1 ዮሐ. 4:8) ከአንዳንድ የእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር በተያያዘ “ወንድሞቼ ስለሆኑ ችያቸው ብኖርም እነሱን መውደድ ግን ይከብደኛል” የሚል አመለካከት ሊኖረን አይገባም። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ጳውሎስ “እርስ በርሳችሁ በፍቅር በመቻቻል ኑሩ” በማለት ከሰጠው ምክር ጋር ይጋጫል። (ኤፌ. 4:2) ጳውሎስ እንዲሁ ‘ተቻችለን እንድንኖር’ ብቻ ሳይሆን ይህንን “በፍቅር” እንድናደርገው እንደመከረን ልብ ማለት ያስፈልጋል። በሁለቱ ሐሳቦች መካከል ልዩነት አለ። በየጉባኤያችን ውስጥ ይሖዋ ወደ ራሱ የሳባቸው የተለያዩ ዓይነት ሰዎች ይገኛሉ። (ዮሐ. 6:44) ይሖዋ እነዚህን ሰዎች ወደ ራሱ ከሳባቸው ወዷቸዋል ማለት ነው። ታዲያ ይሖዋ የሚወደውን የእምነት ባልንጀራችንን እኛስ ልንወደው አይገባም? ይሖዋ ወንድሞቻችንን እንድንወድ የሰጠንን ትእዛዝ ተግባራዊ ከማድረግ ፈጽሞ ወደኋላ ማለት አይኖርብንም!—1 ዮሐ. 4:20, 21
የመጨረሻው የመታሰቢያ በዓል—መቼ?
15. የመታሰቢያው በዓል ለመጨረሻ ጊዜ የሚከበርበት ቀን እንደሚኖር እንዴት እናውቃለን?
15 የመታሰቢያው በዓል ለመጨረሻ ጊዜ የሚከበርበት ቀን ይኖር ይሆን? አዎ። ይህን እንዴት እናውቃለን? ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለሚገኙ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ በየዓመቱ በማክበር “ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ሞቱን [እንደሚያውጁ]” ገልጾ ነበር። (1 ቆሮ. 11:26) እዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው “እስከሚመጣ” የሚለው ቃል እና ኢየሱስ ስለ መጨረሻው ቀን በተናገረው ትንቢት ላይ የተጠቀመበት “ሲመጣ” የሚለው ቃል የሚያመለክቱት በተመሳሳይ ወቅት ላይ የሚፈጸምን ክንውን ነው። ኢየሱስ በቅርቡ የሚመጣውን ታላቅ መከራ በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፤ የምድር ወገኖችም ሁሉ በሐዘን ደረታቸውን ይደቃሉ፤ የሰው ልጅም በኃይልና በታላቅ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል። [ኢየሱስም] መላእክቱን በታላቅ የመለከት ድምፅ ይልካል፤ እነሱም ከአራቱ ነፋሳት፣ ከአንዱ የሰማይ ዳርቻ እስከ ሌላው የሰማይ ዳርቻ ለእሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ።” (ማቴ. 24:29-31) ኢየሱስ “ለእሱ የተመረጡትን” የሚሰበስበው በምድር ላይ የቀሩ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን በሙሉ ወደ ሰማይ ሲወስዳቸው ነው። ይህ የሚሆነው ደግሞ የታላቁ መከራ የመጀመሪያ ምዕራፍ ካለፈ በኋላ ሆኖም የአርማጌዶን ጦርነት ከመፈንዳቱ በፊት ነው። ከዚያም 144,000ዎቹ በሙሉ ከኢየሱስ ጋር ሆነው የምድርን ነገሥታት ድል ያደርጋሉ። (ራእይ 17:12-14) ኢየሱስ ምድር ላይ የቀሩትን ቅቡዓን ለመሰብሰብ ‘ከመምጣቱ’ በፊት የሚከበረው የመታሰቢያ በዓል የመጨረሻው ይሆናል።
16. በዚህ ዓመት በሚከበረው የመታሰቢያ በዓል ላይ ለመገኘት ቁርጥ ውሳኔ ያደረግከው ለምንድን ነው?
16 መጋቢት 31, 2018 በሚከበረው የመታሰቢያ በዓል ላይ ለመገኘት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። በአምላክ ሕዝቦች መካከል ላለው አንድነት አስተዋጽኦ ማድረጋችንን ለመቀጠል እንዲረዳን ይሖዋን እንጠይቀው። (መዝሙር 133:1ን አንብብ።) የመታሰቢያውን በዓል ለመጨረሻ ጊዜ የምናከብርበት ቀን እንደሚኖር እናስታውስ። እስከዚያው ድረስ ግን በመታሰቢያው በዓል ላይ ለመገኘት አቅማችን የሚፈቅደውን ሁሉ እናድርግ፤ እንዲሁም በዚህ በዓል ላይ የሚኖረንን አስደናቂ አንድነት ከፍ አድርገን እንመልከተው።