በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

በሙሴ ሕግ ውስጥ ያሉት መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥንቷ እስራኤል በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ለሚያጋጥሙ ክርክሮች እልባት ለመስጠት ይሠራባቸው ነበር?

አዎ፣ አንዳንድ ጊዜ ይሠራባቸው ነበር። አንድ ምሳሌ እንመልከት። ዘዳግም 24:14, 15 እንዲህ ይላል፦ “ከወንድሞችህም ሆነ በምድርህ . . . ውስጥ ከሚኖሩ የባዕድ አገር ሰዎች መካከል የተቸገረውንና ድሃ የሆነውን ቅጥር ሠራተኛ አታታል። . . . አለዚያ በአንተ የተነሳ ወደ ይሖዋ ይጮኻል፤ አንተም በኃጢአት ትጠየቃለህ።”

የእርሻ ሠራተኛው አቤቱታ የተጻፈበት የሸክላ ስብርባሪ

አንድ ሰው እንዲህ ያለ ሁኔታ ባጋጠመው ጊዜ ያቀረበውን አቤቱታ የያዘ በሰባተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የተዘጋጀ ሰነድ ተገኝቷል። ሰነዱ የተገኘው በአሽዶድ አቅራቢያ ነው። ጽሑፉ የሰፈረው በሸክላ ስብርባሪ ላይ ሲሆን ሐሳቡ፣ የሚጠበቅበትን የእህል መጠን አላስረከበም የተባለን አንድ የእርሻ ሠራተኛ የሚመለከት ነው፤ ሰነዱ እንዲህ ይላል፦ “አገልጋይህ [አቤቱታ አቅራቢው] ከጥቂት ቀናት በፊት ምርቱን አስገብቶ ከጨረሰ በኋላ የሾባይ ልጅ የሆነው ሆሻያሁ መጣና የአገልጋይህን ልብስ ወሰደበት። . . . በጠራራ ፀሐይ ከእኔ ጋር አዝመራውን ሲያጭዱ የነበሩት ጓደኞቼ በሙሉ . . . የተናገርኩት እውነት እንደሆነ ይመሠክራሉ። ምንም ጥፋት የለብኝም። . . . ገዢው የአገልጋዩን ልብስ የማስመለስ ግዴታ እንዳለበት ባይሰማው እንኳ [ለእኔ] ለአገልጋዩ በመራራት ይህን ያድርግልኝ! አገልጋይህ ልብሱ ተወስዶበት እያለ ዝም ማለት የለብህም።”

ሳይመን ሻማ የተባሉት የታሪክ ምሁር እንዲህ ብለዋል፦ “[ይህ አቤቱታ]፣ አንድ ቅጥር ሠራተኛ . . . [ልብሱን] ለማስመለስ ምን ያህል እንደተጨነቀ የሚያሳይ ብቻ አይደለም። አቤቱታ አቅራቢው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኘው ሕግ፣ በተለይም በዘሌዋውያንና በዘዳግም ላይ ስለሰፈሩትና ድሆችን መበደልን ስለሚያወግዙት ትእዛዛት የሚያውቀው ነገር እንደነበረም [ሰነዱ] ይጠቁማል።”