የጥናት ርዕስ 22
ሕይወታችንን ለመምራት የሚረዳን ጥበብ
“ይሖዋ ራሱ ጥበብ ይሰጣል።”—ምሳሌ 2:6
መዝሙር 89 ስማ፣ ታዘዝ፤ ትባረካለህ
ማስተዋወቂያ a
1. ሁላችንም አምላካዊ ጥበብ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? (ምሳሌ 4:7)
ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ውሳኔ አድርገህ ታውቃለህ? ውሳኔ ከማድረግህ በፊት ጥበብ ለማግኘት ጸልየህ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፤ ደግሞም ይህን ማድረግህ ተገቢ ነው። (ያዕ. 1:5) ንጉሥ ሰለሞን “ጥበብ በጣም አስፈላጊ ነገር ናት” ሲል ጽፏል። (ምሳሌ 4:7ን አንብብ።) እርግጥ ነው፣ ሰለሞን እየተናገረ የነበረው እንዲሁ ስለማንኛውም ዓይነት ጥበብ አይደለም። ከይሖዋ ስለሚገኘው ጥበብ እየተናገረ ነበር። (ምሳሌ 2:6) ሆኖም አምላካዊ ጥበብ ዛሬ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመወጣት ይረዳናል? አዎ ይረዳናል፤ በዚህ ርዕስ ውስጥ ስለዚህ ጉዳይ እንመለከታለን።
2. ጥበበኛ ለመሆን የሚረዳን አንዱ ነገር ምንድን ነው?
2 ጥበበኛ እንድንሆን የሚረዳን አንዱ ነገር በጥበባቸው የተነገረላቸው ሁለት ሰዎች የሰጡትን ምክር ማጥናታችንና ተግባራዊ ማድረጋችን ነው። መጀመሪያ የምናየው ሰለሞንን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ “ለሰለሞን እጅግ ታላቅ ጥበብና ማስተዋል” እንደሰጠው ይናገራል። (1 ነገ. 4:29) ሁለተኛ የምናየው ደግሞ በጥበቡ ተወዳዳሪ የሌለውን ኢየሱስን ነው። (ማቴ. 12:42) ስለ ኢየሱስ እንዲህ የሚል ትንቢት ተነግሯል፦ “[በእሱ] ላይ የይሖዋ መንፈስ፣ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ . . . ያርፍበታል።”—ኢሳ. 11:2
3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
3 ከአምላክ ጥበብ ያገኙት ሰለሞንና ኢየሱስ ዛሬ ሁላችንንም ስለሚመለከቱ ጉዳዮች ጠቃሚ ምክር ሰጥተዋል። በዚህ ርዕስ ላይ ሦስቱን እንመለከታለን፦ ለገንዘብ፣ ለሥራና ለራሳችን ተገቢውን አመለካከት መያዝ።
ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ
4. ሰለሞንና ኢየሱስ የነበሩበት የኢኮኖሚ ሁኔታ የሚለያየው እንዴት ነው?
4 ሰለሞን የናጠጠ ሀብታም ነበር፤ የሚኖረውም በቅንጦት ነበር። (1 ነገ. 10:7, 14, 15) በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ ብዙም ቁሳዊ ነገር አልነበረውም፤ የራሴ የሚለው ቤት እንኳ አልነበረውም። (ማቴ. 8:20) ሆኖም ሁለቱም ሰዎች ለቁሳዊ ነገር ሚዛናዊ አመለካከት ነበራቸው፤ ምክንያቱም የሁለቱም ጥበብ ምንጭ ይሖዋ ነው።
5. ሰለሞን ለገንዘብ ምን ሚዛናዊ አመለካከት ነበረው?
5 ሰለሞን ገንዘብ “ጥበቃ እንደሚያስገኝ” ተናግሯል። (መክ. 7:12) ገንዘብ ለሕይወት የሚያስፈልጉንን መሠረታዊ ነገሮችና ምናልባትም አንዳንድ ያማሩንን ነገሮች ለመግዛት ያስችለን ይሆናል። ሆኖም ያ ሁሉ ሀብት የነበረው ሰለሞንም እንኳ ከገንዘብ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች እንዳሉ ተገንዝቦ ነበር። ለምሳሌ “መልካም ስም ከብዙ ሀብት ይመረጣል” ሲል ጽፏል። (ምሳሌ 22:1) በተጨማሪም ሰለሞን ገንዘብ የሚወዱ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ባላቸው እንደማይረኩ አስተውሏል። (መክ. 5:10, 12) ከዚህም ሌላ እምነታችንን በገንዘብ ላይ እንዳንጥል አስጠንቅቋል፤ ምክንያቱም ያለን ገንዘብ በቀላሉ ሊጠፋ ይችላል።—ምሳሌ 23:4, 5
6. ኢየሱስ ለቁሳዊ ነገሮች ምን ሚዛናዊ አመለካከት ነበረው? (ማቴዎስ 6:31-33)
6 ኢየሱስ ለቁሳዊ ነገሮች ሚዛናዊ አመለካከት ነበረው፤ ምግብና መጠጥ የሚያስገኙትን ደስታም ያውቃል። (ሉቃስ 19:2, 6, 7) በአንድ ወቅት ምርጥ የወይን ጠጅ ሠርቷል፤ ይህ የመጀመሪያው ተአምር ነበር። (ዮሐ. 2:10, 11) በሞተበት ቀንም የለበሰው ውድ ልብስ ነበር። (ዮሐ. 19:23, 24) ሆኖም ኢየሱስ ቁሳዊ ነገሮች በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዲይዙ አልፈቀደም። ተከታዮቹን “ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል ማንም የለም፤ . . . ለአምላክም ለሀብትም በአንድነት መገዛት አትችሉም” ብሏቸዋል። (ማቴ. 6:24) ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት እስካስቀደምን ድረስ ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር እንደሚያሟላልን አስተምሯል።—ማቴዎስ 6:31-33ን አንብብ።
7. አንድ ወንድም ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት መያዙ የጠቀመው እንዴት ነው?
7 በርካታ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከገንዘብ ጋር በተያያዘ መለኮታዊውን ጥበብ ተግባራዊ በማድረጋቸው ተጠቅመዋል። ዳንኤል የተባለን አንድ ያላገባ ወንድም እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እንዲህ ብሏል፦ “በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳለሁ በሕይወቴ ውስጥ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ለመስጠት ወሰንኩ።” ዳንኤል አኗኗሩን ቀላል ማድረጉ ጊዜውንና ችሎታውን በብዙ ቲኦክራሲያዊ ፕሮጀክቶች ላይ ለማዋል አስችሎታል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “በመረጥሁት ጎዳና ፈጽሞ አልቆጭም ብዬ በሐቀኝነት መናገር እችላለሁ። በሕይወቴ ውስጥ ለገንዘብ ቅድሚያ ብሰጥ ኖሮ ብዙ ገንዘብ ማግኘት እችል እንደነበረ ጥያቄ የለውም። ይሁንና ገንዘብ ዛሬ ያሉኝን ጓደኞች ሊገዛልኝ ይችል ነበር? ለአምላክ መንግሥት ቅድሚያ እንደሰጠሁ ማወቄ የሚያስገኝልኝን እርካታም ገንዘብ ሊገዛው አይችልም። ምንም ያህል ገንዘብ ባገኝ ይሖዋ ከሰጠኝ በረከት ጋር ሊወዳደር አይችልም።” በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ከገንዘብ ይልቅ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ስንሰጥ እንጠቀማለን።
ለሥራ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ
8. ሰለሞን ለሥራ ሚዛናዊ አመለካከት እንደነበረው እንዴት እናውቃለን? (መክብብ 5:18, 19)
8 ሰለሞን ተግቶ መሥራት የሚያስገኘውን ደስታ “የአምላክ ስጦታ” ሲል ገልጾታል። (መክብብ 5:18, 19ን አንብብ።) “በትጋት ያከናወኑት ነገር ሁሉ ጥቅም ያስገኛል” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 14:23) ሰለሞን ይህን ከራሱ ሕይወት ተነስቶ መናገር ይችላል። ትጉ ሠራተኛ ነበር! ቤቶችን ሠርቷል፤ ወይን ተክሏል፤ የአትክልት ስፍራዎችንና የውኃ ማጠራቀሚያዎችንም ሠርቷል። ከዚህም በተጨማሪ ከተሞችን ገንብቷል። (1 ነገ. 9:19፤ መክ. 2:4-6) ይህ ትጋት የሚጠይቅ ሥራ ነበር፤ በተወሰነ መጠንም ቢሆን እርካታ አስገኝቶለት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ይሁንና ሰለሞን እንዲህ ያሉ ሥራዎችን ማከናወን ብቻውን እውነተኛ ደስታ እንደማያስገኝ ተገንዝቦ ነበር። በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችም ተካፍሏል። ለምሳሌ ለይሖዋ አምልኮ የሚሆን አስደናቂ ቤተ መቅደስ በተገነባበት ወቅት ሥራውን በበላይነት ይከታተል ነበር፤ ይህ የግንባታ ሥራ ሰባት ዓመት ፈጅቷል! (1 ነገ. 6:38፤ 9:1) በዓለማዊም ሆነ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መካፈል ምን እንደሚመስል የሚያውቀው ሰለሞን መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ከሌሎች ሥራዎች እጅግ የላቁ እንደሆኑ ተገንዝቧል። “ሁሉ ነገር ከተሰማ በኋላ መደምደሚያው ይህ ነው፦ እውነተኛውን አምላክ ፍራ፤ ትእዛዛቱንም ጠብቅ” ሲል ጽፏል።—መክ. 12:13
9. ኢየሱስ ለሥራ ተገቢውን ቦታ እንደሚሰጥ ያሳየው እንዴት ነው?
9 ኢየሱስ ታታሪ ሠራተኛ ነበር። ወጣት እያለ በአናጺነት ሠርቷል። (ማር. 6:3) ያደገው ትልቅ ቤተሰብ ውስጥ እንደመሆኑ መጠን ኑሮን ለማሸነፍ ደፋ ቀና የሚሉት ወላጆቹ የእሱን ድጋፍ በማግኘታቸው አመስጋኝ እንደነበሩ ጥርጥር የለውም። ደግሞም ፍጹም ሰው ስለነበር የእሱ ምርቶች ተፈላጊ ቢሆኑ የሚያስገርም አይደለም። ኢየሱስ ሥራውን ይወደው እንደነበረም መገመት እንችላለን። ያም ቢሆን ኢየሱስ ከሥራው ጎን ለጎን ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችም ጊዜ ይመድብ ነበር። (ዮሐ. 7:15) በኋላም የሙሉ ጊዜ ሰባኪ በነበረበት ወቅት አድማጮቹን እንዲህ ሲል መክሯቸዋል፦ “ለሚጠፋ ምግብ ሳይሆን . . . ዘላቂ ለሆነውና የዘላለም ሕይወት ለሚያስገኘው ምግብ ሥሩ።” (ዮሐ. 6:27) ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይም “በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ” ብሏል።—ማቴ. 6:20
10. አንዳንዶች ከሥራቸው ጋር በተያያዘ ምን ፈተና ያጋጥማቸዋል?
10 አምላካዊ ጥበብ ለሥራችን ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል። ክርስቲያኖች “መልካም ተግባር” እንድናከናውንና ‘በትጋት እንድንሠራ’ ተመክረናል። (ኤፌ. 4:28) አሠሪዎቻችን ሐቀኛና ታታሪ መሆናችንን ብዙውን ጊዜ ያስተውላሉ፤ አልፎ ተርፎም የሥራ ባሕላችንን እንደሚያደንቁ ይነግሩን ይሆናል። ታዲያ አለቃችን በይሖዋ ምሥክሮች ይበልጥ እንዲማረክ በማሰብ ተጨማሪ ሰዓት መሥራት ብንጀምርስ? ሳናስበው የቤተሰብ ኃላፊነታችንንና ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎቻችንን ችላ ማለት ልንጀምር እንችላለን። ይህ ከሆነ ሚዛናችንን ለመጠበቅ ለውጥ ማድረግ ያስፈልገናል።
11. አንድ ወንድም ለሥራ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝን በተመለከተ ምን ትምህርት አግኝቷል?
11 ዊልያም የተባለ አንድ ወጣት ወንድም ለሥራው ተገቢውን ቦታ መስጠት ያለውን ጥቅም በቅርብ ከሚያውቀው ሰው ተምሯል። አሠሪው ስለነበረ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “[ይህ ወንድም] ለሥራ ተገቢውን ቦታ በመስጠት ረገድ ምሳሌ የሚሆን ሰው ነበር። ጠንካራ ሠራተኛ ከመሆኑም ሌላ ሥራውን በጥራት ስለሚያከናውን ከደንበኞቹ ጋር ጥሩ ግንኙነት አለው። ይሁን እንጂ ሥራውን ካጠናቀቀ በኋላ የሥራውን ጉዳይ ትቶ ለቤተሰቡና ለአምልኮው ቅድሚያ ይሰጣል። የሚገርመው ደግሞ ከማውቃቸው በጣም ደስተኛ ሰዎች አንዱ እሱ ነው!” b
ለራሳችን ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ
12. ሰለሞን ለራሱ ሚዛናዊ አመለካከት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው? በኋላ ላይ ግን ሚዛኑን የሳተው እንዴት ነው?
12 ሰለሞን ይሖዋን በታማኝነት ያገለግል በነበረበት ወቅት ለራሱ ሚዛናዊ አመለካከት ነበረው። ወጣት እያለ ከአቅሙ በላይ የሆኑ ነገሮች እንዳሉ በትሕትና በመግለጽ ይሖዋ መመሪያ እንዲሰጠው ጸልዮአል። (1 ነገ. 3:7-9) በንግሥናው መጀመሪያ አካባቢም ሰለሞን ኩራት ያለውን አደጋ በሚገባ ያውቅ ነበር። “ኩራት ጥፋትን፣ የትዕቢት መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል” ሲል ጽፏል። (ምሳሌ 16:18) የሚያሳዝነው ግን ሰለሞን ራሱ የሰጠውን ምክር በኋላ ላይ ሳይሠራበት ቀርቷል። ንጉሥ ከሆነ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የኩራት ዝንባሌ ስላደረበት የአምላክን ሕጎች ችላ ማለት ጀመረ። ለምሳሌ ያህል፣ አንደኛው የአምላክ ሕግ አንድ ዕብራዊ ንጉሥ “ልቡ ከትክክለኛው መንገድ ዞር እንዳይል ለራሱ ሚስቶች አያብዛ” ይላል። (ዘዳ. 17:17) ሰለሞን ግን ይህን ሕግ ጥሶ ነበር፤ 700 ሚስቶችና 300 ቁባቶች ነበሩት! ከእነዚህ ብዙዎቹ አረማዊ አማልክትን የሚያመልኩ ሴቶች ነበሩ። (1 ነገ. 11:1-3) ምናልባት ሰለሞን “ምንም አልሆንም” ብሎ አስቦ ይሆን? ሁኔታው ምንም ይሁን ምን ውሎ አድሮ ሰለሞን ከይሖዋ መራቅ የሚያስከትለውን መዘዝ አጭዷል።—1 ነገ. 11:9-13
13. ኢየሱስ ስለተወው ምሳሌ ስናሰላስል ስለ ትሕትናው ምን እንማራለን?
13 ኢየሱስ ትሑት ነው፤ ምንጊዜም ለራሱ ሚዛናዊ አመለካከት ነበረው። ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በይሖዋ አገልግሎት ብዙ አስደናቂ ነገሮችን ማከናወን ችሏል። “በሰማያትና በምድር ያሉ ሌሎች ነገሮች በሙሉ . . . የተፈጠሩት በእሱ አማካኝነት ነው።” (ቆላ. 1:16) ኢየሱስ በተጠመቀበት ዕለት ከአባቱ ጋር እያለ ያከናወናቸውን ነገሮች እንዳስታወሰ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። (ማቴ. 3:16፤ ዮሐ. 17:5) ሆኖም ይህ ኢየሱስን እንዲታበይ አላደረገውም። እንዲያውም ኢየሱስ ራሱን ከማንም በላይ አድርጎ አያውቅም። ለደቀ መዛሙርቱ ወደ ምድር የመጣው “ለማገልገልና በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት እንጂ እንዲገለገል” እንዳልሆነ ነግሯቸዋል። (ማቴ. 20:28) በተጨማሪም “በራሱ ተነሳስቶ አንድም ነገር ሊያደርግ [እንደማይችል]” መናገሩ ልኩን እንደሚያውቅ የሚያሳይ ነው። (ዮሐ. 5:19) በእርግጥም የኢየሱስ ትሕትና አስደናቂ ነው! ሁላችንም ልንከተለው የሚገባ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል።
14. ለራሳችን ተገቢ አመለካከት ስለመያዝ ኢየሱስ ከተናገረው ነገር ምን እንማራለን?
14 ኢየሱስ ተከታዮቹን ለራሳቸው ተገቢ አመለካከት እንዲኖራቸው አስተምሯቸዋል። በአንድ ወቅት ኢየሱስ “የራሳችሁ ፀጉር እንኳ አንድ ሳይቀር ተቆጥሯል” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 10:30) ይህ ሐሳብ በተለይ ራሳችንን ከሌሎች ዝቅ አድርገን የመመልከት ዝንባሌ ካለን በጣም ያጽናናናል። የሰማዩ አባታችን ስለ እኛ በጥልቅ እንደሚያስብና በእሱ ዘንድ ዋጋ እንዳለን ያረጋግጥልናል። የይሖዋ አገልጋዮች ለመሆን ወይም በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሕይወት ለማግኘት እንደማንበቃ ፈጽሞ ልናስብ አይገባም፤ እንዲህ ማድረግ በይሖዋ ፍርድ ላይ ጥያቄ እንደማንሳት ይሆናል።
15. (ሀ) መጠበቂያ ግንብ ለራሳችን ምን ዓይነት ሚዛናዊ አመለካከት እንድናዳብር አበረታቶናል? (ለ) በገጽ 24 ላይ የሚገኘው ሥዕል እንደሚያሳየው በራሳችን ላይ ከልክ በላይ የምናተኩር ከሆነ የትኞቹ በረከቶች ያመልጡናል?
15 ከ15 ዓመታት በፊት መጠበቂያ ግንብ ስለ ራሳችን የሚከተለው ዓይነት ተገቢ አመለካከት እንዲኖረን አበረታቶ ነበር፦ “በእርግጥም ትዕቢተኞች እስክንሆን ድረስ ስለ ራሳችን ከልክ ያለፈ ግምት ማሳደር አይኖርብንም፤ እንዲሁም ምንም እንደማንጠቅም በማሰብም ወደ ሌላው ጽንፍ መሄድ አንፈልግም። ከዚህ ይልቅ የእኛ ዓላማ የራሳችንን ጥንካሬ እንዲሁም ድክመት ከግምት ውስጥ የሚያስገባ ምክንያታዊ አመለካከት ማዳበር መሆን ይኖርበታል። አንዲት ክርስቲያን ሴት ሁኔታውን እንዲህ በማለት ገልጻዋለች፦ ‘መጥፎ ሰው አይደለሁም፤ በጣም ጥሩ የምባልም አይደለሁም። እንደማንኛውም ሰው ሁሉ መልካምም ሆኑ ደስ የማይሉ ባሕርያት አሉኝ።’” c ታዲያ ለራሳችን ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ልብ አልክ?
16. ይሖዋ ጥበብ ያለበት መመሪያ የሚሰጠን ለምንድን ነው?
16 ይሖዋ በቃሉ በኩል ጥበብ ያለበት መመሪያ ይሰጠናል። ይሖዋ ይወደናል፤ ደስተኞች እንድንሆንም ይፈልጋል። (ኢሳ. 48:17, 18) የላቀ ደስታ የሚያስገኘው የጥበብ አካሄድ በሕይወታችን ውስጥ ይሖዋን ማስቀደም ነው። ይህን ስናደርግ ለገንዘብ፣ ለሥራ ወይም ለራሳቸው ከልክ ያለፈ ቦታ የሚሰጡ ሰዎች ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች እንጠበቃለን። እንግዲያው ሁላችንም ጥበበኛ ለመሆንና የይሖዋን ልብ ደስ ለማሰኘት ቆራጥ እንሁን።—ምሳሌ 23:15
መዝሙር 94 ለአምላክ ቃል አመስጋኝ መሆን
a ሰለሞንና ኢየሱስ ታላቅ ጥበብ ነበራቸው። ይህን ጥበብ ያገኙት ከይሖዋ አምላክ ነው። በዚህ ርዕስ ውስጥ ሰለሞንና ኢየሱስ ለገንዘብ፣ ለሥራና ለራሳችን ተገቢውን አመለካከት ስለመያዝ በመንፈስ መሪነት የሰጡትን ምክር እንመለከታለን። በተጨማሪም አንዳንድ ክርስቲያኖች በእነዚህ አቅጣጫዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ ማድረጋቸው እንዴት እንደጠቀማቸው እናያለን።
b በየካቲት 1, 2015 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ከሥራ ደስታ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
c በነሐሴ 1, 2005 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “መጽሐፍ ቅዱስ ደስታ እንድታገኝ ሊረዳህ ይችላል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
d የሥዕሉ መግለጫ፦ ጆን እና ቶም በአንድ ጉባኤ ውስጥ የሚያገለግሉ ወጣት ወንድሞች ናቸው። ጆን ብዙ ጊዜውን የሚያሳልፈው መኪናውን በመንከባከብ ነው። ቶም ደግሞ በመኪናው ሌሎችን ወደ አገልግሎትና ወደ ጉባኤ ስብሰባዎች ይወስዳል።
e የሥዕሉ መግለጫ፦ ጆን ተጨማሪ ሰዓት እየሠራ ነው። አለቃውን ቅር ማሰኘት ስለማይፈልግ አምሽቶ እንዲሠራ ሲጠይቀው ሁልጊዜ እሺ ይላል። የጉባኤ አገልጋይ የሆነው ቶም በዚያው ምሽት ከአንድ ሽማግሌ ጋር እረኝነት ያደርጋል። ቶም በሳምንቱ መሃል የተወሰኑትን ምሽቶች ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እንደሚጠቀምባቸው አስቀድሞ ለአለቃው ነግሮታል።
f የሥዕሉ መግለጫ፦ ጆን በራሱ ላይ የሚያተኩር ሰው ነው። ቶም ግን የራሱን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ይካፈላል፤ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ጥገና በሚካሄድበት ወቅት እገዛ ሲያበረክት አዳዲስ ጓደኞች ማግኘት ችሏል።